Monday, 10 February 2014 07:14

አቶ አስራት ጣሴ መፅሔት ላይ ባወጡት ፅሁፍ ታሰሩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ጠበቃቸው ሰኞ ይግባኝ ይጠይቃሉ
የትላንትናው የፍ/ቤት ክርክርና ውሳኔ

በአዲስ ጉዳይ ሳምንታዊ መጽሔት የጥር ወር እትም ላይ “ከኢህአዴግ ፍርድቤቶች ፍትህ አይገኝም” የሚል ሃሳብ የተካተተበት ጽሑፍ በማውጣት፤ ፍርድ ቤት ገለልተኛ እንዳልሆነ በመግለፅ ዘልፈዋል ተብለው የተከሰሱት የአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል አቶ አስራት ጣሴ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ተከራከሩ፡፡ በኋላ የዋስ መብት ተከልክለው ታሰሩ፡፡  
አቶ አስራት በመጽሔቱ ላይ ባወጡት ጽሑፍ “ከሰሞኑ የአኬልዳማ ድራማ በድጋሚ በተከታታይ እየቀረበና እየታየ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው አንድነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅትን በስም ማጥፋት ወንጀል በፍ/ቤት ከስሶ ገና ውጤት ባልተገኘበት ወቅት ነው፡፡ ክሱም ፍትህ ከኢህአዴግ ፍ/ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን በታሪክ ምስክርነት እንዲመዘገብ ሲባል ነው” በሚል ፍ/ቤቱ ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ዘልፈዋል ይላል - የክስ ቻርጁ፡፡
አቶ አስራት በትናንትናው ዕለት በከፍተኛው ፍ/ቤት ዘጠነኛ የፍትሃብሄር የቤተሰብ ችሎት ከጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጋ ጋር ቀርበው በጠበቃቸው በኩል ተከራክረዋል፡፡ “ለምን ፍርድ ቤቱን ዘለፉ?” በሚል ከዳኛዋ ለቀረበው ጥያቄ፣ አቶ ተማም “ደንበኛዬ ተከሰው የቀረቡት በፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 480 መሰረት ሲሆን እዚህ ችሎት ቆመው ያሰሙት ዘለፋ የለም፣ በችሎቱ ላይም አልነበሩም፤ አንቀፅ 480 ከችሎት ውጭ ለተፈፀመ ጉዳይ አያገለግልም” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
ችሎትን በመዝለፍ አንቀጽ 480፣ ክስ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ሶስት አካላት እንዳሉ የገለፁት ጠበቃው፤ ከሳሽ፣ ተከሳሽ እንዲሁም ችሎቱን የታደሙ ታዛቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ክሱ የሚቀርበውም ዳኝነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የችሎቱን ክብር የሚነካ ዘለፋ ያቀረቡ እንደሆነ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የአኬልዳማን ጉዳይ በተመለከተ  ከአንድነት ፓርቲ ክስ ቀርቦ በሂደት ላይ ያለው በዚህ ችሎት እንደሆነ የጠቆሙት ዳኛዋ፤  “አቶ አስራትም በመፅሔቱ ላይ ይህን ገልፀው ፅፈው እንዴት ችሎት አልዘለፉም ትላላችሁ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ጠበቃው ሲመልሱም፤ “ደንበኛዬ በአጠቃላይ በኢህአዴግ የፍርድ ቤት አደረጃጀት ላይ ችግር እንዳለ ገለፁ እንጂ ይህን ችሎት በተናጠል የዘለፉበት አንዳችም አመላካች ነገር የለም” ብለዋል፡፡ “የደንበኛዬ መጣጥፍ  የኢህአዴግ የፍርድ ቤት ችግር፣ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና የሚመለከት እንጂ ከፍ/ቤት ዘለፋ ጋር አይገናኝም” ሲሉም ተከራክረዋል፡፡
አንቀፅ 480 ስለችሎት ዘለፋ ካሰፈራቸው ውስጥ “ጉዳዩ በተሰራበት ጊዜ” የሚል እንዳለ ለፍ/ቤቱ የጠቆሙት ጠበቃው፤ ደንበኛቸው በችሎት ላይ እንዳልነበሩ፣ የዚህ ችሎት ተከራካሪ እንዳልሆኑ፤ ተከሰው የቀረቡት መፅሄት ላይ አስተሳሰባቸውንና እውነት ነው ያሉትን ነገር በማንፀባረቃቸው ስለሆነ ጉዳዩ “ከክርክር ስነ-ስርዓት ውጭ” ተብሎ በነፃ እንዲሰናበቱ በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡
“ይህን ችሎት አይደለም የተናገሩት የምትሉት ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ በሌላ ችሎት ክርክር አቅርባችኋል?” በሚል የተጠየቁት ጠበቃው፤ ከዚህ በፊት እንዳልተከራከሩ ጠቅሰው የደንበኛቸው መጣጥፍ የሚያጠነጥነው “ጅሀዳዊ አራካት” ከሚለው ዶክመንታሪ ጋር በተያያዘ ሲባልና ሲነገር ስለነበረው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት እውነት ነው ያሉትን ሀሳብ መፃፋቸውን የጠቀሱት ጠበቃው፤ መጣጥፉ የሽብርተኝነት ህጉ ለኢትዮጵያ ተገቢ እንዳልሆነ፣ ኢህአዴግ ከሽብር ይልቅ ሰላምን እንደሚፈራ፣ በአጠቃላይ ኢህአዴግ ያቋቋመው ፍርድ ቤት የአደረጃጀት ችግር እንዳለበት የሚገልፅ ይህን ችሎት በተናጠል አልዘለፈም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “ደንበኛዬ በችሎት ተገኝተው እንዳልዘለፉ በፖሊስ በኩል የላካችሁት የክስ መጥሪያ ምስክር ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት አንድ ሰው ስለፍርድ ቤትም ሆነ ስለማንኛውም ጉዳይ የመናገር፣ የመፃፍና አስተሳሰቡን የማንፀባረቅ መብት እንዳለው ለችሎቱ ያስረዱት ጠበቃው፤ በአንቀፅ 29(6) መሰረትም አንድ ሰው አስተሳሰቡን ሲያራምድ፣ ሲፅፍና ሲናገር ገና ለገና ይህን ያመጣል በሚል ሊገደብ እንደማይገባና ሀሳቡን በማንፀባረቁ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባ አቶ ተማም አስረድተዋል፡፡
ክርክሩ ከተካሄደ በኋላ ጉዳዩ ለውሳኔ ከሰዓት በኋላ 8፡30 የተቀጠረ ሲሆን፤ ፍ/ቤቱ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት የአቶ አስራት ጣሴ ጉዳይ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ስለተገኘ፣ የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ በሚቀጥለው አርብ የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም ውሳኔ እስኪያገኙ በጊዜያዊ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ አቶ አስራትም በተለምዶ “አምስተኛ” እየተባለ ወደሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡
ጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ደንበኛቸው በተከሰሱበት የፍትሃብሄር ስነ-ስርዓት ህግ አንቀፅ 480 ጥፋተኛ ቢባሉ እንኳን የገንዘብ መቀጮ እንጂ ለእስር እንደማያበቃ ገልፀው፤ ውሳኔው ላይ ሰኞ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ፍ/ቤቱ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል ብሎ ወደ እስር ቤት ልኳቸዋል፤ ነገር ግን እኛ በወንጀል ያስጠይቃቸዋል ብለን አናምንም” ያሉት አቶ ተማም፤ “አቶ አስራት የችሎት ስም አልጠሩም፣ አልዘለፉም፤ ይህ ችሎት መጽሔት ላይ በፃፉት ፅሁፍ ጠርቶ ሊጠይቃቸውም አይችልም ብለዋል፡፡ አንድ ሰው በአንቀፅ 480 የሚከሰሰው ችሎት ውስጥ ተገኝቶ ሲዘልፍ ብቻ እንደሆነና አቶ አስራት ግን በጉዳዩ እንደሌሉበት በጠዋቱ የችሎት ውሎ መከራከራቸውን ጠበቃው አስታውሰው፤ ፍቤቱ የሰጠው ውሳኔ ከክሱ ጋር ግንኙነት ስለሌለው ሰኞ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡   

Read 3886 times