Monday, 03 February 2014 13:30

ፍልስፍና - የጥበብ ፍቅር!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(9 votes)

“ለኢትዮጵያዊያን የግሪክ ፍልስፍና እንኳን ሊበዛብን ያንስብናል”

 <አርስጣጣሊስ ስለፍልስፍና ልዩ ባህሪያት ሲያወራ የተለየ ነጻነትና ዘና ማለትን እንደሚፈልግ ይናገራል። በዚህም ደግሞ የግብጽ/ምስር ቀሳውስት የታደሉና በፍልስፍና የላቁ እንደሆኑ ይተርካል። በፍልስፍና የላቁ ናቸው የተባለላቸው ምስሮች፤ የዛሬዎቹ ነጫጭባዎቹ ሳይሆኑ ባለርስቶቹ ጥቋቁሮች ነበሩ(ሐውልቶችን እና የዋሻ ስዕላትን ምስክር መጥራት ይቻላል)። አንቱ የምንላቸው የግሪክ ፈላስፎች በአቅራቢያቸው ያሉ ክፍለ ዓለማትን በማሰስና በማጥናት የታወቁ ነበሩ፤ በመሆኑም ወደ ግብጽ አዘውትረው ይጓዙ ስለነበር ከፍተኛ የሆነ የግብጽ አስተሳሰብ ተጽእኖ ስር ነበሩ - ግሪኮች። ስለ ፈጣሪ ኀልዎት መመራመርን፣በሒሳብ ቀመር መፈላሰፍን፣መንግስታዊ/ፖለቲካዊ ፍልስፍናን እንዲሁም ማህበራዊ አደረጃጀትን በመራመር ግብጾች፣ ካዛሬዎቹ አውሮጳዊያን እንዲሁም ከዚያኔዋ ግሪክም የቀደሙ ነበሩ።

Martin Bernal የተባለው ፕሮፌሰር Black Athena Writes Back በተባለው የጥንታዊ ግብጻዊያንና ግሪካዊያን ሳይንሳዊ ምርምሩ ውስጥ እንዲህ ይለናል፤ “Certain regions {of Greek}, notably Boiotia and the Eastern Peloponnese, had then been settled by Egyptians and Phoenicians who had built cities and civilized the natives. The Phoenicians, for instance, had introduced the alphabet, and the Egyptians had taught the Pelasgians such things as irrigation, the names of the gods, and how to worship them.” የማርቲን በርናልን ሐሳብ ወደአማርኛ ብንቀዳው እንዲህ የሚል ይመስላል፦ የግሪክ ግዛት የነበሩትን ቢዮሺያ እና ምስራቃዊ ጵሎፖነስን ግብጻዊያን እና ፎነሽያን ሰፍረውባቸው ነበር። ለምሳሌም ያህል ፎነሽያዊያን ፊደላትን ሲያስተምሯቸው፣ግብጻዊያን ደግሞ በመስኖ ማረስንና አማልክት ማምለክን እና የአማልክትን ስሞች ለግሪኮቹ አስተምረዋቸዋል እንደ ማለት ነው። ፍልስፍና በግሪኮቹ ባህል የጥበብ ፍቅር ማለት ነው ተብሎ ይተረጎማል። ምናልባትም በቅድመ ሶቅራጥስ ዘመን ውስጥ ታለስ የተባለው የግሪክ ግለሰብ ነበር “እኔ ፈላስፋ ነኝ” አለ የሚባለው። ፍልስፍና ከጥንት ከፍጥረቱ ጥበብን ማፍቀር፣ ማሰብን መውደድ፣ ምርምርን መልመድ እንደማለት ያለ ትርጉም የሚሰጠው ሙያ ነበር። እርግጥ ፍልስፍና የሚለውን ስም በመስጠት በኩል የግሪክ ቃላት ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል።

ፊሎ ማለት ፍቅር፣ ሶፊያ ማለት ጥበብ ነው ይሉታል። ማሰብ፣ መመራመር፣ መጠየቅ፣ ማወቅ፣ መጠርጠር፣ መፍትሔ ማግኘት፣ መበየን እና እንዲህ ያሉ ተግባራትን በስሩ የያዘ ሙያ ነው ፍልስፍና። ከእውቀት ዘርፎች ፍልስፍና የማይዛመዳቸው እና የማይጋባቸው ከቶ ምንም የለም። ፍልስፍና በዚህ ጠባዩ አምባገነናዊ ነው። ሁሉንም ጠቅልሎ ይውጣል። ይህንን ጠባዩን ያልተረዱ ሰዎች ፍልስፍናን እንደ አንድ አንቀጸ እውቀት ብቻ አድርገው ይበይኑታል። ይልቁንም ፍልስፍና ለሁሉም የምናውቃቸው የእውቀት ዘርፎች መሰረት እንደሆነ ይዘነጉታል። ይህ መዘንጋት ግን እንዲህ ቀላል ጉዳይ ሳይሆን ድንበሩ ሰፊ ዝንጋታ ሆኖ እናገኘዋለን አንዳንዴ። ለምሳሌ ፍልስፍና የሚለውን ቃል እና የፍልስፍናን ትርጉም እያምታታን የፍልስፍናን ሙያ ጠቅልለን ለግሪኮች(ጽራዊያን)፣ ከፍ ሲልም ለአውሮጳዊያን ብቻ እንደሆነ አድርገን እናስበዋለን። ግሪክ በእርግጥ ፍልስፍና/ፊሎሶፊያ የሚለውን ስያሜ በመስጠት ድርሻዋን ተወጥታ ይሆናል፤ ጥበብን ማፍቀርን ግን ልታስተምረን አትችልም። ምክንያቱም የግሪክ እንኳን ጥበበኞቿ አማልክቷም ሲደክማቸው እኛው ጋ መጥተው ከድካማቸው ተበረታትተው እና በጥበብ በልጽገው ወዳገራቸው ይመለሱ እንደ ነበር እራሳቸው መስክረዋል።

ኢትዮጵያ ለጥንታዊ ግሪካዊያንም ሆነ ለግብጻዊያን እንደ የአማልክት መኖሪያ ስፍራ ተደርጋ ትቆጠር ነበር። ትሮይ በተባለው የጥንታዊያን ግሪኮች ጦርነት ውስጥም አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የጦር ባለሙያ እንደተሳተፈ እና ጦርነት ለማድረግም እንደረዳቸው እራሳቸው ግሪኮቹ ይተርኩልናል። ከጥንት ጀምሮ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ቅርርብ ስለነበራቸው፣ የኢትዮጵያዊያንን ጠያይም መልክ በማየት የተደነቁት ግሪኮች፣ በቋንቋቸው ውስጥ የእኛን የወል መጠሪያ “ኢትዮጵያ”ን ዳበስ ያለ ቆዳ ላላቸው ሰዎች መጠሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል። ኢትዮጵያ ማለት በኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የኢቶጵ የሆነ ማለት ነው። ኢቶጵ ደግሞ ዓለም በጥፋት ውኃ ከወደመ በኋላ ከፍልስጤም በስተምዕራብ እስከ ዓባይ ምንጭ ድረስ ያለውን ስፍራ እርስት ጉልት አድርጎ የመሰረተና የገዛ ነው። የዛሬ ታሪክ ምሁሮቻችን፣ ኢትዮጵያ ማለት በግሪክኛ “ፊታቸው በእሳት የተለበለበ ሰዎች” ማለት ነው ይሉናል። “ኢትዮጵያ” በመሰረቱ ግሪክኛ አይደለም። ግሪኮች የእኛን ቆዳ ቀለም አይተው ስማችንንም በመዋስ ቋንቋቸው ውስጥ ማካተታቸው፣ በታሪካቸው ውስጥ ለኛ የሚሰጡትን ጉልህ ሥፍራ ማሳያ ነው። አንድን ነገር/ጉዳይ መሰየም ማለት ያንን ጉዳይ መበየን፣መግለጽ፣መወሰን እና ጠባያቱን ማስረዳት እንደ ማለት ይሆናል (ስምን መልአክ ያወጣዋል እንደሚባለው)። ግሪክ እኛን ትሰይመን ዘንድ ታሪካዊም ሆነ እዕምሯዊ መግለጫ የላትም።

እኛ እኮ ዘራችንን ከአዳም ጀምሮ የምንቆጥር፤ የዘፍጥረትን ነገር እንደ ተረት ተረት ከአዳም የሰማን፤ በጽሑፍ ቅርስ በዕድሜ ተወዳዳሪ የሌለው የመጽሐፈ ሔኖክ ባለቤቶች፤ የኖሕ መርከብ ከጥፋት ውኃ የታደገቻቸው የሰው ዘር(የካም፣የሴምና የያፌት) ድቅል ልጆች፤ ሙሴ ከግብጽ በተሰደደ ጊዜ በእረኝነት ያስጠለልን፤ የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች ዋስ ጠበቃዎች፣የሰሎሞንን ጥበብ ለመመርመር ኢየሩሳሌም ድረስ የተጓዝን፤ የሙሴ ታቦት ብቸኛ ወራሾች፤ ግዛታችን ከታችኛው ግብጽ እስከ ህንድ(ህንደኬ) ውቅያኖስ ድረስ የተንሰራፋ ነበርን እኮ - እኛ። የግሪክ ፍልስፍና ለኢትዮጵያዊያን እንኳን ሊበዛብን ያንስብናል። ስለ ፈጣሪ ያለን የግንዛቤ ጥልቀት፣ ስለ ስነ ፍጥረት ብዛትና ባህሪ ያለን የእውቀት ስፋት፣ ስለ ዓለማት ዓይነት፣ ስለ ሰማያት ደረጃና የከተሞቻቸው ዓይነት ያለን ታሪክ ግሪክንም ሆነ አውሮጳን “እንቁልጭልጭ” የሚያስብሉ ናቸው (ግና ምን ያደርጋል የኤቢሲዲውን ድግምት ከዓይናችን ማን ይቅረፍልን?)። አዕምሯችን በአውሮጳ ፍቅር ስለነፈዘ፣ በእንግሊዝኛ ካልተጻፈ በስተቀር እውቀት ያለ አይመስለንም። ኢትዮጵያ ፍልስፍና የላትም መባሉ የበታችነት ስሜት ከተጠናወታቸው የኛው ምሁራን የግል ችግር እንጅ ጉዳዩ አገራዊ ፍልስፍና በማጣችን አይደለም። የኛ አባቶች ውሸታሞች፣ የአውሮጳ ቧልተኞች ደግሞ ሳይንቲስቶቻችን ናቸው። እራሱን የካደ ትውልድ ከዚህ የተሻለ የራስ ግንዛቤ ሊኖረው አይችልም። ይኸው ነው የዛሬ ማንነታችን። ሰሞኑን ካገኘሁት ገድለ አዳም ከተባለ የአባቶቻችን ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ትንሽ ላካፍላችሁ።

አዳም በገነት እያለ መለኮታዊ ብርሃንን የተጎናጸፈ ነበርና ሌላ ብርሃን አስገኝ ነገር አያስፈልገውም ነበር። አዳም ለመጀመሪያ ግዜ ፀሐይን ያያት ወደተረገመባት ምድር ሲወርድ ነበር። መጽሐፉ እንዲህ ይለናል “ብርሃን በወጣ ጊዜም ልባቸው ተመለሰ፤ ፍርሃታቸውም ከእነርሱ ተወገደ። ልባቸውም ጸና፥አዳምም ከቤት ይወጣ ጀመር። በቤቱ በር ውጭ በመጣ ጊዜም ፊቱን ወደ ምሥራቅ አዙሮ ቆመ። ፀሐይን ተመለከተ፥ወጣችም የምታቃጥል ነበረች። ሥጋውንም አቃጠለችው፤ከማቃጠሏ የተነሳም ፈራ። በልቡም ለቅጣት እንደወጣች አሰበ። ከዚህም የተነሳ አለቀሰ፣ደረቱንም መታ፣በፊቱም ከመሬት ወደቀ።” የክስተቱን እንግዳነት አስቡት፤ አንድ በመለኮታዊ ኃይል ይኖር የነበረ የመጀመሪያ ሰው ወደ ማያውቀው ዓለም ድንገት ተወረወረ። የነበረበት ዓለምና አሁን በቅጣት የተወረወረበት ዓለም ህግጋት ደግሞ ፈጽሞ የማይገናኝ። አድማስን ሰንጥቃ ከመውጣቷ በፊት ያለን ብርሃን አይቶ የድቅድቁን ጨለማ መጥፋት እያደነቀ ከተጠለለበት የድንጋይ ዋሻ ወጥቶ ክስተቱን በአንክሮ ሲከታተል፣ ፀሐይ እሳቷን አንቅልቅላ ከተፍ አለች። ፈጽሞ የማያውቀው ጉዳይ ሆነበት፤ቆዳውን/ሥጋውን አቃጠለችው። ግዙፍነቷ እየጨመረ እሳቱ እየለበለበው ሄደ፣ “እግዚአብሔር በጥፋቴ ሊቀጣኝ ይችን ነገር ላከብኝ” ብሎ አሰበ፤ መሸሻ አልነበረውምና እራሱን እስኪስት አልቅሶ መሬት ላይ ባፍጢሙ ተደፋ።

ይህ ነው የአባቶቻችን ምናብ፤ በነበሩበት በነሱ ዘመን ሐሳብ ሳይሆን ከዘመናቸው እርቀው ጥንተ ፍጥረት ውስጥ ገብተው፣ የመጀመሪያ ክስተቶችን ማምሰልሰል መቻል ምንኛ መፈላሰፍ ነው? በእኛው ሃገር የተጻፉ መጻሕፍትን እንደልብ እንዳናጣቅስ የጥንታዊ ቋንቋ እውቀት ያግደናልና፤ ምናልባት በአፍሪካ እና ኢትዮጵያ ፍልስፍና ዙሪያ ለሚነሱ ሐሳቦች የሙግት ማዳበሪያ እንዲሆኑ አንዳንድ መጽሐፍትን ከውጭ ሰዎች ልጠቁም እወዳለሁ። ሀ) C.A Diop “Civilization or Barbarism: an Authentic Anthropology” ለ) G.G.M James “Stolen Legacy” ሐ) Ben-Jochannen “Africa, Mother of Western Civilization” መ) Patter, R. “Black Athena, Afro-centrism and the History of Science” ሠ) Martin Bernal “Black Athena” ኢትዮጵያ ከተጫነባት የዘመን እንቅልፍ እንደ ላስታ ካለው ጭንጫ ድንጋይ ስር ፈነቃቅላ ወጥታ ቁልጭ ያለች የታነጸች ሃገር (እንደ ላሊበላ) ሆና ማየትን እናፍቃለሁ። ምክንያቱም ከጥንትም ምርምሩና ጥበቡ እንዳላት ሰርታ አሳይታናለችና። ቋንቋዋን ማወቅ ነው የተሳነን፣ ከመንፈሷ መዋሃድ ነው አልሆንላችሁ ያለን እንጂ ዛሬም ኢትዮጵያ ከእነ ጥበቧ አለች። በልቦናችን ውስጥ የቀረ እንጥፍጣፊ ጥበብ አለ እንደሆን ከእርሱ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ። ጭላንጭሉን ጥበብ እሹሩሩ እያልኩ ማሳደግ። ኢትዮጵያዊነት ዛሬም አልሞተም የልብ ትርታው ከሩቅ ይሰማል። ያልቀዘቀዘ በረድ ያለ ደም በሰውነቱ ይላወሳል። ይችን ረመጥ ትኩሳት ለማንቀልቀል ምድጃው ስር መርመጥመጥ ግድ ሆኖብኛል። ሁላችንም የጥንት አባቶቻችንን የጥበብ ረመጥ እሳት በልባችን ተሸክመን ነው የምገላወጀው። ይህንን እሳት መቀስቀስና ማንነታችንን ከነሙሉ ክብሩ መግለጥ ደግሞ የኛው የራሳችን የቤት ሥራ ነው። /p>

Read 6756 times