Monday, 10 February 2014 07:58

“የማስተምረውን ልስራ፣ የምሰራውን ላስተምር” በማለት እርሻ የጀመሩት ምሁር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

          በአምቦ እርሻ ኮሌጅ በማታው ክፍለ ጊዜ እየተማሩ በእርሻ ሙያ በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ፣ የእርሻ መምህር ሆኑ፡፡ በዚህ ሙያ ለ25 ዓመታት ከልብ ቢያስተምሩም ጠብ ያለ ነገር አላዩም፡፡ ክፍል ውስጥ በንድፈ ሐሳብ (ቲዎሪ) የሚያስተምሩትና በተግባር የሚሰራው በፍፁም አይገናኙም፡፡ እርሻ ያስተማሯቸው ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የአካባቢው ሕዝብ፣ አገሩ በሙሉ በንድፈ ሐሳብ የተማረውን ወደ ተግባር አይለውጥም፡፡ በዚህም በጣም ተናደዱ፡፡
“የማስተምረውን ልስራ፣ የምሰራውን ላስተምር” በማለት መሬት ጠየቁ፡፡ በዚያን ጊዜ አገሪቷ የምታራምደው ርዕዮተ-ዓለም ሶሻሊዝም ስለነበር፣ መሬት ሊሰጣቸው ቀርቶ ጥያቄያቸውንም ያዳመጠ አልነበረም፡፡ ሐሳባቸውን ለማሳካት ያደረጉት ጥረት ቢከሽፍም በ1967 ዓ.ም ለቤተሰብ ወተት ብለው የገዟት ላም፣ ዛሬ ተራብታ  ሚሊዮን ብሮች ማፍራቷን አቶ ጋዲሳ ጎበና ይናገራሉ፡፡
ብዙ ጊዜ የሕግ ባለሙያዎች፣ ሐኪሞች፣ ነርሶች .. ካልሆኑ በስተቀር፣ ቢዝነስም ሆነ ሳይንስ (ባይሎጂ፣ ኬሚስትሪ)፣ ሒሳብ፣ እርሻ፣ …የሚያስተምሩ መምህራን በንድፈ ሐሳብ የሚሰጡትን ትምህርት ወደተግባር ለውጠው፣ ሕይወታቸውን አሻሽለው ኑሮአቸውን ሲቀይሩ አይታዩም፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ጋዲሳ፣ ታላቅ የምሁር አርአያ (ሞዴል) ናቸው፡፡
በ1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ የነበረችበት ሁኔታ ይታያችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ቢዝነስ፣ የግል ኢንቨስትመንት፣ ሕይወት ማሻሻልና ኑሮን መለወጥ፣ … የሚባሉ ነገሮች አይታሰቡም፡፡ የሶሻሊዝም ጸር ስለሆኑ ውጉዝ ናቸው፡፡ ያሰበ፣ ያሳሰበ፣ … በሚል ሕይወትን የሚያሳጣ ቅጣት ሊጣልበት ሁሉ ይችላል። በዚያን ጊዜ በነበረው አስተሳሰብ “የማስተምረውን ልስራ፣ የምሰራውን ላስተምር” ብሎ መነሳት ታላቅ ብስለት፣ አስተዋይነትና ምጥቀት የሚያሳይ ከፍተኛ ድፍረት ነው፡፡
ለመሆኑ አቶ ጋዲሳ ጎበና ማናቸው? ምሁሩ ኢንቨስተር፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቀድሞው አጠራር በሆሮጉድሩ አውራጃ አቤደንገሮ ወረዳ ገበር በተባለ ልዩ ስፍራ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለዱ ሰው ናቸው፡፡ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሻምቡ ት/ቤት አጠናቅቀው፣ 2ኛ ደረጃን በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ት/ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ተከታተሉ፡፡ ከዚያም በ1962 ዓ.ም ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው፤ ሁለት ዓመት የመምህርነት ኮርስ ተከታትለው በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ ውጤታቸው ጥሩ ስለነበር በቀጣዩ ዓመት እዚያው ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ሞዴል አንድ ት/ቤት እንዲያስተምሩ አስቀሯቸው፡፡ እዚያ ከአንድ ዓመት በላይ አልቆዩም፡፡ ትምህርታቸውን ለማሻሻል በነበራቸው ፍላጎት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣  በኤጁኬሽን በዲፕሎማ ተመረቁና  ሆሳዕና ተመደቡ፡፡ ከዚያም በአሁኑ ዋቸሞ በቀድሞው ልጅ አበበ ት/ቤት አስተማሩ፡፡
ሆሳዕናም አልቆዩም፡፡ በ1966 ዓ.ም ወደ ተማሩበት አምቦ ማዕረገ ሕይወት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው፣ ለ25 ዓመት በትምህርት ሚ/ር ስር ማገልገላቸውን ተናግረዋል - አቶ ጋዲሳ፡፡ በማታው ክፍለ ጊዜ አምቦ እርሻ ኮሌጅ ተምረውም በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ የእርሻ መምህር ሆኑ፡፡ ለትንሽ ጊዜ ትምህርት ሚ/ር ለቀው ግብርና ሚ/ር ገብተው ነበር፡፡ ያኔ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ሲመጣ ለእሳቸው አይሰጥም፤ ሌሎች ናቸው የሚላኩበት። ይህ አሰራር ያበሳጫቸው ነበር፡፡ “ጥሩ ውጤት ስላለኝ በግሌ ለምን አልሞክርም?” በማለት የነፃ ዕድል ትምህርት ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ኤሊኖይ-አሜሪካ ሻንፔን ዩኒቨርሲቲ ውጤታቸውን አይቶ ስኮላርሽፕ ሰጣቸውና፣ በ1977 ዓ.ም ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ በ1980 ዓ.ም በእርሻ አድቫንሲንግ ዲፕሎማ ተቀብለው፣ እዚያው ለሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላ ደርግ ከስልጣን ሲወርድ ወደ አገራቸው ተመለሱና መሬት ተሰጥቷቸው ወደ እርሻ ገቡ፡፡
እንዴት ወደ እርሻ ኢንቨስትመንት ገቡ? ማለታችሁ አይቀርም፡፡ እንዴት እንደሆነ ራሳቸው ያጫውቱናል፡፡ እርሻ የተማርኩት ስለምወደው ነው እንጂ ለጥቅም ብዬ አይደለም፡፡ እርሻ ሳስተምር ተማሪው እንዲገባው በጣም እለፋለሁ፣ እደክማለሁ፤ ለፈተና እዘጋጃለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ ከመጽሐፍ ላይ የማስተምረው ቲዎሪ በተግባር ሲገለፅ ምንም አይገናኙም፡፡ ስለዚህ “የማስተምረውን ልሰራ፣ የምሰራውን ላስተምር” በማለት መሬት ጠየቅሁ። በዚያን ጊዜ የታወጀው የሶሻሊስት አስተዳደር ስለሆነ፣ መሬት ሊሰጠኝ ቀርቶ ያዳመጠኝም አልነበረም፡፡ በዚያ የተነሳ ለቤተሰቤ ወተት ትሆናለች በማለት በ1967 ዓ.ም አንድ ላም ገዛሁ፡፡ ያቺ ላም ጥሩ አያያዝ ስለተደረገላት የምትሰጠው ወተት ጨመረ፣ ከእኛ የተረፈውንም ወተት ለጎረቤቶቻችን እየሸጥን በደስታ ጥሩ መኖር ጀመርን፤ እሷም እየወለደች መርባቱን ቀጠለች፡፡
እንዲህ ጥቅም ካለው ለምን የበለጠ አልሰራበትም? በማለት ግቢ ውስጥ ጥንቸል ማርባት፣ በግ ማድለብ፣ የጓሮ አትክልት መስራት፣ የተወለዱን ጥጆችና ግልገሎች መንከባከቡን ቀጠልኩ፡፡ በዚህ ዓይነት እየሰራሁ ሳለ ቆየሁና፣ አንድ ቀን ንድድ ብሎኝ “የምሰራውና የማስተምረው ካልተገናኘ ከአሁን ጀምሮ እኔ ገበሬ መሆን አለብኝ” ብዬ ወሰንኩ
ጊዜው መቼ ነው?
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በ1976 ዓ.ም ነበር፡፡ ግን፣ ያዳመጠኝ ሰው ባለመኖሩ ትቼው በውስጤ ሲብላላ ኖሮ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚ ሲታወጅ፣ የመጀመሪያው መሬት ጠያቂ እኔ ነበርኩ፡፡ መሬቱ ቢፈቀድልኝም ስላልተሰጠኝ ስከራከር ኖሬ፣ በ1986 መሬቱ ተለቆልኝ ትክክለኛውን እርባታ ጀመርኩ፡፡
መሬቱ ምን ያህል ነበር?
17.5 ሄክታር መሬት በኢንቨስትመንት ተሰጠኝ፡፡
ስራ ሲጀምሩ ካፒታልዎ ምን ያህል ነበር?
ጥቃቅን ቁሳቁስ እንጂ ምንም አልነበረኝም፡፡ ከባንክ የተበደርኩት 83ሺ ብር ብቻ ነበረኝ፡፡
ምን አስይዘው ተበደሩ?
የጓደኛዬን መኖሪያ ቤት አስይዤ ነው የተበደርኩት፡፡
ብድርዎን ከፈሉ’ዴ ታዲያ?
ወዲያው ነዋ!
በዚያ ገንዘብ ምን መስራት ጀመሩ?
የወተት ከብት ማርባት ጀመርኩ፡፡ የወተቱ ምርት ቶሎ ገንዘብ አላመጣ ሲለኝ፣ ተውኩትና በሬ ገዝቼ እርሻ ጀመርኩ፡፡ የእርሻው ስራ ውጤታማ ሆኖ ብድሬን ቶሎ ስለከፈልኩ ባንክ ትራክተር ገዛልኝ። ትራክተሩ እጄ እንደገባ “ለምን አላስፋፋም?” በማለት መሬት ኮንትራት በመውሰድና መንግስትን በኢንቨስትመንት በመጠየቅ አስፋፋሁት፡፡  
አሁን ምን ያህል መሬት እያለሙ ነው?
ከጓደኞቼ ጋርበጆይንት ቬንቸሩ 500 ሄክታር መሬት አለኝ፡፡ በ15 ዓመት ረዥም ኮንትራት የወሰድኩት 48 ሄክታር፣ የበፊቱ 17.5 ሄክታር አለ፣ በእጄ አልገባም እንጂ መንግስትም በቅርቡ የሚሰጠኝ መሬት አለ፡፡ ብዙ ትራክተሮች እየገዛሁ ስለሆነ መሬት በኮንትራት የሚሰጠኝ ሰው በዝቷል፡፡
ምን ያህል ትራክተር አለዎት?
አራት አለኝ፡፡
ማጨጃና ኮምባይነርስ አለዎት?
የለኝም፡፡ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ብዙ እየባከነ ስለሆነ፣የወደፊት ትልቁ ምኞቴ ኮምባይነር መግዛት ነው፡፡ መውቂያዎች ግን ብዙ አሉኝ፡፡ ዩኤስኤአይዲም አላስረከበኝም እንጂ አንድ መውቂያ ገዝቶልኛል፡፡
ከብት እርባታውን ተውት እንዴ?
ለምን እተዋለሁ? እንዲያውም የጊደር እርባታ (ranch) ጀምሬያለሁ፡፡ ቅድም ያያችኋቸውን ዓይነት ጊደሮች እያባዛው እሸጣለሁ፡፡
እንዴት ነው የሚያባዙት?
ቀለብ እንሰጣቸዋለን፣ ይጠቃሉ፣ የስድስትና ሰባት ወር ክበድ (እርጉዝ) ሲሆኑ ይሸጣሉ፡፡ አሁን የእኛን ጊደሮች ፈላጊ በዝቷል፡፡
አንድ ጊደር ምን ያህል ይሸጣሉ?
ሌሎች ከ30 እስከ 35 ሺ ብር ይጠይቃሉ፡፡ እኔ ከዚያ በላይ ነው የምጠይቀው፡፡
ስንት?
ልትገዛ ስትመጣ ነው የምነግርህ እንጂ የተወሰነ ዋጋ የለም፡፡
ስንት ጊደሮች አልዎት?
ከ30 እስከ 40 ይሆናሉ፡፡
ወተትስ የለዎትም እንዴ?
ለዚህ ከተማ የምናከፋፍለው እኛ አይደለንም እንዴ? ቅድምስ ጠጡ ብዬ ያመጣሁት ከየት መሰለህ? ከእርሻዬ ኮ ነው፡፡
ለዚህ ከተማ በቀን ምን ያህል ሊትር ያከፋፍላሉ?
በቀን ከ 300 እስከ 400 ሊትር፣ ከዚያም በላይ ሊሄድ ይችላል፡፡
የሚታለቡ ላሞች ምን ያህል ናቸው?
እርግጠኛ አይደለሁም፤ ከ50 እስከ 60 ሊደርሱ ይችላሉ፡፡
እርሻው ምንድነው የሚያመርተው?
የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የሽንብራ፣ የባቄላ፣ የበቆሎ… ምርጥ ዘር እናመርታለን፡፡ በቆሎ፣ ስንዴ፣ … ስል አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም፡፡ አራት አምስት ስድስት ዓይነት ነው፡፡ ለምሳ ያዘጋጀነው እንጀራ እንኳ ሁለት ዓይነት ነው፤ አንዱ ቢጫ አንዱ ነጭ ነው፡፡ ሽንብራም የምናመርተው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሽንብራ፣ ስንዴ፣ … ለቆላ፣ ለደጋ፣ ለወይና ደጋ እያልን ነው የምናመርተው፡፡
ምርጥ ዘር ታዘጋጃላችሁ እንዴ?
እኛ’ኮ ምርጥ ዘር አምራች ነን፡፡ እኛ ተራ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ … አናመርትም፡፡ ሁሉም ምርጥ ዘር ነው፡፡ መስራች ዘሩን ከመንግስት ገዝተን ዘሩን አባዝተን፣ ምርጥ ዘር መሆኑ ተረጋግጦ፣ ታግ ለጥፈን ነው የምንሸጠው፡፡
ከወተት ላሞች ውጭ የሚያረቡት ዝርያ አለ?
በቅርቡ የቡፋሎ ዝርያ (ጎሽ መሳይ እንስሳ) ከሕንድ አስመጥቼ በግቤ ሸለቆ ውስጥ ለማርባት ተነጋግሬአለሁ፡፡ የእኛ ሰው ጎሽ ስለገደለ ይፎክራል፣ ይሸልላል፣ ይቀባል፡፡ ጦር ወርውሮ ከብቱ ኃይለኛ ስለሆነና ሊገድለው ስለሚችል ቢፎክር ምንም አይደለም፡፡ በጥይት ተኩሶ በሚገደልበት ዘመን መፎከር ትርጉም የለውም፡፡ ቡፋሎ ወይም ጎሽ ለማዳና የዋህ እንስሳ ነው፡፡ የእኛ አገሩ እንደ ሜዳ አህያ ኃይለኛ ስለሆነ አልተጠጋነውም፡፡ የኤስያው ግን ከፍተኛ ወተትና ቅቤ ነው የሚሰጠው፡፡ የሚፈልገው ረግረጋማ ስፍራ ሄዶ ውሃውን ከጠጣ በኋላ ሲተኛ ነው የሚውለው፡፡ ስለዚህ ዘሩን (ሲመኑን) አምጥቼ ከሌሎች ከብቶች ጋር ለማዳቀል እየተነጋገርኩ ነው፡፡
 ይህን እንስሳ ማርባት ለምን ፈለጉ?
ዋተር ቡፋሎ መኖር የሚፈልገው ውሃ ባለበት ረግረጋማ ስፍራ መሆኑ፣ ሁለተኛ ከፍተኛ ምርት መስጠቱ፣ ሶስተኛ ይህ እንስሳ አውሬ ያለመሆኑን እንዲያውቁና አውሬ የሆነ እንዳለ ሁሉ ለማዳም አለ ለማለት ነው፡፡
ከውጭ አገራት የቀሰሙት ነገር አለ?
አዎ! ሙያዬን በተመለከተ በዘር ብዜት ቱርክ፣ ቻይና፣ ኢጣሊያ፣ ጃፓን፣ አፍሪካም ውስጥ ብዙ አገሮች ሄጃለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ቱኒዝ ነበርኩ፡፡ አሁን ደግሞ ቤኒን እሄዳለሁ፡፡
የንብ እርባታ? አላቸው ሲባል ሰምቼ ነበር፡፡ እንዴት ነው?
አዎን! 40 ዘመናዊ ና ከ100 በላይ የሽግግር ቀፎዎች አሉኝ፡፡ ባህላዊ ቀፎ ደግሞ ብዙ ነው ለቁጥርም ይከብዳል፡፡ የማር ማቀነባበሪያ ስላለን እያሸግን እናቀርባለን፡፡
የጓሮ አትክልት አያመርቱም?
አለ! ግን መጠነኛ ነው፡፡ እኛ ለከብቶች መኖና ገፈራ፣ በብዛት የምናመርተው በቆሎ ነው፡፡ እሸቱን ለገበያ እናቀርባለን፣ ተረፈ-ምርቱን ደግሞ ገፈራና ለከብቶች መኖ እናደርጋለን፡፡
ገፈራ ምንድነው?
ገፈራ የሚባለው የበቆሎው ቅጠል ሳይደርቅ ከእህሉ ጋር ታምቆ ለወተትና ለሥጋ ከብት የሚቀርብ ምግብ ነው፡፡
ከዩኤስ ኤ አይዲ ጋር ምን እየሰራችሁ ነው?
ከዚህ ድርጅት ጋር የምንሰራው የእርሻ ምርት ግብአት አቅርቦትና ስርጭት ነው፡፡ እነሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀምና አያያዝ… የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጡናል፤ እኛ ደግሞ ገበሬውን እናሰለጥናለን፡፡ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ገበሬው ይህን የአቅም ግንባታ ካገኘ፣ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፅረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒት፣ … በአግባቡ ከተጠቀመ ምርቱ ይበዛል፣ ገቢው ይጨምራል፣ ኑሮው ይሻሻላል። ገበሬው ምርቱ እንዳይጨምር ማነቆ የሆነበት እነዚህን የምርት ግብአቶች ያለማግኘት ነው፡፡ እኛ እነዚህን ግብአቶች በአንድ ስፍራ እናቀርባለን፡፡ ስለ አጠቃቀምና ጥንቃቄያቸውም እናስተምራለን፡፡ ዩኤስ ኤ አይ ዲ የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል፤ ለጥቂት ባለሙያዎች ደግሞ ደሞዝ ይከፍላል፡፡ ከዚህ ውጪ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጠን ነገር የለም፡፡ የምርት ግብአቶቹን የማቀርበው እኔ ነኝ፡፡
ብዙ የተማረ ሰው በእርሻው ዘርፍ ሲሰማራ አይታይም፡፡ ችግሩ ምንድነው?
በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዋነኞቹ ችግሮች መሬትና ፋይናንስ ናቸው፡፡ የመሬት አቅርቦት የለም። መሬት የምታገኘው ብዙ ተቸግረህ፣ ብዙ ከስረህና ፍዳህን አይተህ ነው፡፡ የተማረ ሰው፣ እውቀት እንጂ ገንዘብ የለውም፡፡ እርሻ ደግሞ ዳጎስ ያለ ካፒታል ይፈልጋል፡፡ ሌላው ችግር፣ “ያለኝን ጥሪት እርሻ ላይ አፍስሼ ውጤታማ ባልሆንስ?” የሚለው ስጋትና ፍርሃት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት፣ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ሲያቅድ እነዚህ ቁልፍ ችግሮች የሚወገዱበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል። ተፈጥሯዊ የሆኑት ድርቅና ከመጠን ያለፈ ዝናም፣ ገበያ እጦት፣ ተባይ፣ … ሌሎች ችግሮች ናቸው፡፡
እርስዎ፣ በ20 ዓመት የእርሻ እንቅስቃሴ ውስጥ እጅግ ፈታኝ ነበር፤ ግን ተወጣሁት ወይም አሁንም በስራዬ ላይ እንቅፋት ሆኖ እየፈተነኝ ነው የሚሉት ችግር አለ?
አለ እንጂ! እኔ በርካታ እልህ አስጨራሽ ችግሮች ገጥመውኝ ተወጥቻቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን እንደመብራት እጅግ የፈተነኝ ችግር አላጋጠመኝም። የመኖ ማቀነባበሪያና የዘር ማበጠሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም፣ መብራት እንዲገባልኝ ለኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን የአምቦ ጽ/ቤት 176ሺ ብር የከፈልኩት በ2003 ዓ.ም ነበር፡፡ ገንዘብ ስከፍል ኮርፖሬሽኑ የተሰጠኝ ማስረጃ “አንድ ደንበኛ ገንዘብ ከከፈለ 7 ቀን በኋላ ይገባለታል” ይላል፡፡ ከ 7 ቀን በላይ ይኼው 4 ዓመት ተቆጠረ፡፡
ገንዘብ እንደከፈልኩ መስመር ዘረጉ፣ ትራንስፎርመር ተከሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ የሚተከሉበት ሕንፃ ከተሰራ አራት ዓመት ጨርሷል፡፡ የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር ጨረታ አውጥተን ለአሸናፊው 700ሺ ብር ከፍለን፣ በ165ሺ ብር ኬብል ገዝተን ጉድጓድ ውስጥ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ መሳሪያዎቹ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከልማት ባንክ ከተገዙ አራት ዓመት ስላለፋቸው ለብልሽት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ችግር እንዲወገድልኝ ያልደረስኩበት መ/ቤት የለም፤ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤትም ያውቃል፡፡
ሲጠይቋቸው ምንድነው የሚሰጡዎት ምላሽ?
ሙስና አለባቸው፡፡ ከእኔ በኋላ ለስድስት ሰው ትራንስፎርመር ተክለው አስገብተዋል፡፡ እኔ ሕጋዊ ሰው ስለሆንኩ ያለደረሰኝ 5 ሳንቲም አልሰጥም። ለማን አቤት! ማለት እንዳለብኝ ግራገብቶኝ ተቀምጫለሁ በማለት አቶ ጋዲሳ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 4343 times