Saturday, 15 February 2014 13:35

“ትልቅ ስኬት የሚያስመዘግብ እንጂ የሚያጐድል አሰልጣኝ መመረጥ የለበትም”

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ሚሉቲን ሴርዶጄቪች (ከኡጋንዳ፤ ካምፓላ)
ከሩብ ምዕተ ዓመት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ ባለፉት ጥቂት አመታት ማንሰራራቱና በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆነ መምጣቱ አንድ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ ስፖንሰሮች፣ ደጋፊዎች እና የፌዴሬሽን አመራሮች እንደየድርሻቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ አህጉራዊ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ የመሆን ምኞታችን ገና አልተሳካም፡፡ ፈተናውም ከእስካሁኖቹ ሁሉ የከበደ ነው፡፡ ለዚህም ነው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ምርጫ፤ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ የማይገርመው፡፡
ለዚህ ትልቅ ሃላፊነት የሚመጥንና የሚስማማ አሰልጣኝ ለመምረጥ በተጀመረው እንቅስቃሴ፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሙያዎች በእጩነት ስማቸው እየተጠቀሰ ውይይት መሟሟቁም ተገቢ ነው፡፡ የተጀመረው ውይይትም፤ በቅንነት፣ በብስለት እና በእውቀት እየዳበረ መሄድ አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ቀደም ሲል በኢትዮጵያና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራትና በደቡብ አፍሪካ የታወቁ ክለቦችን ያሰለጠኑ፤ እንዲሁም አስቀድሞ የሩዋንዳ አሁን ደግሞ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑትን የ44 ዓመቱ ሰርቢያዊ ሚሉቲን “ሚቾ” ሴርዶጄቪች በአሰልጣኞች ምርጫ ዙሪያ አወያይተናቸዋል፡፡

እንደምታውቀው እኔ ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ነኝ። የትኛውም ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ደግሞ ስለደሞዙ በይፋ ለመናገር ፈቃደኛ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ከመናገር እቆጠባለሁ፡፡ ምክንያቱም መቼም ቢሆን የኔ ሩጫ ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ይልቁንም የሁልጊዜ ፍላጎቴ፣ ራዕይ  ላለው ፕሮጀክት መስራት ነው፡፡ እውነት ለመናገር፤ በአሰልጣኝነት በሰራሁባቸው አገራት ሁሉ ከማገኘው ንዋይ ይልቅ የምሰጠው አገልግሎት እና በትጋት ሰርቼ የማልፈው ይበልጣል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፤ በአሁኑ ጊዜ ከውጭ አሰልጣኞች መካከል በምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ቀዳሚውን ስፍራ ለመያዝ የበቃሁት፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አገራት በ14 ዓመታት የስራ ጊዜ ከፍተኛ ልምድ አካብቻለሁ፡፡ ሁሉም የሚያውቀው ደግሞ ለ5 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደታማኝ ወታደር አገልግያለሁ፡፡ እናም በአሰልጣኝነቴ ከገንዘብ ይልቅ በስራዬ ከፍ ያለ ስኬት እና የማይረሳ ታሪክ ትቼ ማለፉን በይበልጥ እፈልገዋለሁ፡፡
አሁን በስራ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በስራዬ በኖርኩባቸው አገራት ውስጥ ከፌዴሬሽኖች እና ከእግር ኳስ ተቋማት ጋር ያለኝ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህም በፌደሬሽን ስራዎች ላይ ጣልቃ ገብቼ ይህን አሰልጣኝ በዚህ ምክንያት ቅጠሩ በማለት ምክር በመስጠት ክብር ለመጋፋት አልፈልግም፡፡ ዋናው ነገር ኢትዮጵያ በአስደናቂ የባህል ትውፊቶቿ፤ ታሪኳ እና የአኗኗር ዘይቤ ልዩ አገር ናት፡፡ ይህን ክብር በመጠበቅ እና በማክበር፤ ከአገሬውና ከህዝቡ ጋር ተዋህዶ ሊሰራ የሚችል ሰው ያስፈልጋታል። ብሄራዊ ቡድኑ ከፊታችን ለሚጠብቁት ውድድሮች ረዥም የዝግጅት ጊዜ የለውም፡፡ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር የሚደረገው  ከ8 ወራት በኋላ ነው፡፡ ይህ የማጣርያ ውድድር በመስከረም አካባቢ ተጀምሮ በ3 ወራት ውስጥ 6 ጨዋታዎች የሚደረጉበት ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ይህን ከባድ ማጣርያ በከፍተኛ ዝግጅት በብቃት መወጣት እንዲችል በፍጥነት ውጤታማ አሰልጣኝ ያስፈልገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰሩ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ጋር በታላቅ የስራ ፍቅር ተከባብሮ እና በጓደኝነት ተቀራርቦ የመስራት ልምድ አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውንም ይጨምራል፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ለፈፀሟቸው ስኬታማ ተግባራት አድናቆት አለኝ፡፡ ሌሎችንም አደንቃለሁ ለጊዜው ግን፣ የአሰልጣኝ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ከኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች እገሌን ብዬ አድናቆቴን ብገልጽ ተገቢ አይሆንም፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ፤ በሙያችን የተዋወቅን አሰልጣኞች ሁሉ፤ ያለኝን ከበሬታ እና አድናቆት ያውቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በከፍተኛ ትጋት የሚሰሩ እና የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያንሰራራ ሁሉም በላቀ ደረጃ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው አስባለሁ፡፡ በአሰልጣኝነት ሙያዬ ከኢትዮጵያውያን ጋር በመስራቴ ብዙ ትምህርት እና ልምድ ተጋርቻለሁ፤ አጋርቻለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሁሉም ያለኝን የከበረ ምስጋና እገልፃለሁ፡፡ ባለሙያዎችን በስም እየጠራሁ ያልዘረዘርኩት አሁን ጊዜው ስላልሆነ ነው፡፡   በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ግን የማስበውን ነገር ሁሉ በዝርዝር ለመናገር ወደኋላ አልልም፡፡
የውጭ አገር  አሰልጣኞችን በተመለከተ አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለበት አጣዳፊ ሁኔታ የሚሆን ባለሙያ በተፈለገው መስፈርት እና ብቃት በቀላሉ ማግኘት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እኔም ለዚህ ሃላፊነት የሚመጥንና የሚስማማ የውጭ አሰልጣኝ ማን ነው ብባል፤ አንድም ሰው በአዕምሮዬ ሊመጣ አይችልም። ጥሩ አሰልጣኝ ለማግኘት በቂ ጊዜ ወስዶ መስራት ያስፈልጋል። ለአዲሱ አሰልጣኝ ቅጥር የሚሰሩትን ሁሉ በስራቸው እግዚአብሔር ይርዳቸው ነው የምለው። አሰልጣኝ ምርጫ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አሁን እግር ኳሱ ባለበት የተነቃቃ መንፈስ ለተሻለ ለውጥና ለላቀ እድገት በብቃት ተስማምቶ የሚያገለግል ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ካላቸው ትልቅ ስሜት ጋር የሚስተካከል ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ የሚሰራ አሰልጣኝ እንጂ የሚያጎድል ሰው መመረጥ የለበትም፡፡ ማንም ሰው ደጋፊዎችን የማስከፋት እና ተስፋ የማስቆረጥ መብት የለውም፡፡ ከዚህ ጥቅል አስተያየት ባሻገር፣ የአሰልጣኝ ምርጫን በተመለከተ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የተነሳ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እገሌ  ብዬ ለመጠቆም አሁን አልችልም፡፡
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝንት ከሚፈለጉ እጩዎች አንዱ ሆኜ ስሜ በመነሳቱ ብቻ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ለአሰልጣኝነቴ ዋጋ የሰጠ እውቅና በመሆኑ ከልብ ያስደስተኛል፡፡ አንድ ባለሙያ፣ ከምንም ነገር በላይ ለሙያው እውቅና ሲሰጠው ነው እርካታ የሚሰማው፡፡ ቢሳካ፤ ህልሜ እውን እንደሆነ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም  አሰልጣኞች ትልልቅ ብሄራዊ ቡድኖችን በሃላፊነት ለመምራት ይፈልጋሉ፡፡ ሃቁን ልንገርህ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር እና ስሜት እንዲሁም ልዩ ብሄራዊ ክብራቸውን ለሚያውቅ ሰው፤ ይህን ትልቅ ሃላፊነት ሲያገኝ፣ የዘወትር  ህልሙ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ትልቁ ሃይል፤ በሃላፊነታቸው ለህዝብ ደስታን መፍጠር ነው፡፡ ለ90 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን  ደስታ መፍጠር የሚቻልበት ሃላፊነትን ማግኘት እጅግ ያጓጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ታላቅ ክብር  ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጠሩ መነቃቃቶች እና ውጤቶች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ ማንም አይፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ውጤታማ እቅዶችን የያዘ ብቁ አሰልጣኝ የሚያስፈልገው። የአጭርጊዜ እቅዱ በ2015 በሞሮኮ የሚስተናገደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ በ2018 ራሽያ የምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ነው፡፡ አዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እነዚህን አቅዶች ማሳካት የሚችል ፤ የተነቃቃውን ለውጥ በማስቀጠል ለላቀ እድገት የሚተጋ ሊሆን ይገባል፡፡ በምንኖርባት ፕላኔት ውስጥ፤ ለዚህ ሃላፊነት የሚስማማ፤ ይህን ከባድ ሃላፊነት በብቃት መወጣት እና መስራት የሚችል አንድ ባለሙያ አውቃለሁ፡፡ ግን እገሌ ብዬ ስሙንና ማንነቱን ለመንገር መብት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰው፤ በሌላ አገር የኮንትራት ስራ ላይ ስለሚገኝ ነው፡፡
እንደሁልጊዜው ልባዊ መልካም ምኞቴን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለአንተም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም፡፡ በርቱ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትክክለኛ ቦታው ከምርጦች ተርታ ነው፡፡ እዚያ ቦታ እንዲደርስ ሁላችሁም በህብረትና በትጋት ስሩ፡፡ ከስምንት አመት በፊት ከጋዜጣችሁ ባደረግነው ቃለምልልስ፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ብትሆን በማለት መልካም ምኞትህን ገለጽህልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የመሆን ልባዊ ምኞት እንዳለ ሆኖ፤ እኔ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆንኩ አልሆንኩ  ምንግዜም የዋልያዎቹ ቁርጠኛ ደጋፊ ሆኜ እቀጥላለሁ፡፡


Read 3407 times