Monday, 03 February 2014 12:57

“የስራ ፍሬውን ስንነጥቀው ይበረታታል” ብሎ መመኘት ሃጥያት ነው

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(14 votes)

          የሰበቡ አይነትና የስያሜው ብዛት ለጉድ ነው። “የሃብት ልዩነትን ለማጥበብ”፣ “የድሆችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ”፣ “የአገር ኢኮኖሚን ለመገንባት”፣ “ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ”፣ “አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ” ... ማለቂያ የለውም። የኋላቀር ባህል ምሶሶና ማገር ሆነው ለዘመናት የዘለቁ፣ ዛሬም በሁሉም ፓርቲዎች፣ በአብዛኛው ምሁርና ዜጋ፣ እንደ “ቅቡል” እና እንደ “በጎ” የሚቆጠሩ እነዚህ ሁሉ ሰበቦች ሲደረደሩ የምንሰማው ለምን አላማ ነው? ሃብት ከሚያፈሩ አምራቾችና ከቢዝነስ ሰዎች ገንዘብ ለመውሰድ! የንጥቂያው መጠን እጅግ ቢለያይም፤ በደርግ ዘመን እንደተረገው በንብረት ውርስም ሆነ በዝርፍ፣ አሁን እንደሚደረገው በተለያዩ የታክስ አይነቶችም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር፤ በተመሳሳይ አስተሳሰብ (ሰበብ) የሚፈፀሙ ናቸው። ከሃብታሞች ወስዶ ለድሆች ለመስጠት! ብዙዎቻችን በዚህ አስተሳሰብ እንስማማለን። እንደ ደርግ እጅግ ካልመረረ በቀር፣ በሃሳብ ደረጃ በጎ ነው ብለን እንቀበላለን። በውጤቱም፣ ነፃ ትምህርት፣ ነፃ ህክምና፣ ነፃ ጉርሻ እናገኛለን ብለን እናምናለን። እና ደግሞ፣ በየአመቱ እድገት እንዲመዘገብ እንጠብቃለን። እኮ እንዴት? ሃብት የተዘረፉና የተነጠቁ ሰዎች፣ ነገም እንዲሁ ከዛሬ የበለጠ የሚዘረፍና የሚነጠቅ ሃብት ይፈጥሩልናል ብለን እንመኛለና።

እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ፣ አላዋቂነትና ሃጥያት የመሆኑን ያህል፣ ብዙም ሳያራምድ ለውድቀት የሚዳርግና ኋላቀር የድህነት ስቃይ ውስጥ አስሮ የሚያስቀር አጥፊ አስተሳሰብ ነው። እንዴት? አጥፊ አስተሳሰብ በተግባር ምን እንደሚመስል በትንሹ ለመመልከት ከፈለጋችሁ፤ ማንንም የማያከራክሩ ቁልጭ ያሉ መረጃዎችን ልጥቀስስላችሁ። መረጃዎቹ፣ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች (ከኤክስፖርት ቢዝነስ) በየአመቱ ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ የሚያሳዩ ናቸው። ምናልባት አንዳንዶቻችን፣ ‘የኤክስፖርት እና የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ እኔን አይመለከቱም’ የሚል ስሜት ያድርብን ይሆናል። አይምሰላችሁ። አንደኛ ነገር፤ በአምራችነት ወይም በድጋፍ ሰጪነት፣ በነጋዴነት አልያም በተቀጣሪነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የኑሮ መተዳደሪያቸውን የሚያገኙት ከኤክስፖርት ገቢ ነው፤ የሰሊጥና የቡና ገበሬዎችን፣ የአበባ እርሻ ተቀጣሪዎችን፣ የወርቅ ማዕድን ቆፋሪዎችን ወዘተ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ምግብ ለማዘዝ፣ መፅሃፍ ለመግዛት ወይም ሶፋ ለማሰራት፤ የኔ፣ ያንተ ወይም የሷ ደንበኞች ይሆናሉ። የኤክስፖርት ገቢ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይመለከተናል። የቡና አዝመራ ደርሶ ገበያው ሲደራ፤ የይርጋ ጨፌ ወይም የጂማ አካባቢዎች ጠቅላላ የቢዝነስ እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚደምቅ ማየት ትችላላችሁ።

ሁለተኛ ነገር፣ ዘይትና መድሃኒት፣ ልብስና ኮምፒዩተር፣ ወረቀትና መኪና ... ሕይወትን የሚያመቻቹልንና በየእለቱ የምንገለገልባቸው ተመሳሳይ ቁሳቁስ፤ በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የመጡ ናቸው። ሶስተኛ ነገር፣ ከአስፋልት ‘ሬንጅ’ እስከ አርማታ ብረት፣ ከጄኔሬተርና ሞተር እስከ ተራቀቁ ማሽኖች፣ ለኢንቨስትመንትና ለእድገት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል። የሞባይልና የኢንተርኔት ኔትዎርክ የሚዘረጋው፤ መንገድና ግድብ የሚገነባው በምን እንደሆነ እናውቅ የለ? የውጭ ምንዛሬ ከሌለ፣ የህዳሴ ግድብም ሆነ የባቡር መስመር አይኖርም። ምን አለፋችሁ? ባለፈው ጥቅምት ወር አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን በሚመለከት ባወጣው ባለ 78 ገፅ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው ትልቁና ብቸኛ አገራዊ ስጋት ምን መሰላችሁ? ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል ገንዘብ ማጣትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት! “ Risks: Persistent shortfalls in the financing of planned infrastructure investment and a tightening of foreign exchange availability could constrain medium-term growth in the absence of policy adjustments....” (IMF Country Report No. 13/308) የኤክስፖርት እና የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ፣ ሁላችንንም የሚመለከት ብቻ ሳይሆን፣ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው - በተለይ በተለይ ደግሞ አሁን ከባድ ችግር ውስጥ መግባቱ ሲታይ! ኤክስፖርት ሲብረከረክና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሲደነቃቀፍ፣ ቶሎ መላ ካልተበጀለት ጠቅላላ ኢኮኖሚውና ሕይወታችን ይናጋል። አሁን የተፈጠረውን ችግር በደንብ ስታዩት፣ አሳዛኝም አስገራሚም ነው። አሳዛኙ ነገር፣ መብረክረኩና መደነቃቀፉ የተከሰተው፣ በአንዳች ፈታኝ ችግር ሳቢያ ሳይሆን፤ በመንግስት ፍላጎት፣ ፈቃድና ውሳኔ አማካኝነት ነው።

ተረጋጉ፤ ውሳኔውን ሳታዩ፣ መንግስትን ብቻ ለመውቀስ አትቸኩሉ። ገንዘብ በብዛት እየታተመ የአገሪቱ ብር መርከሱን የተመለከቱ የአለም ባንክና አይኤምኤፍ፣ የዶላር ምንዛሬ ከወደ 26 ብር ገደማ ከፍ እንዲል ሃሳብ ቢያቀርቡም፣ መንግስት እሺ አላለም። ብዙ ሰዎች፣ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ይህንን የመንግስት ውሳኔ እንደበጎ ተግባር ይቆጥሩታል። ግን እንደምታዩት፣ “የውጭ ምንዛሪ የብዙዎችን ሕይወት የሚነካና ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ስለሆነ መንግስት ይቆጣጠረው። ከዋጋ በታች በ19 ብር ብቻ ያሰኘንን ያህል ዶላር መግዛት እንችላለን” የሚለው ሃሳብ አያዋጣም። ዶላር የሚያመጡልንን አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎችን እያከሰረ የዶላር ምንጫችንን ከማድረግ ያለፈ ውጤት የለውም። አስገራሚው ነገር፣ ካሁን በፊት፣ በተመሳሳይ ውሳኔ ሳቢያ አገሪቱ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የገባችበትና ነገሩ እንደማያዋጣ በግልፅ የታየበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ አምስት አመት እንኳ አልሞላውም። ነገር ግን፣ አጥፊው አስተሳሰብ ስላልተለወጠ፣ አሁንም እዚያው ችግር ውስጥ ተመልሰን ገብተናል። እስቲ የአስር አመቱን ውጣ ውረድ እንመልከት። እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ፣ ያለ አንዳች እድገት ሲንፏቀቅ የነበረው የኤክስፖርት ገቢ፣ አንገቱን ቀና ማድረግ የጀመረው በ1996 ዓ.ም ነው። በዚያው አልቆመም። ኢህአዴግ፣ “ተሃድሶ” በሚል ስያሜ መጠነኛ የነፃ ገበያና የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች፣ ለእድገቱ ጥሩ መነሻ የሆኑ ይመስለኛል። ለማንኛውም፤ ከጠቅላላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር የኤክስፖርት ገቢም ለተከታታይ አመታ ያለማቋረጥ እያደገ ነበር። ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ፣ በአምስት አመታት ውስጥ ሶስት እጥፍ ለመሆን በቃ - ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ።

በሚሊንዬሙ ማግስት ግን፣ ግስጋሴው ድንገት ተንገራግጮ ቆመ። እንዲያውም ወደ ኋላ መንሸራተት ዳዳው። በ2001 ዓ.ም የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ፣ ከከርሞው ቢያንስ ቢያንስ በሃምሳ ሚሊዮን ዶላር ቀንሷል። ምን ተፈጠረ? በተደጋጋሚ እንደምትሰሙት፣ የአገሪቱ ጠቅላላ የኢኮኖሚ እድገት ከሞላ ጎደል አልተቋረጠም። ታዲያ ለምን የኤክስፖርት እድገት ተቋርጦ ወደ ኋላ ተንሸራተተ? ለነገሩማ፣ የኤክስፖርት ቢዝነስ መብረክረክ የጀመረው ከ2000 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነው። በተከታዩ አመት ደግሞ ባሰበት። ምን ጉድ ተፈጠረ? የተደበቀ ነገር የለውም። አገሬውን ጉድ ያደረገ የዋጋ ንረት (Inflation) ነው የተፈጠረው። የዋጋ ንረቱ፣ የኤክስፖርትን ቢዝነስ እንዴት እንዳዳከመ ለማሳየት ልሞክር። ቅጥ ባጣ የብር ሕትመት ሳቢያ ብር ሲረክስ፤ የሸቀጦች ዋጋ (ለምሳሌ የጤፍና የዘይት) እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያ (ለምሳሌ የትራንስፖርትና የቤት ኪራይ) እየናረ መምጣቱ አይገርምም። ብር ሲረክስ፣ የአብዛኛው ነገር ዋጋና ክፍያ ይንራል። በእርግጥ ዶላርን እንደ ማንኛውም ሸቀጥ ብንቆጥረው፣ ብር በረከሰ ቁጥር የዶላር ምንዛሬም በዚያው ልክ እየናረ መምጣቱ አይቀርም።

ግን ሳይንር ቀረ። “የውጭ ምንዛሬ፣ የሕዝቡን ኑሮ ስለሚነካ፣ ለአገር ኢኮኖሚና ለመሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ ስለሆነ መንግስት ሊቆጣጠረው ይገባል” ይባል የለ? ከጥቃቅን ለውጦች በስተቀር፣ የምንዛሬ ተመኑን የሚቆጣጠረው መንግስት ነው። በወቅቱ፣ የሁሉም ሸቀጦች ዋጋ ሲንር፣ የዶላር ዋጋ ላይ ብዙም ለውጥ ያልታየውም፣ በሌላ ምክንያት ሳይሆን መንግስት ስለከለከለ ብቻ ነው። ቡና በማምረት ወይም ቡና ወደ ውጭ በመላክ የምትተዳደሩ ቢሆን፣ ኪሳራው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አስቡት። ከህዳር 98 ዓ.ም ጀምሮ፣ በአመቱ ታህሳስ 99 ዓ.ምን፣ ከዚያም እስከ መስከረም 2001 ዓ.ም ድረስ ያሉትን ሃያ ወራት ብቻ ተመልከቱ። በዶላር ሲታሰብ፣ የምታገኙት ገቢ ብዙም አልተለወጠውም። ከኤክስፖርት የምታገኙት ገቢ በወር መቶ ዶላር ከነበረ፤ ከአመት ኋላ፣ እንደገና ከሃያ ወራት በኋላ ያንኑን ታገኛላችሁ። ዶላሩን በግል ልትጠቀሙበት ለምሳሌ ከውጭ እቃ ገዝታችሁ ልታመጡበት አትችሉም። ክልክል ነው። ዶላሩ እጃችሁ ውስጥ አይገባም። መንግስት ነው፣ ራሱ በሚወስነው የምንዛሪ ተመን በብር መንዝሮ የሚሰጣችሁ። ዶላሩን በብር ይገዛል ማለት ነው። ዋጋውንም ራሱ ይወስናል።

ያመጣችሁትን ዶላር ለመንግስት አስረክባችሁ፣ በብር ትንቀሳቀሳላችሁ። እና፣ ህዳር 98 ዓ.ም ላይ ስንት ብር ኪሳችሁ ይገባል? መንግስት በዘጠኝ ብር ሂሳብ አስልቶ፣ ለመቶ ዶላር 900 ብር ይሰጣችኋል። እህልና ዘይት ትገዙበታላችሁ፤ ለቤት ኪራይና ለትራንስፖርት ታውሉታላችሁ። በአጭሩ የወር ወጪያችሁን ትሸፍኑበታላችሁ። ከአመት በኋላስ? ከአመት በኋላማ፣ የሸቀጦች ዋጋና የአገልግሎት ክፍያዎች ጭምረዋል - ብር እየረከሰ ስለመጣ። አሁን የወር ወጪያችሁን ለመሸፈን አንድ ሺ ብር ገደማ ያስፈልጋችኋል። ወደ ውጭ የምትልኩትን ቡና፣ እዚሁ አገር ውስጥ ብትሸጡት፣ እንደሌላው ሸቀጥ ሁሉ ዋጋው ስለሚንር አንድ ሺ ብር ያወጣላችኋል። ግን፣ ቡናውን ወደ ውጭ የመላክ ግዴታ እንጂ አገር ውስጥ የመሸጥ መብት የላችሁም። በህግ የታወጀ ነገር ነው። እና፤ ታህሳስ 99 ዓ.ም ላይ ከኤክስፖርት መቶ ዶላር ስታመጡ ስንት ብር ታገኛላችሁ? ብር ቢረክስም፣ መንግስት የምንዛሬ ዋጋ አልቀየረም። አሁንም በዘጠኝ ብር ሂሳብ፣ ለመቶ ዶላር 900 ብር ይሰጣችኋል። ነገሩ፣ ለመንግስት ሊጥመው ይችላል። ከዋጋ በታች እየተመነና የረከሰ ብር እየሰጠ፣ “ለሕዝብ ጥቅምና ለመሰረተ ልማት ግንባታ” የሚውል ዶላር መግዛት ችሏላ። ለእናንተ ግን ኪሳራ ነው፣ የአንድ ሺ ብር የሚያወጣ ቡና ብትሸጡም፣ ኪሳችሁ ውስጥ የሚገባው ግን 900 ብር ብቻ ነው። ከእያንዳንዱ መቶ ብር፣ አስር ብር ሲወስድባችኋል፤ ቀላል ኪሳራ አይደለም። “ደግነቱ፣ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግና ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከፈል መስዋእትነት ነው” እንበል? ከሃያ ወራት በኋላስ? የብር ኖት በገፍ ስለታተመ፣ እንደገና የአገሬው ብር በጣም ረክሷል። የሸቀጦች ዋጋም ሆነ የቤት ኪራይ፣ በእነዚሁ ወራት በአማካይ በሃምሳ አምስት በመቶ ያህል ንሯል። አሁን፣ የተለመደችዋን የወር ወጪ ለመሸፈን 1600 ብር ያስፈልጋችኋል። ለነገሩማ የቡና ዋጋም ጨምሯል። ክልክል ሆነ እንጂ፣ ቡናውን በአገር ውስጥ መሸጥ ብትችሉ 1600 ብር ያወጣል። ምን ያደርጋል? ቡናውን ወደ ውጭ የመላክ የህግ ግዴታ ተጭኖባችኋል። ዛሬም፣ የምታገኟት መቶ ዶላር አልተለወጠችም። ጊዜው መስከረም 2001 ዓ.ም ነው።

መንግስት፣ “አሻሽያለሁ” ብሎ ለአንድ ዶላር በአስር ብር ሂሳብ፣ አንድ ሺ ብር ይሰጣችኋል። ስድስት መቶ ብሩን መንግስት ይወስደዋል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአገሪቱ ብር ስለረከሰ፣ የዶላር ምንዛሬ ወደ 16 ብር ገደማ መሆን ሲገባው፤ መንግስት በአስር ብር ብቻ እንዲሆን ያደርጋል። “ከኔ ሌላ፣ ከኔ ፈቃድ ውጭ፣ ማንም ሰው ዶላር መያዝና መግዛት አይፈቀድለትም። ለኔ መሸጥ አለባችሁ። ብቸኛ ገዢ ነኝ። በዚያ ላይ ዋጋውን የምወስነው እኔው ነኝ። ስለዚህ በ16 ብር ከመግዛት በአሰር ብር ብቻ መግዛት ከቻልኩ ምን አሳሰበኝ?” ... የየቅፅበቷን ብቻ በቁንፅል እያየ ለመቀጠል የሚፈልግ ከሆነ፣ በፍፁም አያሳስበውም። እንዲያውም ይጥመዋል። ከእያንዳንዱ ዶላር ስድስት ብር “እያተረፈ” ነዋ። በዚህ መንገድ በ2000 ዓ.ም፤ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር “አትርፏል” ማለት ይቻላል። ችግሩ ምን መሰላችሁ? በሥራ የተገኘ ትርፍ አይደለም። ከኤክስፖርተሮች የተወሰደ ብር ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኤክስፖርት መስክ የተሰማራ አምራች ወይም የቢዝነስ ሰው፣ 1600 ብር የሚያወጣ ምርቱን ሲሸጥ፣ አንድ ሺ ብር ብቻ ያገኛል። ስድስት መቶ ብሩን መንግስት ይወስድበታል።

ታዲያ፣ በጥረት ያፈራው ንብረት እንዲህ እንደዘበት እየተነጠቀ ለመቀጠል የሚፈልግ አምራች ወይም የቢዝነስ ሰው ይኖራል? ማንም አይፈልግም። ግን፣ ወዲያውኑ ሥራውን እርግፍ አድርጎ ይተወዋል ማለት አይደለም። ለበርካታ ወራት የተንከባከባቸውን የቡና ተክሎች ነቃቅሎ ይጣላቸው? ለአዝመራ የደረሰውን የቡና ፍሬ በከንቱ ያባክነው? በስንት ትግል የተከለውን ፋብሪካ ያፍርሰው? ባዶ ከመቅረት፣ 1600 ብር የሚያወጣውን ሸቀጥ ኤክስፖርት አድርጎ አንድ ሺ ብር ቢያገኝ አይሻለውም? ይሻለዋል። ነገር ግን፤ አማራጭ በማጣት ስራውን ለመቀጠል ይሞክራል እንጂ፣ ምርቱን ለማሳደግ የሚጣጣርበት ምክንያት አይኖረውም። እናስ፤ በ2000 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የኤክስፖርት የእድገት ግስጋሴው ድንገት ተንገራግጮ መቆሙና በተከታዩ አመት ወደ ኋላ መንሸራተቱ ይገርማል? ከመነሻው፣ የብር ኖት አለቅጥ ከማተም በመቆጠብ ብር እንዳይረክስ ማድረግ እንጂ፣ ብር ከረከሰ በኋላ የዶላር ምንዛሪን በቀድሞው ተመን ላይ ቆልፎ ማቆየት አላዋጣም። እንዴት ሊያዋጣ ይችላል? በኤክስፖርት መስክ የተሰማሩ አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎችን በግድ እየዘረፍን (ከእያንዳንዷ የዶላር ገቢ ስድስት ብር ነጥቀን በነፃ እየጎረስን)፤ በየአመቱ ሳያቋርጡ ተጨማሪ ዶላር የሚያመጡና ሳይነጥፉ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆኑልን አስበንና አምነን መቀመጣችን፣ እጅግ አላዋቂነትም እጅግ ሃጥያትም ነው።

በነፃ ጉርሻ ላይ መተማመን ሞኝነት ነው፤ በንጥቂያ የሚገኝ ነፃ ጉርሻ ላይ መተማመን ደግሞ ህግ ያልወጣለት የወንጀል አመል! አስገራሚው ነገር፤ ቅድም እንደጠቀስኩት፣ ነገሩ ሁሉ እንደ ሞኝነትና እንደ ነውር ሳይሆን፣ እንደ ቅቡልና እንደ በጎ ነገር መታሰቡ ነው። የዚህ አስተሳሰብ ውጤት በተግባር በጎ እንዳልሆነ በ2001 ዓ.ም ዋዜማ ላይ ጎልቶ መታየት ሲጀምርስ? የመንግስትም ሆነ የብዙ ሰዎች ነባር አስተሳሰብ አልተለወጠም። ለጊዜው ከውድቀት ለመዳን ግን፣ የምንዛሪ ማስተካከያ ተደረገ - ለዚያውም ሶስት ተከታታይ ማስተካከያ። መስከረም 2001 ዓ.ም ላይ ከአስር ብር በታች የነበረው የዶላር ምንዛሪ፣ ጥር እና ሐምሌ ላይ፣ እንደገና ከጥቂት ወራት በኋላ በተደረጉ ማስተካከያዎች፣ የምንዛሪ ተመኑ ቀስ በቀስ ወደ 14 ብር ተጠግቷል። የተዳከመው የኤክስፖርት ቢዝነስ ተነቃቃ። በ2002 ዓ.ም፣ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የተገኘው ገቢ በግማሽ ቢሊዮን አድጎ፣ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ደረሰ። እንዲያም ሆኖ፣... (ዝርፊያው በግማሽ ያህል ቢቀንስም) የኤክስፖርት ቢዝነስ ሙሉ ለሙሉ ከችግር ተላቋል ማለት አይደለም። በዚሁ ጊዜ ውስጥ የአገሪቱ ብር በተወሰነ ደረጃ መርከሱ አልቀረም። እናም፤ በአማካይ 1700 ብር የሚያወጣ ምርት፣ ወደ ውጭ በመቶ ዶላር የሚልኩ አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎች፣ መቶ ዶላሩን ለመንግስት አስረክበው 1400 ብር ብቻ ነው የሚያገኙት - ሶስት መቶ ብር ያስቀርባቸዋል። ይሄው ችግሩ ሙሉ ለሙሉ የተስተካከለው፣ መስከረም 2003 ዓ.ም ነው። መጀመሪያ ነገር፣ ቅጥ ያጣ የብር ኖት ህትመት ስለተቋረጠ፣ የአገሪቱ ብር ቁልቁል መርከሱን አቁሟል። የሸቀጦች ዋጋ ተረጋግቷል። ይህም ብቻ አይደለም። የዶላር ምንዛሬ ወደ 17 ብር ገደማ እንዲሆን ተደረገ።

ውጤቱስ? በዚያው አመት ነው፣ በአገሪቱ የኤክስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቁ እድገት የተመዘገበው። ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ተነስቶ 2.75 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ። ምን ዋጋ አለው? ለአፍታ ተቋርጦ የነበረው የገንዘብ ሕትመት፣ ብዙም ሳይቆይ እንደገና የብር ኖቶችን ያርገፈግፍ ጀመር። በአገሪቱ ውስጥ ያለው የገንዘብ ኖት፣ በጥቂት ወራት ውስጥ በሃምሳ በመቶ ጨመረ። በዚያ አልቆመም። የህትመት ትዕዛዙ ረገብ ያለው ከአመት በኋላ ነው። አሁን የአገሪቱ ብር በ2003 ዓ.ም ከነበረው የመግዛት አቅም ጋር ሲነፃፀር፣ የያኔው ስድስት ብር እና የአሁን አስር ብር፣ ዋጋቸው ተቀራራቢ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ያኔ 17 ብር የነበረው የዶላር ምንዛሪ ዛሬ ወደ 26 ብር ገደማ መሆን ነበረበት። ነገር ግን ትንሽ ነው ፎቀቅ ያለው። ምርታቸውን ወደ ውጭ የላኩ አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎች የውጭ ምንዛሪ ይዘው ሲመጡ፣ መንግስት ዶላሩን የሚረከባቸው (የሚገዛቸው) ከ19 ብር ባነሰ ሂሳብ ነው። ከእያንዳንዷ ዶላር ላይ፣ ከሰባት ብር በላይ ያስቀርባቸዋል። እንዲያም ሆኖ፣ በየአመቱ ምርታቸውን እያሳደጉ ተጨማሪ ዶላር እንዲያመጡ እንጠብቃለን? ብዙዎች ይጠብቃሉ። ግን እንደጠበቁት ሊሆን አይችልም። የጥረት ውጤቱ ሲዘረፍና የስራ ፍሬው ሲነጠቅ ይበልጥ የሚነቃቃና የሚበረታታ ሰው እንዲኖር መጠበቅ ክፉ ሃጥያት ነው።

ሃጥያት መሆኑን ደግሞ፣ በቁጥር ማየት እንችላለን። በ2003 ዓ.ም አስደናቂ እድገት የተመዘበበት የኤክስፖርት ቢዝነስ፣ በቀጣዩ አመት እድገቱ ረገብ ካለ በኋላ፣ አምና ደግሞ በመቶ ሺ ዶላር ያህል ወርዶ ወደ ኋላ ተንሸራተተ። ዘንድሮም የኋሊት ጉዞው አልተገታም። አምና የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ዘንድሮ በስድስት ወራት የተገኘው ገቢ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። በዚህ አዝማሚያው፣ በአመቱ መጨረሻ ሶስት ቢሊዮን ሊደርስ አይችልም። ለነገሩማ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ እንደሰፈረው፣ ዘንድሮ ወደ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የኤክስፖርት ገቢ ይገኛል ተብሎ ነበር የታሰበው። አልሆነም። ይልቅ፣ ወደ ፊት እያሰለስን ወደ ተለመደው ውድቀት እየተመለስን ከመዘፈቅ ለመዳን፤ አምራቾችንና የቢዝነስ ሰዎችን ከታች ሰንክሎ የሚጥል “የመስዋዕትነት” አስተሳሰብን እንደ በጎ ሃሳብ መቀበላችንን እናቁም።

Read 5700 times