Monday, 03 February 2014 13:19

“ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ!...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(14 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሚስት ነፍሰ ጡር ነች፡፡ ባል ማታ መሸት አድርጎ ይመጣል፡፡ እናላችሁ… ቤት ሲደርስ እራት እንዲበላ ሲጠየቅ፣ ከጓደኞቹ ጋር ውጪ መብላቱን ይናገራል። ይሄኔ ሚስት “ምን በላህ?” ብላ ትጠይቀዋለች፡፡ ባልም “የበግ ቅቅል…” ይላል፡፡ ከዛ ለሽ ይላሉ፡፡
ውድቅት ሌሊት ላይ ሚስት ድንገት ብድግ ትላለች፡፡ ባልም ያመማት መስሎት ደንግጦ “ምን ሆንሽ?” ይላታል፡፡ እሷም “አማረኝ…” ትለዋለች፡፡
እሱም “ምን አማረሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ ምን ትለዋለች መሰላችሁ…“የበግ ቅቅል አማረኝ…” ይታያችሁ… በዛ ውድቅት ሌሊት የበግ ቅቅል!
ይሄኔ ባል ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው…“በዚህ ሌሊት የበግ ቅቅል ከየት ላመጣልሽ ነው! ከፈለግሽ ድንች ቀቅለሽ ብዪ!”
እናላችሁ…በብዙ ቦታ “አማረን…” ባልን ቁጥር… አለ አይደል… “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” የሚል ነገር በዝቶብናል፡፡ ደግሞላችሁ…“አማረኝ” የምንለው የቅንጦት ምናምን ነገር ሳይሆን መብታችን የሚፈቅድልንን፣ ማንንም ሳንለማመጥ ማግኘት የሚገባንን አገልግሎት ቢሆንም “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” ባይ እየበዛብን ግራ ገብቶናል፡፡  
“የበግ ቅቅል አማረኝ…” ስንል “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” የሚባልበትን ዘመን ያሳጥርልንማ!
እኔ የምለው… ቅቅል ምናምን ነገር ከተነሳ አይቀር…አንዳንድ ምግብ ቤቶች ምግባቸውን የሚያበስሉት በምንድነው? አሀ…ግራ ገባና! አንዳንዴ ‘ጥብስ’ ምናምን ተብሎ የሚመጣልን እኮ ሥጋውን ገና አፋችሁ ስታደርሱ ‘የሚያጉረመርም ድምጽ’ የሰማችሁ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ አሀ… ሥጋውን እኮ ብርድ አንዘፍዝፎት ፀሀይ እየሞቀ ካለ በሬ ላይ ቆረጥ አድርገው ያመጡት ይመስላላ!
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የ‘አማረኝ’ ነገር ከተነሳ …በውሰትም ቢሆን ቤት ውስጥ ኮምፒዩተርና ሲ.ዲ.ኤም.ኤ ምናምን ይኑርማ። አሀ…“ፌስቡክ አማረኝ…” ብትል ምን ሊኮን ነው!
የፌስቡክ ነገር ኮሚክ እየሆነ እኮ ነው… በእኛ አገር ቶሎ ‘ስልጣኔ ቀብ’ አድርጎ ‘የማሻሻል’ ጥበብ (ቂ…ቂ….ቂ…) ባልና ሚስት በአንድ አልጋ ሁለት ጫፍ ላይ ሆነው በፌስቡክ ‘ቻት እንዳይደራረጉ’ ፍሩልኝማ፡፡
(ሞባይል የመጣ ሰሞን አንድ ጠረዼዛ ላይ ተቀምጠው በሞባይል ስልኮቻቸው ይነጋገሩ የነበሩ ‘ፍሪኪዎች’ ትዝ አይሏችሁም!)
በዛ ሰሞን በፌስቡክ የተዋወቃትን ሴት በአካል ሲያገኛት ‘ማሞ ሌላ መታወቂያ ሌላ’ ስለሆነችበት ሰው አንድ ወዳጄ ሲያጫወተኝ ነበር፡፡ ዕድሜ ለ‘ፎቶሾፕ’… ምን ችግር አለው…ሁሉም ይስተካከላል፡፡  ቁመት ሲታደል “ሊስት ውስጥ የለህበትም…” ተብሎ የተባረረው የእኔ ቢጤው ሁሉ ፌስቡክ ላይ ማይክል ጆርዳንን አክሎ ቁጭ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…በፌስቡክ ፎቶዋ… “የሚገርመው እኮ እንዴት እስከዛሬ ኢንተርናሽናል ሞዴል እንዳልሆነች ነው…” የሚባልላት… አለ አይደል… በአካል ስትመጣ… በኩዊን ላቲፋ ‘ሸንቃጣነት’ የምትቀና አይነት ሆና ቁጭ፡፡
ለክፉም ለደጉም “ፌስቡክ አማረኝ…” ከመባሉ በፊት መዘጋጀቱ አሪፍ ነው፡፡
አስቸጋሪ ነው…ለምሳሌ “ቤተመንግሥት መግባት አማረኝ…” ብትል ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ምን ማድረግ መሰላችሁ…እኔ ነኝ ያለ ደረቅ፣ ዳግም አረቄ ማጠጣት፡፡ ልክ ነዋ… አይደለም አራት ኪሎ ያለው…አለ አይደል… የእንግሊዟ በኪንግሀም ቤተመንግሥት ትገባለቻ! አይ… የእኛው እኮ ‘ቤተመንግሥት’ የሚለው ስሙ አልለቅ ብሎት ነው እንጂ  እውነተኛ ‘ንጉሥ’ የለበትም ይቅርታ…‘ላይኖርበት ይችላል’፣ ብዬ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… (እነ እንትና ‘ነገር’ አልገባ እያለኝ እስከመቼ እንደምከርም አሁንም ግራ እንደገባችሁ ነው፣ አይደል!)
“የበግ ቅቅል አማረኝ…” ስንል “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” የሚባልበትን ዘመን ያሳጥርልንማ!
ሀሳብ አለን…በ‘ሰማንያ ፊርማ’ ወቅት ‘አሜንድመንት’ ይካተትልን፡፡ እናላችሁ… ‘ሚስት ነፍሰ ጡር በምትሆንበት ወቅት ሊያምሯት የማይገቡና ቢያምሯትም የማያስቀይሙ ነገሮች’ በሚል በ‘አባሪ’ ይያያዝልንማ!
እናማ…
“ሥልጣን አማረኝ፡፡”
“ሀብታም መሆን አማረኝ፡፡”
“ባልዋልኩበት ሜዳ ‘የቡድንና ቡድን አባቶች’ ውስጥ ያለመፈረጅ አማረኝ፡፡”
“በዜግነቴ በጋራ እንጂ በትውልድ ስፍራዬ በግል ያለመመዘን አማረኝ፡፡”
“እከሌ የተባሉትን ባለሥልጣን ማናገር አማረኝ።”…..ምናምን አይነት አማረኝ ነገሮች ይከለከላሉ… ግልግል ማለት አይደል!
ደግሞላችሁ…
“አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መስማት አማረኝ፡፡”
“‘የዛሬውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው…’ የሚሉ የክብር እንግዶች አማሩኝ፡፡”…ምናምን አይነት ነገሮች… አለ አይደል… ቢጠየቁም ችግር የለውም፡፡
እናላችሁ… እንደው ዝም ብሎ “አማረኝ…” ማለት ብቻ ሳይሆን የሚሆነውና የማይሆነው መለየት አለበታ! ግራ የተጋባው ለምን መሰላችሁ… ‘በሌላው ያየነው’ ሁሉ ለእኛም ይደርስ እየመሰለን… “አማረኝ…” ማለት በማብዛታችን ነው፡፡
“የበግ ቅቅል አማረኝ…” ስንል “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” የሚባልበትን ዘመን ያሳጥርልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መቼም አንዲት ነፍሰ ጡር “አማረኝ” ካለች… አለ አይደል… እንደ ምንም ለማግኘት መሞከር ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ…“ጓደኛህ አማረኝ…” ብትለው የት ውስጥ ይገባል! (እኔ የምለው… ይሄ… “አፈር አማረኝ…”  “ትርፍራፊ ምግብ አማረኝ…” የሚሉት ነገር አለ፣ ቀረ?)
ለነፍሰ ጡሮች ጓደኛ አታሳዩማ! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ብዙ ነገሮች ያምሩናል፡፡ ስድብና መወነጃጀል የማንሰማበት ሀያ አራት ሰዓት ‘አምሮናል’፡፡ ልክ ነዋ… ሰዉም፣ ሬድዮኑም፣ ቲቪውም ጋዜጣውም፡ አንድም ክፉ ቃል የማያወጡበት፣ ሌላውን የማይኮንኑበት ሀያ አራት ሰዓት ‘አምሮናል’፡፡
ንግግራችን መሀል ላይ ተቆርጦ የእኛንም ‘ወሽመጥ የማይቆርጥበት’፣ ከመንገድ ማዶ እያየነው ያለ ወዳጃችንን “የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” የማንባልበት፣ የአሥር ደቂቃ የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ ‘አምሮናል’፡፡
“ኧረ የትውልዱ ብዙ አባላት ወዴት እየሄዱ ነው!” “ኧረ እባካችሁ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመኖሪያ ኮንዶሚኒየሙ፣ በየመዝናኛው ብዙ ወጣቶች ገደሉ አፋፍ እየተጠጉ ምነው ዝምታ በዛ!” … ምናምን አይነት እሮሮዎች የሚቀንሱበት ብሎም የሚጠፉበት ዘመን ‘አምሮናል’፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀደም ጋዜጣ ላይ የቢሮ ሴቶች  ከሥራ ሰዓት ውጪ ትርፉን ቢዙ ‘እያጧጧፉበት ነው’ ተባለ አይደል! እንዲህ ነው የሥራ ክቡርነት! አሀ…የዳያስፖራ ወዳጆቻችን “አሥራ ስድስት ሰዓት ነው የምንሠራው” እያሉ ሲሸልሉብን ሴቶቻችንም አሥራ ስድስት ሰዓት ‘ይሠሩልን’ ጀመራ!
“የበግ ቅቅል አማረኝ…” ስንል “ከፈለጋችሁ ድንች ቀቅላችሁ ብሉ…” የሚባልበትን ዘመን ያሳጥርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7403 times