Saturday, 22 February 2014 13:14

ከመሸ ብትመጡ …

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

“ለሜላት ያለህ ፍቅር ለማክዳ ካለህ ፍቅር እንደሚበልጥ ማቲማቲካል ሎጂክ በመጠቀም በፍጥነት አስረዳ” አለው አቃቤ ህጉ፤ ለተከሳሹ፡፡ ተከሳሹ አይኑን ጣራው ላይ ሰቅሎ መልስ ሲፈልግ ለቅፅበት ከቆየ በኋላ የሸመደደውን እንደሚለፈልፍ ተማሪ መንተባተብ ጀመረ፡፡
“X ኢዝ ኢኩዋል ቱ … እኔ ለእንግሊዝኛ ግጥም ያለኝ ፍቅር
“Y ኢዝ ኢኩዋል ቱ … እኔ ለማክዳ ያለኝ ፍቅር
ዜን - “X ኢዝ ግሬተር ዛን “Y”
ናው ሌት “Z” ቢ ኢኩዋል ቱ እኔ ለሜላት ያለኝ ፍቅር
ስለዚህ “Z” ከ “Y” መብለጡ እኔ ከምወደው ስራዬ ተባርሬ ለሜላት ስል መታሰሬ ግልፅ ስለሆነ
ዜር ፎር “Z” ኢዝ Greater than “X”
“በትክክል መልሰሀል፤ አሁን ወደ መስቀለኛው ጥያቄ እንሂድ” አለ አቃቤ ህጉ፤ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ለተከሳሹ ከሰጠው በኋላ፡፡ ጥያቄውን በፍጥነት ሰረዘበት፡፡
“በሳጥን ነው ወይንስ በሰሌን መቀበር የምትፈልገው?”
“ባልቀበር እመርጣለሁ?” መለሰ ተከሳሹ፡፡
“መቀበርህማ አይቀርም! የተጠየቅኸውን ብቻ መልስ”
“በሰሌን ይሻለኛል”
“ለምን?”
“የሬሳ ሳጥን ውድ ነው፤ ሳጥኑን ከሞተ ሰው ጋር ከመቅበር በህይወት ያለ ሰው እንደ አልጋ ቢገለገልበት ይሻላል”
“መልካም … በአለም ላይ ስንት አልጋ እንዳለ ቁጥሩን አስልተህ ንገረኝ?”
“የአለምን ህዝብ ቁጥር የሚያክል አልጋ አለ፡፡ ስምንት ቢሊዮን አልጋ ማለት ነው፡፡ … ነገር ግን ሰው ሲሞት አልጋው አብሮት ስለማይቀበር፣ የአልጋው ቁጥር ሁሌ እያሻቀበ ይሄዳል” ብሎ ተከሳሹ በጉጉት የአቃቤ ህጉን ፊት ተመለከተ፡፡ አቃቤ ህጉ በመልሱ አልረካም፡፡
“ለምሳሌ አንተ አልጋ የለህም፤ አልጋህን የት እንዳደረስከው ተናገር፤ ገድለህ፣ ቆራርጠህ አልቀበርከውም?”
“እኔ አልጋዬን አልገደልኩትም … የመጠጥ ሂሳብ ክፈል እያለ ጋሽ ያሲን ሲያስፈራራኝ ለቆራሌው ሸጥኩት እንጂ አልጋዬን ገድዬ አልቀበርኩም…”
አቃቤ ህጉ፤ ድንገት ተበሳጭቶ ወደሱ ተንደረደረ፡፡ በጥፊ ይጠፈጥፈው ጀመር፡፡ ተጠፍጣፊው ለመጮህ ቢሞክርም ድምፁ አልወጣ አለው፡፡ ደግሞ ጥፊው እንደ አለንጋ በማጅራቱ ዞሮ የሚጠመጠም አይነት ነው፡፡ ጥፊው በጣም ይቀዘቅዛል፡፡
እያጓራ ባንኖ የነቃው ይኼኔ ነው፡፡ ፊቱ ላይ እየተጨፈጨ ያለውን የሚከረፋ ሽታ ያለውን መወልወያ ለመሸሽ ተኝቶበት ከነበረው ጥጥ ፍራሹ ደንብሮ በአራት እግሩ ዳኸ፡፡ ምን እየተከሰተ እንደሆነ ሊገባው አልቻለም፡፡
አይኑን በሚጭበረበረው ብርሐን እንደምንም ለመግለጥ ጣረ፡፡ የታላቅ ወንድሙን ሱሪ እና የጫማውን ጠረን አወቃቸው፡፡
ታላቅ ወንድሙ ከበላዩ ቆሟል “ምን አባክ ሆነህ ነው” አለ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ፡፡ (ታላቅ ወንድሙ ቢሆንስ ለምንድነው በእርጥብ መወልወያ የሚገርፈው?)
የታላቅ ወንድሙን ሱሪ ጨምድዶ ለመቆም ሲሞክር ወደቀ፡፡ የታላቅ ወንድምየው ሱሪው እንዳይወልቅ …ያኛውን ሲጠፈጥፍ የነበረበትን የረጠበ ፎጣ ጥሎ በሁለት እጁ ቀበቶውን አፈፍ አድርጐ ያዘ፡፡
“ምን ፈልገህ ነው?” እያለ ታናሽየው፤ አሁንም ለመቆም በመንደፋደፍ ላይ ነው፡፡ ጥንብዝ ብሎ ሰክሯል፡፡ በህልሙ ሲታየው የነበረው የፍርድ ቤት ትዕይንት እና ከነቃ በኋላ ያለው ቅዠት አንድ ሆኖበታል፡፡ “ምን አጥፍቼ ነው እኔ የምከሰሰው” እያለ እንደመነፋረቅ አደረገው፡፡
“ባክህ አቦ ተነስ እና ልበስ! እማማ ትልቋ ሞታለች … አስከሬኗን በመኪና ይዤ መጥቻለሁ… ተነስና ሲስተር ቤት እንሂድ … ተነስ አልኩህ!” አለው ታላቅየው፤ያኛውን በፎደፎደበት በካልቾ ለማለት እየቃጣ፡፡ ታላቅ ወንድምየውም ተኝቶ አለመንቃቱ እንጂ ከታናሽየው ባላነሰ ሁኔታ ሰክሯል፡፡ አይኑ ተጐልጉሎ ወጥቶ ሊወድቅ ይመስላል፡፡
“ተነስ አልኩህ … አንት የተማርክ አህያ! … ደሞ አልጋውን የት አደረስከው … ሰርተህ አትብላና እቃ እያወጣህ ሽጥ”
… ትንሽየው ክንፉ እንደተሰበረ ዝንብ መሬቱ ላይ እያጉተመተመ ይሽከረከራል፡፡ ታላቅየው ብብት እና ብብቱ ስር ሰቅስቆ ገብቶ አነሳው፡፡ ቅድም ከተኛበት ለማንቃት ያረጠበውን ቆሻሻ ፎጣ ጭንቅላቱ እና ማጅራቱ ላይ አለበሰው፡፡ አልብሶት ወደ ደጅ ወጣ፡፡ ትንሽየው በፎጣ የተሸፈነ ጭንቅላቱን ይዞ ይወዛወዛል፡፡ በጥቂቱ መንቃት ጀምሯል፡፡
ያኛው ሲመለስ በነጠላ የተጠቀለለ ድርቅ ብሎ የተገተረ ነገር ተሸክሟል፡፡ በሩ በነጠላ የተሸፈነውን አስከሬን እንዳይነካው ተጠንቅቆ አስገባው፡፡ ባለ ጥጡ ፍራሽ ላይ የሴት አያታቸውን ሬሳ አጋደመው፡፡
ትንፋሹን ሽቅብ ቁልቁል እያለ “ስማ እኔ መኪና ውስጥ አድራለሁ… አንተ ቁጭ ብለህ አስከሬኑን ጠብቅ … ትሰማለህ? ለሲስተር መርዶውን ጠዋት አስነስተን ብንነግራት ይሻላል … በዚህ ሰአት አስከሬን ይዘን ብንሔድ ማዘር ትደነግጣለች፡፡ ጠዋት ቤት ቀስ ብለን ሄደን ለሲስተር እንነግራትና ሲስተር ለማዘር ቀስ ብላ ታርዳት?”
ትንሽየው አሁንም በስርአት አልነቃም፡፡ ተመልሶ መሬት ላይ ቁጭ አለ፡፡ ያኛው እንደገና በካልቾ ሊለው ተንደርድሮ መጣ፡፡ ትንሸየው ለመከላከል ተነስቶ ቆመ፡፡ ታላቁን ማክበር ድንገት ሲያቅተው የታወቀው አይመስልም፡፡ የረጠበውን ፎጣ አንዱ ስርቻ ወርውሮ ሙልጭ አድርጐ ታላቅየውን ሰደበው፡፡ መሐይምነቱን … ከሚሰራው ስራ ያነሰ የሎንቺና ሾፌር መሆኑን … ወዘተ ነገረው፡፡
የታላቅየው ስራ የሎንቺና ሾፌርነት ነው፡፡ አያትየው ከእሱ ጋር ካልኖርኩ ብለው ሰበታ ከሚገኘው የሾፌሩ የወንደላጤ ቤት የገቡት ከወር በፊት ነበር፡፡ ሾፌሩን የልጅ ልጃቸውን ከመምህሩ የበለጠ ይወዱታል፤ እሱም ይወዳቸዋል፡፡
ችግሩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው እየዘነጋ … በየደረሰበት ከተማ ሲያድር አሮጊቷ እየተጐዱ መሄዳቸውን ልብ አለማለቱ ነው፡፡ ከባድ ሳል ጀመራቸው፤ የኮሶ አረቄ ገዝቶላቸው መፍትሄ እንደሚያገኙ አስቦ ነበር፡፡ ይሄንን አስተሳሰቡን ነው ታናሽየው መሐይም ብሎ የዘለፈው፡፡
ሾፌሩ በታናሹ ከተሰደበ በኋላ ለትንሽ ቅጽበት ፀጥ አለ፡፡ ማስፈራራቱን ግን አልተወም፡፡ “ልብ አድርግ ቁጭ ብለህ አስክሬኑን ጠብቅ፡፡ ተመልሼ ቼክ አደርግሀለሁ … ተኝተህ ባገኝህ … እንደቅድሙ በፎጣ ሳይሆን በድንጋይ ፈጥፍጬህ ከአሮጊቷ ጋር አብራችሁ ትቀበራላችሁ” አለው እና ወጣ፡፡ ወደ ሎንቺናው፤ ገብቶ ለመተኛት፡፡ አሁን ግን ስለተናደደ …እና ግራ ስለተጋባ ቶሎ አይተኛም፡፡ ለአሮጊቷ ሞት ተጠያቂ መሆኑ ውስጥ ውስጡን ሳይሰማው አይቀርም፤ እንቅልፍ አይወስደውም፤ እዛው የመኪናው ኪስ ውስጥ የሸጐጣትን አረቄ አውጥቶ ሲጋት ማደሩ ነው፡፡ ብቻ በሩን ወርውሮ ዘግቶ ሄደ፡፡ የእንጨቷ በር ተገንጥላ ልትወድቅ ነበር፡፡ የጭቃ ቤቱ ግድግዳ ብዙ ጓል አረገፈ፡፡
ትንሽየው እንደዚህ ሰካራም ከመሆኑ በፊት መምህር ነበር፡፡ ከሁለት ሦስት አመታት በፊት፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ከሁለት ተማሪዎቹ ጋር የአይን ፍቅር ይዞት … እንደ ጐረምሳ አፈቀርኩ የሚላቸውን እየጠራ በማስፈራራት ፍቅር የሚገለፅ መስሎት የትምህርት ሂደቱን በመበጥበጡ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንዲቀየር ተደረገ፡፡ ግን መስተካከል አልቻለም፤ ግድግዳ ስር ተለጥፎ ሴቶቹን እየጠበቀ እንደለመደው (ለፍቅር ሲል) ማስፈራራቱ አልተው አለው፡፡ ሴቶቹን የሚያጅብ ወንድ ተማሪን ጥርስ ሲያወልቅ በፖሊስ ተከሰሰ፡፡ ተፈረደበት፡፡ ለስምንት ወራት ታሰረ፡፡ ከእስር ሲፈታ “እስፔሻል ክላስ” ጠጪ ሆነ፡፡
መምህሩ ከመሬቱ ላይ እየተንፏቀቀ ተነስቶ ወደተጋደመው የአያቱ ሬሳ ቀረበ … ነጠላውን ገለጥ አድርጐ አያቸው፡፡
“ሰው ሲሞት የቁመቱ እና የፊቱ ርዝመት ይጨምራል እንዴ?” አለ ለራሱ፡፡ በስካሩ ምክንያት ስለ አያቱ ድንገተኛ ሞት ለማዘን እንኳን አቅም የለውም፡፡ አጠገባቸው ተቀምጦ መጠበቅ ይጀምርና ወለሉ ላይ ተደፍቶ አፈሩ በአፍንጫው ሲገባ ይነቃል፤ ፊቱን በውሃ አጥቦ እንደገና ቁጭ ለማለት ይሞክራል፡፡ በስተመጨረሻ መረረው፡፡ የአሮጊቷን አስከሬን ወደ ግድግዳው አስጠግቶ፣ እንዳይነካቸው ተጠንቅቆ ከጐናቸው ገባና ተኛ፡፡ ገና ጭንቅላቱን ከማሳረፉ ማንኮራፋት ጀመረ፡፡
“የእንግሊዝኛ መምህር እንደመሆንህ አንድ የእንግሊዘኛ ግጥም ጥያቄ እጠይቅሀለሁ” አለው አቃቤ ህጉ፡፡ “ግጥሙን ከጀርባዬ ደብቄ ይዤዋለሁ፤ አንተ የትኛው እጄ ግጥሙን እንደያዘ እና ግጥሙ ምን አይነት እንደሆነ ትነግረናለህ” አለው አቃቤ ህጉ፡፡
“የግጥሙ ቅርፅ ኳርቴት ነው … ገጣሚው ማን እንደሆነ አይታወቅም”
“በትክክል መልሷል፤ ሙሉ ነጥብ ታገኛለህ” አለው አቃቤ ህጉ፤ ሞቅ ካለ ጭብጨባ ጋር
“ግጥሙን በቃሌ ልበልላችሁ”
“ማን ጠየቀህ?!” አለ አቃቤ ህጉ፤ያጨበጨበበት እጁን በመደነቅ ደረቱ ላይ አጣምሮ፡፡ “ሳትጠየቅ መመለስ ፍርድ ቤቱን መዳፈር ነው” ብሎ አስጠነቀቀው፡፡
… “ግን እኮ ሜላት እና ማክዳ አሁን ፍርድ ቤት ውስጥ አሉ፤ አላግባብ መከሰሴን ያውቃሉ፡፡ እኔ የእውቀት ማነስ የለብኝም፡፡ የእንግሊዘኛ ግጥም እንደማውቅ አውቀው እንዲያደንቁኝ እፈልጋለሁ። ስለማያደንቁኝ አይደል የሚንቁኝ? … ስለዚህ ክቡር አቃቤ ህግ፤ ከፍርድ ቤቱ ፈቃድ እያፈነገጥኩ ቢሆንም … በአይን ፍቅር ምክንያት የናቁኝ እነዚህ ሁለት ሴት አህዮች እንዲያደንቁኝ እና እንዲያከብሩኝ ስል ግጥሙን በራሴ ፈቃድ በቃሌ እለዋለሁ”
“As I was going up the stair
I met a man who wasn’t there
He wasn’t there again today-
I wish to God he’d go away”
ግጥሙን በጥሩ አነባበብ በወፍራም ድምፅ ደርድሮ ሲጨርስ፤ እነ ሜላት እና ማክዳ ወደተቀመጡበት ማጅራቱን አዙሮ አይኑ ማተረ። በእነ ሜላት ቦታ ላይ አሮጊቷ አያቱ በነጠላ የተሸፈነ ገፃቸውን ገልጠው በሞት ምክንያት የረዘመ ፊታቸውን አጋልጠው ቁጭ ብለዋል፡፡
በርግጐ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ወዲያው ቀና አለ፡፡ የአሮጊቷ አስከሬን ከጐኑ ተጋድሟል፡፡ በእንቅልፍ ልቡ አቅፎአቸው እንዳልነበረ እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ ዘገነነው፡፡ ጃኬቱን ደርቦ ደጅ አስፋልቱ ዳር ወደቆመችው የወንድሙ ሎንቺና ገሰገሰ፡፡ በሾፌር በር በኩል መወጣጫውን ረግጦ በመስኮት ተመለከተ፡፡
በእንቅልፍ ልቡ መሪው ላይ ላለመደፋት ሲል፤ የአሽከርካሪ ቀበቶውን አስሮ ሾፌሩ ተኝቷል፡፡
በሩን ከፍቶ ታላቅ ወንድሙን ቀሰቀሰው። ሲቀሰቅሰው ባለፈው ምሽት በጀመረው ድፍረት ሳይሆን እንደ ጥንቱ በአክብሮት ነው፡፡ ብዙ ከወዘወዘው በኋላ (በፎጣ መጠብጠብ ሳያስፈልገው) ተነሳ፡፡ ሳይነጋገሩ … ተጋግዘው አሮጊቷን በሎንቺናው የመጨረሻ ወንበር ላይ አጋደሟት። ሬሳው እንዳይንከባለል አሰሩት፡፡ የሁለቱም አይን ተጐልጉሎ ሊወድቅ ምንም አልቀረውም። እህታቸው እና እናታቸው አይናቸውን ሲያዩ ግን በለቅሶ ምክንያት አለመቅላቱን ወዲያው ያውቃሉ፡፡
ሾፌሩ እና መምህሩ ወንድማማቾች፤ በጋቢናው ግራ እና ቀኝ ገቡ፡፡ ሞተሩ ተቀሰቀሰ፡፡ ጋቢናው በሆነ ሽታ ተበክሏል፡፡ አረቄና ምግብ ሲቀላቀሉ የሚፈጠር ጠረን ነው፡፡ አረቄና ምግብ ከውጭ ሆኖ የሚቀላቀሉት ሲመለሱ ወይንም ሲያስመልሱ ብቻ ነው፡፡ ማርሹ ዙሪያ ያለችው ጐድጓዳ ስፍራ ታላቅየው ማታ በጠጣው መጠጥ እና ሀሞት ምልሰት ተሞልታ ተንጣላለች፡፡
አንድ ቃል ሳይለዋወጡ መኪናውን አስነስተው … ለሁለቱም ታላቅ ወደ ሆነችው እህታቸው ቤት በዝምታ ገሰገሱ፡፡  

Read 4496 times