Monday, 27 January 2014 09:10

“ጐንደርን ለአገር ቤት” እና “ጐንደርን ለህፃናት” ለንባብ በቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

           ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ከጐንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጃቸው “ጐንደርን ለአገር ቤት” እና “ጐንደርን ለህፃናት” የተሰኙ የቱሪዝም ዳይሬክተሪዎች ታትመው  ባለፈው ሳምንት ጐንደር ከተማ በሚገኘው ቋራ ሆቴል ተመረቁ፡፡ የምረቃ ስነስርዓቱን የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ ከፍተውታል፡፡
ከዚህ በፊት “ጐንደርን ለአገር ቤት” የተሰኘ የጐንደር ቱሪዝም ማውጫ በእንግሊዝኛ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን የአገር ውስጥ ጐብኚዎችና የጐንደር ከተማ ነዋሪዎች ስለጐንደር ቅርሶች ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ቅርሶቹን እንዲንከባከቡ በማሰብ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ  መቅረቡን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ት ህይወት ሀብታይ ተናግራለች፡፡ ማውጫው በዋናነት የጐንደርን ዋና ዋና መስህቦች ያካተተ ሲሆን በተለይም የአፄ ፋሲለደስ ግንቦችን፣ ደብረ ብርሃን ስላሴን፣ የአፄ ፋሲለደስ መዋኛን እንዲሁም  ጐንደር ያሏትን ፓርኮችና ሙዚየሞች የሚያስቃኝ ነው፡፡
በዚሁ እለት “ጐንደርን ለህፃናት” የተሰኘ መጽሐፍም የተመረቀ ሲሆን ህፃናት የጐንደርን መስህቦች እንዲያውቁና በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በሚያስችላቸው መንገድ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን በዚህ አመት ብቻ የቱሪዝም ማውጫ ሲያስመርቅ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል “የሰሜን ሸዋ የቱሪዝም ዳይሬክተሪ” እና “የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፓርኮች ዳይሬክተሪ”ን አስመርቋል፡፡ ድርጅቱ በየሁለት ወሩ የሚወጣና ቱሪዝም ላይ አተኩሮ የሚሰራ “ቱባ” የተሰኘ መጽሔት እንደሚያዘጋጅም ይታወቃል፡፡

Read 1652 times