Saturday, 22 February 2014 12:40

‘አርባ/ስድሳ’፣ ‘አሥር/ዘጠና’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጾም መግባቱም አይደል! ጿሚዎች… ‘እውነተኛ ጾም ያድርግላችሁማ!’
ስሙኝማ…አንድ የኃይማኖት አባት ስለ ጋብቻ እያስተማሩ ነበር፡ እናላችሁ…የተለመዱትን ነገሮች ከተናገሩ በኋላ ምን አሉ መሰላችሁ… የዘንድሮ ጋብቻ መቶ በመቶ አይደለም፣ አርባ/ስድሳ ነው፡ ስለዚህ ተቻቻሉ፡፡” አሪፍ አይደል!
ስሙኝማ…እንደምንሰማውና አንዳንድ ጊዜም እንደምናየው ዘመናዊው ትዳር ውስጥ የሚታዩ ነገሮች ለማስረዳትም አስቸጋሪ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ሴቷ አሥር፣ ወንዱ ዘጠና የሆኑበትን ትዳር አስቡት፡፡ አረቄውን ሲገለብጥ ያመሽና ሆዱን ገልብጦ ቤት ይገባል፡፡ ከዛ ድሮ የሚያውቃቸውንና ካመሸበት ቤት የሰማቸውን ስደቦች ያወርድባታል፡፡ ራት ይቀርብለታል፡
“ሴቱ በየቤቱ ስንት ይሠራል፣ ይሄን የጎርደሜ ወንዝ የመሰለ ልቅላቂሽን ወጥ ብለሽ ታቀርቢያለሽ!” እሷ እኮ ልቡ ሌላ ዘንድ “ልቡ ውጪ ውጪ እንዳይል…” ብላ ዘጠኝ ሰዓት የጣደችውን ወጥ ያወጣችው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነው! ደግሞም ጆርዳና ኩሽናም ይሁን ሌላ ላይ ያየችውን የማጣፈጫ ዘዴዎች ሁሉ ተጠቅማለች፡፡
“እሺ አሁን ይሄ ወጥ ምን ጎደለው ነው የምትለው!”
“ዝም በይ! አፍ አለኝ ብለሽ ታወሪያለሽ!” በስድብ ካለፈላትም ጥሩ ነው፡፡ እናማ… ‘ክላይማክሱ’ ላይ ምን ይላል መሰላችሁ…“እኔ እኮ አንቺን ያገባሁ ጊዜ ዓይኔን ምን ጋርዶኝ እንደነበር…!”
ደግሞላችሁ አረቄው ያልታሰበበትን የሰውነት ክፍል ‘ይተነኩስና’ እንትንዬ ነገር ሲፈልግ እንኳን…አለ አይደል…“አሁን መለፍለፉን አቁሚ! አውልቂና አልጋው ላይ ውጪ!…” ምናምን የሚል ትዕዛዝ ነው። “ዛሬ ቀኑን ሙሉ ሆዴን ሲቆርጠኝ ነው የዋለው…” “ቡአ ወረደኝ መሰለኝ ሲያቀለሸልሸኝ ይኸው ሦስት  ቀኔ…” ምናምን ብሎ ምክንያት አይሠራም፡፡
እናላችሁ… በሴት አሥር ወንድ ዘጠና ያለው ግንኙነት ደግሞ ምን አለፋችሁ… ‘ትዌልቭ ይርስ ኤ ስሌቭ’ ፊልም ላይ ያለውን ‘የባሪያና አሳዳሪ’ ነገር ሊሆን ምንም አይቀረው፡፡
ደግሞላችሁ…ወንድ አሥር ሆኖ ሴት ዘጠና ስትሆን ሌላ የተከታታይ ፊልም ጽሁፍ በሉት፡፡ በሆነ ነገር ይተነኳኮሱና “ተው እባክህ…አሁን አዲስ አበሻ ቀሚስ መግዛት ቁም ነገር ሆኖ ነው! የሰዉ ባል ስንት ነገር ያደርጋል…”
“አምስት ሺህ ብር ከየት ላምጣ…ደሞዝተኛ ነኝ እኮ! በቀደም አይደለም እንዴ ለቀሚስና ለቦዲ ብለሽ ሦስት ሺህ ብር የወሰድሽው!”
ከት ብላ ትስቅበታለች፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በማሾፍ ከት ብላ መሳቅ የምትወድ ሚስት ላለችው አባወራ እዘኑለት፡፡ ያን ጊዜ ነው…“ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” የሚያሰኘው!)
“ሦስት ሺህ ብር ገንዘብ ሆና ስትከነክንህ ኖራለቻ! የሰው ባል መኪና ይገዛል…” ትላለች። (እኔ የምለው…የሰውን ባል ማጣቃሻ የሚያደርጉ ሚስቶች…የሚያወሩት ‘መላ ምት’ ነው ወይስ የ‘ተግባር’ ተሞክሮ! ቂ…ቂ…ቂ… መታወቅ አለበታ!)
እናላችሁ…‘ክላይማክሱ’ ላይ ምን ትላለች መሰላችሁ…“ድሮም ስንጋባ እማዬ ‘ይሄ ሰውዬ ቀፎኛል’ ስትል የነበረው ለካስ እውነቷን ነው…”
እናላችሁ……ወንድ አሥር ሴት ዘጠና የሆኑበት ግንኙነትም ስንትና ስንት ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ይወጣው ነበር!
እኔ የምለው በቃ የሰው እንትናዬና የሰው እንትና ‘እነሆ በረከት’ መባባል.. አለ አይደል… “እና ምን ይጠበስ!” የሚያስብል ሆነና አረፈው! ነው ወይስ ነገሩ ሀያ/ሰማንያ ለሆነ ትዳር በወር ይሄን ያህል ጊዜ የራስ ካልሆነ ሰው ጋር ‘እነሆ በረከት’ ምናምን የሚፈቅድ ያልተጻፈ ህግ አለ!
እናማ ዘንድሮ… ስኳርም ሆነ ጨው የሆነ ነገር ሲመዘን እንኳን አንድ ኪሎ ግራም ማለት ዘጠና ግራም ሊሆን ይችላል፡፡ ዕድለኛ ከሆናችሁ ዘጠና አምስት ግራም፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የዘንድሮ የጓደኝነት ግንኙነት በአብዛኛው ሀያ ሰማንያና አሥር ዘጠና ነው፡፡ ምንም አይነት ከልብ የሆነ መተሳሰብ የሌለበት አንዱ በአንደኛው ተጠቃሚ የሚሆንበት፡፡ ልክ ያ ‘ተጠቃሚነት’ ሲያበቃ ‘ጓደኝነቱም’ ያልቅለታል፡፡
እናማ…የእውነት ካወራን አይቀር… ምን አርባ/ስድሳ ያልሆነ ነገር አለ! የት ቦታ ነው ልባችሁን የሚሞላ ‘መቶ በመቶ’ አገልግሎት የምታገኙት!  ስንት ቦታ ነው ጥራቱ የተሟላ መቶ በመቶ’ ምርት የምታገኙት!  የት ቦታ ነው “እንከን የማይወጣለት ግሩም ባህሪይ ያለው…” የሚባል ‘መቶ በመቶ የሆነ ሰው የምታገኙት!  
ሁሉም ነገር በ‘ኮንዶሚኒየም ተሞክሮ’ እየተመራ ይመስላል፡፡
ለነገሩ በደረጃው ያሉ የቦሶቻችን ነገር አይታችሁ እንደሆነ ምናልባት አርባ/ስድሳ የተቀራረበበት ጊዜ ከነበረ እንጃ…ግን ወደ ዘንድሮ ሁሉም ነገር ወደ አሥር ዘጠና እየተጠጋ ይመስላል፡፡ የሚሰማን ጠፋሳ! እናማ… ምን መሰላችሁ በርካታ ቦታዎች ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት የማግኘታችን ዕድል ከአሥር/ዘጠናም እያነሰ ነው፡፡
እናላችሁ… መቶ በመቶ የሚባል ነገር ቀርቷል፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…”የስ ሜን” (“yes men”) አልበዙባችሁም! አለ አይደል… የራሳችንን አእምሮ ሳናሠራ ሌላው የተናገረውን የምናስተጋባ፣ ያደረገውን “ይበል፣ ይበል” የምንል ማለት ነው፡፡
እናላችሁ…ዓላማ አለን ከሚሉን በላይ ሰውና አገርን መቀመቅ የሚከቱ ዓላማቸው ‘የሆድ ጉዳይ’ ብቻ የሆኑ… አለ አይደል… ‘ሀያ/ሰማንያ’፣ ‘አሥር/ዘጠና’ የሚል ሳይሆን በ‘ዜሮ/መቶ’ ራሳቸውን ተገዢ ያደረጉ “የስ ሜን” (yes men) ናቸው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በድሮ ጊዜ ቢሆን ንጉሦችና ነገሥታት ዙሪያቸውን በ”yes men” ይከበባሉ፡፡
እናላችሁ…“የስ ሜን” (yes men) የጌቶቻቸውን የሌላቸውን ገድል እየተረኩላቸው፣ ማን እንደሰጣቸው የማይታወቀውን ኒሻን እየደረደሩላቸው… ምን አለፋችሁ የመላዕክትን ክንፍ ሊቀጥሉላቸው ምንም አይቀራቸው፡፡ ዘንድሮም እንደነዚህ አይነት “የስ ሜን” (yes men) የሆንን እየበዛን ነው፡፡ ዜሮ/መቶ በሆነ ግንኙነት የሚሉንን ለመሸከም፣ የሚነግሩንን “እሰይ፣ እሰይ…” ብለን አጨብጭበን ለመቀበል፣ “ዝለል!” ሲሉን “ስንት ሜትር?” የምንል…የዜሮ/መቶ ሰዎች በዝተናል፡፡    
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ስድብ እዚህም ደረጃ ደረሰና አረፈው! የምር…አይ የ‘ጦቢያ’ ነገር የሚያሰኝ ነው፡፡ የድሮዎቹ የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጥር ሲጠየቁ “አምስት መቶ አንሞላም…” ምናምን አሉ የተባሉት እንኳን የሆነ መስመር ላይ ቆመዋል፡፡ ጥያቄ አለን…በአእምሮ ‘ብስለት’ና በምላስ ‘ስለት’ መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት ይጠናልንማ! ታዲያ ልክ ልካችንን ሲነግሩን እንደ ደነዘዝን የ‘ሜሊኒየሙ የልማት ግብ’ ምናምን የሚሉት ጊዜ ሊደርስ አይደል! እኔ የምለው…ብዙዎቻችን ነቅተንም እንቅልፍ ላይ የሆንን አይመስላችሁም፡፡
የምር… ብዙ ነገራችን ላይ የሆነ ድንዛዜ አይታያችሁም! ነገርየው’ኮ “አልበዛም ወይ ድንዛዜ…” አይነት ነገር እየሆነ ነው፡፡
(ጥቆማ አለን… “ጊዜ ሲከዳ መሬቱ ያድጣል” የሚሏትን አለማወቅ ስንቱን አንስቶ ዘጭ እያደረገው ነው! “ጊዜ ይከዳል…” አራት ነጥብ፡፡)
የምር ግን አንዳንዴ “ምንድነው እንዲህ መላ ያሳጣን?” ትላላችሁ፡፡ ለምንድነው ‘ዕብድ’ የሚያክል ጉርሻ በሁለት ጉንጮቹ የሚያላምጠው ሰው፣ በሌላኛው ሰው ግማሽ ጉንጭ እንኳን የማትሞላ ቅምሻ የሚናደደው? እናማ…የአሥር/ዘጠና አስተሳሰብ ‘ሁሉን’ ነገር ለእኛ፣ ‘ትንሽ’ ወይም ‘ምንም’ ነገር ለሌላኛው ሰው አይነት ህይወት ውስጥ ከቶናል፡፡
የምር እኮ…የምንጨነቀው ጎተራችንን ስለሞላው የራሳችን እህል ሳይሆን በአንዲት አቁማዳ ስለተሸከፈችው የሌላኛው ሰው ሹሮ እህል ነው። አሁን አንድ አቁማዳ ሹሮ የትኛውን ረብጣ ብር ታመጣና ነው!
እና የ‘አርባ/ስድሳ’፣ የ‘አሥር/ዘጠና’ አስተሳሰብ እያራራቀን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3693 times