Saturday, 22 February 2014 13:10

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሰራር ፈተና ላይ ወድቋል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

        ከተመሰረተ ስልሳ አምስት አመቱን ያስቆጠረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አለምአቀፋዊ ተቋምነቱ እና የብዙዎችን ይሁንታ ያገኘበት ሀላፊነቱ በተግባር በሚያከናውነው ስራ አንፃር ሲመዘን ጥያቄ ላይ የወደቀ ድርጅት ነው፡፡ አሁን በሀላፊነት ላይ ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን የመንግስታቱን ድርጅት የመለወጥ ሀሳብ በተደጋጋሚ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን፣ ድርጅቱን በዋና ፀሀፊነት ካገለገሉ ስምንት ሰዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ናቸው ስለ ለውጥ ምንም ተናግረው የማያውቁት፡፡ የተወሰኑ ለውጦች በተለያዩ ጊዜዎች የተደረጉ ቢሆንም፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ግን ምንም አይነት ለውጥ አለመደረጉ ጥያቄዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲበረቱ አድርጓል፡፡
በድርጅቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች የአባል አገሮቹን ያህል የበዛ እና የተወሳሰበ ቢሆንም፣ በማሻሻያዎቹ ላይ ጥናት ያደረገው ዛክ ቱከር፣ ጥያቄዎቹን በሶስት ዋና ዋና ምድቦች ይከፍላቸዋል። አንደኛው ጥያቄ፡- በመንግስታቱ ድርጅት ውስጥ እንደ ባህል የተያዘውና እንደ አሰራር እየተከተለ ያለው መንገድ፣ ውሁዳን ሊሂቃንን ያካተተው የአባል አገሮች ቡድን የመንግስታቱን ድርጅትም ሆነ የአለም ፖለቲካ አድራጊ እና ፈጣሪ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ የሚያተኩረው ደግሞ፡- በመንግስታቱ ድርጅት እንደ አንድ ግብ የተቆጠረው ግሎባላይዜሽን በአባል አገሮች ሉኣላዊነት ላይ እየጋረጠ ያለው ስጋት ላይ ነው፡፡ ድርጅቱ ግጭቶችን በመከላከልም ሆነ ሰብአዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ሰብአዊ አገልግሎቶችን በብቃት አይወጣም የሚለው ሶስተኛው ጥያቄ ነው፡፡
በለውጡ ላይ የድርጅቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክር ቤት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። በድርጅቱ ቻርተር መሰረት የምክር ቤቱ ሚና ወደ ጥናት እና አማካሪነት ያተኮረ ነው፡፡ ነገር ግን፤ በሚሰራበት የምርምር፣ የባህል፣ የትምህርት፣ የጤና እና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ልክ እንደ ፀጥታው ምክር ቤት  በድርጅቱ ስም ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችልበት አቅም ሊሰጠውም ይገባል፡፡ ይህ መደረጉ ደግሞ በድርጅቱ ውሳኔ ላይ የብዙሃን ድምፅ እንዲካተት እና በተለይ በአሁኑ ወቅት ክፍተት ያለበት ከሰብአዊ ድጋፎች ጋር የተያያዙ ስራዎች ምላሽ እንዲያገኙ ያስችላል ይላል ዛክ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ላይ ለውጥ ሲነሳ፣ የብዙዎችን ትኩረት የሚስበው የፀጥታው ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ፤ አራቱን የሁለተኛው የአለም ጦርነት አሸናፊዎች ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይና በቋሚ አባልነት  እና በየሁለት አመቱ የሚቀያየሩ አስር ተለዋጭ  አባላትን ይይዛል፡፡ ይህ ምክር ቤት ከሰላም እና ከደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፍተኛው የድርጅቱ ክንፍ በመሆኑ ማዕቀቦችን ይጥላል፣ የሀይል እርምጃዎችን ያፀድቃል ወይንም ይሽራል፡፡ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የዘጠኝ አባላት ድምፅ ሲያስፈልግ የቋሚ አባላቱ ሙሉ የስምምነት ድምፅ ግን የግድ ያስፈልጋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች እና ለማሻሻያ ይረዳሉ በሚል በተጠራ የከፍተኛ ባለሙያዎች ፓናል ሪፖርቱን ለድርጅቱ አቅርቧል፡፡ በፓናሉ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት የተሰጠውን ሚና መወጣት እንዳቃተው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከሞላ ጎደል ሽባ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የመነቃቃት አዝማሚያ ቢታይም፣ ከተወሰኑ ውጤታማ ስራዎች በስተቀር አንድን አሳሳቢ ጉዳይ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል ወይም ለተፈጠረ ቀውስ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የሀይል መጠላለፍ እና መቆላለፉ በመጉላቱ፣ ቋሚ የምክር ቤቱ አባሎች ጥቅም ማስጠበቂያ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ጊዜዎች ምክር ቤቱን ለማሻሻል የተደረጉ ሙከራዎች በተለይ የምክር ቤቱ አባልነት ላይ ይደረጉ በሚባሉ ማሻሻያዎች ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ውድቅ ሲሆኑ ተስተውለዋል፡፡
በፓናሉ ላይ የምክርቤቱን አባላት ቁጥር ከአስራ አምስት ወደ ሀያ አራት በማሳደግ ሁለት ሞዴሎች ለውይይት ቀርበው ነበር፡፡ አንዱ ሞዴል፡- ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የሌላቸው ስድስት አዲስ የቋሚ አባላትን ማካተት ሲሆን፣ ሁለተኛው ሞዴል ደግሞ አዲስ የቋሚ አባላትም ሳይኖሩ በየአራት አመቱ የሚለዋወጥ መቀመጫ ይኑር የሚሉ ናቸው፡፡
የፀጥታው ምክር ቤትን ጉዳይ አስመልክቶ የተሰጡ ብዙ አስተያየቶች አሰራሩ መሻሻል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አምስቱ አገሮች በሞኖፖል ጠቅልለው የያዙት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት በራሱ ከመሰረታዊዎቹ የህግ መርሆዎች ጋር ይጋጫል፡፡ አገሮቹ ውሳኔዎች እንዲያልፉ ወይም እንዲወድቁ ድምፅ የሚሰጡት ከሰብአዊ መብቶች ወይም ከአለም አቀፍ ህግ በመነሳት ሳይሆን፣ ከራሳቸው መንግስት ጥቅም እና ፍላጎት አንፃር ነው። የፀጥታው ምክር ቤት የተቋቋመው አለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነትለ ለማስከበር ቢሆንም እያገለገለ ያለው ግን ለየአገሮቹ የኢኮኖሚ ጥቅም እና የጡንቻ ብቃት መለኪያነት ነው፡፡ ምእራባውያኑ በአለም ላይ ዲሞክራሲን የማስፈን እውነተኛ ፍላጎት ካላቸው ሥራው መጀመር ያለበት በመንግስታቱ ድርጅት፣ በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት ነው፡፡ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቱ የተሰጠው ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ በመሆኑ ሰላም ማምጣት አልተቻለም፡፡ ይህ አሰራር፣ ክፍፍል እና ብዙ ተቃርኖ ያላቸው ቡድኖች እንዲፈጠሩ እድል ሰጥቷል፡፡ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት በመንግስታቱ ድርጅት ውስጥ ያለ የዲሞክራሲ መርሆችን የሚሸረሽር አሰራር ነው፡፡
በአለም ላይ ያሉ አገሮችና ህዝቦች እጣፈንታ በአምስት አገሮች ፍላጐት እንዲወሰን በመፈቀዱ ምክንያት አለማችን ይሆናሉ ተብለው የማይገመቱ እልቂቶችንና አሳዛኝ ክስተቶችን እንድታስተናግድ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሩዋንዳው እልቂት፣ የዳርፉር እና የሶሪያ ሰብአዊ ቀውሶች እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። የመንግስታቱ ድርጅት ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት እልቂት ቀድሞ መከላከል ያልቻለው ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባላቸው አሜሪካን እና ፈረንሳይ ውሳኔ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ከየጥቅሞቻቸው በመነሳት፡- አሜሪካ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ፣ ፈረንሳይ ደግሞ አጋሮቿን ላለማጣት በሚል የግል ስሌት ውስጥ በመግባታቸው  ነው … ብዙሀን በአደባባይ እንደ በግ የታረዱት። የሲሪላንካው አማፂ ቡድን “ታሚል ታይገርስ” ላይ በመንግስት በኩል ይደርሱ የነበሩ ኢ-ሰብአዊ እርምጃዎችን ለመታደግ በሚል መንግስት ላይ ሊጣል የነበረ ማእቀብ ውድቅ የተደረገው በቻይና ሲሆን መነሻውም ቻይና ከሲሪላንካ መንግስት ጋር ያላትን ወዳጅነት ላለማሻከር ሲባል ነበር፡፡ ሶስተኛ አመቱን የያዘውና  በመንግስታቱ ድርጅት የዘመኑ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ የታየበት ነው የሚባለው የሶሪያ ጉዳይም ከዚህ ጨዋታ የዘለለ አይደለም። ለችግሩ መፍትሄ በሚል የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ፣ በቻይና እና በራሺያ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የበሽር አላሳድ መንግስትን የሚደግፉት ቻይና እና ራሺያ፣ የውሳኔ ሀሳቡ መንግስትን ብቻ በመኮነን ተቃዋሚ ሀይሎችን በዝምታ ያለፈው በዚሁ የውሳኔ ሀሳብ በመሆኑ ድምፃቸውን መንፈጋቸውን ይገልፃሉ፡፡ በመንግስታቱ ድርጅት የራሺያ አምባሳደር ቪታሊ ቸርኪን የአገራቸውን ውሳኔ አስመልክቶ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት፣ የውሳኔ ሀሳቡ ሁሉንም ወገኖች በእኩል የሚኮንን ሳይሆን የአላሳድን መንግስት በተናጠል የሚኮንን በመሆኑ አገራቸው ልትቀበለው እንደማትችል ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ፤ ጃፓን፤ ህንድ እና የብሪክስ አገሮች የፀጥታው ምክር ቤት አሰራር ላይ የማሻሻያ ለውጥ እንዲደረግ ከሚጎተጉቱ አገሮች እና አካባቢያዊ ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ባለው አሰራር የብዙሀንን ጥቅም ማስከበር እንደማይቻል በተለያዩ ማስረጃዎች አስደግፈው ያቀርባሉ። ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን ቢደረግም ሆነ አገሮች እና አካባቢያዊ ድርጅቶች የመብቱ ተጠቃሚ መሆን ቢችሉ እንኳን፣ የራስን ጥቅም ማስላትን አያስቀርም፤ መጠላለፉን ከማወሳሰብ በስተቀር የሚሉም አሉ፡፡

Read 6158 times