Saturday, 22 February 2014 13:06

የመርካቶ ታሪካዊ ቅርስነትና መስህብነት እያከተመ ነው

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

በታሪካዊው የመርካቶ ዘጋቢ ፊልም ታሪካዊ ስህተቶች ተካትተዋል

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያሰራው ዘጋቢ ፊልም “መርካቶና አዲስ ከተማ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ የ1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ እርዝማኔ ያለው ዘጋቢ ፊልሙ፤ በ“እመቤት መልቲሚዲያ ፕሮዳክሽን” የተዘጋጀ ሲሆን አርቲስት እመቤት ወልደገብርኤል ናት  የምትተርከው፡፡
በዲቪዲ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ለሁለት ዓላማዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መርካቶ የተመሠረተችበትን  75ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር፣ የተለያዩ አካላት ልዩ ልዩ እቅዶችን ሲነድፉ ቢቆዩም እቅዶቹ ሳይተገበሩ ቀርተዋል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ የተዘጋጀበት አንዱ ዓላማም ለበዓሉ ማድመቂያ  ነበር፡፡
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ በልማት ሳቢያ እየጠፋ ያለውን የመርካቶ የግብይት ሥርዓት፣ እንቅስቃሴና ታሪካዊ ቅርሶች በምስል ቀርፆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ነው፡፡ ይሄኛው ዓላማ በእርግጥም ተሳክቷል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ተሰርቶ በዲቪዲ ወጥቷል። ነገር ግን በፊልሙ ላይ ስለቅርስ ዋጋ የተሰጡት ምስክርነቶችና ማብራሪያዎች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባልደረባ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በሰጡት ምስክርነት፤ “ገበያን በቅርስነት የምንይዝበት ምክንያት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ያለበት ቦታ ስለሆነ ነው፡፡ ገበያ ለብዙ ነገር ምክንያት ነው፡፡ ዕቃ፣ ሀሳብ፣ ፍቅር፣ ቴክኖሎጂና የእውቀት ልውውጥ ይካሄድበታል፡፡ ገበያ ሕብረተሰብን ነው የሚያቅፈው፡፡ ሕንፃ የተወሰኑ ግለሰቦችን ነው የሚይዘው፡፡ ገበያ ስንል ግን ሁሉንም ጠቅልሎ የሚያቅፍ ነው፡፡”  
መርካቶ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ያሉት ነጋዴዎች የሚመጡባት የንግድ ቦታ ናት ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፤ ወደ መርካቶ እየገባ የሚወጣው ሕዝብ እንደ አገር ውስጥ ቱሪስት ታይቶ የገበያው ዕድገትና ልማትም ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን በዘጋቢ ፊልሙ ላይ አሳስበዋል። በአዲስ መልክ የምትለማው መርካቶ የመናፈሻ ቦታዎች እንዲኖሯትና ንጽሕናዋ እንዲጠበቅም አደራ ብለዋል - ምሁሩ፡፡  
“የውጭ አገር ቱሪስት አዲስ አበባ ሲመጣ መርካቶን ሳይጎበኝ አይሄድም” የሚሉት ደግሞ በክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት፣ የቱሪስትና ልማት ቅርስ አስተዳደር የስራ ሂደት መረጃ ኦፊሰር ወ/ሮ ዙፋን ፍቅሬ ናቸው፡፡ ቅርሶች ያለፈውን ትውልድ የጥበብ አሻራ ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፉ ናቸው የሚሉት ወ/ሮ ዙፋን፤ እነዚህን ቅርሶች የመጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ሕብረተሰብ ክፍል ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
ቱሪስቶችን የሚስበው ታሪክና ቅርስ ነው ያሉት የስራ ሂደት መሪዋ፤ “የውጭና የአገር ውስጡን ቱሪስት ብቻ ሳይሆን በመርካቶ ለሚገለገለው ሕብረተሰብም ገበያዋ ምቹ እንድትሆንለት ቴክኖሎጂ-ተኮር  አሰራር መዘርጋት አለበት” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ  የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ኃ/ማርያምም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ መርካቶ የአገራችን ትልቋ ገበያ በመሆኗ ምክንያት የቱሪስቶችን ቀልብ ትስባለች ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ እንዲህ ዓይነት ቅርሶችን ጠብቆ ማቆየት በብዙ አገሮች የተለመደ መሆኑን ፊሊፒንስን በምሳሌነት በመጥቀስ ያስረዳሉ። “በፊሊፒንስ ማኒላ በሚባል ቦታ እንዲሁም በአንትራሞስ አካባቢ ታሪካዊ የሆኑ የግንባታ ስራዎች ስለሚገኙ፤ ያንን ቅርስ ከልለው በማቆየት በዙሪያው አዲስ የሰፈራ መንደር ለመስራት ሞክረዋል” ብለዋል፡፡
በዕድገት እንቅስቃሴ ውስጥ ጥንታዊ ነገሮችና አስተሳሰቦች እርስ በእርስ የሚቃረኑበት ሁኔታ አለ የሚሉት አቶ አበራ ኃ/ማርያም፤ “ዕድገትን መግታት አይቻልም፤ መርካቶ ትልቅ ገበያ እንደመሆኗ ትልቅ አገልግሎት መስጠት አለባት፡፡ የነጋዴውም የተገበያዩም ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ገበያዋ መለወጥና ማደግ አለባት፡፡ አሁን ጥያቄው ታሪካዊቷን መርካቶ እንዴት አድርገን ነው በቅርስነት ለትውልድ የምናስተላልፈው?” ሲሉ ይጠይቁና ራሳቸው አስገራሚ መልስ ይሰጣሉ፡፡
አዲስ አበባ  ከጣሊያን ወረራ በፊት፣ በጣሊያን ወረራ ወቅትና ከወረራው በኋላ በሦስት ዘመን ሊከፋፈል የሚችል ታሪክ አላት ያሉት አቶ አበራ፤ መርካቶም በዚህ ውስጥ ስላለፈች ሦስቱን ዘመን የሚያሳዩ ቅርሶችን መርጦ በማስቀረት ሌላውን ፎቶግራፍ በማንሳት፣ ቪዲዮ በመቅረጽ ዶክመንት አድርጎ ልማቱ መፋጠን እንዳለበት ያሳስባሉ - ዘጋቢ ፊልሙ የተዘጋጀበት አንዱ ምክንያት ይኸው መሆኑን በመግለፅ፡፡
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ መርካቶ ውስጥ እየጠፉ ያሉ ነገሮች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የሚጠቁሙ  መረጃዎችና ምስክርነቶች ቀርበዋል፡፡ “ዱቄት ተራ” ሥሙን ብቻ ይዞ እንደቀረ፣ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ የሚገኘው “ጌሾ ተራ” በመጥፋት ሂደት ላይ እንደሆነ፣ በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረው ሲኒማ ራስ ፈርሶ አዲስ ሕንፃ ሊገነባበት እንደታቀደ፣ ከ “ቄጠማ ተራዎች” አንዱ ሙሉ ለሙሉ እንደጠፋ፣ በቆጮ ንግድ ሁለት ፀጉር አብቅያለሁ ያሉት ወይዘሮ በልማቱ ምክንያት እንዳይፈናቀሉ ያቀረቡት ተማጥኖ … የመርካቶ ታሪካዊ ቅርስነትና የቱሪስት መስህብነት እያከተመ መምጣቱን ጠቋሚዎች ናቸው፡፡
መርካቶ ምን ትመስል እንደነበር ለመጪው ትውልድ ታሪክ ለማስቀመጥ በተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ታሪካዊ ስህተቶች ተካትተዋል፡፡ በንጉሡ ዘመን መርካቶን በአዲስ መልክ ለማልማት ሁለቱ አዳራሾች (የመሀል ገበያ ሕንፃዎች) ፈር-ቀዳጅ የግንባታ ሥራዎች ናቸው መባሉ፤ በፍራሽ ተራ የሚገኘው የሐጂ አህመድ ሳላህ ሻይ ቤት ለመርካቶ የመጀመሪያው ነው የሚል አዲስ ታሪክ መፈጠሩ፤ በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረውና ለባቡር መስመር ዝርጋታው ሲባል የፈረሰው የቁጭራ ባንክ የነበረበት መክሊት ሆቴል ሕንፃን ያሰሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ናቸው የሚሉና ሌሎችም ከስህተቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለእንዲህ ዓይነት ስህተቶች መፈጠር ዋናው ምክንያት የሚመስለኝ ደግሞ የቀድሞው ዘመን ጥረቶችና ሥራዎች ከአሁኑ ጋር እንዲያያዙ ባለመደረጋቸው ነው፤እንጂማ ባለፉት 20 ዓመታት መርካቶን በቅርስነት እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል፣ ለውጥና ዕድገቷ በምን መልኩ መመራት እንዳለበት በተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት በጣም ብዙ ሙከራዎች ተደርገው ነበር፡፡
በ1985 ዓ.ም ተለጣፊ ሱቆች ከመርካቶ የተነሱበት አብይ ምክንያትም ገበያዋን የማልሚያ ጥርጊያ መንገድ ለማመቻቸት ነበር፡፡ ዛሬ በጨረታ መሬት ለመውሰድ ተጋፊው የበዛበት የሊዝ ፖሊሲ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1986 ዓ.ም ሲወጣ ያለ ጨረታ መሬት በመውሰድ በዕድሉ እንድትጠቀም ግብዣ የቀረበው ለመርካቶ ነበር፡፡ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በ1995 ዓ.ም ሲፀድቅ መርካቶ ውስጥ መፍረስ ያለባቸውና የሌለባቸው ቤቶች ተለይተው ቀጣይ መልኳ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ሞዴል ተሰርቶላት ነበር፡፡
በ1998 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ጂቲዜድና የንግዱ ሕብረተሰብን የሚወክሉ አካላት ያሉበት የመርካቶ ማሌኒየም ግብረ ኃይል ተዋቅሮ የነበረ ሲሆን ካከናወናቸው ተግባራት መካከልም “Merkato Guide Book” በሚል ያሳተመው መፅሃፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለ አደራው ከንቲባ በነበሩበት ጊዜም መርካቶን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ዛሬም እየተሰራ ነው፡፡
የቀደመው ዘመን ሥራ ከአሁኑ ጋር እየተያያዘ፣ እየጎመራ፣ እየበሰለ ባለመምጣቱ ግን መርካቶን በልዩ የቅርስ ቦታነት መጠበቅ የማይቻልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
መርካቶ የሚታዩና የሚዳሰሱ ብቻ ሳይሆን የማይታዩና የማይዳሰሱ ብዙ እሴቶች ባለቤት ነበረች፡፡ የመርካቶ ብቻ ሊባል የሚችል ገጽታና ባህልም ነበራት፡፡ በብድር፣ በእቁብ፣ በዕድር … የተሰናሰሉ  ማህበራዊ መስተጋብሮች ጎልተው የሚታዩባት የገበያ ሥፍራም ነበረች፡፡
“መርካቶና አዲስ ከተማ” በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ እንደተገለፀው፤ የመርካቶ ታሪክ በበራሪ ወረቀት፣ በመጽሔትና በተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርፆ የሚቀመጥ ሲሆን አዲሷ መርካቶ በኒውዮርክ፣ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ዱባይ እና በመሳሰሉት አገራት እንዳሉት የገበያ ስፍራዎች ሆና ትለማለች። ይሄንንም ለማሳካት  መንግሥት፣አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ክፍለ ከተማ እየተጉ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ አሁንም ግልፅ ያልሆነልኝ ግን በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ስለ ቅርስና ዕድገት የተሰጡት እርስ በእርስ የሚጋጩ መረጃዎች  ናቸው፡፡ 

Read 3994 times