Saturday, 22 February 2014 12:44

ቴሌኮም በስድስት ወር ከኔትዎርክ መቆራረጥ እገላግላችኋለሁ ብሏል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(21 votes)

ሲዝን - 2
“ዋናው ነገር ጤና --- እድሜ መስተዋት ነው እናያለን ገና”
ለትራንስፖርት ችግሩ 12ሺ በራሪ ወረቀት ታትሟል
23 ዓመት የዘገየው የአውሮፕላን ስጦታ ለህወሓት ተበረከተ

እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ “ፖለቲካ በፈገግታ ሲዝን - 2” ይቀርባል ማለት ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ፅሁፍን በሲዝን ከፋፍሎ በማቅረብ ፈር-ቀዳጅ ነኝ አይደል? የታሪክ ሽሚያ ተጀምሯል ብዬ እኮ ነው፡፡ (ባለቤትነቴ ይመዝገብልኝ!)በእርግጥ እኔም ብሆን ከየትም አላመጣሁትም።  “ሰው ለሰው” እና  የእነ ሰይፉ ቶክ ሾው ሲያደርጉ አይቼ ነው! (እኔ ግን ፅሁፍ በድጋሚ አላቀርብም!) በዚህ አጋጣሚ በሲዝን-2 ምንም ዓይነት የቅርፅ ለውጥ እንዳላደረግሁ ስገልፅላችሁ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ወደ ወጋችን ከመግባታችን በፊት ግን እንኳን ለህወሓት 39ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!! ለማለት እወዳለሁ (አይመለከተንም የምትሉ ዝለሉት!)  
ስለህወሓት በዓል ሳነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ከጥቂት ሳምንት በፊት በቀድሞ የህወሃት አባላት  የተመሰረተው “አረና” የተባለ ተቃዋሚ ፓርቲ፤በትግራይ የስብሰባ ቅስቀሳ ሲያደርግ አባላቱ እንደታሰሩበት ገልፆ ነበር። ከዚያ ደግሞ “የህወሓት 39ኛ የልደት በዓል ስብሰባዬን አስተጓጎለብኝ” የሚል ስሞታ በዚሁ ጋዜጣ ላይ አነበብኩ፡፡ መጀመርያ ላይ እንዴት ሊሆን ይችላል ብዬ ከራሴ ጋር ተሟግቼ ነበር። በኋላ ግን “ጠርጥር አይጠፋም ከገንፎ መሃል ስንጥር” አልኩ - ለራሴ፡፡ እንኳንም ጠረጠርኩ! ለምን መሰላችሁ? ከህወሓትም ቢሆን አንዳንድ “አድርባይ ካድሬዎች” አይጠፉማ! እነሱማ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ የህወሓትን ህልውና የሚያስጠብቁ መስሏቸው ነበር፡፡ ያልገባቸው ምን መሰላችሁ? ህወሓት የታገለው ለነፃነት እንጂ ለአፈናና ለጭቆና አለመሆኑን ነው!
እናላችሁ ---የአረናን ስብሰባ ያስተጓጎሉት ህወሓት 17 ዓመት ሙሉ ለምን እንደታገለ በቅጡ ያልገባቸው “ፍሬሽ ካድሬዎች” እንደሆኑ ጠርጥሬአለሁ፡፡ ወይም የድል አጥቢያ አርበኞች! እንጂማ ቱባዎቹ  ታጋዮች ያንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ለአፈናና ለጭቆና ሳይሆን ለነፃነትና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ (አንዳንዶች ሥልጣን ሲጨብጡ ቢዘነጉትም!) ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ ስብሰባው የተስተጓጎለው በህወሃት 39ኛ ዓመት የልደት በዓል ሰበብ መሆኑ ነው፡፡ (በዓል እኮ ኢመርጀንሲ አይደለም!)
እኔ የምላችሁ----የኢህአዴግ ድርጅቶች የምስረታ በዓላቸውን ሲያከብሩና ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ሲያካሂዱ ለምንድነው እርግማን የሚያወርዱት? (የፓርቲ ባህል ይሆን?) ባለፈው ሰኞ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው ኦህዴድ ያወጣውን የብስጭት መግለጫ ሰምቼ ግርም አለኝ፡፡ ደሞ እኮ ያ ሁሉ እርግማን የወረደው ማን ላይ እንደሆነ ብናውቅ አርፈን እንቀመጥ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን የእርግማኑ ባለቤት አልተገለፀልንም፡፡ አገር ውስጥ ይኑር ውጭ? የምናውቀው ነገር የለም፡፡  እንዴ ---- ካልጠፋ ጊዜ ለምንድነው በጉባኤና በበዓል ወቅት ጠላት እየፈጠሩ እርግማን የሚያወርዱት? ቢያንስ በዓሉን በፌሽታ አክብሮ በነጋታው መደንፋት ይቻላል እኮ! (የፀረ-እርግማን አዋጅ እንዲረቀቅ ፒቲሽን እያሰባሰብኩ ነው!)
በበዓል ወቅት ደስ የሚለው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? እንደ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት የአውሮፕላን ስጦታ ማበርከት! (“ያለው ማማሩ” አሉ!) አልበሽር የህወሓትን በዓል እኮ ሞቅ አደረጉት! (የልብ ወዳጅ ይሏል ይሄ ነው!) ትንሽ ቅር ያለኝ ምን መሰላችሁ? ስጦታው ትንሽ በመዘግየቱ! ይታያችሁ---በዚህች አውሮፕላን ነበር  ታጋይ መለስና ጓዶቻቸው በ1983 ዓ.ም ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት፡፡ (ታሪካዊ አውሮፕላን ናት እኮ!) እኔማ ፓይለቱንም ይሰጡናል ብዬ እየጠበቅሁ ነው (ታሪካዊ ፓይለት ነዋ!)
እስቲ ከበዓል ወጎች ወደ ልማታዊ ወጎች ደግሞ እንግባ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን  መብራት፣ ውሃ እና ስልክ እንዲሁም ትራንስፖርት በሌሉበት ነው ስለልማት የምናወጋው፡፡ ግን ይሁን ---ምንም ቢሆን የእድገት ምስቅልቅል የፈጠረው ችግር ነው፡፡  እንደ ማንኛችንም የመዲናዋ ነዋሪ በትራንስፖርት ችግሩ  ግራ የተጋባው ኢቴቪ፤ ሰሞኑን ምን እንዳደረገ ታውቃላችሁ? የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተ ምላሽ የሚሰጠው ቢያጣ ተራ አስከባሪዎችን መፍትሄው ምንድነው ሲል ጠየቀ (“የቸገረው እርጉዝ ያገባል” አሉ!) ናላችሁ--- አንድ ተራ አስከባሪ ለኢቴቪ ጥያቄ እንዲህ ሲል መለሰ “የትራንስፖርት እጥረት የሚፈጠረው ሠራተኛው ከየመሥሪያ ቤቱ በአንድ ጊዜ ግር ብሎ ስለሚወጣ ነው” አለና መፍትሄውን ሲያስቀምጥም “ሠራተኛው ተራ በተራ ቢወጣ እኮ መጨናነቅ ሳይፈጠር ሁሉም ዘና ብሎ ወደ ቤቱ ይገባል” ብሎ አረፈው - ተራ አስከባሪው፡፡ አስቂኝ መፍትሄ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች መቶ በመቶ  ይሻላል፡፡
 የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ያለችውን ስሙልኝ “ቢሮው እንደቢሮው የምንሰራው ሥራ አለ፤ ባለድርሻ አካላቱም እንደ ባለድርሻ አካላት---” በቃ! ይሄን ብቻ ነው ማለት የቻለችው፡፡ (ምንም አላለችም እኮ!) አንድ ሌላ የቢሮው ሃላፊ ለትራንስፖርት ችግሩ መፍትሄው ምንድነው ሲባሉ ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? ተሳፋሪዎች ችግር ሲገጥማቸው ለቢሮአቸው ይጠቁሙ ዘንድ 12 ሺ በራሪ ወረቀቶችን አሳትመው ማሰራጨታቸውን ተናገሩ (በራሪ ወረቀት ታክሲ አይሆንም እኮ!) ከሁሉም ግን የታክሲ ባለንብረቶች ማህበር መሪ የሰጡት መፍትሄ ይሻላል “ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከተፈለገ ዘርፉ ባለሃብቶችን አማላይ መሆን አለበት፤በአሁኑ ሰዓት  ወደ ዘርፉ የሚገባ ባለሃብት የለም” ብለዋል፡፡ (“እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር---” አሉ!)
 ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው ሰሞን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዴት አገኛችሁት? እኔ በበኩሌ ታዝቤአቸዋለሁ - ጠ/ሚኒስትሩን። እንዴ---ከእኛ ከነዋሪዎቹ እሮሮ ይልቅ ለእነ መብራት ሃይል ጥብቅና የቆሙ መሰሉ እኮ፡፡ (ፓርቲያቸው አዟቸው ይሆን እንዴ?) እውነቴን እኮ ነው … በውሃ እጦት … በመብራት መጥፋት …በኔትዎርክ መቆራረጥ የምንሰቃየው እኛ እያለን እሳቸው ቃላቸውን ጠብቀው ለማያውቁት ተቋማት ተሟገቱላቸው፡፡ (ሰው አግኝተዋል?) እኔማ እንደዚያን እለት ንግግራቸው፣ ፓርቲያቸው የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ያደረጋቸው  መስሎኝ ነበር፡፡ እናላችሁ…የምንጠጣው ውሃ እያሳጣን ለሚያስጨንቀን ተቋም ሲከራከሩ “ውሃና ፍሳሽ በየጊዜው ውሃ ሲቋረጥ ህብረተሰቡን ይቅርታ ይጠይቃል” አሉ፡፡ (የኛ አገሩን አልመሰለኝም!)
ለነገሩ ይቅርታ ተባልንም አልተባልንም አይሞቀንም አይበርደንም (ለምደነዋላ!( ለጊዜው ግን ለአዲስ አበባ ነዋሪ አንገብጋቢው ጉዳይ ይቅርታ አይደለም፡፡ ውሃ ነው! መብራት ነው! ኔትዎርክ ነው! ጠ/ሚኒስትሩ ሽንጣቸውን ገትረው የተከራከሩላቸው እነመብራት ኃይል፤ነዋሪውን  ይቅርታ ካልጠየቅን ብለው ድርቅ የሚሉ ከሆነ ግን እንዲህ ያደርጉ፡፡ የይቅርታ የሥራ ሂደት ባለቤት ይሹሙ፡፡ (ራሱን የቻለ ሥራ እኮ ነው!) እስከዚያው አላስችል ካላቸው ደግሞ በየቀኑ ይቅርታ መጠየቁን ስለማይችሉት አንዴ የስድስት ወሩን ወይም የዓመቱን ይቅርታ ያሽሩን (መብራት፤ውሃና  ኔትዎርክ መጥፋቱ እንደሆነ አይቀር!)
በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቪዥን ሰሞኑን በእነ ቴሌና መብራት ኃይል ላይ የሰራው ፕሮግራም አንጀቴን አርሶኛል፡፡ (ቀላል አሸሞሩባቸው!)  ያውም እኮ በሙዚቃ እያጀቡ ነው፡፡  የደንበኞች ቅሬታን ያሰሙና የአብዱ ኪያርን “እስከ መቼ---” የሚል ዘፈን ይለቃሉ - በማጀቢያነት፡፡ ከዚያ ደግሞ የቴሌኮሙ  ኃላፊ በ6ወር ውስጥ የኔትዎርክ ችግር እንደሚፈታ ሲናገሩ ያሰሙንና  “ዋናው ነገር ጤና… ዕድሜ መስተዋት ነው እናያለን ገና” የሚል ዘፈን ያስኮመኩሙናል፡፡ (ለካስ አሽሙር ከፅሁፍ ይልቅ በቲቪ ይመቻል!) እኔማ ---የሌሎችም ባለስልጣናት ንግግርና መግለጫ እንዲህ በዘፈኖች ታጅቦ ቢቀርብልን  ብዬ ተመኘሁ፡፡ (ከእነለዛው ነው ታዲያ ማለቴ ከእነአሽሙሩ!)
  በመጨረሻ የ100 ብር የሞባይል ካርድ የሚያሸልም ጥያቄ ላቅርብና ልሰናበት፡፡
ጥያቄ - ከሚከተሉት ውስጥ ለቴሌ ኔትዎርክ መቆራረጥ ምክንያት የሆነው የትኛው ነው?
ሀ. ሳቦታጅ (አሻጥር)
ለ. ሰማይ ጠቀስ ፎቆች (ባይኖሩንም)
ሐ. የኦፕቲክ ፋይበር ስርቆት
መ. የመብራት መጥፋት
ሠ. ኪራይ ሰብሳቢነት
ረ. ሁሉም መልስ ናቸው
አሸናፊዎች የ100 ብር ካርዳቸውን የሚያገኙት በቴክስት ሜሴጅ ነው - እንደ ቴሌ ፍቃድ ማለት ነው፡፡
(ኔትዎርክ ከተገኘ ይሸለማሉ!)





Read 5422 times