Monday, 27 January 2014 08:54

ሃብታሞች የበለጠ ሲበለፅጉ፤ድሆች የበለጠ እየደኸዩ ነው

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(8 votes)

1 በመቶ ያህሉ ባለፀጎች 95 በመቶውን ሃብት ተቆጣጥረዋል

ባለፈው ሳምንት ከተለያዩ  አገራት የተውጣጡ  ከአንድ ሺ በላይ የቢዝነስ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጭዎች “አለምን እንለውጥ” በሚል መሪ ቃል በስዊዘርላንድ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በፎረሙ ከተነሱት አጀንዳዎች መካከልም የኢኮኖሚ እድገት ዝግመት፣ ስራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከፎረሙ ስብሰባ ቀደም ብሎ ኦክስፋም “ዎርኪንግ ፎር ዘ ፊው” በሚል ርእስ  ይፋ ባደረገው ጥናት፤ ሰማኒያ አምስት የሚሆኑ የአለማችን ሀብታሞች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአለም ሀብት እንደተቆጣጠሩ ያመለከተ ሲሆን እነዚህ ባለፀጎች  1.7 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት እንዳካበቱ ተገልጿል፡፡ ከሰማንያ አምስቱ ቱጃሮች ውስጥ 31ዱ አሜሪካውያን ሲሆኑ በሃብት መጠን በአንደኝነት የሚመራው በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተሰማራው  ሜክሲካዊው ቢሊዬነር ካርሎስ ስሊም ሄሉ ነው - በ73ቢ. ዶላር የሃብት መጠን፡፡ የሁለተኛነት ደረጃ የያዘው አሜሪካዊው የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ ሲሆን የሀብቱ መጠን 67 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተጠቅሷል፡፡ ሌላው አሜሪካዊ  ባለፀጋ ዋረን በፌ፤ በ53.5 ቢሊዮን ዶላር የሦስተኝነት ደረጃ ይዟል። የአለማችን ሀብታም ሴት በመሆን ቀዳሚነቱን የያዘችው ሊሊያን ቤተን ኮርት ስትሆን፤ ሎሪያል በሚል በሚታወቀውና ከቤተሰቧ በወረሰችው የመዋቢያ ምርቶች ኩባንያዋ የ30 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ማካበት ችላለች ተብሏል፡፡
ከግማሽ በላይ የአለማችን ሀብት አንድ በመቶ በሚሆኑ ጥቂት ባለፀጎች ተይዟል የሚለው የኦክስፋም ጥናት፤ በሀብታሞች እና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት ካለፉት ሰላሳ አመታት ወዲህ በእጅጉ እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሶ፤ የአለም ሀብት በተወሰኑ ግለሰቦች እጅ ተጠቅልሎ መያዙ ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ስርአት ለመዘርጋት እንቅፋት እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የኦክስፋም ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ባይናይማ፤በዓለም ህዝቦች መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ልዩነት እየሰፋ መምጣት ለማህበራዊ ውጥረቶችና  ግጭቶች መባባስ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “በአለም ላይ እየሰፋ የመጣውን የሀብት ክፍፍል ልዩነት ማጥበብ ካልተቻለ፣ ድህነትን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ውጤት ያመጣል ብለን ተስፋ አናደርግም” ብለዋል - ዳሬክተሩ፡፡
ካለፉት ሰላሳ አመታት ወዲህ ከአስር ሰዎች ሰባቱ የኢኮኖሚ ልዩነቱ እጅግ እየሰፋ በመጣባቸው አገራት እንደሚኖሩ “ዩኤስ ቱዴይ” ለተባለው ጋዜጣ የተናገሩት ከአጥኚዎቹ አንዱ ኒክ ጋላሶ፤ እስካሁን ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተደረገ ፖለቲካዊ ሙከራ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡  በኢኮኖሚ ፎረሙ ላይ የተሳተፉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ጄኒፈር ብላንክ በበኩላቸው፤ ስራ አጥ የሆኑና በቂ የሙያ ክህሎት የሌላቸው ወጣቶች ቁጥር መብዛት በዓለም ላይ አለመረጋጋትና ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል ጠቅሰው፤ ብዙዎች ኢ-ፍትሀዊውን የሀብት ክፍፍልና ሙስናን በመቃወም ቁጣቸውን ለመግለፅ ወደ አደባባይ መውጣታቸውን  እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ “እርካታን ማጣት መጠነ ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል፤ በተለይ ወጣቶች ለነገ የሚያዩት ተስፋ ከሌላቸው ሁሉንም ወገን የሚጎዳ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው” ሲሉ አሳስበዋል - ባለሙያው፡፡ እጅግ የተራራቀ የሀብት ልዩነት የዘመናችን መገለጫ ነው፤ ሲሉ በቅርቡ የተናገሩት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማም፤ “ይሄ የሃብት ልዩነት እንደ ሰው ያለንን ዋጋ እያጠፋው ነው” ብለዋል፡፡
ኦክስፋም በጥናቱ ላይ እንዳስቀመጠው፤ ከመቶ አንድ እጅ የሚሆኑት የአሜሪካ ሀብታሞች፣ ከኢኮኖሚ ቀውሱ በኋላ  95 በመቶ እድገት ያስመዘገቡ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆነው ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የድህነት መጠንም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሃብታሞቹ ይበልጥ እየበለፀጉ ድሆቹም ይበልጥ እየደኸዩ ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት በሀብት ክፍፍል ላይ ያለው ልዩነት ከ1920ዎቹ ወዲህ የታየ የመጀመሪያው ሰፊ ክፍተት እንደሆነ የሚናገሩት መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገው የአለምአቀፉ የሰራተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ ፊሊፕ ጂኒንግስ፤ የኦክስፋም ጥናት የአለም ኢኮኖሚ መልክ በእጅጉ እየተለወጠ መምጣቱን ያሳያል ይላሉ። “ጥቂት ሀብታሞች ከግማሽ በላይ የምድሪቱን ሀብት ተቆጣጥረው ሲጠቀሙ ሚሊዮኖች ግን እህል ሳይቀምሱ ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩትም በረሀብ ይሞታሉ” ብለዋል - የዓለምን አስከፊ እውነታ ጂኒንግስ ሲገልፁ፡፡

Read 6404 times