Saturday, 15 February 2014 13:05

ደራስያን ማህበር በሁለት መድረኮቹ ምን አከናወነ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

          “ደራሲ፣ አከፋፋይና አዟሪ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መፃሕፍት የተካሄደው ውይይት ለኢትዮ ደራስያን ማህበር አዲሱ አመራር የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ነበር፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተጋበዙበት በዚህ የውይይት መድረክ፤ የመፃሕፍት ስርጭትን ተግዳሮት በሚመለከት ለውይይት መነሻ የሚሆን ሐሳብ ያቀረቡት ደራሲና ጋዜጠኛ ደሳለኝ ሥዩም ናቸው፡፡
በቀድሞ የአገራችን የድርሰት ታሪክ፤ ደራሲያን ሥማቸው በመጽሐፋቸው ላይ እንዳይወጣ እስከ ማድረግ የሚደርስ ትህትና እንደነበራቸውና ለአእምሮ ጭማቂ ውጤት ዋጋ የመጠየቅ ባህል እንዳልነበረ ያስታወሰው ደሳለኝ ስዩም፤ በወቅቱ በቀናነት የተፈፀመ ቢሆንም፤ ቆይቶ ግን ያስከተለው ጉዳት ቀላል አይደለም ብሏል፡፡ አንባቢያን የመጽሐፍን ዋጋ ዝቅ አድርገው እንዲገምቱ ያደረጋቸው አንድም በዚህ ምክንያት ነው ሲል አስረድቷል፡፡
ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተቋማት ወንበርና ጠረጴዛ ለመግዛት በሚጨነቁት መጠን መፃሕፍት ለመግዛት የማይጓጉበት ምክንያት፤ ቀበሌዎች ለወጣቶች መዝናኛ ሲያደራጁ መፃሕፍት አሰባስበው ወደ ማዕከሎቹ ለማስገባት ዝቅ ያለ ትኩረት የሚሰጡት…የቆየው ልማድ በፈጠረው ተጽዕኖ መሆኑንም ደራሲና ጋዜጠኛ ደሳለኝ አመልክቷል፡፡
ይህ ችግር ባልተቀረፈበት፣ የአገሪቱ የሕትመት ኢንዱስትሪም በሚገባው መጠን ባላደገበት፣ የሚታተሙት መፃሕፍት በብዛትም ሆነ በጥራት በማይቀርቡበት ሁኔታ ደራሲው ያስቀመጠውን ዋጋ እየፋቁ አዲስ ዋጋ መለጠፍ የዘርፉ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  መሆኑን ከማነጋገር አልፎ የዕለቱ የውይይት መድረክ እንዲሰናዳ ምክንያት መሆኑን ዳሰሳ አቅራቢው ካመለከተ በኋላ “ማሳያዎቼ” ያላቸውን መረጃዎች አቀረበ፡፡
የ32 ብሩ መጽሐፍ 3 ቁጥርን ወደ 8 በመለወጥ 82 ብር እንደተባለ፤ 18.70 የተቀመጠለትን ዋጋ ከነጥብ በፊት ያለውን ቁጥር በማጥፋት 70 ብር ለመሸጥ እንደተሞከረ፤ የ25 ብሩ መጽሐፍ ላይ ከፊቱ ዜሮ በመጨመር በ250 ብር ሲሸጥ ማየቱን ደሳለኝ ስዩም ገልጿል፡፡ ይህንን አሰራር ተቃውመው በጋዜጣ የፃፉና በሬዲዮ የተናገሩ ደራሲያንን ሥራ ላለማከፋፈልና ላለማዞር ተስማምተው የተማማሉ ነጋዴዎች እንዳሉም በዳሰሳ ጽሑፍ አቅራቢው ተመልክቷል፡፡
ዋጋቸው ለመፋቅ ምቹ ያልሆኑ መፃሕፍትን ለመያዝ አዟሪዎች ፍላጐት እንደሌላቸው፤ በዚህም ምክንያት ደራሲያን የመጽሐፍ ዋጋ ሲወስኑ ለመፋቅ ምቹ እንዲያደርጉት በአከፋፋዮች እንደሚነገራቸው  ዋጋውን ብቻ ሳይሆን የመጽሐፉ ሽፋን መያዝ ስላለበት ምስልና ቀለም ወሳኞቹ እነሱ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፆ ዳሰሳውን ካጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሸሩ፡፡
በአገራችን ብዙ ነገር ሲጨምር የመፃሕፍት ዋጋ ባለበት ነው የቆመው፡፡ 40.90 ዋጋ የተቀመጠለት መጽሐፍ፤ 40ው ተፍቆ በ90 ብር የሚገዛ ካለ የገዢ አቅም እንዳለ ነው የሚያመለክተው፡፡ ሌሎች ከሚወስኑልን እኛ ለምን ቀድመን አናስተካክልም?
በእኛ አገር ግብይት የመከራከር ባህል ስላለ፣ መጽሐፍ አዟሪዎችን ዋጋ ፍቀው አዲስ እንዲለጥፉ ያደረጋቸው ይህ ልማድ ነው፡፡
የቀድሞ ዘመን መፃሕፍት ከገበያው በመጥፋታቸው ምክንያት ከመጀመሪያ ዋጋቸው በብዙ እጥፍ የጨመረ ዋጋ እንዲለጠፍባቸውና እንዲጠራላቸው ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በገበያው የሚፈለጉ መፃሕፍት አሳትሞ ለአንባቢያን የሚያደርስበትን ዘዴ ቢፈልግ…
ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፤ ደራሲያን በሥራቸው እንደማይጠቀሙት ሁሉ አከፋፋዮችም አዟሪዎችም ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ለትንሽ “የአርከበ ሱቅ” በወር ከ3ሺህ ብር በላይ ኪራይ ከፍለው መጽሐፍ ነግደው ለመኖር የሚጥሩ አሉ፡፡ መጽሐፍ አዟሪዎችም ከሕግና ደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሳደዱ ነው የሚሰሩት፡፡
አሁን ለተፈጠረው ችግር ብቸኛ ተጠያቂ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዘርፉ የተፈጠረውን ተግዳሮት እያዩ፤ አዟሪዎች ለመፋቅ የሚመቻቸውን ዋጋ በመጽሐፋቸው ላይ የሚያሰፍሩ ደራሲያን አሉ። መጽሐፉ ላይ 40 ብር ከ95 ሣንቲም የፃፈ ደራሲ አስቦበት ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል፡፡
አንዱ ከተጐዳ ችግሩ ሌሎች ዘንድም መድረሱ አይቀርም፡፡ በተለይ የደራሲያንን ተሰጥኦ የሚጐዳ ነገር ለመጽሐፍ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰብን ንቃተ ህሊና የሚያንጽ ምንጭም ነው የሚያደርቀው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትልቅ ችግር ለመቅረፍ የደራሲያን፣ የአሳታሚዎች፣ የአከፋፋዮችና የአዟሪዎች ጠንካራ ማህበራት መመስረትን ይጠይቃል፡፡ ይሄን ካደረጋችሁ አሁን እየተነገረ ያለው ችግር ብቻ ሳይሆን የወረቀት ዋጋ ውድነት ማስቀነስን ጨምሮ መንግሥት ባወጣቸውና በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ላይ ጫና ማሳደር ይቻላችኋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችና አስተያየት ከተንሸራሸረ በኋላ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ ችግሩን የሚመሩት ማህበር ብቻውን መቅረፍ እንደማይችል አመልክተው ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዋቀር ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ ተሰብሳቢዎችም በሀሳቡ ስለተስማሙ፣ ከመፃሕፍት ጋር በተያያዙ ከሚሰሩ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርስቲ፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከፖሊስ፣ ከመከላከያ…የተውጣጡ ተወካዮችን በመምረጥ ጉባኤው ሲጠናቀቅ ኮሚቴው የሚደርስበትን ውጤት፤  ማህበሩ እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቶ ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ያሰናዳው ሌላው መድረክ፤ ባለፈው ማክሰኞ ጥር  27 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የተከናወነ ሲሆን፤ ፕሮግራሙም ደራሲ መስፍን ሃብተማርያምን የሚዘክርና በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከተው አስተጽዋኦ ዕውቅና ያለመ ለመስጠት ነበር፡፡
አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የአመራር ኃላፊነቱን ከተረከበ 4 ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፤ ለ2006 ዓ.ም ተግባራዊ ሊያደርግ ካቀዳቸው ፕሮግራሞች መካከል በሕይወት ያሉና የሌሉ ደራስያንን መዘክርና ዕውቅና መስጠት ነው ያሉት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ ቀዳሚውን መድረክ ለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም በመስጠት መጀመራቸውንና በዚህ ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ የሚሆኑ ሦስት መድረኮች ለማሰናዳት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በበኩላቸው፤ “በደቦ ያዘጋጀነው ነው” ያሉትን የደራሲ መስፍን ሃብተማርያም የሕይወትና የሥራ ታሪክ አቅርበዋል፡፡ “የአንድ ደራሲ ታሪክ የአንድ አገርና ሕዝብ ታሪክ ነው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ “ሁለገቡ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ መስፍን ሀብተማርያም ከሕዝብ ሳይነጠል፣ ወደ ኋላም ቀርቶ ሕዝብ ሳይጐትተው፣ ከፊት እየቀደመ ሕዝብን ያስተማረ ነው” በማለት አድንቀውታል፡፡
“ብሔራዊ ጀግኖች ይኑሩን” በሚል ርዕስ ቀጣዩን ንግግር ያቀረቡት መጋቢት ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ሲሆኑ “ከዚህ ቀደሙ ልምዳችን እንደታየው የሞተን የምናመሰግነው የቆመውን ለማበሳጨት ነው” በማለት የመደናነቅና የመከባበር ችግር እንዳለብን በቀልድ እያዋዙ ገልፀዋል፡፡
 የጋራ ዛፍ፣ ሜዳ፣ ወንዝ…እያለን በጋራ የምናከብረው ብሔራዊ ጀግና እንዴት እናጣለን? ሲሉ የጠየቁት መጋቢ ሃዲስ፤ ገበሬዎቿን የምትሸልም አገር ለሰው ልጅ ዕውቀት መዳበር ትልቁን ሚና የሚጫወተውን ደራሲ መዘንጋት ተገቢ ነው ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ደራሲ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ የሰውን ልጅ ብልሹና አውሬ ፀባይ ለማረቅ የሚጥር ነው ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ “አእምሮ የሰው ልጅ መመሪያ የሚመነጭበት ማዕከላዊ እዝ ነው፤ በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር አእምሮን ዙሪያውን በአጥንት በተሸፈነ ቦታ ያኖረው፡፡ ደራሲያን ደግሞ ባለ ልዩ አእምሮ ናቸው” ብለዋል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ የሚባሉ የቅኔ ሊቅን ጠቅሰው “የቀድሞውን እያመሰገንን በሄድን ቁጥር ለመጪውም ይተርፈናል” ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ አፄ ቴዎድሮስን፣ ዮሐንስን፣ ምኒልክን አገራዊ ማድረግ ትተን የመንደር ጀግኖች ለማድረግ መትጋታችን ትክክል አይደለም ካሉ በኋላ ቀዳሚው ኋለኛውን የሚያለሰልስ፣ የሚሞርድ ብርጭቆ ወረቀት መሆኑን አንዘንጋ በማለት አሳርገዋል፡፡
ዕውቅናና አክብሮት ለመስጠት በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በተመረጠው በደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ሥራዎች ላይ ሁለት ወጣት ምሁራን ጥናታዊ ሥራቻቸውን ያቀረቡበት ቀጣዩ ፕሮግራም ነበር፡፡ ባዩልኝ አያሌው ባቀረበው ጥንታዊ ፅሁፍ “መስፍን ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ሐያሲ፣ የዘመናዊ ወግ ፀሐፊ፣ ጋዜጠኛ” መሆኑን ገልፆ “ወግ ምንድነው? ባሕሪያቱስ?” በሚል  በመስፍን ሀብተማርያም ሥራዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን አስቃኝቷል፡፡
የፒኤችዲ ተማሪው ገዛኸኝ ፀጋው በበኩሉ፤ “በመምህርነት ሙያ እንዳቅሜ ከገጠር እስከ ከተማ እየተዟዟርኩ ሳስተምር ካስተዋልኩት ነገር አንዱ መስፍን ሀብተማርያም ወግ መፃፍ የሚችሉ ብዙ የልጅ ልጆችን ማፍራት መቻሉን ነው” ካለ በኋላ፤ ከ1951 -1960 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይቀርቡ የነበሩ “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” እና ደራሲ መስፍን ሃብተማርያም የነበራቸውን ግንኙነት የሚያስቃኝ ጥናቱን አቅርቧል፡፡ “በዘመኑ የቀረቡት የመስፍን ግጥሞች ወጣቶች በብዕር ያደርጉት የነበረውን ትግል አቅጣጫ ወደ ሌላ የመራ ይመስለኛል” በማለትም አጠቃሏል፡፡
ቀጣዩ ንግግር አቅራቢ የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ሲሆኑ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጥቅስ በማስቀደም ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡ “መጀመር ቀላል ሲሆን መጨረስ ከባድ ነው፤ ሊያስመሰግን የሚገባው መጨረስ ነው እንደተባለው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዛሬ የጀመረው ሳይሆን ይበልጥ የሚያጓጓው፤ መድረሻና ዘለቄታው ነው፡፡ ይህ ጅማሬ ተቋማዊ ሆኖ በሚቀጥለውስ ማን ይሆን የሚሸለመውና ዕውቅና የሚሰጠው? የሚል ጉጉት በሕዝብ ዘንድ ለመፍጠር በትጋት መስራት እንዳለባችሁ አደራ እላለሁ፡፡”
ዕውቅናና ሽልማት ከተሰጠው በኋላ ደራሲ መስፍን ሃብተማርያም በበኩሉ፤ “በአሁኑ ጊዜ በሕመም ምክንያት የተጐዳሁ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት መድረክ አዘጋጅታችሁ ስታበረታቱኝ፣ መልካም ምኞት ስትገልፁልኝ፣ ቅንነታችሁን ስላሳያችሁን ተበረታትቻለሁ” በማለት አመሰግኗል።
የደራሲ መስፍን ሀብተማርያምን ያልታተሙ ሥራዎች ለአንባቢያን ለማድረስ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሚችለውን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ቃል በተሰጠበት በዕለቱ ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛና ገጣሚ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን የ1000 ብር ስጦታ ለደራሲ መስፍን ሀብተማርያም አበርክቷል፡፡ የመድረክ ዝግጅቱ በሙዚቃና ወጣቶች ባቀረቧቸው የተለያዩ ግጥሞች የደመቀ ነበር፡፡   



Read 3416 times