Monday, 03 February 2014 13:51

ወንጀል እና ቅጣት

Written by  ሃዊ
Rate this item
(7 votes)

         ወጠምሻው ከአይገር ባሱ እንደወረደ መሮጥ በመጀመሩ አይናችንን አሳረፍንበት፡፡ እኔ እና ጓደኛዬ የሙዚቃ ቤቱ ደጃፍ ተቀምጠናል፡፡ በጠዋቱ ቅመናል፡፡ አፋችን ተለጉሟል፡፡ ከትራንስፖርት እንደወረደ መሮጥ የሚጀምር ሰው ወይ የቸኮለ ነው፣ ካልሆነ የሆነ ጥፋት ፈጽሟል፡፡ መጀመሪያ፣ አሯሯጡ ሶምሶማ ይመስል ነበር፡፡ ሁለት ወይ ሶስት ሰዎች ከኋላው ተከታትለው ወርደው ያሳድዱት ጀመር። የተከተሉት መኖራቸውን አንገቱን ቆልምሞ ሲያይ ሩጫውን ከሶምሶማ ወደ ሽምጥ ለወጠው፡፡ ሙዚቃ ቤቱ ደጃፍ ቁጭ ብለን አባሮሹን እየተከታተልን ነው፡፡ ሙዚቃ ቤቱ ሙዚቃ አያወጣም። እንደ ባለቤቱ እና እንደ እኔ ጭጭ ብሏል… ሙዚቃ መስማት ካቆምን ሁለት ዓመት ገደማ አልፎናል፡፡ የድምጽ ብክለት ህጉ ከፀደቀ በኋላ …ጮክ ብሎ መናገርም ሆነ ጮክ ያለ ሙዚቃ መክፈት… አምስት ዓመት ያሳስራል፡፡

ፀጥታን ከተለማመድነው ቆይተናል፡፡ ጫት መቃሙን አጠንክረን የያዝነው ለፀጥታ ስለሚያግዘን ነው፡፡ የድምጽ ብክለት ህጉ “ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ድምጽ መፍጠርን” የሚከለክል ቢሆንም፤ ከተከለከለው በላይ ፍርሐቱን አስከንድቶ ሁሉም ድምጽ ባለማውጣት ውሎ ማደር ለምዷል። ወጣቱ በፍጥነት እየሮጠ በረጅሙ አስፋልት መንገድ እኛ ወደ ተቀመጥንበት እየቀረበ ነው፡፡ ከኋላ የሚያሳድዱት ሰዎች እጃቸውን እያወናጨፉ የሚሮጠውን ወጣት እንዲያዝላቸው ምልክት ይሰጣሉ፡፡ አፋቸውን ግን ጥርቅም አድርገው ዘግተዋል፡፡ የሚሰጡትን ምልክት ከሁለታችን በስተቀር ያየ የለም፡፡ እኛ ደግሞ ከአይናችን በታች ያሉት ቅልጥሞቻችን ፈዘዋል፡፡ በመሠረቱ የሌባና ፖሊስ ጨዋታ የመጫወቻ እድሜአችን አልፏል፡፡ ወጣት እና ወጠምሻ አይደለንም፡፡ በዛ ላይ የሯጩ ጥፋት ግልጽ አልሆነልንም፡፡ ምናልባት የብክለት ህጉን በማፍረሱ ሊሆን ይችላል፤ ወጣቱ እግሬ አውጪኝ የሚለው፡፡ የብክለት ህጉ፣ በድምጽ ላይ ብቻ አይደለም የፀደቀው፡፡ ህጉ ከዚህ ቀደም ተሰምተው ለማያውቁ የፍትህ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ሰጥቷል። የህጉ ዝርዝር ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ማንም… ምን የተከለከለ… ምን ደግሞ የተፈቀደ እንደሆነ በቅጡ አልገባውም፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር ከማድረግ ታቅቧል፡፡ ለምሣሌ፤ ሰው ትክ ብሎ ማየት የካሳ ክፍያ እንጂ በእሥራት አያስቀጣም፡፡ መልኳ የተዋበ ሴትን ትክ ብዬ አይቼ ክፍያውን ብከፍል ይሻላል ብሎ የሚደፍር አይገኝም፡፡

ወጣት በሙሉ በውብ ልጃገረዶች መሀል አቀርቅሮ ሲያዘግም ይውላል።…. የፀሀይ መነጽር ማድረግም ክልክል የለውም፤ ቢሆንም ከፀሐይ መነጽሩ ጀርባ “አፈጠጥክብኝ” ከሚል ውንጀላ ለመዳን አዳሜ መነፅር ማድረግ እርግፍ አድርጐ ትቷል፡፡ ወጣቱ በፊት ለፊታችን እየሮጠ አለፈ። እኛም እንዳናፈጥበት ተጠንቅቀን ታዘብነው፡፡ ለነገሩ፣ አሳዳጆቹ በእጃቸው በሚሰጡት ምልክት ጥፋተኛውን ያዙልን እያሉ ቢሆንም ከፖሊስ በስተቀር ማንም ሰው ሌላውን በእጁ ሊነካው እንደማይችል ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በፍቃድ ካልሆነ ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ሌላውን ሰው መንካት አይችልም። የብክለት ቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ይሰጣል። ሁለት ሰዎች ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ መነካካት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሰርተፊኬት ካወጡ በኋላ መነካካት ይችላሉ፡፡ ባል እና ሚስት መጋባታቸው ከተረጋገጠ ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡ ለእናት እና ለልጅ ዝምድናቸው በአግባቡ በዲ.ኤን.ኤ ተመርምሮ ከታመነበት መተቃቀፍ ይችላሉ፡፡ ምርመራው ረጅም ጊዜ ሊፈጅ ስለሚችል እስከዛው ሳይነካኩ መቆየት ግድ ነው፡፡ እየተሳደዱ ያለፉትን ሰዎች በፀጥታ፣ ከጀርባ መመልከት ቀጠልኩ፡፡

ወንጀለኛው የትኛውን ህግ አፍርሶ ይሆን ብዬ ራሴን እየጠየቅሁ በአይኔ ብቻ ሳይሆን በሃሣቤ ተከተልኳቸው፡፡ ምናልባት ድምጹን ጮክ አድርጐ ተናግሮ ይሆን ሰው? በትከሻው ሰውን ገፍቶ አልፎ ይሆን? ሴት ጠቅሶ ይሆን? አስነጥሶ ይሆን …. የትኛውንም ጥፋት ፈጽሞ ሊሆን ይችላል፡፡ የተከለከሉትን ህጐች “ለማስከበር” ሲሉ ህግ “ማፍረስ” የሚችሉት ፖሊሶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ጮክ ብለው “ያዘው!” ይላሉ፡፡ የፖሊስ መኪና ሳይረን ያጫሀሉ፡፡ አምልጦ ለመሰወር የሚሞክር ወንጀለኛ ላይ ይተኩሳሉ፡፡ ይኼንን ለነብሱ የሚሮጥ ወጣት የሚያባርሩ ሰዎች፣ ፖሊስ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ፖሊስ እስኪደርስ ድረስ ማባረራቸውን መቀጠል አለባቸው። የዜግነት ግዴታቸው ነው፡፡ ወጣቱ የሚሮጠው ፖሊስ ከመምጣቱ በፊት ለመሰወር እንጂ ከጀርባው እያሳደዱት ያሉት ሰዎች እንዳይደርሱበት አይደለም፡፡ እሱ ሸሽቶ ቤቱ ከገባ የሚያሳድዱት ሰዎችም ተከትለውት ቢገቡ… ጐኑ ከመቆም በስተቀር የሚፈጥሩት ነገር የለም። ጠላታቸውን መንካትም ሆነ አፍጥጦም ማየት አይችሉም፡፡ ቢሰድቡትም በወንጀል ይጠየቃሉ፡፡ እኔ እያሰብኩ …. እነሱ እየተባረሩ ከአይን ርቀው ተሰወሩ፡፡ እኔና ጓደኛዬም ተቀምጠን ቀረን። ትንሽ ቆይቼ ሽንት ለመሽናት ወደ ውስጥ ገባሁ። “ህዝብ በተሰበሰበበት መሽናት ክልክል ነው”። ህዝብ በተሰበሰበበት ሲጋራም ሆነ ማንኛውም የሚጨስ ነገርን መለኮስ ክልክል ነው፡፡ የሲጋራ አና ሌሎች የሚጨሱ ነገሮች ገበያ ግን ጨምሯል እየተባለ ይወራል፡፡ እንግዲህ ሁሉም በድብቅ ጥላ ጥላውን እየሄደ ህግ አያከብርም ማለት የሚፈልጉ ናቸው ወሬውን የሚያስወሩት፡፡ በብክለት ህጐቹ መፅደቅ የረኩ ሰዎች በሚዲያ ቀርበው አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ የሚሰጡት አስተያየት ግን ጮክ ብሎ ቢደመጥ የድምጽ ብክለቱን ህግ ስለሚያፈርስ ድምጽ ተቀንሶ ወይንም ጠፍቶ ነው የሚደመጠው፡፡ እነሱም የሰጡት አስተያየት ያለ ድምጽ የተቀረፀ ሊሆን ይችላል፡፡ ከብክለት ህጐቹ ውስጥ አንደኛው አንቀጽ፣ በቀለም ረብሻ ላይ የጸደቀ ነው፡፡

ቦግ ያሉ ቀለሞች የተቀቡ ቤቶች ቀለማቸው ወደ ፈዛዛ እንዲቀየር የሚያስገድድ ነው፡፡ ህጉ ለአልባሳትም ይሰራል። በጣም ደማቅ ቀለም ያላቸው ልብሶችን በማምጣት፣ በህዝብ መሀል መቅለሽለሽ የሚፈጥሩ የጨረቃ ጨርቅ ፋብሪካ እና ልብስ አስመጪዎች በግምገማ እንዲታገዱ ሆነዋል፡፡ መኪና አሽከርካሪዎች ለመኪናቸው ጥገና የሚያደርጉት ህይወታቸውን ከአደጋ ለመታደግ ሳይሆን በጭስ እና በድምጽ ብክለት ላለመከሰስ ሲሉ ነው፡፡ ሽንቴን በቀስታ ሸንቼ ስጨርስ ማፏጨት ለምን እንዳማረኝ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ማንም የሚሰማኝ የለም፡፡ በዛ ላይ ክሱም ቀለል ያለ ነው። ፍርድ ቤት መመላለሱ ግን ያሰለቻል፡፡ ባላፏጭ ይቅር፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት እና በኋላ የሟች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል…ይላሉ፡፡ የሞት ወይንም የነብስ ማጥፋት ዋና ምክንያት የነበሩት ንኪኪ እና ንግግር በመከልከላቸው የሟች ቁጥር ቀንሷል፡፡ የአእምሮ ህመምተኛ ቁጥር ግን በጣም አሻቅቧል። የሻቀበውን ህመምተኛ ለማስተናገድ የሚችሉ ብዙ ሆስፒታሎች በየመቶ ሜትሩ ተከፍተዋል። ብዙውን ጊዜ ፀጥ ባለው ከተማ ውስጥ ከፍ ብሎ የሚሰማው ድምጽ የሚመነጨው ከእነዚህ ሆስፒታሎች እያፈተለከ ነው።

የአእምሮ ህመምተኞቹ የብክለት ህጐቹን ለማክበር አይገደዱም፡፡ ህመምተኛ እስከሆኑ ድረስ። እንደ አእምሮ ህመምተኞቹ ከክልከላው ህግ ለመገላገል ሲል ልብሱን ጥሎ አበድኩ የሚል ብዙ ነው፡፡ ከብዙዎቹ ግን… በጥልቅ ምርመራ ጥቂቶቹ ብቻ መታመማቸው ተረጋግጦ ወደ ሆስፒታል የመግቢያ ፈቃድ ያገኛሉ። ፈቃድ ሳያገኙ የቀሩት ወደ ፍርድ ቤት ይላካሉ፡፡ “አብጃለሁ” በሚል የድምጽ ብክለት የፈፀሙ አምስት አመት ይፈረድባቸዋል። እንደ አእምሮ ህመምተኞች እሥረኞችም በቁጥር ብዙ ናቸው፡፡ የብዙውን ቁጥር አቻችለው የሚይዙ እሥር ቤቶችም በብዛት ተገንብተዋል፡፡ ብዙ መሻሻሎችን ህጉ አስከብሯል የሚሉ ባለስልጣናት በቴሌቪዥን ይቀርባሉ፡፡ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የንግግራቸውን ድምጽ ማድመጥም ሆነ አፍጥጦ በቲቪ የሚቀርበውን ባለሥልጣን ማየት ግን ያስከስሳል፡፡

ተመልሼ ከጓደኛዬ ጐን ልቀመጥ ስል ጓደኛዬን አጣሁት፡፡ ምናልባት ሊያለቅስ ወደ ሙዚቃ ቤቱ ጓዳ ገብቶ ይሆናል፡፡ በህዝብ ፊት ማልቀስ ክልክል ይሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባት አልቃሹ ምንም ድምጽ ካላወጣ ቢያለቅስ የማንንም መብት አይጋፋም…. እንባውን በሌላ ሰው ላይ ጠብ እስካላደረገ ድረስ… ቢያደርግስ ምን አለበት? … አሲድ አይደል…? ዝናብ እንኳን እንባውን በሁሉም ሰው አናት ላይ ወቅት ጠብቆ ያርከፈክፍ የለ?!…. …ባለ ሙዚቃ ቤቱ ጓደኛዬ የሙዚቃ አፍቃሪ ነው፡፡ የሚወደውን ነገር ወደ ሥራ ቀይሮ አትራፊ ነበር፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት፡፡ ዘንድሮ…የሙዚቃ ሲዲዎቹን እያገላበጠ በትዝታ ጆሮው ያደምጣል፡፡ ከድምጽ ብክለቱ ህግ መጽደቅ በኋላ ሁሉም የሙዚቃ አፍቃሪ ወደ ንባብ ዞረ፡፡ በሚዲያ ላይ በተስተናገዱ ብዙ አስተያየቶች ህጉ “ትውልድን ወደ ንባብ መመለስ ችሏል” ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ ትንሽ ቆየና… በጽሁፍ እና ንባብ ላይ አሉታዊ ንጭንጮች ይሰነዘሩ ጀመር፡፡ ጽሁፎቹ በውስጣቸው ድምጽ አልባ፣ ጭስ አልባ፣ ሽታ አልባ፣ ቀለም አልባ… ብክለትን የያዙ መሆናቸው በህግ አውጭው አካል ስለተደረሰበት ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ፀደቀ፡፡ ማንም ሰው በቀን ውስጥ ከተሰጠው ቃላት በላይ መጠቀም ተከለከለ፡፡ ለሥራው ከሚያስፈልገው በላይ ቃላት ተጠቅሞ የተገኘ እንዲከሰስ ተወሰነ።

ስራ ለሌላቸው “የእግዜር ሰላምታ” ያህል የሚበቁ ቃላት ለዕለት ፍጆታ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ለፖለቲከኞች እና ለህግ አስከባሪዎች የሚሰጠው የቃላት ኩፖን ከየትኛውም የሥራ መሰክ ላቅ ይላል፡፡ ቃላት እንደ ደመወዝ ሆኑ፡፡ ፖለቲከኞቹ የተፈቀደላቸውን ቃላት ተጠቅመው ህግ ሲነግዱ እና ህግ ሲያተርፉ ይውላሉ። በሃሳቤ እና በትዝታዬ መሀል እየተወዛወዝኩ ድንገት ጨነቀኝ፡፡ ጓዴ ራሱን በገመድ አንጠልጥሎ ቢሆንስ…? “ራሱን ለመግደል ሞክሮ ሳይሳካለት የቀረ ሰው አስር አመት ይቀጣል” የሚለው ህግ ትዝ አለኝ፡፡ “ራሱን ለመግደል ሞክሮ ከተሳካለት ግን በሟቹ ወንጀለኛ ፈንታ በቅርቡ የነበረው ሰው ይከሰሳል” የሚለው ህግ ወደ ሙዚቃ ቤቱ ጓዳ አስሮጠኝ፡፡ አሯሯጤ የጥርጣሬ ነው፡፡ ፈራ ተባ፡፡ መሮጥ ክልክል ይሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁማ? ጓዴ እንደሰጋሁት ተሰቅሎ ጠበቀኝ፡፡ ማመን ቸገረኝ፡፡ ማመን መቸገር ክልክል ነው? ብዬ በድንጋጤዬ ላይ ተወናበድኩ፡፡ እሱን የመንካት ፈቃድ ባይኖረኝም… እግሩን ይዤ ከፍ አደረኩት።

እሱ ተገላግሏል፡፡ ከህግ ነጻ ሆኗል፡፡ ወደ ውጭ ወጥቻለሁ፡፡ ቆሜአለሁ፡፡ ማሰብ አቁሜአለሁ፡፡ ቅድም አሳዳጆቹን አስከትሎ…ፈርጥጦ የሮጠው ወጣት በፖሊሶች ተይዞ ከታች ወደኔ አቅጣጫ ሲመጣ ይታየኛል፡፡ አባራሪዎቹ ዙሪያውን አጅበውታል፡፡ እንደ በግ ሁሉም አንድ ላይ ዝም ብለዋል፡፡ ወደኔ ቀረቡ፡፡ “ምን አጥፍቶ ነው? ለምን አሰራችሁት?” ብዬ ጮህኩኝ፤ ጆሮአቸው አጠገቤ ሲደርስ፡፡ ከጉሮሮዬ የወጣው ድምጽ ግን ከእኔ አፍ ቢወጣም እነሱ ጆሮ የመድረስ ኃይል አልነበረውም፡፡ ጩኸቴን ደገምኩት። ፖሊሶቹ ዞረው አዩኝ፡፡ ይዘው የመጡትን ወንጀለኛ ትተው ወደኔ አመሩ፡፡ “አብደህ ነው?” አለኝ፤ ከሦስቱ ህግ አስከባሪዎች አንዱ፡፡ አፉን ለሁለት ዓመት በደንብ አድርጐ የተጠቀመ ይመስላል፡፡ የተፍታታ አንደበት አለው፡፡ አላበድኩም አልኩት፡፡ ወይንም ያልኩት መሰለኝ። “ስለዚህ ወንጀለኛ ነህ ….. ተጨማሪ ቃል መናገር ከቀጠልክ ወንጀልህ ይጠብቃል” ብሎ አስጠነቀቀኝ። “የጠበቀ ወንጀል ላሳይህ…. ና” አልኩት፤ ጓደኛዬ ወደ ተንጠለጠለበት እየመራሁት፡፡ እጄ ላይ ካቴናውን ሲያስር…. ተይዞ ወደ መጣው… ወደ ወጣቱ ሯጭ አንገቴን ቀልሼ “ምን አበጅተህ ነው?” አልኩት፡፡ ወንጀል ጥፋት መሆኑን መቀበል አቁሜያለሁ። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት፡፡ “ምን ትክክል ሰርተህ ነው የታሰርከው?” ብዬ ጥያቄዬን የበለጠ ግልጽ አደረኩለት፡፡ “ልቤ ውልቅ እስኪል ስቄ ነው” አለኝ፡፡ “በማን ላይ?” “በራሴ ላይ” አለኝ፡፡ ሳቁ ወደ ኩርፊያ ተለውጧል። የእኔ ሳቅ ግን ድንገት ገነፈለ፡፡ ስለ ራሴ፣ ልቤ ውልቅ እስኪል… ከዛች ቅጽበት ጀምሬ ዘብጥያ እስክወርድ ድረስ ሳቅሁኝ፡፡ በሳቄ ርዝመት ልክ ፍርዱ እንደሚጠብቅብኝ ማወቄ ጭራሽ ግድ አልሰጠኝም።

Read 3695 times