ከ15 ዓመት በላይ እስር ሊያስቀጣቸው ይችላል
ከቀበሌው ሊቀመንበር ጋር በመመሳጠር ንብረትነቱ የመንግስት የሆነን ቤት፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ራሱ አዛውሮ ሲጠቀም ተደርሶበታል የተባለው ግለሰብና ተባብረዋል በሚል የተጠረጠሩት የቀበሌው ሊቀመንበር ላይ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ ክስ መሰረተባቸው፡፡
ሲኖሩበት የነበረውን የመንግስት ቤት ወደ ግል ይዞታቸው ለማዞር የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል በተባሉት አቶ በዳሳ ጫልቺሳና ከ1989-99 ድረስ በዘለቀው የቀበሌ ሊቀመንበርነት ስልጣናቸው ተጠቅመው ቤቱ የመንግስት መሆኑን የሚያስረዱ መረጃዎች እንዲጠፉ አስደርገዋል በተባሉት አቶ መንግስቱ ኃ/ጊዮርጊስ ላይ የአታላይነት የሙስና ክስ መመስረቱን የአቃቤ ህግ የክስ ማመልከቻ ይጠቁማል፡፡ በማስረጃነትም 12 የሰው ምስክሮች እና 14 የሰነድ ማስረጃዎች ተቆጥረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲቀርቡ ባስተላለፈው ትእዛዝ መሰረት፤ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት አቶ በዳሳ፤ የዋስትና መብቴ ይከበርልኝና ጉዳዩን በውጭ ሆኜ ልከታተል ቢሉም አቃቤ ህግ በክስ ማመልከቻው የጠቀሰው የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ፣ ከ15 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ ስለሚችል ፍ/ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
በእለቱ ያልቀረቡትን ሁለተኛ ተከሳሽ ኮሚሽኑ እንዲያቀርብ ያዘዘው ፍ/ቤቱ፤ መዝገቡን ለመጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡