Monday, 03 February 2014 13:21

‘… ሁኔታ ነው ያለው’ እና ሌሎችንም በጨረፍታ!

Written by  ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
Rate this item
(1 Vote)

            ንባቡ እናልፋለን፡፡ ንባቡ ላይ የሚቸገር ተማሪ ሲኖር ተመልሶ ወደ ቁጥር ይከለሳል። አንዲት ፊደል ያለ አግባብ ከላላች ወይም ከጠበቀች መምሬ ቄሱ፤ “ተመለስ!” ብለው በቁጣ ያዝዛሉ፡፡ ተማሪው ተመልሶ አስተካክሎ ያነብበዋል፡፡ እንዲህ እየተባለ ተማሪው ሲገራና ሲሞረድ ከርሞ፣ አስተማማኝ ብቃት ሲያሳይ፣ ወደ ዳዊት ትምህርት እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ አሁን ዩ ኬ ጂ ገባ ማለት ነው፡፡
መቸም ከዕድሜው ገፋ ተደርጐ የተሰጠው ሰው በጣም ዕድለኛ ነው፡፡ ያለፈባቸውንና ከኋላ ሊመጡ የነበሩትን ክስተቶች ሁሉ ደርሰው ሊያይ በመታደሉ ዘወትር ፈጣሪውን ማመስገን አለበት፡፡ ዕድሜ ፀጋ ነው፡፡ እኔ እንኳ በዚህች ከሰባ መልስ ስልሳ ዘለል ዕድሜዬ፣ ብዙ ደግና ክፉ ሁኔታዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ማንም ሰው በዕድሜ ዘመኑ ብዙ ነገሮችን እንደሚያየው ሁሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ካልሁ በኋላ ወደ ጉዳዬ በቀጥታ ላቅና፡፡ ዛሬ ዲቃላና ለጆሮ የሚሰቀጥጡ የተወላገዱ የቃላትና የሐረጐች አስነዋሪ አነጋገርና አጻጻፍን እየሰማንም፣ እያነበብንም ነው፡፡ የማወራው ስለ አማርኛ ቋንቋ መሆኑን ልብ በሉልኝ ታዲያ! የዛሬን አይበለውና ያኔ ድሮ የአማርኛ ቋንቋ መማር የምንጀምረው ቄስ ተማሪ ቤት ነበር፡፡ ሀ ሁ ፊደል፣ ቁጥር፣ ሀ ግዕዝ ለ ግዕዝ፣ አቡጊዳ፣ መልዕክተ ዮሐንስ በስንት ጭንቅ አጥንተን ስንጨርስ ወንጌል ቁጥር እንገባለን፡፡ ዛሬ እንደሚባለው ከነርሰሪ ወደ ኤል ኬ ጂ ገባን ማለት ነው፡፡ ከዚያም የወንጌልን ቁጥር ስንወጣው ወደ ንባቡ እናልፋለን፡፡

ንባቡ ላይ የሚቸገር ተማሪ ሲኖር ተመልሶ ወደ ቁጥር ይከለሳል፡፡ አንዲት ፊደል ያለ አግባብ ከላላች ወይም ከጠበቀች መምሬ ቄሱ፤ “ተመለስ!” ብለው በቁጣ ያዝዛሉ፡፡ ተማሪው ተመልሶ አስተካክሎ ያነብበዋል፡፡ እንዲህ እየተባለ ተማሪው ሲገራና ሲሞረድ ከርሞ፣ አስተማማኝ ብቃት ሲያሳይ፣ ወደ ዳዊት ትምህርት እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ አሁን ዩ ኬ ጂ ገባ ማለት ነው፡፡ የ ዩ ኬ ጂ የዳዊት ትምህርቱን ተማሪው ቀጥሏል፡፡ ዳዊት የገባ ተማሪ ሁሉ በተለያየ የንባብ አወራረድ ዳዊት በመድገም ተወጥሮ ይከርማል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው ከመልዕክተ ዮሐንስ ጀምሮ በግዕዝ ስለሆነ የተማሪው ፍዳ ነው፡፡ ዳዊትን ሰባት ጊዜ ተወጥቶ፣አንደበቱ ተፈትቶ፣ ዳዊትን አሳምሮ ዘልቆታል ተብሎ ሲታመን፣ የራሱ የጊዜ ምድብ ይሰጠውና ከመምሩ እግር ሥር ከፊት ቁጢጥ ብሎ ለፈተና ይቀርባል፡፡ አሁን ‘ፋይናል ኤግዛም’ ተቀመጠ ማለት ነው፡፡ እሱ ሲያነበንብ፣ መምሩ ሲያርሙ ይከረምና ካልሆነለት መልሶ እንዲከልስ ይደረጋል፡፡ ከሆነለት ደግሞ እንዲያልፍ ይፈቀድለታል፡፡

የቄስ ተማሪ ቤት ትምህርት ይህ ብቻ አይደለም። እንዳሁኑ ዘመናዊ ትምህርት ሁሉ፣ እዚያም የትምህርት ክፍለ ጊዜ አለ፡፡ ተማሪው በመላ ማለትም፣ ፊደል ቆጣሪውም ሆነ ዳዊት ደጋሚው በየደረጃው ጧት ጧት እስከ ስድስት ሰዓት የንባብ ትምህርቱን ይማርና ለምሣ ይለቀቃል፡፡ ከቁምጣ ሱሪው ውስጥ ዳቦውን ያወጣና ቆሎ የተዘፈዘፈበትን የጠርሙስ ውሃ ጐንጨት እያለ ምሳውን ይበላል። ‘ላንቺ ቦክስ’ ከፍቶ ‘በርገር’ ወይም ‘ፒዛውን’ በላ፣ ‘ኦሬንጅ ጂዩሱን’ ጠጣ ማለት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን በእግራም ሳህን እንጀራ በወጥ ተሰጥቶት ይዞ ይመጣል፡፡ ባብዛኛው ዳቦና ቆሎ የሚሰጠው እንጀራ ጠፍቶ ወይም እህል ተወድዶ ሳይሆን፣ ልጅ ሆዱ ከሞላ እንቅልፍ ያበዛና ትምህርቱን በቅጡ ሊማር አይችልም በሚል አስተሳሰብ እንጂ፤ ፈጣሪ ይመስገን ዘመኑስ የጥጋብ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የቤት ውሻ እንኳ እንደ ልቡ ስለሚበላ የጠገበ ሆዱን ለፀሐይ ሰጥቶ ያለ ሃሣብ እንቅልፉን ሲለጥጥ ነበር የሚውል። ታዲያ ይህ ይሆን የነበር ገጠር እንዳይመስላችሁ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እኔው ራሴ ያለፍኩበት የህይወት መንገድ ነው፡፡ ተማሪው ከምሳ መልስ እርሳሱን ቀርጾ ከደብተሩ ጋር ያዘጋጅና ለእጅ ጽሁፍ ይዘጋጃል፡፡ የእያንዳንዱን የፊደል እግር የታችኛው መስመር ላይ እኩል እንዲያሳርፍ ተነግሮት፣ ፊደላቱን ጥሩ እያሳመረ እንዲጽፍ ይታዘዛል፡፡ ለሁለት ሰዓታት ያህል ልዩ ልዩ ጽሁፎች እየተሰጠው ሲጽፍ ይቆይና ከመምሩ ዘንድ ወስዶ ያሳርማል፡፡ ሥርዓተ-ነጥብ ይማራል። ነጠላ ሰረዝ፣ ድርብ ሰረዝ፣ ነቁጥ (አራት ነጥብ)፣ የቃለ-አጋኖ ምልክትና ሌላውን ሁሉ በዝርዝር ያስጠኑታል፡፡

የት እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ይማራል፡፡ እያንዳንዱ አንቀጽ ገባ ተብሎና በአዲስ መስመር ተጀምሮ መጻፍ እንዳለበት ያስተምሩታል። ብቁ ሆኖ እስኪጨርስ ድረስ ይህ ሁኔታ ጠበቅ ባለ ክትትል ይቀጥላል፡፡ የእጅ ጽሁፍ ክፍለ ጊዜ ሲያበቃ ደግሞ የቃል ትምህርት ይጀምራል፡፡ ከአቡነ ዘበሰማያት ጀምሮ ውዳሴሃ ለእግዚዕትነ ማርያም እያለ እስከ መጨረሻው በቃሉ እንዲይዝ ይደረጋል፡፡ እንዲህ እያለ የዕለቱ ትምህርት ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ይደመደማል፡፡ ነገም ያው ነው፡፡ ታዲያ ሲያጠፋና ቃላት ሲያወላግድ፣ ሲገርፉበት ሽንት በቋንጃ የሚያስወርድ ‘ጉማሬ’ እንለው የነበር ጢስና ሞራ ጠግቦ የለሰለሰ፣ ነፍስ የሚያወጣ የበሬ ቁርዝ ስላለ ያንን መቅመስ ነው፡፡ አንድ የአለንጋ ግርፍ ከተጋለጠው ባት ላይ ሲያርፍ፣ ከቃል ጥናቱ ትምህርት ውስጥ ሦስት ወይም አራት ዓረፍተ ነገሮች ወደ ልብ ዘልቀው ይገባሉ፡፡ ከዚህ በኋላ እዚያው እንደ ገቡ ይቀሯታል እንጂ ልጁ በህይወት እስካለ ድረስ ምንም መውጫ ቀዳዳ የላቸውም፡፡ የቄስ ተማሪው በየዕለቱ በዚህ ሁኔታ በቀለም እየታሸ፣ ለሁለትና ለሦስት ዓመታት አበሳውን እያየ ቄስ ተማሪ ቤት ይቆያል፡፡ መምሬ እገሌ አጠቃላይ ምዘና ካደረጉና ብቃቱና የቀለም ቋት መሆኑ በተደጋጋሚ ፈተና በቅጡ ሲረጋገጥ፣ ወደ ዘመናዊ ትምህርት እንዲሄድ ይፈቀድለታል፡፡

ብራቮ!…. አሁን ዩ ኬ ጂ ን አለፈና ተመረቀ! አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ከገባ በኋላ ይኸው የአማርኛ ትምህርት የበለጠ ተጠናክሮ ይጠብቀዋል። ከሰዋስው ጀምሮ እስከ ድርሰት አጻጻፍ ዘዴ ይማራል፡፡ ስምንቱን የንግግር ክፍሎች ማለትም፡- ስም፣ተውላጠ ስም፣ ቅጽል፣ ግስ፣ ተውሳከ ግስ፣ መስተዋድድ፣ መስተጻምር፣ ቃለ አጋኖ እያለ ስልቱንና አጠቃቀሙን ጠለቅ አድርጐ በተግባር ያጠናል፡፡ አምስቱን የስም ዓይነቶችን አገባባቸውን ጨምሮ በጥልቀት ይማራል፡፡ የተፀውዖ ስም፣ የወል ስም፣ የጥቅል ስም፣ የቁሳቁስ ስም፣ የነገር ስም … እያለ፡፡ እንዲህ ነበር ድሮ፡፡ ዘንድሮስ? ዘንድሮማ! እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ስምንተኛ ክፍል ደርሶ የአማርኛ ጋዜጣ ማንበብ የማይችል ልጅ አታውቁም? ያኔ ግን አንድ ልጅ ቄስ ተማሪ ቤት ዳዊት ከደገመ የአማርኛ መጻሕፍትን ቡን አድርጐ ያነብ ነበር፡፡ ጋዜጣንማ ወዲያው ፉት ነው፡፡ ቄስ ተማሪ ቤት የሚማር ልጅ ልክ ጥሬ ዕቃ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥቅጦ፣ ተሞርዶ፣ ቅርጽ ይዞ፣ ለስልሶና አምሮ ለሽያጭ እንደሚወጣ ሁሉ፤ እሱም በቀለም ተሞልቶ፣ በግብረ ገብ ትምህርት ተሞርዶ፣ የወገኑንና የሀገሩን ፍቅር ከነፍስና ከሥጋው አዋህዶ፣ ሥነ ሥርዓት ያለው ትሁትና አስተዋይ ልጅ ሆኖ፣ ወደ ህብረተሰቡ ይቀላቀላል፡፡ አወይ ዘመን! ያ ዘመን ተመልሶ ይመጣ ይሆን? ማን ያውቃል? ዓለም ክብ ናትና ተመልሶ ዞሮ ይመጣ ይሆናል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ያለፈ የቄስ ተማሪ፣ በበኋላው የህይወት ዘመኑ ባብዛኛው አእምሮ ስል፣ አንደበተ-ትብ፣ ትህትና እና ትልቅ ስብዕና ያለው ሰው ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ በሀገር ደረጃ እንኳ ያለፉትንም ሆነ አሁን በህይወት ያሉትን ብዙ ትላልቅ ሰዎች ለማየት ችለናል፡፡ ዛሬ የምናደንቃቸው ታላላቅ የድርሰት ሰዎችም የተገኙት በዚህ ሁኔታ አልፈው ነው፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል? በነበር ቀረ እንጂ! እንዲያው ለነገሩ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልቅም ክሽን ባለ ቋንቋ ብዙ የአማርኛ መጻሕፍት ተጽፈው የምናነብ ይመስላችኋል? አሁን ለተማሪው በሚሰጠው የአማርኛ ትምህርት አካሄድ ጨክነን የምንዘልቅ ከሆነ፣ ቋንቋውን እየበረዘና እየቀለጣጠመ የሚጽፈውን ዓይነት ሳይሆን፣ እንደ ቀደሙት ደራሲያን አንቱ የሚባሉ የብዕር ሰዎችን ወደፊትም እናፈራ ይሆን? አሁን የችግሩን ፍንጥቅጣቂ እዚህም እዚያም በውል እየተመለከትን ስለሆነ፣ የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ ሙሉውን መልስ በአጥጋቢ ሁኔታ ይሰጠናል። ድሮ እንደዚያ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ዘመኑ ዘምኖ ነው መሰለኝ ሌላ ሆነ፡፡ የዘንድሮ ልጅ ‘አበበ በሶ በላ’ እና ‘ጫላ ጩቤ ጨበጠ’ እያለ ከተማረ በቂ ነው፡፡ አማርኛ ምን ይሠራል? ኪስ አይገባ ነበር።

‘አንቶኔ ፐርቼዝ’ ያደረገው ጫማ እንዴት ቤስት መሰለህ! ተብሎ ከተወራ ሌላ ምን ይፈልጋል? ጊዜው የሚፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ “እንደ ቄሱ፣ አጐንብሱ” ይባል የለ! ደግሞስ እራሱን መከላከል ያልቻለ ቋንቋ …. ኧረ! ይበለውማ!.... የታባቱ! ‘ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ’….. እንዲሉ እንዲህ እንዲህ እያልሁ ሳይታወቀኝ እዚህ ስለደረስሁ አሁን በቀጥታ ወደ ጉዳዬ እገባለሁ፡፡ …. ‘ሁኔታ ነው ያለው’ - ይህ ሐረግ አሁን አሁን በብዛት ሲነገር የምንሰማው ነው፡፡ ያለ ቦታውም አጓጉል ከጥቅም ላይ እየዋለ ፀያፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እስቲ ከሰማሁት የማስታውሰውን በጥቂቱ ለዋቢነት ላቀርብ፡፡ ጉዳዬን ልተኩስ ታክሲ ተሳፍሬ ወደ ቦታው እየሄድሁ ነው፡፡ አንድ ከጐኔ የተቀመጠ የማላውቀው ተሳፋሪ ሰው፣ እሱ ከሚያውቀው ሰው ጋር በስልክ ያወራል፡፡ ያወራውን ባብዛኛው አልሰማሁትም፡፡ ‘አዎ! ትናንት ጋንዲ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በደህና የተገላገለችበት ሁኔታ ነው ያለው’ ብሎ ሲናገር ግን ጆሮዎቼ ተስገብግበው ልቅም አድርገው ሰሙልኝ፡፡ አጠራጣሪና ሥጋትን የሚፈጥር አነጋገር ስለሆነብኝ፣ ከሰውየው አነጋገር የተነሳ ያቺ ስለ እሷ የተወራላት ነፍሰ ጡር ሴት በሰላም መገላገሏን ተጠራጠርሁ። አንድ ነገር እርግጠኛ መሆኑ የሚታወቀው ዓረፍተ ነገሩ በግስ ተደምድሞ በአራት ነጥብ ሲዘጋ ነው። ሰውየው የተናገረው ቆየት ብሎ ትዝ ሲለኝ ግን የዘመኑ ፈሊጥ በመሆኑ ሌላ ሌላ ነገር ማሰብ ጀመርሁ፡፡ ይህ ሰው፣ ‘አዎ! ትናንት ጋንዲ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በደህና ተገላግላለች ብሎ ትክክል ቢናገር ምነው? ዓሣን በመንጠቆ ይዘው ካላወጡት ውሃ ላይ ተወልዶ፣ ውሃ ላይ ነው ሲዋልል ዓሣ የሚሞት፡፡

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ይባላልና፣ “ውሃ ወላዋይ!… ዓሣ ወላዋይ!” የሚል ነበር እንዴ የሙሉቀን ዜማ? እናንተዬ… ተሳሳትሁ መሰል!? “ቀደም ብሎ ፀሐይ የወጣችበት ሁኔታ ነው”- “ዛሬ ሻወር የወሰድኩበት ሁኔታ ነው” ..- ቸልሲና አርሴናል 1-1 የወጠበት ሁኔታ ነው ያለው”…- በዘንድሮ ዓመት ከፍተኛ ገቢ የታየበት ሁኔታ ነው ያለው… ወዘተ ይባል ተይዟል ደረት ተነፍቶ፡፡ እጅግ የሚያሳፍርና አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ምኑ ላይ ደረስነው እባካችሁ? “ቀደም ብላ ፀሐይ ወጣች”…- “ዛሬ ሻወር ወሰድሁ” “ቼልሴ አርሴናል 1-1 ወጡ” “በዚህ ዓመት ከፍተኛ ገቢ ተገኝቷል” ማለት ቀረ እንዴ? ወይስ ሲያወሩ እየተጠራጠሩ ነው ልበል? ደግሞስ እንዲህ እያሉ ስላወሩ የሚገኝ ምናምን ነገር ይኖር ይሆን? እኔ ይህን አላውቅምና ትነግሩኛላችሁ፡፡ Bomb የእንግሊዝኛ ቃል ነው አይደል? አዎ ነው እንጂ! ታዲያ ቃሉን በአማርኛ ወርሰነዋልና ስንጽፈው ያው ቦምብ እያልን መሆን አለበት። ይህ የምርጫ ነገር ሳይሆን አፍንጫችንን ተይዘን የምንገደድበት ነገር ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን ቦንብ እየተባለ ብዙ ቦታ እየተጻፈ እናነብባለን። ከራርመን ደግሞ የእንግሊዝኛውን ቃል Bonb ብለን ሳንጽፍ እንቀራለን? ጉዳችን አያልቅም እኮ! የራሳችን ችግር ሳያንሰን ጥርሳችንን አግጥጠን የሰው ቋንቋ ማበላሸት ልንያያዝ ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩ እሱስ ቢሆን መች ቀረለት፡፡ በአንዳንድ የንግድ ሱቆች ግንባር ላይ በእንግሊዝኛ የተጻፋት ማስታወቂያዎች ልብ በሉ እስቲ፡፡ እንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት ላይ የማይገኙና እኛው ራሳችን ከብብታችን ስር ቆፍረን ያወጣናቸውን በድን ቃላት በየቦታው ማንበብ ይቻላል፡፡ ‘Film Production. Dintal Clinic, Youth Acadamy ….የመሳሰሉትን ሙት የእንግሊዝኛ ቃላት ተጽፈው አላያችሁም እንዴ? ለማንኛውም ግን ድሮ ት/ቤት እያለን የምናውቀው በመሆኑ እንግሊዞች በቋንቋቸው ቀልድ አያውቁምና እንዳይሰሙን፡፡

የራሳቸውን ሊያስነኩ ቀርቶ አልፈው ተርፈው እንኳ የራሳችንን ልሳን አስጠልተው አንደበታችንን ሳንወድ በግድ ወደ እነርሱ ልሳን እየለወጡልን አይደል! እንዲያው ለምናልባቱ ለትምህርትም ሆነ ለሥራ አንድ ቀን እነርሱ ሀገር እግር ቢጥለን ጥሩ ስለማይሆን ካሁኑ መጠንቀቁ የሚከፋ አይመስለኝም፡፡ ‘ዋ! … አለች አሞራ’ ተብሎ የለ! በጥራዝ ነጠቅ አነጋገር፣ “ጨርቁ የተሠራበት ማቴሪያል ከሌላ ይለያል” “… የተባለው ሶፍት ድሪንክ ጠቃሚ የሆኑ ሚኒራሎችን የያዘ ነው…” ይባልልኛል። ይኸ የቀረበው ምሳሌ ሊሆነን እንጂ ጉዳችንማ መች በዚህ ያልቃል፡፡ “ጨርቁ የተሠራበት ቁስ ከሌላ ይለያል” የተባለው ለስላሳ መጠጥ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ማዕድናትን የያዘ ነው…” ተብሎ ለምን አይነገርም? እኛ ስላልፈለግን ብቻ አናውቀውም እንጂ የአማርኛ ቋንቋ ግን የቃል እጥረት የለበትም፡፡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ፤ ጣፈጠም መረረም በየዕለቱ ማስታወቂያ እናነብባለን፣ እንሰማለን አይደል! አዎ!…. እንኮመኩማለን እንጂ! “የእገሌ ፈርኒቸር እጅግ የተዋበና ኮምፎርት ያለው ነው” እየተባለ ማስታወቂያ ላይ ይለፈፋል፡፡ አጀብ እኛ፣ ወይ አንሞት ወይ አንተኛ አለ ይባላል፣ ግራ የገባው ያራዳ ልጅ፡፡ እስቲ ይታያችሁ፣ ካልጠፋ ቃል የእንግሊዝኛውን ፈርኒቸር እና ኮምፎርት አማርኛ ላይ ወሰዶ መፐወዝ ምን ይባላል? ምን የሚሉት ቅብጠት ነው? ውሃና ዘይት ለመቀላቀል እንደ መሞከር እኮ ነው፡፡ የጋራ ሀብት የሆነውን ቋንቋ መልኩን አጥፍቶ ሚስቶ ለማድረግ ማነው የሌለውን ፈቃድ የሰጣቸው? ወይስ ባለቤት የለውም ተብሎ ነው? “የእገሌ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስ እጅግ የተዋበና ምቹ ነው” ቢባል ያልሰለጠነ ፋራ ሊያስብል ነው እንዴ? ጉራማይሌው የማስታወቂያ እወጃ፣ ገበያ ያሸሻል እንጂ ገዢ አያግተለትልም እኮ! ወይስ መዘመኑ ነው? ‘ተኖረና ተሞተው!’ አሉ እማሆይ ድንቄ፡፡ በአጠቃላይ ዕይታ ግን እንዲህ ልበል፡፡

በእንግሊዝኛ አንድ ዓረፍተ ነገር አስተካክሎ ጽፎ ራሱን በትክክል መግለጽ የሚቸገረው ግለሰብ፣ እንዲያው ለቄንጥ ብቻ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላትን አማርኛ ውስጥ እየወሸቀ ሲናገር በተሰማ ጊዜ መጥፎ ግምት ላይ ይወድቃል፡፡ እንግዲህ የሚናገርን ሰው ሩቅ ሳንሄድ በቀላሉ ከጐናችን እናገኛለን። ወጣም ወረደ፣ ራስን መሆን ጥሩ ነገር ነው፡፡ አይመስላችሁም? ከዚህ ጋር አያይዤ ደግሞ አንድ ነገር ለመናገር ይፈቀድልኝ፡፡ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠሩ ሰዎች ቋንቋውን ጠንቅቀው ያወቁ መሆን እንዳለባቸው እርግጥ ነገር ነው፡፡ በቃለ መጠይቅ ወቅትም ሆነ በሌላው የየዕለቱ ሥራቸው ላይ ከአማርኛ ጋር የእንግሊዝኛ ቃልን እየቀየጡ ባይናገሩ መልካም ነገር ይሆናል፡፡ ከማያስፈልግ ትችትም ይድናሉና፡፡ በዚያ ላይ በሳልነታቸውን አመላካች ስለሚሆን በጥንቃቄ አስበውበት ከዚህ ከንቱና አፀያፊ ነገር ራሳቸውን እንዲያርቁ በእጅጉ ይመከራል፡፡ አማርኛን በተመለከተ ግን ማንም ፍላጐቱ ያለው ሰው፣ የቀደሙ የትላልቅ ደራሲያን ድርሰቶችንና ሌሎችንም የማጣቀሻ መጻሕፍትን እያገላበጠ ትክክለኛውን ቃልና ቃሉ የሚጻፍባቸው ፊደላት፣ አረባባቸውንና ብዜታቸውን በውል ተገንዝቦ ቢጠቀምባቸው፤ ይጠቅመዋል እንጂ ምንም የሚጐዳበት ነገር የለም፡፡ ግን ሰዎች! እንዴት ነው ነገሩ? ፍላጐቱና ተነሳሽነቱስ አለ? ጊዜዉስ ይመቸናል? ወይስ በቃ እንዲሁ እንደ በቀቅን (ቀ እና ቅ ይጠብቃሉ) ልንቀረው ነው? - ግራ ገባን እኮ! እጅ እግር የሌለው ለያዥ ለገራዥ የቸገረ ነገር…

Read 2121 times