Saturday, 15 February 2014 12:47

የዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊነት?!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

         በ፲፭፺፪ ዓ.ም ግድም የተወለደው ዘርአ ያዕቆብ የጠየቀው ጥያቄ ነው ይህ “ሰዎች ስለምን ይዋሻሉ?” ብዬ አሰብኩ።” ዘርአ ያዕቆብ ጽኑ የምርምር መንፈስ ውስጥ ሁኖ ይኼንን ጥያቄ ያምሰለስላል። “ምናልባትም የሚያገኙት አንዳች ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል፤ አሊያም ከሰዎች ዘንድ ከበሬታን እናገኛለን ብለውም ያስቡ ይሆናል” ባይ ነው ዘርአ ያዕቆብ። “ወሐሳዊ ብእሲሰ ዘየኀሥሥ ንዋየ አው ክብረ በኀበ ሕዝብ ለእመ ይረክብ ዘንተ በፍኖተ ሐሰት ይትናገር ሐሰት እንዘ ያስተማስሎ ጽድቀ።” ለዘርአ ያዕቆብ የገንዘብ ፍቅርና /ከንቱ ውዳሴ/ ከፍተኛ የስህተት ምክንያቶች ናቸው፤ ምክንያቱም ቁልቁል በሐሰት ጎዳና ያንደባልሉናልና። ውሸቱን እውነት አስመስለው እያወሩ፣ ክብርንና ገንዘብን ለማግኘት ይቋምጣሉ ይለናል።
ክርስቶስ የተፈተነባቸው የኃጢያት ዋናዎች የሚባሉት ፍቅረ ንዋይ (የሥልጣን ፍቅር፣ከንቱ ውዳሴ)፣ ትምክህት እና ስስት ናቸው። እነዚህ ምግባራት የስህተቶች ሁሉ አለቆች እንደሆኑ ተደርገው ይታሰባሉ፤ በኢትዮጵያዊያን ጥንታዊ ባህል። አንዳንዶቻችን እውቀቱ ሳያንሰን ንባቡ ሳይጎድለን፣ ከእነዚህ መርዛም ማሰናከያዎች መጠበቅ ይሳነን እና ቁልቁል የሐሰትን ጎዳና እንደባለላለን። ብዙዎች ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጭ ለመሸፈን ሲሉ የማያምኑበትን ሥራ እየሰሩ፤ ʽለምን የማታምንበትን ሰራህ ሲባሉ “ምን ይደረግ? የኑሮ ጉዳይ ነውʽ ይላሉ። በመጠኑ መኖር ሲቻል ገንዘብ ካገኘሁበት ምን ቸገረኝ የሚባለው ጉዳይ እዚህ ጦስ ውስጥ ይከትታል። የሥልጣን ጉዳይን መቼም ነጋሪ አያስፈልገንም፤ ይኸው እለት እለት ይጠብሰናል። ስስት ዛሬ ላይ መልኳን ቀይራ መንገድ ቅድሚያ ለመሰጠጣጠት እንኳን ፋታ የማታስገኝ ሆናለች። ዘርአ ያዕቆብም “ለሰዎች ለምን ይዋሻሉ?” ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፣ ከኃጢያት ዋናዎቹ ካልናቸው ጋር ተመሳሳይ ነው (ኢትዮጵያዊ አይደል እርሱስ)።
ከዛሬ አራት መቶ አመት ግድም የኖረውን ዘርአ ያዕቆብን በስድስት ʽግልብʽ መሞገቻ ሐሳቦች ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ለሚከትቱ ሰዎች ምላሽ ማቅረብን ወደድኩ።
፩) ለሦስት ወር ዳዊት፣ ለአራት አመት ቅኔ እና ለአስር አመት ደግሞ የመጽሐፍትን ትርጉም ተማርኩ ይለናል የአክሱሙ ልጅ ዘርአ ያዕቆብ። እንግዲህ ይታያችሁ… በአብነት ትምህርት ከውሻ እና  ከችጋር (እከክ) ጋር እየታገለ ከአስራ አራት አመት በላይ መከራውን የሚታገስ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ በስተቀር ማንም እንዳልሆነ ታሪካችን ምስክር ነው። ገና ከጅምሩ እድሜዬ ለትምህርት እንደ ደረሰ አባቴ ለመምህር ሰጡኝ ሲለን እኮ፣ የዛኔዋን ኢትዮጵያን ባህል እንጅ፤ አውሮጳማ ʽዘመናዊʽ ትምህርትን ከጀመረችው ሰነባብታለች።
፪) «ወጥንተ ሙላድየሰ እምካህናቲሃ ለአክሲም። ወባእቱ ተወለድኩ አነ ተወለድኩ እም፩ ነዳይ መስተገብር ውእተ አድያመ አክሱም።» ዘርአ ያዕቆብ በቀላል ግዕዝ ስለ ራሱ ውልደት እና ዘር እንዲህ ነው የገለጠው። ከካህናት ዘር ከደሃ ቤተሰብ፣ በአክሱም ከተማ ተወለድኩ እንደ ማለት ነው ትርጉሙ። እንግዲህ ዘሩን ከካህን የሚጠቅስ አክሱም የሚወለድ የደኃ ልጅ የሚሆን ሮማዊ/አውሮጳዊ ከተገኘ እሰየው ነው። ግን ይኸም ኢትዮጵያዊ ለሆኑት እንጅ ለማንም አይቻልም።
፫) የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡት አንዳንድ ሰዎች፣ የሃሳቡን አደረጃጀት እና አቀራረብ ከአውሮጳዊያን በማመሳሰላቸው የተነሳ ነው። ነገር ግን የዘርአ ያዕቆብን የሐሳብ ክረት (ጥንካሬ) ብናየው፣ በየቅኔ ቤቱ ከሚነሱ ሙግቶች ጋር ሲወዳደር ʽእዚህ ግባʽ የማይባል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ዘርአ ያዕቆብ እንኳን ከኢትዮጵያዊያን ፍልስፍና በልጦ ሊያስንቅ እና የባዕድ ሰው ነው ሊያስብለው ይቅርና በየቅኔ ማህሌቱ መድረክ ሊያሳጣው የሚችል ጉዳይ ነው። ነገር ግን እንደ ካናዳዊው ፕሮፌሰር ክላውድ (ገላውዴዎስ) ሰምነር የመሰሉ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ እድሜያቸውን የፈጁ ተመራማሪዎች፣ የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ አያስገቡትም።
፬) ሌላው አስገራሚው ጉዳይ ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ባይሆን ኖሮ (አውሮጳዊያን ካቶሊካዊያን ስለሆኑ) እንዴት እነ ዮሐንስ ካቶሊካዊ ከሆነው ከንጉሥ ሱስንዮስ ጋር አጣልተውት  ወደ ዋሻ ይሄዳል፤ ሰዎቹ እንደ ሚሉት አውሮጳዊ ቢሆን ኖሮ ʽወደ ቀይባህር ሸሸሁʽ አይልም ነበር እንዴ?
፭) ዳዊቱን አንግቦ መሰከዱ ፍጹም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያሳያል፤ ምክንያቱም በባህላዊ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ መዝሙረ ዳዊት እራስንም፣ሃገርንም፣ቤተሰብንም መጠበቂያ የጸሎት መጽሐፍ ነውና። ምንም እንኳን በቃላችን ብናጠናው ከስህተት እና ከግድፈት ለመዳን ፊደሉን ከመጽሐፉ እያነበቡ መጸለይ ልማድ ነው። s
፮) ለብዙዎች ፈረንጆች ያሳደዱት መነኩሴ እመስላቸው ነበር፤ ይለናል ዘርአ ያዕቆብ። ይህንን የሚለን ከስደቱ ከተመለሰ በኋላ ነበር። ዘርአ ያዕቆብ ከስደት የተመለሰው ሱስንዮስ ከሞተ በኋላ ፋሲል ከነገሰ በኋላ መሆኑ ይታወቃል። በፋሲል ዘመን ደግሞ በታሪክ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈረንጆች አባርራ በሯን ሁሉ ለባእዳን የዘጋችበት ዘመን ነበር። ይህ ከሆነ እንዴት አውሮጳዊው ዘርአ ያዕቆብ በፋሲል ዘመን በሰላም ከዋሻ ወጥቶ እንፍራንዝ ውስጥ ሊኖር ቻለ? ከእርሱ አንደበት እስኪ እንስማ፦ «ወበ፲፻ወ፮፻ወ፳፭ {1625} አመተ እምልደቱ ክርስቶስ ሞተ ሱስንዮስ ንጉሥ ወነግሠ ወልዱ ፋሲለደስ ህየንቴሁ ወውእቱሰ አፍቅሮሙ ቅድመ ለፈረንጅ በከመ አቡሁ ኢሰደዶሙ ለግብጻዊያን ወኮነ ሰላም ውስተ በሐውርተ ኢትዮጵያ። አሜሃ ወጻእኩ እምግብየ ወሖርኩ ቅድመ በሐውርተ አምሐራ…» እግዜር ያሳያችሁ፤ሰ እንግዲህ ፈረንጆች እና ሱስንዮስ ተባብረው ብዙ ኢትዮጵያዊያን መነኮሳትን እና የሃይማኖት አባቶችን ካሳደዱና ከገደሉ በኋላ ፋሲለደስ ነገሰ (ሃይማኖት ይመለስ፤ ፋሲል ይንገስ የሚለውን መፈክር አስታውሱ)። ፋሲል ሲነግስ ሃይማኖት ተመለሰ፤ የተሰደደ መነኩሴም የሃይማኖት አባትም ወደየ ገዳሙና አጥቢያው ተመለሰ። ይህንን ዜና የሰማው ድንጉጡ ዘርአ ያዕቆብ ከዋሻው ወጣና ወደ ጎጃም መጓዝን ፈለገ ነገር ግን መንገድ ላይ እንፍራንዝ ሲደርስ ለነፍሱ የሚስማማው ቦታ እግዚአብሔር አመላከተው እና አቶ ሀብቱ ቤት ተጠለለ። እንፍራንዝ እስኪደርስ ድረስ ግን በየመንገዱ ስደተኛ መነኩሴ እየመሰላቸው ሰዎች ሁሉ ያዝኑለት እንደነበረና ልብስና ምግብ ይሰጡትም እንደ ነበር ይተርክልናል።
እንዴው ለመሆኑ ብራና ዳምጦ ቀለም በጥብጦ መጽሐፍ የሚጽፍ የአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አውሮጳዊ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ። ዘርአ ያዕቆብ ግን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ እንዲህ ይለናል። «ወበህዳጥ መዋዕል አስተዳለውኩ ቀለመ ወሰሌዳ ወጸሐፍኩ ፩ደ መጽሐፈ ዘመዝሙረ ዳዊት ወእግዝእ ሀብቱ ወኩሎሙ እለ ርእይዋ ለጽሕፈትየ አንከሩ እስመ ሠናይት ይእቲ።»
መዝሙረ ዳዊትን በብራና የሚጽፍ፤ ከዚያም ሲያልፍ የእጅ ጽሕፈትህ ታምራለች እየተባለ መንደሩ ሁሉ ጻፍልን እያለ የሚማጸነው ሮማዊ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማግኘታችን በእውነት አዲስ ታሪካዊ ግኝት የሚያስብል ነው። በታሪካችን እንደምናውቀው የፈረንጅ አስተማሪዎች ውሏቸው ከመኳንንቱ ከሹሟሙንቱ ጋር እንጅ እንደው እንዳልባሌ እንፍራን ውስጥ የአቶ ሀብቱ ባሪያን (አገልጋይ)አግብቶ የገጠር ከተማ ውስጥ መኖር እንዴት ይቻለዋል።
በዚያ በአውሮጳዊያን ዘመነ አብርሆት አንድ አውሮጳዊ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስራ አራት አመት በላይ በየ አብነት ትምህርት ቤት እየተንከራተተ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ትምህርት ሊማር ይችላል?  በዘርአ ያዕቆብ ዘመን እኮ የነበሩት አውሮጳዊያን ኢትዮጵያን ለማሰልጠን፣ ከድንቁርና ለማውጣት የመጡ እንጅ ለኛ ባህላዊ እሴቶች ግድ የነበራቸው እኮ አልነበሩም፡፡ (ዛሬስ ግድ አላቸው እንዴ?)። እውነቱን ለመናገር የዘርአ ያዕቆብ አልባሳት አሊያም ወዙ ያረፈባቸው እቃዎች ተገኝተው፣ የዘረመል (DNA) ምርመራ ተደርጎ አውሮጳዊነቱ ቢረጋገጥ እንኳን ቅዱስ ጊዮርጊስን አሊያም አቡየ ጻዲቁን ኢትዮጵያዊ ያደረግናቸውን ያህል እርሱም ኢትዮጵያዊ ከመሆን አያመልጥም።
እንደው ነገሩን ለማነሳሳት ያህል እነዚህን ጉዳዮችን አነሳኋቸው እንጅ ጠንካራ መሞገቻ ይሆኑኛል ብዬ ተመክቼባቸው አይደለም። አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት የፍልስፍናው መልክ ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ መነጋገር ይቻላል። በእርግጥ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን “ዘርአ ያዕቆብ ያንስብናል፤ የኢትዮጵያን ፍልስፍና አይወክልም” የሚል ድንቅ መሞገቻ አላቸው እሰየው ነው። እነ ቅዱስ ያሬድን፣እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን፣ እነ ተዋኔን በደንብ አጥንተን የህዝብ መወያያ እስከምናደርጋቸው ድረስ ግን ዘርአ ያዕቆብን ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን።
የግዕዝ ጥቅሶች በሙሉ ከዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ መፅሐፍ የተወሰዱ ናቸው፡፡

Read 3400 times