Saturday, 10 December 2011 09:08

ኢህአዴግና የ“አኬልዳማ” አንደምታ መንግስት ህገመንግስቱን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ማክበርም አለበት

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት የዘወትር ጭንቀቱ ተመልካቾቹን ማስተማርና ማዝናናት የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “አኬልዳማ” የተሰኘ ባለሶስት ክፍል አስደማሚ “ዶኪውመንታሪ ፊልም” ለሶስት ተከታታይ ቀናት አቅርቦ “ሲያዝናናን” ሰንብቷል፡፡ በሶስት ክፍል የቀረበው ይሄው ፊልም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ እንደነበረች ያስታውስ፣ ዛሬም የኤርትራ መንግስትና የእሱ ነጭ ለባሽ የሆኑ እንደ ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግ ያሉ ሽብርተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ከተያያዝነው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ሊያደናቅፉንና ሀገራችንንም ዳግማዊ ባግዳድ ለማድረግ ሌት ተቀን እያደቡ እንደሚያድሩ ይተርካል፡፡

የእነሱ ጋሻ ጃግሬ የሆኑ አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና አባሎች እንዲሁም የግሉ ፕሬስ ጋዜጠኞች ደግሞ ህጋዊ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባልነታቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ የአሸባሪ ድርጅቶችን የሽብር አላማ ለማስፈፀም ወዲያና ወዲህ ሲሉ፣ መንግስት እንዴት ቀድሞ እንደነቃባቸውና በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው፣ የተጠርጣሪዎችን “የእምነት ቃል” ዋቢ በማድረግ የሚተርከው ይኸው ፊልም፤ በመጨረሻም መንግስት አጠንክሮ የተያያዘውን የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ህዝቡ እንዲረዳና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግ ይማፀናል፡፡
ይህን “አዝናኝ” ወቅታዊ ፊልም ያቀረበልን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ ፊልሙን ለማዘጋጀት በድርሰት፣ በፊልም ቀረፃ፣ በፊልም አርትኦትና በትረካ ዝግጅቱ ላይ ካደረገው ጥረት ይልቅ ያዘጋጀውን ፊልም እኛ ተመልካቾቹ አንዱም ክፍል ሳያመልጠን እንድንከታልለት ያደረገው ጥረትና ዝግጅት ይበልጣል፡ከዚህ በፊት በኢህአዴግ ተሠርተውና ተዘጋጅተው የቀረቡ የጦርነትና የግጭት ፊልሞችን ልክ እንደ መደበኛ ፕሮግራም በተደጋጋሚ ለህዝብ ሲያቀርብ የምናውቀው ኢቴቪ፤ “አኬልዳማ”ን ከ13 ዓመት በላይ የሆኑ ተመልካቾች ብቻ እንዲመለከቱት የእድሜ ገብ ማስቀመጡ በአዲሱ ዓመት ያሳየው አስደማሚ መሻሻል ነው፡፡
ምንም እንኳን ኢቴቪ ፊልሙን ሲያስተዋውቅ አስፈሪና ሰቅጣጭ አስመስሎ ቢያቀርብልንም ፊልሙ ሲታይ ግን የተባለለትን ያህል አስፈሪም ሰቅጣጭም አልነበረም፡፡ በእርግጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተከሰቱ አደጋዎች (በምልሰት ቴክኒክ የቀረቡ) ሰቅጣጭ ናቸው፡፡ በተረፈ ግን ከፊልሙ ታሪክ አስፈሪነት ይልቅ ይበልጥ የሚያስፈራው የፊልሙ ማስታወቂያ ነበር፡፡ አንዳንድ የፊልም ሃያስያን ይሄን ዶኪዩመንታሪ እንዲሄስ ኢቴቪ ዕድሉን ቢሰጣቸው የ“አስፈሪነት መስፈርቶችን ያላሟላ “አሸባሪ ፊልም” እንደሚሉት ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡
ኢቴቪ ዘንግቶት ይሆናል እንጂ በራሱ ጣቢያ ከዚህ የበለጡ አስፈሪ የጭራቅና የጅብ ተረቶችን እየተረከልን ነው ያደግነው፡፡ ጭራቁ እረኛውን ቀቅሎ ሲበላው፣ አንበሳውና ነብሩ በጉንና ፍየሏን ሰባብሮ ሲበሏቸው፣ ጀግናው አርበኛ የጠላቱን ሚስትና ልጆች በጥይት ገድሎ ቤታቸውን ሲያቃጥልና የመሳሰሉ ቀን ቀን የሚያስፈሩ፤ ሌሊት ሌሊት በጭንቀት የሚያቃዡ ብዙ ተረቶችን ለዘመናት አሳይቶናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይም ያሁኑ በአስፈሪነቱ እምብዛም የተሳካለት አይመስልም፡፡
የፊልሙ አዘጋጆች ምንም እንኳን ፊልሙ መሸከም የማይችለውን ርእስ ቢያሸክሙትም አሸባሪ ርእስ በመስጠት ረገድ የተሳካላቸው ይመስላል - የእብራይስጥ መሰረት ያለውን ቃል ለርእስነት በመምረጥ፡፡ ችግሩ ግን ይሄን ርእስ የመረጡት የቃሉን ትርጉምና መንፈስ ተረድተውት ሳይሆን እንደው ቀልባቸው ስለወደደው ብቻ ስለመሆኑ መገመት እችላለሁ፡፡
የዚህ ዶኪዩመንታሪ ፊልም አዘጋጆች ይሄን ርዕስ መምረጣቸው የሚያስተቻቸው ትርጉሙን ወይም ፍቺውን ለማወቅ ምንም ጥረት አለማድረጋቸውን ስንገነዘብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የላቀ ዕውቀትና ችሎታ የሚጠይቅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ በቀላሉ አንቱ የተባሉ የሀይማኖት ሊቃውንትን በማማከር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በማገላበጥ በቀላሉ የሚገላገሉት ነገር ነበር፡፡ ለነገሩ የአኬልዳማን ቃል መሠረታዊ ታሪክና ፍቺ በቀላሉ ለመረዳት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የእየሱስ ክርስቶስንና የደቀመዛሙርቱን ታሪክ የሚዘክረውን አንዱን የወንጌል ክፍል አንድ ዙር ብቻ ማንበብ በቂ ነበር፡፡
ኢቴቪ የቃሉን ትርጉም በቅጡ ሳይረዳ ለፊልሙ ርዕስ ቢመርጥም እኛ ታዳሚዎቹ ግን ፊልሙን በተመለከተ ከአንዳንድ ጥርጣሬዎቻችን ጋር የገባንን ያህል ገብቶናል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለአመታት አለአንዳች መሠልቸትና አዘኔታ ሲያቀርብልን በኖረው ከህይወታችንም ሆነ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ጨርሶ የማይገጣጠምና ይልቁንም ተቃራኒ የሆነ መረጃና ፕሮግራም የተነሳ እውነትን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብዙ ጊዜ እያጣናት በመኖራችን የተነሳ በ”አኬልዳማ” ተከታታይ ፕሮግራም ውስጥም ያየነውን ሁሉ “ሀሰት” ነው በሚል ጨርሰን ብናጣጥለው አሊያም የመረጃውን እውነትነት ክፉኛ ብንጠራጠረው፣ እንደ ድርጅት ሊከፋብን ቢችልም ለምን እንዲህ አደረጋችሁ በሚል ሊያዝንብን ግን ጨርሶ አይገባም፡፡
አይሁዶች እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥማቸው የሚናገሩት አንድ አባባል አላቸው፡፡ “ከምኩራቡ ጫፍ ትወጣ ዘንድ ያደረገህን መሰላል አያያዝህ፣ የጫፉ ላይ ማንነትህንና የአወራረድ እጣህን ያሳያል” ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጉዳይም እንዲሁ ነው፡፡
የትናንት ጉዞው ለዛሬው እንዲህ ያለ ሀሜትና የአለመታመን እጣ አብቅቶታል፡፡ ይህንን ጉዳይ ታሳቢ በማድረግም ኢህአዴግ በ”አኬልዳማ” ተከታታይ ፊልም ካቀረበልን የፀረ ሽብርተኝነት ጉዳይና ትግል ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ለመረዳት ችለናል፡ከነዚህ ጉዳዮች አንዱ፤ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትነት ተደራጅተው በኢትዮጵያ በሚካሄደው የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ የበኩላችንን እናበረክታለን ከሚሉት ድርጅቶች ውስጥ
በአፍራሽ ሚናቸውና በተሳሳተ አቋማቸው የተነሳ የራሳቸውን የተፈጥሮ የፖለቲካ ሞት እንዲሞቱ የተውናቸውን ድርጅቶች ኢህአዴግ “ጠላት አታሳጣኝ” በሚል ዓይነት ስለት አለአቅማቸው አቅም ሰጥቶ፤ አለልካቸው የትየለሌ አሳክሎና የሌለ ሀይልና ጉልበት ሰጥቶ ግዙፍ የፖለቲካ ሰብዕና አጐናጽፎአቸዋል፡፡ ይሄም ኢህአዴግ የሚመራውን ህዝብ ሁለንተናዊ ማንነት ዛሬም ድረስ መረዳት ያልቻለና የተደናገረ ድርጅት አስመስሎታል፡፡ እንደ ኦነግ፣ ኦብነግም ሆነ ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ ድርጅቶች፤ በሽብር እንቅስቃሴ አላማቸውን ማስፈፀምና ግባቸውን መምታት የማይችሉት፣ ኢህአዴግ እንደሚያምነው “ጀግናው” የኢህአዴግ መንግስት በሥልጣን ላይ በመኖሩ ሳይሆን በሽብር የህዝብን ልብ መማረክም ሆነ ማንበርከክ ስለማይቻል ብቻ ነው፡፡
በ”አኬልዳማ” ፊልም ከቀረበልን መልእክትና መረጃ መረዳት የቻልነው ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ሽብርተኝነትን በተመለከተ በጣም የፈራውና በፍርሃቱም የተሸበረው ራሱ ኢህአዴግ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛ ማስረጃው ደግሞ ሽብርተኝነትን አስቀድሞ መከላከል በሚል ሰበብ የሚወስዳቸውን የሀይል እርምጃዎች፣ የሚያስራቸውንና መልሶም የሚፈታቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጨንቆና ተጠቦ በሶስት ክፍል፤ በድጋሚ የቀረበበት ጊዜ ሳይቆጠር ለሶስት ተከታታይ ቀናት ካቀረበልን የ”አኬልዳማ” ፊልም የተረዳነው ይህንን ነው፡፡
ነገር ግን ከቀደምት ታሪኩ በቀላሉ ለመረዳት እንደቻልነው፣ ከውልደቱ እስከዛሬው የጐልማሳነት እድሜው አንድ ጠላት ሳይፈጥር አንዲት ሌት አድሮ የማያውቀው ኢህአዴግ፤ አለአንዳች የተጠናና የታቀደ ፖለቲካዊ ግብ ቀደም ብለን የጠቀስናቸውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ መልእክቶችን ለማስተላለፍ ብቻ ይህንን ፊልም አዘጋጅቶ አቅርቦልናል ብለን ከደመደምን እንደየዋህ ልንቆጠር እንችላለን፡፡ እንዲህ ያለ የሞኝና የየዋህ ፖለቲካ፣ ኢህአዴግ በታሪኩ እንኳን ተጫውቶት ቀርቶ ሞክሮት እንኳን አያውቅም፡፡ እናም የ”አኬልዳማ”ን ፊልም አዘጋጅቶ በማሠራጨት ኢህአዴግ ሶስት ዋና ዋና የፖለቲካ ግቦችን ለመምታት የተንቀሳቀሰ ይመስላል፡፡ በ”አኬልዳማ” ፊልም ኢህአዴግ ሊያሳካው የፈለገው አንዱ ፖለቲካዊ ግብ፤ የፀረ ሽብር ህጉን በዋናነት በመጠቀም፤ እንደ “አኬልዳማ” አይነት የፕሮፖጋንዳ ፊልም በማሰራጨት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማስፈራራት የእግር መትከያ ቦታ እንዳያገኙ አድርጐ ከህዝብና ከደጋፊያቸው መነጠል እንዲሁም ተቺና ተቃዋሚ የሆነውን የፕሬስ አፍም ፀጥ ማሰኘት ነው፡፡ ሁለተኛው ዋና የፖለቲካ ግቡ ደግሞ እንደ 97 ዓ.ም አይነት አስደንጋጭ የምርጫ ሽንፈት በቀጣዩ ማናቸውም አይነት ምርጫ እንዳያጋጥም ቀድሞ መከላከልና መዘጋጀት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አባላቶቹን አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ መመሪያና አደራ አሸክሞ ካሠማራቸው ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግም ሆነ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በልማታዊ መንግስት መርህ ዘወትር በእድገትና በብልጽግና ጐዳና መራመዳችንን ብቻ በመንገር ጊዜአቸውን ቢያጠፉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀትና የመልካም አስተዳደር እጦት እየተንገላቱ፣ በአስጨናቂ ህይወት ውስጥ እንደሚኖሩ መካድም ሆነ ሸፍኖ መከላከል አልተቻለም፡፡ ታላላቅ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ጊዜ ይቀርብላቸው የነበረውን የህዝብ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሮሮ፣ የምቀኞችና የእነ “በሬ ወለደ” ወሬ ነው በማለት ቢያስተባብሉትም የችግሩ ስፋትና ጥልቀት በራሱ ጊዜ አንዳንዶቹን በምክር ቤቶቻቸው እንዲናዘዙት አስገድዷቸዋል፡ በህዝቡ ላይ የተጫነው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ቀንበርና የመልካም አስተዳደር ችግር በጊዜ ሀይ ካልተባለ መዘዙ ከባድ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ እንዲህ ተቸገርኩ የሚል ህዝብ ደግሞ ጥሪው ሰሚ ጆሮ ሲያጣ የምርጫ ጊዜ ድምጽህን በነፃነት ስጥ የተባለ ቀን ቅጣቱ አያድርስ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ቅጣት በ97 ምርጫ እየተናነቀውም ቢሆን አጣጥሞታል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ አሁን እያደረገው ያለው በምርጫ ቦርድ ያልታወጀ ፀረ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ፀረ ተቺና ተቃዋሚ ፕሬስ የሆነ የማጥላላት የምርጫ ዘመቻ ነው፡፡
ሶስተኛው የኢህአዴግ የፖለቲካ ግብ፤ በፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት እንደዚሁም የግሉ ፕሬስ አባላትን የፍርድ ሂደት አላግባብ ለመጫን፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ሰበብ በተቃዋሚዎችና በጋዜጠኞች ላይ እየወሰዳቸውና ወደፊትም የሚወስዳቸውን የሀይል እርምጃዎች ህዝቡ እንዲደግፈውና ተጠርጣሪዎቹን ከፍርድ ቤት ህጋዊ ስርአት ውጪ በወንጀለኛነት ፈርጆ እንዲፈርድባቸው ሌላ ተጨማሪ የህዝብ ፍርድ ቤት ማቋቋም ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን የፖለቲካ ግብ ለማሳካት አስቦ እንደተንቀሳቀሰና የቱንም ያህል ተሳክቶልኛል ብሎ እንደሚያስብ ለማወቅ ከፈለጋችሁ በዚሁ በዝነኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥናችን የ”አኬልዳማ”ን ፊልም በተመለከተ ከዜጐች የደረሰኝ አስተያየት ነው እያለና እየመረጠ የሚያቀርበውን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡
ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካኝነት ያቀረበልን የ”አኬልዳማ” ፊልም ከዚህ በላይ ያነሳናቸውን አጠያያቂ ጉዳዮች እንዲሁ ይሁኑ ብለን ብናልፋቸው፣ ሳናነሳውና ሳንጠይቃቸው የማናልፋቸው የህግ ጥያቄዎችን ማስነሳቱን ግን ቸል ማለት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ይህን ፊልም አዘጋጅቶ በማሰራጨት አላግባብ ካገኘው ወይም ለማግኘት ከሞከረው የፖለቲካ ጥቅም በተጨማሪ የሀገሪቱን መሠረታዊ የህግ ስርአት ጥሷል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ስርአት ማናቸውም አካል በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ አስመልክቶ እንኳን የፍርድ ቤቱ አሠራር ላይ ተጽእኖ ማድረግ የሚችል ጉዳይ ይቅርና ዝርዝር መግለጫ እንኳ መስጠት በህግ የተከለከለ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካኝነት ባሠራጨው ፊልም፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ወንጀለኛ አድርጐ በማቅረብ ህገመንግስታዊ ህጋዊና ሰብአዊ መብታቸውን ጥሷል፡፡ ጉዳዩን በዋናነነት የያዘው ፍርድ ቤት በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ሳይፈርድባቸው፣ ኢህአዴግ በ”አኬልዳማ” ፊልሙ ራሱ ከሳሽ ራሱ ምስክር ራሱ ፈራጅ በመሆን፣ ተጠርጣሪዎቹን አሸባሪ ናቸው ብሎ በማቅረብ ለተጨማሪ የህዝብ ፍርድ አቅርቧቸዋል፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ታዲያ ጉዳያቸውን በመመርመር ለምን ይደክማል?
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለወትሮው ለጥቃቅን ጉዳዮች ሁሉ የሚጨነቀው ፍርድ ቤት፤ ጉዳያቸውን የሚያይላቸው ተጠርጣሪዎች እንዲህ የመሰለ ህገወጥ የመብት ጥሰት ሲካሄድባቸውና በራሱ በፍርድ ቤቱ አሠራር ላይ ጣልቃ ሲገባ እያየ ምንም አይነት ህጋዊ የተቃውሞ ድምፁን አለማሰማቱ፣ በእውነቱ በጣም የሚገርምና በገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳበት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሌላም ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በ”አኬልዳማ” ፊልም ውስጥ በአሸባሪነት የቀረቡት ተጠርጣሪ ተከሳሾች፤ ሰጡት ተብሎ የቀረበውን ቃል ሲሰጡ ለመሆኑ የህግ ጠበቆቻቸው በቦታው ተገኝተው ነበር? የሰጡትን ቃል የሰጡት ከህግ አንፃር ሊያስከትልባቸው የሚችለው ጥቅምም ሆነ ጉዳት ተገልፆላቸውና ከህግ ጠበቆቻቸው ጋር እየተመካከሩ ነው?
ተከሳሾቹ ተጠርጣሪዎች በፊልሙ ውስጥ ሰጡ ተብሎ የቀረበውን ቃል የሰጡት በፈቃዳቸው ነው ወይስ በሀይልና በተጽእኖ? ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት ይገባናል፡፡ በተለይ ከተከሳሾቹ አንዱ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ “ለበርካታ ተከታታይ ቀናት መርማሪዎች በአካሌና በሞራሌ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል፤ ምግብ ተከልክዬና እርቃኔን ሆኜ እጄ ወደ ኋላ ታስሮ ለበርካታ ቀናት ውሀ እላዬ ላይ እየተደፋብኝ እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር እንድናገር አስገድደውኛል” በሚል ለተከበረው ፍርድ ቤት ያቀረበውን አቤቱታ ስናስታውስ፣ ከላይ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በተለይም ቃላቸውን የሰጡት በፈቃዳቸው ነው ወይስ በሀይልና በተጽዕኖ የሚለውን አብይ ጥያቄ ደግመን ደጋግመን ለመጠየቅ ግድ ይላል፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አመታት ህገመንግስቱ የሁሉም ነገር ቁልፍ የሆነ ህግ መሆኑንና ማናቸውም ዜጋም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ይህን ህገመንግስት ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ሀላፊነት እንዳለበት አበክሮ ሲያስገነዝበን ኖሯል፡፡ ይህ አስገንዝቦት ለትክክለኛነቱ አንዳችም አይነት አቃቂር የሚወጣለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በተግባር ስናየው እንደኖርነው፣ ኢህአዴግ ቀን ከሌት ተጨንቆ እየተጋበት ያለው ማስገንዘቡ ላይ እንጂ የተግባር አፈፃፀሙ ላይ ለእኛና ለራሱ የሚያገለግሉ ሁለት የአፈፃፀም ደንቦች ያሉት ይመስላል፡፡ በሌላ አነጋገር ህገመንግስቱን ማክበርና ማስከበር ያለብን እኛ ብቻ ስንሆን ከኢህአዴግ የሚጠበቀው ግን ማክበር ሳይሆን ማስከበር ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ እንዴት ብትሉ… የመንግስትነት ጉልበቱን ብቻ ተማምኖ በተደጋጋሚ ጊዜ የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች ሲጥስ ለአመታት አይተነው እናውቃለና! በ”አኬልዳማ” ፊልም እንደተደረገው አይነት የዜጐችን ህገመንግስታዊ፣ ሰብአዊና ህጋዊ መብታቸውን የሚጥስ ተመሳሳይ ፊልም፤ ዜጐች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች አዘጋጅተው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለህዝብ እይታ እናቅርብ ቢሉ የሚያገኙት መልስ ለማናችንም ግልጽ ነው፡፡ ለኢህአዴግ ግን በፈለገው ቀንና ጊዜ ሊያደርገው የሚችለው ቀላልና የተለመደ ነገር ነው፡፡ ለምን ቢባል መንግስት ነዋ!
ህጉንና የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች መሠረት አድርገን ጉዳዩን ስንመረምረው ግን ድርጊቱ አይን ያወጣ የመብት ጥሰት ነው፡፡ በዜጐች ላይ የመብት ጥሰት መፈፀም ደግሞ የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች መጣስ ማለት ነው፡፡ የዜጐችን ህገመንግስታዊ መብቶች መጣስ ደግሞ የለየለት የሽብር ተግባር መፈፀም ማለት ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉ መንግስታት አምባገነን መንግስታት ብቻ ናቸው፡፡ የህገመንግስቱን ድንጋጌዎች በማናቸውም መልኩ መጣስ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለአመታት የታገሉለትን የመብትና የነፃነት ትግል በማንአለብኝነት መናቅና ማንቋሸሽ፤ ለትግሉም አካላቸውንና ህይወታቸውን ያለአንዳች ስስት ቤዛ ያደረጉትን ሰማዕታት ዋጋና ክብር መንሳት ማለት ነው፡ ስለዚህ በእርጋታ እያስተዋልን ብንጓዝ ለአገርም ለህዝብ ለመንግስትም ይበጀናል፡፡

 

Read 2531 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:19