Saturday, 15 February 2014 13:33

መከላከያ በሜዳው፤ ደደቢት ከሜዳ ውጭ ጥሎ ለማለፍ ይፋለማሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ  ደደቢት እና  መከላከያ በቅድመ ማጣርያ  የመልስ ጨዋታዎቻቸው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦችን ጥሎ ለማለፍ ትንቅንቅ ያደርጋሉ፡፡ ከሳምንት በፊት ደደቢት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የዛንዚባሩን ኬኤምኬኤም በሜዳው 3ለ0 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ዳዊት ፍቃዱ፤ ሺመክት ታደሰ እና ማይክል ጆርጅ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ  መከላከያ ከሊዮፓርድስ ከሜዳ ውጭ በተገናኘበት ጨዋታ 2ለ0 ተሸንፏል፡፡
በኬንያው ብሄራዊ ስታድዬም ናያዮ በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለሊዮፓርድስ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት አምበሉ ማርቲን ኢምባላምቦሊ እና ጃኮብ ኬሊ ናቸው፡፡ ደደቢት ከኬኤምኬኤም ጋር ከሜዳው ውጭ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ከ2ለ0 በታች መሸነፍ፤ አቻ መውጣትና በማናቸውም ውጤት ማሸነፍ ጥሎ ለማለፍ ይበቃዋል፡፡
መከላከያ ደግሞ የኬንያውን ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ በሜዳው አስተናግዶ 3ለ0 ከዚያም በላይ በማሸንፍ የማለፍ  እድሉን ይወስናል፡፡  በቅድመ ማጣርያው ከኢትዮጵያው ደደቢት እና ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ጥሎ ማለፍ የሚችለው ክለብ በአንደኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ የሚገናኘው ከቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ኤስፋክሲዬን ጋር ነው፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያው መከላከያ እና ከኬንያው ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ ጥሎ የሚያልፈው በአንደኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ የሚገናኘው  ከደቡብ አፍሪካው ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ ወይም ከቦትስዋናው ጋብሮኒ ዩናይትስድ አሸናፊ ጋር ይሆናል፡፡ ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ጋብሮኒ ዩናይትድስን 2ለ0 አሸንፎታል፡፡

Read 1499 times