Saturday, 22 February 2014 12:36

አቶ አስራት ጣሴ - ከ10 ቀን እስር በኋላ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“የሙስና አዋጁ እንደገና ሊፈተሽና ሊታይ ይገባዋል”
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ የነበሩትና በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ፤ በቅርቡ አዲስ ጉዳይ መፅሄት ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “ፍ/ቤትን ደፍረዋል” በሚል ተከሰው ያለዋስትና መብት በ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለአስር ቀናት ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሰኞ ተሲያት ላይ ተለቀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በክሱ ዙርያ፣ በዋስትና መብትና በእስር ቆይታቸው ዙርያ ተከታዩን አጭር ቃለመጠይቅ አድርጎላቸዋል፡፡

የቀረበብዎትን ክስ እስቲ ያብራሩልን ?
ክስ የቀረበብኝ በፍትሃ ብሄር ወንጀል አንቀፅ 480 ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ሰው በችሎት ላይ ታዳሚ ሆኖ፣ በጠበቃነት ወይም በከሳሽና በተከሳሽነት ቀርቦ ያልተገባ ድርጊት ሲፈፅም የሚከሰስበት አንቀፅ  ነው፡፡ እኔም መጀመሪያ በዚህ አንቀፅ ነበር ክስ የቀረበብኝ፤ በኋላ ላይ ግን ወደ ወንጀል ዞሮ ተፈረደብኝ-  በአንቀፅ 449 ተራ ቁጥር 2(ለ)፡፡ በዚህ የወንጀል አንቀፅ… የተከሰሰ ግለሰብ ከፍተኛ ቅጣቱ የ6 ወር እስራት ነው፡፡ የፍርድ ማቅለያ አቅርብ ተባልኩ፤ ነገር ግን የለኝም አልኩ።  ምክንያቱም ጠበቃዬ አቶ ተማም አባ ቡልጉ መጀመሪያ በተከሰስኩበት አንቀፅ ነበር ክርክሩን ያቀረቡት፤ ነገር ግን ባልተከሰስኩበት አንቀፅ የ5 ወር እስር በ2 ዓመት ገደብ  ተፈርዶብኛል፡፡ ሁለት ዓመት ለኔ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ይሄን ነገር ፖለቲካዊ መነሾ (ፖለቲካሊ ሞቲቬትድ) እንዳለው አድርጌ ነው ማየት የምፈልገው፡፡ የ2007 ምርጫ ቀርቧል፤ በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ንቁ ሆኜ መሳተፍ አለብኝ፤ በገዥው ፓርቲ እና መንግስት ላይ እንዲሁም በፍትህ ስርዓቱ ላይ አስተያየት መስጠት ይጠበቅብኛል፡፡ እነዚሀ ሁሉ ጉዳዮች መደረግ ባለባቸው ጊዜ ነው ይሄን እንደ ማስፈራሪያና ማሸማቀቂያ ለመጠቀም የተፈለገው። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት መሻሻል ለቆመው ተቃዋሚ ሁሉ መልእክቱ ጥሩ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ነገር ግን በተወሰነው ፍርድ ላይ ይግባኝ እንጠይቃለን፡፡
ወደ ማረፊያ ቤት ሲላኩ ለምን የዋስ መብት አልጠየቁም?
እንዳጋጣሚ ጠዋት ጠበቃ ይዤ ነው የቆምኩት፡፡ ፍ/ቤቱ ለከሰዓት ቀጠረን፡፡ ጠበቃዬ ሌላ ጉዳይ ስለነበራቸው፣ በእርግጠኝነት ክሱ የቀረበበት አንቀፅ ቢበዛ የሚያስቀጣው ገንዘብ ቢሆን ነው ብለውኝ ሄዱ፡፡ የኔ ፅሁፍ “ሽብርተኝነት የህወኀት ኢህአዴግ ስጋት” የሚል ሲሆን የፀረ-ሽብር ህጉን ነው በስፋት የሚተነትነው፡፡ “አኬልዳማ” እና “ጀሃዳዊ ሃረካት” የተሰኙት ዶክመንተሪ ፊልሞች በፅሁፉ የተነሱት እንደ ምሳሌ ነው፡፡ ይሄም በየጊዜው በኢሬቴድ እየተዘጋጀ የሚተላለፈው ሰውን ለማሸማቀቅ፣ ለመብቱ የሚቆመውን ሁሉ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ ነው፤ በዚህም ደግሞ ፍትህ አልተገኘም በሚል የፍትህ ስርአቱን የሚተች ነው እንጂ በተለየ መልኩ ችሎቱን የሚዘልፍ አይደለም” የሚል መከራከሪያ የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 29 (ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚደነግገውን) በመጥቀስ ጭምር ጠበቃዬ ከተከራከረ በኋላ ግፋ ቢል ቅጣቱ የገንዘብ ነው፤ የእስራት ቅጣት የለውም ብሎኝ ነበር፡፡ ከሰዓት በኋላ ግን ፍ/ቤቱ “ጥፋተኛ ሆነው ስላገኘንዎት በቀጥታ ፖሊስ ወደ ማረፊያ ክፍል እንዲወስድዎ” የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈ። በዚያ መሃል የዋስትና መብቴን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ይጠይቀኛል ብዬ ነበር የጠበቅሁት፤ ዝም ሲለኝ ግን መጠየቅ የማልችል መሰለኝና እኔም ዝም አልኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ቃል በቃል የዋስትና መብቴ ይጠበቅ የሚል ጥያቄ አላነሳሁም፤ ነገር ግን ፍ/ቤቱ “በዚህን ያህል ዋስትና ተለቀዋል፤ በውጭ ሆነው ይከራከሩ” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፍ ይችል ነበር፡፡ ከትእዛዙ በኋላም ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስጄ ከአርብ እስከ ሰኞ ያሉትን ቀናት እዚያ ካሳለፍኩ በኋላ ቀሪዎቹን ቀናት ደግሞ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንድቆይ ተደርጓል፡፡
በማረሚያ ቤት የገጠምዎት ችግር ነበር?
በጭራሽ! በግሌ አንድም ማዋከብና ማንገላታት አልገጠመኝም፡፡ ከእስረኞቹ የተደረገልኝ አቀባበልም ጥሩ ነበር፡፡ በርካታ እስረኞች አውቀውኛል፡፡
በእውነት የእስር ጊዜዬ የተመቸ እንዲሆን አድርገውልኛል፡፡ መጀመሪያ ያስገቡኝ ዞን አንድ የሚባለው ውስጥ ነበር። 1602 እስረኞች ነበሩ፤ ሁላችንም መሬት ነበር የምንተኛው፡፡
ለኔ ጥሩ ቦታ በመስጠት ተንከባክበውኛል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እና ፖሊሶችም ያደረሱብኝ ምንም ጫና እና እንግልት የለም፤ ማንንም እስረኛ እንደሚያስተናግዱት አስተናግደውኛል፡፡
የፍ/ቤቱ የገደብ ውሳኔ አስተያየት እንዳልሰጥ ታስቦ የተደረገ ይመስላል ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ አስተያየቶችና ትችቶችን ከመሰንዘር ይቆጠባሉ ማለት ነው? ውሳኔው ተፅዕኖ ይፈጥርብዎታል?
በምንም አይነት አይፈጥርብኝም፡፡ በምንም ሁኔታ ተፅዕኖ ሊፈጥርብኝ አይችልም፤ አይገባምም፡፡  ይሄን ተፅዕኖ ለመቋቋም የማልችል ከሆነ፣ እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋም ለመኖር ያስቸግረኛል፤ ስለዚህ በምንም መመዘኛ ተፅዕኖ አያደርግብኝም፤ ነገም ተመልሼ መታሰር ካለብኝም እታሰራለሁ፡፡ እነ አንዷለምም፣ እስክንድርም፣ በቀለ ገርባም እኮ እድሜ ልክ ተፈርዶባቸው ለዲሞክራሲ የሚፈለገውን ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ብቀበለውም በኔ አቋም ላይ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም፡፡
በእስር ቤት ቆይታዎ ምን ታዘቡ?
በእውነት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቆየሁባቸው ስምንት ቀናት በዚህች ሃገር የፍትህ ስርአቱ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ በዚህች ሃገር ፈታኙ ጉዳይ የፍትህ ጉዳይ እንደሆነ፣ የልማቱም ተግዳሮት የፍትህ እጦት መሆኑን፣ የሃገር ሰላምና መረጋጋትን የሚፈትነውም የፍትህ አለመኖር እንደሆነ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ሌሎችም በርከት ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለወደፊት በማስረጃ እስደግፎ ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ሁኔታዎች ከፈቀዱ በዝርዝር ለማቅረብ ፍቃደኛ ነኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንዱ የታዘብኩት፣ እኛ ፖለቲከኞቹ ብዙ ጊዜ ሰጥተን የምንተቸው የፀረ-ሽብር አዋጁን ነው፤ በማረሚያ ቤት ቆይታዬ የተረዳሁት ግን፣ የፀረ - ሙስናም አዋጅ ሊፈተሽና ሊታይ እንደሚገባው ነው፡፡ ይህ አዋጅም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የፖለቲካ ባላንጣን ማጥቂያ መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል ታዝቤአለሁ፡፡ የማረሚያ ቤት አያያዝ ባልተፃፈ ህግ የሚመራበት ሁኔታ እንዳለም ተረድቻለሁ፡፡ አንድም የግል ጋዜጣ እና መፅሄት ማረሚያ ቤት ሲገባ አላየሁም፡፡ ይሄ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱ መፈተሽ አለበት፡፡
ለስንተኛ ጊዜ ነው የታሰሩት?
በዚህ ስርዓት ለሁለተኛ ጊዜ ነው የታሰርኩት፤ በምርጫ 97ም ታስሬ ነበር፡፡

Read 5083 times