Monday, 10 February 2014 06:56

በፅንስ ማቋረጥ ምክንያት በደረሰ አደጋ ሃኪሙ ተከሰሰ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

         ለህክምና የመጣችውን ነፍሰሡር ፅንስ ያለ ጥንቃቄ አስወርዶ በአካላቷ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል፤  ተጐጂዋን ለመርዳትም ፍቃደኛ አልበረም የተባለው የግሎባል ከፍተኛ ክሊኒክ ባለቤት ዶ/ር በላቸው ቶሌራ፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተከሰሰ፡፡
ሃኪሙ ባለፈው ህዳር ወር  ደም መሰል ፈሳሽ ነገር አይታ ወደ ሆስፒታሉ ለህክምና የሄደችውን የሁለት ወር ነፍሰጡር ወ/ት በላይነሽ ይመር፤ በጣቱ ብቻ በመመርመር “የፅንሱ አቀማመጥ ጥሩ አይደለም” በሚል እንድታስወርደው ይጠይቃታል፡፡ ወ/ት በላይነሽ ከተስማማች በኋላም፤ ጥንቃቄ በጐደለው ሁኔታ በማህፀኗ ውስጥ ብረት በማስገባት፣ የማህፀኗ ግድግዳ 3.2 ሴ.ሜትር እንዲሸነቆር፣70 ሴ.ሜትር የትንሹ አንጀት እንዲበላሽ ወይም እንዲሞትና ተቆርጦ እንዲወጣ እንዲሁም፣ 300 ሲሲ ደም ወደ ሆዷ እንዲፈስ በማድረግ በፈፀመው በቸልተኝነት በአካል ላይ ከባድ ጉዳት የማድረስ ወንጀል የመጀመሪያ ክስ ቀርቦባታል፡፡  
ተከሳሹ ግለሰቧን 987 ብር አስከፍሎ ውርጃ እንድትፈፅም ካደረጋት በኋላ ደሟ ፈሶ እራሷን ስትስት፣ ተገቢውን የህክምና እርዳታ ሳያደርግላት ወይም ለከፍተኛ የጤና ተቋም እርዳታ እንድታገኝ ተገቢውን መረጃ ሳይፅፍ፣ በራሱ መኪና የካቲት 12 ሆስፒታል  በመውሰድ “የማውቀው ዶክተር አለ ልጥራው” ብሎ ተጎጂዋን ጥሎ የጠፋ ሲሆን በፈፀመው በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን ያለመርዳት ወንጀል ሁለተኛ ክስ ቀርቦበታል፡፡ ጉዳዩን እያየ ያለው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት ተከሳሹ “ይከላከል አይከላከል” የሚለውን ብይን ለመስጠት ለፊታችን ማክሰኞ የካቲት 4  ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 3030 times