Monday, 03 February 2014 13:26

ህገወጥነትን ያባባሰው እገዳ!

Written by  ከለማ መርሻ lemmamersha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

              ባሳለፍነው ሳምንት በአንድ ስብሰባ ለመካፈል ወደ ናይሮቢ መሄደ ነበረብኝ፡፡  ቦሌ ከሚገኘውና የሀገር ኩራታችን ከሆነው አየር መንገድ የደረስኩት፣ ከበረራ ሰዓቴ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ቀደም ብዬ ቢሆንም አየር ማረፊያው ገና ከማለዳው በሰዎች ግርግር ሞቅ ደመቅ ብሎ ነበር፡፡ ጉዳዮቼን ጨራርሼ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መስኮት ተራዬ ደርሶ ስቀርብ፣ አንድ የቢሮ ሰራተኛ ፓስፖርቴን አገላብጦ ከጨረሰ በኋላ ለምን እንደምጓዝ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ለስብሰባ መሆኑን  አስረዳሁ፡፡ ኮስተር ብሎ ትንሽ ማስፈራሪያ ቢጤ መናገር ጀመረ፡፡  
“ይኸውልህ  በናይሮቢ አድርገህ ወደ ሌላ አረብ ሃገር ብትሄድ ውርድ ከራሴ በል” አለኝ። “እንዴ ወዳጄ፤ እንዲህ አትስጋ” በማለት ሌሎች ሀገሮች ደርሼ መመለሴን ከፓስፖርቴ ላይ እንዲረዳ በማድረግ የኤግዚት ቪዛዬን ተቀብዬ ወደ አውሮፕላኑ አመራሁ፡፡
ከኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መስኮት ሰራተኛ ጋር ያደረግሁት ክርክር፣ መንግስት በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የውጪ ስራ ስምሪት በተለይም ደግሞ የአረብ ሀገራትን በተመለከተ ያወጣውን እገዳ ተከትሎ የተዘረጋ የክትልልና ቁጥጥር ስርአት ውጤት መሆኑን ገምቻለሁ፡፡ ምንም እንኳ ሰራተኛው ያሳየኝ ምግባር ባያስደስተኝም። ከዚያም በቀጥታ ወደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ድሪም ላይነር” አውሮፕላን  አዘገምኩ፡፡
የአጋጣሚ ነገር ሆኖ አውሮፕላኑ ውስጥ የደረሰኝ የመካከለኛው መቀመጫ ሲሆን በግራና በቀኝ ተቀምጠው ጉዞዬን የሚጋሩኝን መጠባበቄን ያዝኩኝ፡፡
አብዛኛው ሰው መቀመጫውን ይዟል። ከመግቢያው በስተግራ ሆስቴሷ “በዚህ በኩል ይከተሉኝ” እያለች ሁለት ልጅ እግር ሴቶችን ይዛ መጣችና፣ “እርስዎ በዛ በኩል፣ እርስዎ በዚህኛው” ስትል በግራና በቀኝ በኩል አስቀመጠቻቸው፡፡
ሴቶቹ “ቀበቶቻችሁን እሰሩ” ሲባል ግራ ግብት ሲላቸው ሆስቴሷ ረዳቻቸው፡፡ አውሮፕላኑ መሬትን ለቆ ከደመናው ሰማይ ጋር ሲቀላቀል ለሁለቱም ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ “የመጀመሪያችሁ በረራ ነው እንዴ?”  ለነገሩ ምላሹን እያወቅሁ ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፡፡ ሁለቱም በአንገት ንቅናቄያቸው ገለፁልኝ፡፡ “ወደየት እየሄዳችሁ ነው?” ሁለተኛ ጥያቄ ነበር፡፡ “ወደ ናይሮቢ” በስተቀኜ ያለችው መለሰችልኝ፡፡ “ከአሁን በፊት ናይሮቢን ታውቋታላችሁ?” እንደማያውቋትና ወንድማቸው ኑ ብሏቸው እየሄዱ መሆኑን በስተቀኜ ያለችው መለሰችልኝ፡፡  
ስሜን አስታዋወቅኋቸው፡፡ እያመነቱ ሁለቱም ስማቸውን ነገሩኝ፡፡ በስተቀኜ ያለችው አሰገደች፣ በስተግራዬ ያለቸው ራህመት፡፡ ስማቸውን ስሰማ እህትማማች እንዳልሆኑ ተረዳሁ፡፡ ሆስቴሷ ቁርስ ስታስተናግዳቸው ድንብርብራቸው ወጣ፡፡  ይኔ እንደማይከፈልበት በመንገር ዘና ብለው እንዲጓዙ አረጋጋኋቸው፡፡ ሁለቱም ሃይለኛ የቡና ሱስ እንዳለባቸው የተረዳሁት ቡና ይፈልጉ እንደሆን ስጠይቃቸው ነበር፡፡ አላቅማሙም፤ ሁለተኛም ተደገመላቸው፡፡
ትንሽ ስንግባባ አመኑኝ መሰለኝ እውነተኛ ታሪካቸውን አጫወቱኝ፡፡ መንገዳቸው ወደ ኩዌት ነው፡፡
ለካስ “ናይሮቢ ያለው ወንድማችን ጋ ነው የምንሄደው” የሚለውን አንድ ደላላ በደንብ አድርጎ አስጠንቷቸው ነው እንጂ እነሱስ ናይሮቢ ሲደርሱ በትራንዚት ወደ ኩዌት ነው የሚበሩት፡፡ እዚህ አውሮፕላን ውስጥም ደላላው 24ቱን ሴቶች ጥንድ ጥንድ አድርጎ እንዳሳፈራቸው አወጉኝ፡፡ አሰገደች  የመጣችው ከደሴ ሲሆን ራህመት የባሌ ልጅ ናት። የፓስፖርታቸውን ጉዳይ ተውትና እውነተኛ እድሜያቸው የአሰገደች 21፣ የራህመት 17 ነው፡፡ ደላላው መንግስት ወደ አረብ ሀገራት የሚደረገውን ጉዞ ስላገደ፣ ከየአካባቢያቸው ሲመጡ ከከፈሉት ብር በላይ አዲስ አበባ ሲደርሱ እንዳስከፈላቸው አውቶቢስ ተራ አካባቢ አንድ ሆቴል ውስጥ ለሳምንት ከመሰሎቻቸው ጋር አስቀምጧቸው በየእለቱ ሲጠየቁ የሚመልሱትን ያስጠናቸው እንደነበር በዝርዝር ነገሩኝ፡፡  
ድንገት ጭንቅላቴ ወደ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መስኮት ሰራተኛው ወሰደኝ፡፡ “እኔን ጠይቆኝ የነበረውን ጥያቄ እነዚህን ልጆች ጠይቋቸው ቢሆን ኖሮ በፌስታል ልብስ አንጠልጥለው ሲወጡ መከልከል ይችል አልነበረ? ወይስ ደላሎቹ ሌላ ኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ሰንሰለት በመንግስት መዋቅር ውስጥ መስርተዋል?” ስል ለጊዜው ምላሽ መስጠት የማልችለውን ጥያቄ ለራሴ አቀረብኩ፡፡
ኢትዮጵያ ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤት፣ የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ እና ከ3000 ዘመን በላይ የመንግስትነት ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ የሰው ልጅ ዛሬ ለደረሰበት የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ መሰረት የሆኑ ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ትውፊቶችን በማበርከት ለዓለም ስልጣኔ ታላቅ አስተዋፅዖ አበርክታለች፡፡ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር ለማዋል በተደረገው ወረራ ተስፋፊዎችን በመመከት፣ በቅኝ ገዥዎች ሥር ያልወደቀችና ለመላዉ ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ሐገር ነች፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን በተተበተቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ታስራለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ድህነት ትልቁን ስፍራ ይዞ ይገኛል፡፡ ከሃምሳ ፐርሰንት በላይ የሀገሪቱ ወጣት ስራ አጥ መሆኑን የጥናት ውጤቶች የሚያሳዩባት ሃገር፣ አብዛኛው ሰው የተሻለ ኑሮ፣ ስራና እንጀራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገሮች መሄድን ምርጫ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ደህንነታቸው ተጠብቆና መብቶቻቸው ተከብረው በተለያዩ ሀገራት ስራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ፣ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠርና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ከማመቻቸት ጎን ለጎን አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አግባብ መፍጠሩ ተገቢና የሌሎች ሀገራት ልምድም የሚያሳየን ነው፡፡
የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጥቅምት 14 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ ከጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ  ለስድስት ወራት ለስራ ወደ ውጭ በተለይም መካከለኛው ምስራቅ መጓዝ የተከለከለ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ይህም እገዳ የተጣለው በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ረገድ የሚታዩ የህግ፣ የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች ተፈትሸው፣ ተገቢው ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው ድረስ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ለእገዳው ሌሎችም ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡  የግል ስራና ሰራተኞች ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ የህግ ክፍተት ያለበት መሆኑ፣ ኤጀንሲዎች  ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙትን ውል ተግባራዊ አለማድረጋቸው፣ ዜጎች ለስራ ከሚሄዱባቸው ሀገራት ጋር የተጠናከረ ግንኙነት ለመመስረትና ነባሩን የዲፕሎማሲ ግንኙት ለመፈተሽ፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንፅላ ጽ/ቤቶች ለስራ ወደ ውጪ ሀገር የሄዱ ዜጎችን መብት ከመጠበቅ አኳያ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ ለመገምገም፣ እንዲሁም በህጋዊ መልክ ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ከህገወጥ ደላሎች ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑ ስለተደረሰበት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዘሪሁን ከበደ እንዳሉት፤ ህጋዊ ፍቃድ ከወሰዱ ኤጀንሲዎች አብዛኞቹ በህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል፡፡  በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ወንድሙ ጫማና  የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የውጪ ስራ ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ፤ “በነዚህ የጉዞ እገዳ ወራት ውስጥ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ለስራ የሚልኩ ደላሎችና ኤጀንሲዎችን ለመከለካከልና ለመቆጣጠር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ተናቦ ለመስራት የሚያስችል እቅድ ተግባራዊ ተደርጓል” ሲሉ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኃን በአፅንኦት ገልፀው ነበር፡፡ ለዚህም ሲባል ከሀገር መውጫ መንገዶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል መባሉን አስታውሳለሁ፡፡
ከዚህ በፊት በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መልኩ ወደ ውጭ ሀገር በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለስራ ሄደው የሚኖሩ ዜጎችን መብት በማስጠበቅ ረገድ የላኩዋቸው ኤጀንሲዎችን መንግስት የመከታተል ሃላፊነት እንዳለበትም በመግለጫው ተብራርቷል፡፡
ከ2003 እስከ 2005 ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ420 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡ ይህ አሃዝ በህገወጥ መንገድ የሄዱት ከተጨመረበት ደግሞ በሁለት እና በሶስት እጥፍ ሊያድግ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ይሄ ሁሉ የአንድ ሰሞን መግለጫና ግርግር የነበረ ሲሆን የሳውዲ አረቢያ ጋዜጣ “አረብ ኒውስ” ሰሞኑን ባስተላለፈው ዘገባው፤ እገዳው በተላለፈ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ አንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ወደ አረብ ሀገራት ተጉዘዋል - በህገወጥ መንገድ ማለት ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች በውስጤ ተፈጠሩ፡፡ መግለጫው  “በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ረገድ የሚታዩ የህግ፣ የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች በመገኘታቸው” ሲል ይህ አሰራር የሚመለከተው ማንን ይሆን? የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይንስ ሌላ? ይህ ዕገዳ ሲወጣ ምንም እንኳ ህጋዊ ተብለው ያሉት አንዳንድ ኤጀንሲዎች (ደላሎችን በመጠቀም ህገወጥ የሆነ ስራ እየሰሩ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም) በሀገሪቱ መንግስት ፓርላማ የወጣውን የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት በመፃረር እየሰሩ እንደነበር ካመነ፣ እስካሁን ፍቃድ የሰጣቸው አካል የት ሄዶ ነበር? የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ከተከለከለ በኋላ ከኤጀንሲዎቹ በላይ ሆነው ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ደላሎችና በጥቅም የተሳሰሩ ሃላፊዎችን የመቆጣጠርና የመከታተል እንዲሁም የመቅጣት ሃላፊነትስ የማን ነው? እውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ይህን ትልቅ የስራ ዘርፍ ለመሸከምና ለማንቀሳቀስ ብቃትና አቅምስ አለውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነብ፣ በየቀኑ ከምንሰማውና እኔም ከተመለከትኩት ተነስቼ፣ በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የወጣው እገዳ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመስኮት ወደ በር ያመጣ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡    
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በካፒቴን ልዑልና የስራ ባልደረቦቹ የሚዘወረው ድሪም ላይነር አውሮፕላን ናይሮቢ የሚገኘው ጆሞ ኬኒያታ አውሮፕላን ጣቢያ አርፏል፡፡ አሰገደችና ራህመትን የመሳሰሉ ምንም ወደማያውቋት ናይሮቢ የመጡ ልጅ እግር የክፍለ ሃገር ሴቶች፣ ወዴት እንደሚሄዱ ግራ ግብት ብሏቸዋል፡፡ ከአውሮፕላኑ ወርደው ሜዳ ላይ ፈሰዋል፡፡ አሰገደችና ራህመት ጠጋ አሉኝና ቀጥለው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠየቁኝ፡፡ ምን ተብለው እንደመጡ ጠየቅኋቸው፡፡ “ስትወርዱ በኤመሬትስ አየር መንገድ ያሳፍሯችኋል ተብለን ነበር”፡፡ አሉኝ፤ አዘንኩኝ፡፡ መግባቢያ ቋንቋ የላቸው፡፡ አውላላ ሜዳ ላይ ጥያቸው መሄድን አልፈቀድኩም፡፡ ለጆሞ ኬኒያታ አውሮፕላን ጣቢያ ሰራተኞች፤ ትራንዚት ጉዞ እንዳላቸው አስረድቼና መልካሙን ተመኝቼላቸው ተለያየን፡፡ የሳምንት ቆይታዬን ጨርሼ የመልስ ጉዞዬን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳደርግ፣ ራህመትና አሰገደች ታወሱኝ። የት ደርሰው ይሆን? እነዛ “ሰው በላ” ደላሎች ምን አድርገዋቸው ይሆን? ይህንን እያሰብኩ ከመንደራቸው ስለሚወጡና ስለሚቀሩ እንስት እህቶቼ አዘንኩ፡፡  

Read 1975 times