Saturday, 15 February 2014 13:07

(እውነተኛ ታሪክ - ዘ ዴይሊ ቢስት እንደዘገበው)

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(38 votes)

የእነ ሶፊ መንገድ…
ከሴተኛ አዳሪነት ወደ ፋርማሲስትነት

“… በአጠቃላይ ታሪኩ ይሄው ነው፡፡ ሶፊያ በድጋሚ እንኳን ደስ አለሽ!!” በማለት ንግግሩን ቋጨ - ኢሻይ ሃዳስ፡፡ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው የዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር በጭብጨባ ተናወጠ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች፣ የዕለቱ ተመራቂዎች፣ የተመራቂዎች ቤተሰቦች… ሁሉም በደስታ እንባ ተራጩ፡፡  ሁሉም የየራሱን ደስታ ትቶ፣ በሁለቱ ደስታ ፈነደቀ - በኢትዮጵያዊቷ ተመራቂ በሶፊያና በእስራኤላዊው እንግዳዋ በኢሻይ ሃዳስ፡፡
ሶፊያ ብቻዋን ናት፡፡
የኔ የምትለው ወዳጅ ዘመድ ወይም  ጓደኛ ያልነበራት ባይተዋር! ብቻዋን ነው፣ ባልጠና ጉልበት ከኑሮ ጋር ትግል የጀመረችው፡፡ ስትወድቅ ስትነሳ ከጎኗ ማንም አልነበረም፡፡ ወድቃ ከምትቆዝምበት ድንገት ደርሶ ካቃናት፣ ቀና አድርጎ ካቆማት፣ መንገዷን ከጠረገላት፣ ደግፎ ከዚህ ካደረሳት ካልተወለዳት ዘመዷ በቀር እሷ ሰው አልነበራትም፡፡
አሁን ሶፊያ ብቻዋን አይደለችም፡፡ እንደሌሎች ተመራቂ ጓደኞቿ በደስታዋ ቀን ከጎኗ የሚቆም፣ “እንኳን ደስ አለሽ!” ብሎ እቅፍ አበባ የሚሰጣት፣ እቅፍ አድርጓት ፎቶግራፍ የሚነሳ፣ የራሷ ሰው መጥቶላታል - በእቅፏ ውስጥ ሆኖ ከእንባዋ በስተጀርባ ሲፍለቀለቅ የምታየው እስራኤላዊው ኢሻይ ሃዳስ፡፡
ይህ ሰው ከአመታት በኋላ ጊዜ ቆጥሮ፣ በዚህች ልዩ ዕለት ከጎኗ እንደሚገኝ የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ እሷ የምታውቀው ሰውዬው ከአመታት በፊት የህይወቷን ጉዞ ወደሌላ አቅጣጫ መርቶ ለዚህች ልዩ ዕለት እንዳበቃት ብቻ ነው፡፡ ይሄን ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ይሄ ምንጊዜም ከልቧ የማይጠፋ እውነት ነው - በጊዜ የማይሻር፡፡
በ1996 ዓ.ም… ከወርሃ ሃምሌ የመጨረሻዎቹ ቀናት በአንደኛው…
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ736 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ አንዲት የመሸባት የገጠር ከተማ… ጨለማው ውስጥ ተኮራምታ የምታንጎላጅ መንደር… መንደሯ ውስጥ አንዲት የከተማዋ ብቸኛ ቡና ቤት… ቡና ቤቷ ውስጥ አንዲት ጉብል - ጥግ ላይ ተቀምጣ የምትቆዝም፡፡
እጅ እግርን የሚያደነዝዝ ቆፈን፣ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ከሚያንሰፈስፍ ብቸኝነት ጋር ተባብሮ የሚያሰቃያት የ19 አመቷ ኮረዳ፣ ከጠባቧ ቡና ቤት አንድ ጥግ ላይ ተኮራምታ ቁጭ እንዳለች ትተክዛለች፡፡ አንድ ሁለት ማለት ያሰኘው የመሸበት ጠጪ እስኪመጣ፣ በራሷ ሃሳብ ተውጣ ትቆዝማለች፡፡ ተስተናጋጅ ብቅ እስኪል፣ የህይወቷን ጣጣ ታወጣ ታወርዳለች፡፡
ወላጆቿን የነጠቃት ክፉ ሞት፣ ተራውን ጠብቆ መጥቶ እሷንም እስኪገላግላት ለቡና ቤቷ ደንበኞች መጠጥ እያመላለሰች ትጠብቃለች፡፡ ደጋፊ ዘመድ አጥታ ባቋረጠችው ትምህርት ምትክ፣ የመከራን ሀሁ ስትቆጥር ውላ ማምሸት ከጀመረች ሁለት ሳምንታት አልፈዋታል፡፡ የመሰደብ… የመጎንተል… የመዋረድ… የመናቅ…. እንዲህና እንዲያ የመሆን የማይገፉ አስቀያሚ ሁለት ሳምንታት!
ሶስተኛው ሳምንት ከመምጣቱ በፊት…
ከአስጠሊታዎቹ ምሽቶች ባንደኛዋ፣ የመሸበት ተስተናጋጅ ወደ ቡና ቤቷ ጎራ አለ፡፡ ፈረንጅ ነው - ከጥቁሩ ጨለማ ውስጥ ድንገት ብቅ ያለ የነጭ ጥቁር እንግዳ፡፡
“ወይ ጣጣ!... መቼም እንቅልፍ የሚነሳ አንዳንድ ሰው አይታጣ!... ይሄ ደሞ ምን ያለው ነው፣ ሌት አጋምሶ የሚመጣ?!” ስትል በውስጧ እያጉተመተመች ከተቀመጠችበት ተነሳች፡፡ ወደተቀመጠበት በማምራትም ጎንበስ ብላ ምን እንደሚፈልግ በትህትና ጠየቀችው፡፡ እርግጥ ለወጉ ብላ ነው እንጂ፣ ምን እንደሚፈልግ አጥታው አይደለም፡፡ ቢራ ወይም ወሲብ፣ ከሁለቱ አንዱ ነው ወንዶችን ከመሸ ወዲህ የሚያመጣቸው፡፡
“ምን ልታዘዝ?” በትህትና ጠየቀች አስተናጋጇ፡፡
የ58 አመቱ እስራኤላዊ የማስታወቂያ ፕሮዲዩሰር ኢሻይ ሃዳስ፣ ከፊቱ ላለችው አስተናጋጅ መልስ አልሰጣትም፡፡ ለአርኪዎሎጂ ጥናት ከአገሩ የወጣው ሃዳስ፣ እንደ ድንገት ነው እዚህ የተገኘው። ስለመሸበትና ጉዞውን መቀጠል ስለማይችል ነው፣ እዚህች ትንሽዬ የገጠር ከተማ ለማደር ወስኖ ድንኳን የጣለው፡፡ ከወዲያ ወዲህ እያለ ሲናፈስ ድንገት አይኑ ውስጥ ወደገባችው ወደዚህች አንድ ላገሯ ቡና ቤት ጎራ ያለው በአጋጣሚ ነው፡፡ እንዲሁ ሁኔታውን ለማየት፡፡
“ምን ልታዘዝ ?” ስትል ግራ በመጋባት ደግማ ጠየቀች አስተናጋጇ፡፡ የፈረንጁ ሁኔታ አላማራትም። ወሲብ ሊሸምት ጎራ ያለ አይናፋር ፈረንጅ ሳይሆን አይቀርም ስትል አሰበች፡፡ ጥቂት ቆይታ ደግሞ፣ ችግሩ የቋንቋ ሊሆን እንደሚችል ጠረጠረች - ያለመግባባት፡፡  
እሷ እንደጠረጠረችው ችግሩ የቋንቋ አልነበረም። ኢሻይ ሃዳስ ከፊቱ የቆመችውን አስተናጋጅ በድምጽ ሳይሆን በገጽ መረዳት የቻለ ሰው ነው፡፡ አፍ አውጥታ ከጠየቀችው አልፎ፣ ከውስጧ የደበቀችውን ሰምቶ መረዳት ችሏል፡፡ ፊቷ ላይ ምሬት አንብቧል፡፡ መላ ሁኔታዋ ላይ ደስታ ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ባይተዋርነት ተመልክቷል፡፡ ይህቺ ከፊትለፊቱ የቆመች ሴት፣ እንደነዚያ ባንኮኒው ስር ቁጭ ብለው ሲያሽካኩ እንደሚያያቸው ሁለት የስራ ባልደረቦቿ አይደለችም፡፡ ቢያንስ እንደነሱ የውሸትም ቢሆን እየሳቀች ኑሮን ለማሸነፍ የሚሆን አቅም የላትም፡፡
“መላ ነገሯን ሳየው፣ ያለቦታዋ ያለች ሴት እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ ቡና ቤቷ ውስጥ የነበሩት ሌሎች ሁለት አስተናጋጆች፣ ዕጣ ፈንታቸውን በጸጋ የተቀበሉ ይመስላሉ፡፡ እሷ ላይ ግን የሆነ ነገር አነበብኩ፡፡ አለ አይደል የሆነ የተደበቀ ነገር…” ይላል ኢይሻ ሃዳስ በወቅቱ ስለተከሰተው ነገር ሲያስታውስ፡፡ እግር ጥሎት በምሽት ወደ ቡና ቤቷ ጎራ ያለው ሃዳስ፣  መጠጡን ችላ ብሎ ቀልቡን ወደዚህች ልጅ እግር አስተናጋጅ ያደረገውም ሆነ፣ ጥቂት አግባብቷት ካሜራውን መዝዞ ቃለመጠይቅ ያደረገላት፣ ይሄን የተደበቀ ነገር ፍለጋ ነው፡፡
ሲቃ እየተናነቃት ታሪኳን በሙሉ ዘክዝካ ነገረችው፡፡ ነግራው ስትጨርስ አይኖቿ እንባ እንዳቀረሩ አቀርቅራ ዝም አለች፡፡
“እኔ እምልሽ ሶፊያ… የሆነ ገንዘብ ብታገኚ ምን መስራት ነው የምትፈልጊው?” ሲል ድንገተኛ ጥያቄ ሰነዘረላት ሃዳስ፡፡
“መማር!... ተምሮ ነርስ መሆን!!” ለእንዲህ ያለ ድንገተኛ ጥያቄ ቆጥባ ያስቀመጠችው መልስ ያላት ይመስል ፈጥና መለሰች፡፡
እስራኤላዊው እንግዳ ለራሱ ቃል ገባ፡፡ ከዚህ ሲኦል የሆነ ኑሮ ሊያወጣትና ወደ ህልሟ ደግፎ ሊያደርሳት ወሰነ፡፡ ያቋረጠችውን ትምህርት አጠናቅቃ ኮሌጅ እስክትገባ ድረስ ወርሃዊ ወጪዋን እንደሚሸፍንላት ነገራት፡፡ ይህን የሚያደርገው ግን ከዚህ አሰቃቂ የቡና ቤት ስራ በአፋጣኝ ከወጣች ብቻ መሆኑን አስረዳት፡፡
ሶፊያ ድንገት እግር ጥሎት የመጣን አንድ የማታውቀው ሰው አምና፣ የአስተናጋጅነት ስራዋን ለመልቀቅ ከብዷት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን፣ ከዚህ ስራ የምታጣው ነገር እንደማይኖር ስለገባት በሃሳቡ ተስማማች፡፡ ስራውን እንደምታቆም፣ ትምህርቷን እንደምትቀጥል በአንዲት ቁራጭ ወረቀት ላይ አስፈረማት፡፡
በነጋታው ጧት…
እስራኤላዊው መንገደኛ ልብሶቿን በአሮጌ ፌስታል የሸከፈችውን ሶፊያን አሳፍሮ በ300 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኝ ሰፋ ያለች ከተማ መኪናውን ሲያሽከረክር ታየ፡፡
እዚያች ከተማ ደርሰው ነገሮችን ካመቻቸላት በኋላም፣ ለጊዜው ለአንዳንድ ወጪ መሸፈኛ የሚሆናት 300 ዶላር ሰጥቷት፣ በየወሩ ገንዘብ እንደሚልክላት ቃል ገብቶላት አድራሻውን ሰጥቷት ተሰናበታት፡፡ ቃል አክባሪ ይሁን ቀልማዳ እርግጠኛ ያልሆነችበትን የሰው አገር ሰው ከልቧ አመስግናውና ቸር እንዲያደርሰው ተመኝታለት ተለየችው፡፡
ሃዳስ እውነቱን ነበር፡፡
 የገባውን ቃል የሚያከብር ትልቅ ሰው ነው፡፡ ሃዳስ ለቃሉ የሚታመን እውነተኛ ፈረንጅ ነው፡፡ ሶፊያን ተሰናብቶ ወደ እስራኤል ከተመለሰ በኋላም፣ ስለ ሶፊያ ማሰቡን አላቆመም፡፡ የገባላትን ቃል ከመፈጸም ወደ ኋላ አላለም፡፡ ወር ከወር እየጠበቀ ለሶፊያ አንድ መቶ ዶላር መላኩን ቀጠለ፡፡ ሶፊያም ትምህርቷን ቀጠለች፡፡
ሶፊያና ሃዳስ ቢራራቁም አልተለያዩም፡፡ በየጊዜው ይጻጻፋሉ፡፡ ኢ-ሜይል ይደራረጋሉ። ትምህርቷን በጥሩ ሁኔታ እየተማረች እንደሆነ ትነግረዋለች፡፡ በደስታ ይፈነጥዛል፡፡ በርቺ ይላታል።
በዚህ ሁኔታ ዘጠኝ አመታት አለፉ…
ስለ ሶፊያ ያጫወታቸው የሃዳስ ጓደኞች ነገሩ አልጣማቸውም፡፡  “ይሄን ያህል አመት ምን የሚሉት ትምህርት ነው?  ወዳጄ  የምትላት ሴት ትምህርት ማለቂያ ያለው አይመስልም! ዝም ብለህ ነው ገንዘብህን የምትገፈግፈው! ” በማለት እየተጃጃለ መሆኑን ሊነግሩት ሞከሩ፡፡
እሱ ግን ለእንዲህ ያለው ወሬ ጆሮ መስጠት አልፈለገም፡፡ እርግጥ ዘጠኝ አመት ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ሶፊያ ትምህርቷን ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ፈጅቶባታል፡፡ እሱ ግን  በእርግጥም ትምህርቷን እየተከታተለች እንደሆነ የሚያረጋግጥበት መንገድ አልነበረውም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ ሃዳስ በወሬና በጥርጣሬ ተነስቶ ቃሉን ማጠፍ  አልፈለገም፡፡ ገንዘብ መላኩንም አላቋረጠም፡፡
የሆነ ቀን…
ሃዳስ ከሶፊያ የተላከ ኢ-ሜይል ደረሰው፡፡
“እንኳን ደስ አለህ ሃዳስ!... በቅርቡ በፋርማሲ በዲግሪ እመረቃለሁ!...” ይላል መልዕክቱ፡፡ ሃዳስ መልዕክቱን አንብቦ እንደጨረሰ በደስታ ፈነደቀ። ከአቅሙ በላይ የሆነ፣ ሊሸከመው አቅም ያጣለት፣ ሊቋቋመው የቸገረው ደስታ ውስጡን አጥለቀለቀው።
ሃዳስ ከኢትዮጵያ ለተላከለት የሶፊያ የኢ-ሜይል መልዕክት ምላሽ አልላከም - ራሱ ወደ ሶፊያ መጣ እንጂ!
የምረቃዋ እለት…
“… በአጠቃላይ ታሪኩ ይሄው ነው፡፡ ሶፊያ በድጋሚ እንኳን ደስ አለሽ!!” በማለት ንግግሩን ቋጨ - ኢሻይ ሃዳስ፡፡
ይሄን ተከትሎ… ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው የዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር በጭብጨባ ተናወጠ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች፣ የዕለቱ ተመራቂዎች፣ የተመራቂዎች ቤተሰቦች… ሁሉም በደስታ እንባ ተራጩ፡፡  ሁሉም በየራሱ መደሰቱን ትቶ፣ በሁለቱ ደስታ ፈነደቀ - በኢትዮጵያዊቷ ተመራቂ በሶፊያና በእስራኤላዊው እንግዳዋ በኢሻይ ሃዳስ፡፡
ከምረቃው በኋላ…
ሶፊያ ለመንፈስ አባቷ ለሃዳስ ሌላ የምስራች አበሰረችው - “የልጅ እናት ሆኛለሁ!”
ሃዳስ የሰማውን ለማመን ተቸግሮ እያለ፣ የሶስት አመት ድንቡሽቡሽ ህጻን ድክድክ እያለ ወደ እሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ የሶፊያ ልጅ ነው፡፡
“ልጅ መውለዴን ለምን እንዳልነገርኩህ ታውቃለህ ሃዳስ?… ያኔ ቡና ቤቷ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንገናኝ ፣ ትምህርቴን ሳልጨርስ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ እንደማልገባ ቃል ገብቼልህ አልነበር?!... ቦይ ፍሬንድ መያዜንና ማርገዜን ብነግርህ ቃል አባይ ናት ብለህ እንዳትከፋ ሰግቼ ነው የደበቅሁህ!... ከቦይፍሬንዴ ካረገዝኩ በኋላ ትዳር እንድንመሰርት ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር፡፡ እኔ ግን እምቢ አልኩት!... ምክንያቱም ትምህርቴን ሳልጨርስ ትዳር አልይዝም ብዬ ቃል ገብቼልሃለሁ!... አልተቀየምከኝም አይደል ሃዳስ?” አለች ሶፊያ ልጇን አቅፋ ወደ ሃዳስ እየተጠጋች - ፈገግ እንዳለች፡፡
ሃዳስ እንዳልተቀየማት በፈገግታ ፀዳል የፈካው ፊቱ ነገራት፡፡
“በፍጹም አልቀየማትም!... እሷ’ኮ… በሰው ልጅ ላይ ያለኝን እምነት እንዳላጣ  ያደረገችኝ ትልቅ ሰው ናት!...” ብሏል እስራኤላዊው ኢሻይ ሃዳስ፡፡

Read 26174 times