Monday, 03 February 2014 12:55

የዋሊያዎቹ ግምገማ ፈሩን እየሳተ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ማነው ተጠያቂ ጋዜጠኞች፤ አሰልጣኙ፤ ተጨዋቾች፤ ፌደሬሽኑ? በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ምድብ የነበሩት ጋና እና ሊቢያ በሚያደርጉት የዋንጫ ጨዋታ ዛሬ ሊፈፀም ነው። በምድብ 3 የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሊቢያ 1ለ0 እንዲሁም በጋና 2ለ0 መሸነፉ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ምድብ እርስ በራስ በተገናኙበት ጊዜ ጋና እና ሊቢያ 1 እኩል አቻ ተለያይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ያለበት ምድብ በደቡብ አፍሪካ በተደረገ አህጉራዊ ሻምፒዮና ለዋንጫ ጨዋታ የደረሱ ሁለት ቡድኖችን ሲያስገኝ የቻን የዋንጫ ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዓመት በፊት እዚያው ደቡብ አፍሪካ በተስተናገደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ቡድን በምድብ 3 ከናይጄርያ፤ ቡርኪናፋሶ እና ዛምቢያ ጋር ተደልድሎ ነበር። በምድብ ጨዋታዎች ዋልያዎቹን ናይጄርያዎች 2ለ0 እንዲሁም ቡርኪናፋሶ 4ለ0 አሸንፈው እርስ በራስ ተገናኝተው 0ለ0 አቻ ከተለያዩ በኋላ በፍፃሜ ጨዋታ ናይጄርያ 1ለ0 ቡርኪናፋሶን በማሸነፍ ዋንጫውን ወስዳለች፡፡ ሊቢያ እና ጋና ለቻን የዋንጫ ያለፉት ተጋጣሚዎቻቸውን በመለያ ምቶች አሸንፈው ነው፡፡ ጋና ናይጄርያን 4ለ1 ስታሸንፍ ሊቢያ ደግሞ ዚምባቡዌን 5ለ4 በመርታት ለፍፃሜው ደርሰዋል።

የሊቢያው አሰልጣኝ ሃቪዬር ክሌሜንቴ በወጣቶች ስብስብ የተጠናከረው ቡድናቸው ለዋንጫ ጨዋታ የደረሰበትን አስደናቂ ጥረት እንደሚከሩበት የተናገሩ ሲሆን፤ የጋና አሰልጣኝ ማክሲም ኒኮዲ በበኩላቸው በቻን ውድድር ምርጥ ብቃት ያሳዩ ወጣት ጋናውያን ዋንጫውን በመውሰድ ለጥቋቁሮቹ ክዋክብቶች የዓለም ዋንጫ እድል መነቃቃት እንዲፈጥሩ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ሊቢያ በአህጉራዊ ውድድር ለዋንጫ ጨዋታ ስትደርስ ከ1982 እኤአ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን በ2009 እኤአ ላይ በኮትዲቯር በተካሄደው 1ኛው ቻን ላይ በዋንጫ ጨዋታ በዲሪ ኮንጎ 2ለ0 ተሸንፋ ዋንጫውን ያጣችው ጋና ክብሩን መልሶ ለማግኘት አጋጣሚ ተፈጥሮላታል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለቻን ውድድር ባዘጋቸው 3.2 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ መሰረት ሻምፒዮን ቡድን 700 ሺ ዶላር፤ ለሁለተኛ ደረጃ 400ሺ ዶላር፤ ለደረጃ የሚጫወቱ ሁለት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 250ሺ ዶላር፤ በሩብ ፍፃሜ የወደቁ አራት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 175ሺ ዶላር፤ በምድባቸው 3ኛ ደረጃ ያገኙ 125ሺ ዶላር እንዲሁም በየምድባቸው አራተኛ ደረጃ ይዘው የጨረሱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 100ሺ ዶላር እንደሚከፈላቸው ታውቋል። 3ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮና ቻን ውድድር ዛሬ በዋንጫ ጨዋታ ኬፕታውን በሚገኘው የኬፕታውን ስታድዬም ሲደረግ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በክብር እንግድነት የሚገኙ ሲሆን በታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ሙዚቀኞች እና ዳንሰኞች ልዩ የመዝጊያ ስነስርዓት እንደሚደረግም ታውቋል፡፡ ከዋንጫ እና የደረጃ ጨዋታዎች በፊይት በቻን ውድድር በተደረጉ 28 ጨዋታዎች 72 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም በአንድ የቻን ጨዋታ 2.6 ጎል በአማካይ የሚቆጠርበት ሆኗል፡፡

በደቡብ አፍሪካ መስተንግዶ የቻን ውድድር ለ3ኛ ጊዜ በስኬት እንደተከናወነ እየተገለፀ ሲሆን፤ በውድድሩ የሚመዘገብ ውጤት በወዳጅነት ጨዋታ ደረጃ ለፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ነጥብ የሚያሰጥ ሊሆን መብቃቱ አዲስ የለውጥ ምእራፍ ነው ተብሏል። በቻን ውድድር ተሳታፊ በሆኑ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ለአፍሪካ እግር ኳስ ተተኪ የሚሆኑ ታዳጊ ተጨዋቾች በብዛት መታየታቸው፤ ተመጣጣኝ ፉክክሮች መደረጋቸውም ተደንቋል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ2015 ለሚደረጉ ውድድሮች የማጣርያ ጨዋታዎች ድልድን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ በ2015 እኤአ ላይ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተዘጋጀው የማጣርያ ፕሮግራም ላይ 51 አገራት ተሳታፊ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአህጉራዊ ውድድሮች ባስመዘገበችው ውጤት ለምድብ ማጣርያ በቀጥታ ካለፉት 21 አገራት አንዷ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ29 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና በዋና ውድድር በነበረው ተሳትፎው 4 ነጥብ፤ በ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ተሳትፎው 1 ነጥብ፤ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች በ7 ነጥብ አስመዝግቦ በአጠቃላይ 12 ነጥብ ለምድብ ማጣርያ ካለፉት 21 አገራት መካከል 16ኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በተያያዘ ካፍ በ2015 በሀ20 እና በሀ17 ብሄራዊ ቡድኖች ለሚደረጉ የቅድመ ማጣርያ ውድድሮች የጨዋታ ድልድል አሳውቋል። ኢትዮጵያ በ2015 ሴኔጋል በምታዘጋጀው የሀ20 ሻምፒዮና በቅድመ ማጣርያ ከሲሸልስ ጋር የትገናኝ ሲሆን በደርሶ መልስ ጥላ ለማለፍ ከበቃች በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ተጋጣሚዋ ደቡብ አፍሪካ ነች፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 በሀ17 ኒጀር ለሚደረገው የታዳጊዎች አህጉራዊ ሻምፒዮና የቅድም ማጣርያ እንድትሳተፍ የቀረበውን ግብዣ ሳትቀበል ቀርታለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ዛሬ በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ከጋዜጠኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን የነበረውን ተሳትፎ በሚመለከት የግምገማ መድረክ ሊያወያይ እንደሆነ ታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ፤ ተጨዋቾች እና ፌደሬሽን ከናይጄርያ ጋር በካላባር ከተደረገው የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ በተለያዩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች ከስፖርት ጋዜጠኞች የጀመሩት ንትርክ ሰሞኑን ተባብሷል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ከ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ጨምሮ በቻን ውድድር ላይ የነበሩ ተጨዋቾች እና ከቡድኑን አባላት በኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ስብስባ ያደረጉ ሲሆን በዚሁ መድረክ አንዳንድ ተጨዋቾች በቻን ተሳትፎ ውጤቱ የጠፋው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የሚሰጡት አስተያየት አዕምሯችንን በመረበሹ እና በመበጥበጡ በማለት አቤቱታ ማሰማታቸው ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር ያሳየው ደካማ እንቅስቃሴ እና ውጤቱ ከምን የመጣ ነው? በሚል ርዕስ በተካሄደው ስብሰባ ተጨዋቾቹ አስተያየት ሲሰጡ ከመጀመሪያው ቀን ሽንፈት በኃላ በነበሩት ሁለት ጨዋታዎች ሜዳ ውስጥ እንዴት መጫወት እንዳለብን እስክንዘነጋ ድረስ የጋዜጠኞቹ ትችት ተፅእኖ ነበረው ብለው አማርረዋል፡፡

Read 1658 times