Monday, 10 February 2014 07:10

የ54 ሚሊዮን ብር ዘረፋ ለመከላከል!

Written by  አያሌው አስረስ (ነጋድራስ)
Rate this item
(11 votes)

                     “ሳንቲሞችን ጠብቃቸው እንጂ ብሮች ያለምንም ችግር እራሳቸውን ይጠብቃሉ” የሚለው አነጋገር ለተነሳሁበት ጉዳይ የልብ ራስ ሆኖ የሚቆጠር ነው። ሳንቲሞችን ከብክነት መከላከል ንፉግነት ወይም ስግብግብነት አለመሆኑም ሰሚ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ባለፈው ታህሳስ ወር ሁለተኛ ሳምንት መግቢያ ላይ ወደ አዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ በታክሲ ከቦታ ወደ ቦታ ስንቀሳቀስ ከታሪፍ በላይ እንድከፍል መደረጌን ለማስቆምና ሳንቲሞችን ለመቆጠብ ነው። መንግሥት በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ታሪፍ፣ አሁንም ድረስ በሥራ ላይ ነው፡፡ ምናልባትም በየካቲት ወርም ሊቀጥል ይችላል፡፡ በታሪፉ መሠረት፣ እስከ 2.5 ኪሎ ሜትር 1.45፣ እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር 2.80፣ እስከ አስር ኪሎ ሜትር 4.00 ብር ነው ክፍያው፡፡ እኔ በብዛት የምገለገለው የመጀመርያ ሁለቱን ርቀቶች ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር የነበረው ታሪፍ 2.65 ቢሆንም፣ ታክሲዎች በራሳቸው ጊዜ ጨምረው ሕዝቡን 2.70 (ሁለት ብር ከሰባ ሳንቲም) ሲያስከፍሉት መክረማቸውን የትራንስፖርት ቢሮው የመረጃ ማዕከል ባልደረባ ገልፃልኛለች። በታህሳስ ወር የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ እነሱ በጉልበት በጨመሩት ላይ ተጨምሮ 2.80 ሆነ ማለት ነው፡፡

ሕጉን የሚያስከብርና ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም አካል አለመኖሩን በሚገባ የሚያውቁትና የትራንስፖርት ቢሮውን ልብ በትክክል የተረዱት የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች አሁንም በራሳቸው ጊዜ ዋጋ ጨመሩ። 1.45 የነበረውን ወደ 1.50፣ 2.80 የነበረውን 2.90 አሻገሩት፡፡ በዚሁ በጥር ወር ደግሞ 2.80 ሊከፈልበት የሚገባው ጉዞ 3.00 ብር እየተከፈለበት ነው፡፡ የታክሲ ረዳቶች ሶስት ብር ሲጠይቁ ትንሽም እንኳ ጥፋት እየፈፀሙ መሆናቸው አይሰማቸውም። በእነሱ ዘንድ ትክክለኛ ሥራ እየሰሩ ነው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሄጄ ነበር፡፡ መገናኛ የየካና የቦሌ ክፍለ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ጽ/ቤቶች አሉ፡፡ “ሕግ የሚያስከብርልኝ ማነው?” አልኳቸው፡፡ የየካው ትራንስፖርት ቢሮው ባልደረባ “ማንም!” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ አልሰጡኝም፡፡ የነገሩኝ ቀኑን፣ ሰዓቱንና የመኪናውን የሰሌዳ ቁጥር ይዤ ለሚመለከተው የክፍለ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ማመልከቻ በመፃፍ ክስ ከመሰረትኩ፣ እኔ በተገኘሁበት ተከሳሹ ቀርቦ እንደሚጠየቅና እንደሚቀጣ ነው፡፡ እሳቸው በዚህ መንገድ አንድ ሹፌር ማስቀጣታቸውንም ገለፁልኝ፡፡

በየጊዜው በማድረጋቸው ጉዞዎች በቋሚነት የሚገጥሙኝ ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በየካ ትራንስፖርት ቢሮ ባልደረባ ምክር መሠረት ማመልከቻ አያያዝኩ የምቆምባቸውን የትራንስፖርት ቢሮዎች ሳስበው አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት “ሳስበው ሳስበው ደከመኝ” በጣም ደከመኝ፡፡ ይህ ደግሞ በግልጽ የሚያሳየው ታሪፉን የሚያስከብር ወይም ለማስከበር የተነሳ አንድም አካል አለመኖሩን ነው። ሰውየው ከእንደበታቸው አይውጣ እንጂ ያሉት “ማንም ህግ የሚያስከብር የለም!” ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከስምንት ሺህ በላይ ባለ ቀይ ሰሌዳ ታክሲዎች አሉ፡፡ ከእነሱ ሌላ ከሁለት ሺህ የማያንሱ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶች አሉ፡፡ አንድ መኪና ከአስር ያላነሰ የደርሶ መልስ ጉዞ (70 ኪሎ ሜትር) በየቀኑ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዞው በትርፍ የሚይዛቸውን ጨምሮ በአማካይ ለ150 ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል፡፡ እነዚህ ታክሲዎች በየቀኑ ከታሪፍ በላይ 150ሺ ብር ክፍያ ይሰበስባሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በወር 4.5 ሚሊዮን፣ በዓመት 54 ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡

እያንዳንዱ ተሳፋሪ እየከሰሰ መብቱን እንዲያስከብር ክፍት መተው ሕገወጥ ድርጊት እንዲፈፀም ልቅ ከመተው የሚተናነስ አይደለም፡፡ ለእኔ ይሄ መንግሥት ህግን ማስከበር እንዳቃተው ማሳያ ነው፡፡ ታክሲ ላይ ብቻ አይደለም፣ በየትኛውም የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለሸማቹ ወይም ለተገልጋዩ የሚያስብ አእምሮ አልተፈጠረባቸውም የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በሸማቹ ወይም በተገልጋዩ ሕዝብ ኪስ የሚያድር ገንዘብ ነገ ተመልሶ የእነሱ መሆኑን ማሰብም ተስኗቸዋል፡፡ ኪሱን ገልብጠው አራግፈው ወደ ቤቱ ቢመልሱት የሚሰማቸውን ደስታም መገመት አይከብድም፡፡ ሕዝቡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ከታክሲ ረዳቶች ጋር ተጨቃጭቆ መብቱን ማስከበር ይችላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ጉዞዬ በማቀርበው ጥያቄ የገጠመኝ ዘለፋና ማሸማቀቅ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ ከፍሎ መገላገል የሚያስመኝ ነው።

በእኔ እምነት ታሪፉንም ሆነ ሌሎች የተገልጋዩን ሕዝብ ጥቅሞች ማስጠበቅ ያለባቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የእኔ አይነት ተሳፋሪዎች ሳይሆኑ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት፣ የየክፍለ ከተማው ትራንስፖርት ቢሮዎችና የባለ ታክሲዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተቋቋሙት የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ናቸው፡፡ በተለይ የታክሲ ማህበራት “ጥቅማችን ለምን ይቀርብናል” ብለው እስካልተነሱ ድረስ የቀጠሯቸውን የታክሲ ረዳቶችና ሹፌሮች “እጃችሁን ወደ ደንበኞቻችን ኪስ አትክተቱ” ማለት ይችላሉ፡፡ በትክክል በጉዳዩ ከአመኑበት ደግሞ ቃላቸው ተግባራዊ መሆኑን እንደኛው ተሳፋሪ እየሆኑ ሊፈትሹት ሊከታተሉት ይችላሉ፡፡ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከልብ ከተነሳ ችግሩን መፍታት ያቅተዋል ብዬ አላምንም፡፡ የመጀመርያ እርምጃ መሆን ያለበት የታክሲ ባለንብረቶችን፣ ሹፌሮችንና ረዳቶቻቸውን የተሳፋሪውን ጥቅም የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ማሳመን ነው፡፡ ሁለተኛው እያንዳንዱ ታክሲ እንደሚሄድበት መስመር ሁሉ በግልጽ በሚታይ ቦታ የታሪፉን ዝርዝር እንዲለጥፍ ማድረግ፣ ማስገደድና መቆጣጠር ነው፡፡

ሶስተኛው ማህበራት የሚደራጁት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታንም ለመወጣት በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ማህበር አባሉ ሕግ ማክበሩን እንዲከታተል የሚያደርግ ሕግ ወይም ደንብ ማውጣት ነው። በመጨረሻ ከሳንቲም መልስ ችግር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጉዳቶችንና ውዝግቦችን ለማስቀረት የሚታየኝ አማራጭ መፍትሄ፣ ባለታክሲውና ተሳፋሪው በየተራ እየተጉዱ መልስ የማይጠየቅበት ዝግ ማለትም ብር ፣ ሁለት ብር፣ ሶስት ብር ወዘተ--- የሚሉ ታሪፎች ማውጣት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በተለያየ ጊዜ ከታሪፍ በላይ አስከፍለውኝ ለሚመለከተው አካል አቤት ለማለት ብዬ የሰበሰብኳቸውን የታክሲ ሰሌዳ ቁጥሮች ቀድጄ የጣልኳቸው ሲሆን “መልስ አለኝ” ብዬ ከመናገርና የሚሰጡኝን ከመቀበል ውጪ መከራከሩንም አቁሜዋለሁ፡፡ እኔ የምናፍቀው ሕግ የሚያስከብር መንግሥት ማየት ብቻ ነው፡፡ ያኔ ዘረፋ ይቆማል፡፡

Read 3560 times