Monday, 10 February 2014 07:28

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት ላይ የተጧጧፈው ዘመቻ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የፍ/ቤቱን ሸፍጥ ያጋለጡት አውሮፓዊ በአፍሪካ መሪዎች ተደንቀዋል
አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት የሚደረግ አዲስ ኩሸት ነው ተብሏል
“አውሮፓ የሚሏት እርም የለሽ አህጉር፣ እነሆ ከአንድ መቶ ሃያ አመታት በኋላም አፍሪካንና አፍሪካውያንን ለመዝረፍ እየሞከረች ነው!” አሉ እንግሊዛዊው የፖለቲካ ተመራማሪ ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፡፡
“አውሮፓውያን ያቋቋሙትን ‘አለማቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት’ የተባለ መላ ተጠቅመው አፍሪካውያንን ባህር አሻግረው እያጋዙ፣ ሆነ ብለው በሰየሙት የይስሙላ ችሎት ላይ እያቆሙ ነው” ሲሉ ደገሙ ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፡፡
ይህም በአዳራሹ ውስጥ የነበሩ በርካቶችን በደስታ አፍለቀለቀ፡፡ ዙሪያ ገባውንም በጭብጨባ አደበላለቀ፡፡ እርግጥም የሰውዬው ንግግር ብዙዎችን ማስደሰቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ አዳራሽ ውስጥ ከታደሙት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች አብዛኞቹ፣ ከአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ጋር ቂም የተያያዙና በባላንጣነት የሚተያዩ ናቸው፡፡
በአፍሪካ ፖለቲካዊና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ በርካታ መጽሃፍትን ለንባብ በማብቃት የሚታወቁት የፖለቲካ ተመራማሪው ዶክተር ዴቪድ ሆይሌ፣ ባሳለፍነው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አበባ በተካሄደው 22ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ነበር፣ የአገራቱ መሪዎች በተገኙበት ሁለት መጽሃፍቶቻቸውን በይፋ ያስተዋወቁት፡፡
በአፍሪካውያን መሪዎች ተጨብጭቦላቸው ከተመረቁት የዶ/ር ዴቪድ ሆይሌ መጽሃፍት አንዱ፣ ‘የአለማቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የአውሮፓ ጓንታናሞ ቤይ?’ የሚል ርዕስ አለው፡፡ መሪዎቹ ያጨበጨቡት ለርዕሱ ብቻ አይደለም፡፡
“አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ ለአውሮፓውያን አፍሪካን እንዳትረጋጋ በማድረግ፣ ፖለቲካዊ የበላይነቷን የማሳጣትና የማዕድን ሃብቷን በገፍ የመዝረፍ ድብቅ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ሆኖ ከርሟል!... ተቀማጭነቱ በሄግ የሆነው ፍርድ ቤቱ፣ አፍሪካን እንደገና ቅኝ ለመግዛት የሚደረግ አዲስ አውሮፓዊ ኩሸት መገለጫ ነው!...” ለሚለው መደምደሚያው ጭምር እንጂ፡፡
ዶክተር ዴቪድ እንደሚሉት፣ ፍርድ ቤቱ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 130 በላይ አገራት ተፈጸሙ በተባሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና ወንጀሎች ዙሪያ ከ8ሺህ 300 በላይ የክስ ማመልከቻዎች ቢደርሱትም፣ እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2013 መጨረሻ ድረስ የወንጀል ምርመራ የጀመረው በ8 አገራት ላይ ብቻ ነው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ ሰውዬው እንደገለጹት፣ የፍርድ ቤቱን ተልዕኮ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሌላው አስገራሚ ነገር፣ እነዚሁ ስምንት አገራትም ሁሉም አፍሪካዊ መሆናቸው ነው - ኡጋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የመካከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኮትዲቯር፣ ማሊና ሊቢያ፡፡
“አንድ እንኳን አፍሪካዊ ያልሆነ አገር፣ በፍርድ ቤቱ የወንጀል ምርመራ እየተደረገበት አይደለም። ራሱን አለማቀፍ የፍትህ ተቋም አድርጎ የሰየመው ይህ የይስሙላ ፍርድ ቤት፣ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ የሰሯቸውን የጦርነት ወንጀሎች በተመለከተ በቂ ማስረጃ ከያዘባቸው የተለያዩ አውሮፓ አገራት መንግስታት፣ አንዱን እንኳን ለፍርድ ለማቅረብ አልደፈረም!... ይህም የተቋሙን አድሏዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብለዋል ዶ/ር ዴቪድ፡፡
የአውሮፓን ‘ሸፍጥ’ ባጋለጠው አውሮፓዊ የባዳ ዘመዳቸው፣ ዶ/ር ዴቪድ ልባቸው ቅቤ የጠጣ የአፍሪካ መሪዎችም፣ “እኛም ሰሚ አጥተን ነው እንጂ፣ ለፍትህ ቆሜያለሁ እያለ ፍትህን ስለሚገድለው ስለዚህ ወገኛ ተቋም ቀድመን ተናግረናል” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል፡፡
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ እ.ኤ.አ በ2013 በኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታና በምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ላይ ክስ መመስረቱን ተከትሎ፣ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ከአፍሪካ ህብረት ቀዳሚ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ህብረቱ በዚህ ተቋም ላይ እምነት እንደሌለውና አካሄዱም አህጉሪቱን ክፉኛ የሚጎዳ ህገወጥ ተግባር እንደሆነ በይፋ ከመናገር አልፎ፣ በአህጉሪቱ መንግስታት ላይ የሚሰነዝረውን ውንጀላም መሰረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል፡፡
ህብረቱ በጥቅምት 2013 በጠራው የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ላይ የአለማቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እውቅና የሚነሳ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ተሰሚነት ያላቸው የአህጉሪቱ ቁልፍ መሪዎችም፣ በተቋሙ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በተለያዩ አህጉራዊና አለማቀፋዊ መድረኮች ላይ ማስተጋባታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ “አፍሪካ ላይ ወዳነጣጠረ የፖለቲካ መሳሪያነት ዘቅጧል” ሲሉ በይፋ የተቹትን ይሄን ፍርድ ቤት፤ የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮሪ ሙሴቬኒም እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ዘልፈውታል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ ዶ/ር ዴቪድም የአፍሪካ መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በተቋሙ ላይ የሚሰነዝሯቸውን ትችቶች የሚደግፍ ንግግር ነው በህብረቱ ጉባኤ ላይ ያሰሙት፡፡ “ራሱን አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እያለ የሚጠራው የውሸት ፍርድ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልከቱ፡፡ እጅግ ብዙ የመሰሪነት ስራዎችና ተንኮሎችን ሲጎነጉን፣ የአፍሪካ አገራትን በማስፈራራት አልያም መደለያ በማቅረብ በግዳጅ የፍርድ ቤቱ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ሲሞክር እኮ ነው የኖረው!” በማለት፡፡
በህብረቱና በአለማቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መካከል የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን ተከትሎ፣ የአፍሪካዊ መንግስታት አለማቀፍ ወንጀሎችን የሚዳኝ የራሳቸውን ክልላዊ የፍትህ ተቋም ወደመፍጠር እንዲገቡ አስገድዷል፡፡
ዶ/ር ዴቪድ እንደሚሉት፤ አውሮፓውያን ይሄንን የአፍሪካ ህብረት አማራጭ ለማሰናከል በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መድበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1998 በአለም ዙሪያ የሚገኙ 122 አገራትን በአባልነት ይዞ በተመሰረተው አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ 34 አገራትን የፍርድ ቤቱ አባላት በማድረግ ከሁሉም አህጉራት ቀዳሚ የሆነችው አፍሪካ ናት፡፡ “ፍርድ ቤቱ 18 የእስያ ፓሲፊክ፣ 18 የምስራቅ አውሮፓ፣ 27 የካረቢያንና 25 የምዕራብ አውሮፓ አገራትን በአባልነት ቢይዝም፤ ጣቱን የቀሰረው ግን በፈረደባት አፍሪካ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ ነው ፍርድ ቤቱን ፍትሃዊነት በጎደለው ሁኔታ ፍትህን አስከብራለሁ ብሎ የሚዳክር የይምሰል ተቋም የሚያደርገው” ብለዋል ዶክተር ዴቪድ፡፡
በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ የሚታወቁት ዶ/ር ዴቪድ፤ ስለ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጸረ - አፍሪካ ተቋምነት ሲናገሩ ቅንጣት ታህል ማመንታት አይታይባቸውም።
“አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አውሮፓዊ ተቋም ነው፡፡ አፍሪካን እዳኛለሁ ብሎ የተነሳ አውሮፓዊ ፍርድ ቤት ነው፡፡ እውነታው ይሄና ይሄ ብቻ ነው!!” በማለት ነው፣ ዶ/ር ዴቪድ በህብረቱ 22ኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በሙሉ ልብ የተናገሩት፡፡ ይህ የዶክተሩ ንግግር፣ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ ለፍርድ ይቅረቡ ብሎ በወሰነባቸውና ከችሎት ፊት ሊገትራቸው በሚፈልጋቸው በእነኡሁሩ ኬንያታና ኦማር ሃሰን አል በሽር ልብ ውስጥ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል፡፡
ዶ/ር ዴቪድ ሆይሌ ለንባብ ያበቁት አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የአውሮፓ ጓንታናሞ ቤይ?’ የተሰኘና 345 ገጾች ያሉት መጽሃፍ፤ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አጠቃላይ ዓላማና የመጨረሻ ግብ፣ አፍሪካን መልሶ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ማድረግ እንደሆነ ያትታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ራሱን እንደገለልተኛና ከአድልኦ የጸዳ ተቋም አድርጎ ለማሳየት ቢጥርም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው ባይ ናቸው ዶክተሩ፡፡
ፍርድ ቤቱ 60 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን የሚያገኘው ከአውሮፓ ህብረት እንደመሆኑ፣ በአውሮፓ አገራት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በድፍረት ለማጋለጥና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ሞክሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም ፍርድ ቤቱ፣ እጅ ያጠራቸውንና ከአጋሮቹ ጋር የፖለቲካ ንክኪ ያላቸውን የአፍሪካ አገራት እየመረጠ በመወንጀል፣ እድሜ ዘመኑን የገፋ የአውሮፓውያን ተላላኪ ነው ይላሉ፤ ዶክተሩ በመጽሃፋቸው፡፡
“አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመውጣትና ነጻነቷን ለመጎናጸፍ ለዘመናት ታግላለች፡፡ ትልቅ መስዋዕትነትም ከፍላለች፡፡ አሁን ደግሞ ከወደ አውሮፓ ዘመን የወለደው ሌላ ‘ህጋዊ’ የቅኝ ግዛት ሙከራ እየተሰነዘረባት ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ ዝም ማለት የለባትም፡፡ መክታ መመለስ እንጂ!” ብለዋል ጸሃፊው፡፡
ዶ/ር ዴቪድ በመጪው መጋቢት ወር በይፋ ለንባብ ያበቁታል ተብሎ የሚጠበቀውና ‘ጀስቲስ ዲናይድ፣ ዘ ሪያሊቲ ኦፍ ዘ ኢንተርናሽናል ክሪሚናል ኮርት’ የሚል ርዕስ በሰጡት ሁለተኛው መጽሃፋቸውም፣ ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ አህጉር ላይ አነጣጥሮ እየሰራ ያለውንና ለወደፊትም ሊሰራ ያሰባቸውን ኢ-ፍትሃዊ ተግባራት በዝርዝር ይዳስሳል ተብሏል፡፡

Read 3838 times