Tuesday, 04 March 2014 10:59

ኤል.ጂ ኩባንያ በ1.4 ሚሊዮን ዶላር የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሊገነባ ነው

Written by  መታሰቢ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

በየዓመቱ 700 ሺህ ዶላር ይመደብለታል ተብሏል
ኤል.ጂ ኤሌክትሮኒክስ በአዲስ አበባ ከተማ በ1.4 ሚሊዮን ዶላር የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሊገነባ ነው፡፡ የመሰረት ድንጋዩ ባለፈው ረቡዕ  የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አቶ ወንድወሰን ክፍሉ በተገኙበት ተቀምጧል፡፡
ኤል.ጂ ግሩፕ ከኮርያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ ጋር በጋራ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሚት አካባቢ ለሚገነባው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በኤሌክትሮኒክ ጥገና ላይ ስልጠና ለሚሰጠው ኮሌጅ ግንባታ 1.4 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል የመደበ ሲሆን በየዓመቱ 700ሺ ዶላር ተጨማሪ በጀት እንደተያዘለት የኤል.ጂ ግሩፕ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ያንግ ኪ.ኪም ገልፀዋል፡፡
የኮሌጁ ግንባታ እስከመጪው ጥቅምት ወር የሚጠናቀቅ ሲሆን ኮሌጁ በየዓመቱ 150 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን  ተገልጿል፡፡ ኮሌጁ ስራውን በሚጀምርበት ወቅት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በስልክና ቴሌቪዥን ጥገናዎች ስልጠና ከመስጠቱም በላይ በኢትዮጵያ የሚከናወነውን የእርሻ ፕሮጀክት በግብርና ቴክኖሎጂ ለማገዝ እንደሚሰራ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና ኤል.ጂ በሰንዳፋ አካባቢ የሚገኘውን የኤል.ጂ ኤሌክትሮኒክስ የተስፋ መንደር፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በተገኙበት አስመርቋል፡፡ መንደሩ የግብርና ባለሙያውን አቅም በማሳደግ ለገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት እንዲችል የሚያግዝ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች የተሰራው ንፁህ የመጠጥ ውሃና ት/ቤትም  ተጎብኝቷል፡፡  

Read 2315 times