Monday, 27 January 2014 08:43

ለዋልያዎቹ ትንሳዔ በወጣት ፕሮጀክቶች መስራት ያስፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

            በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ወደ ሩብ ፍፃሜ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ዛሬ ናይጀሪያ ከሞሮኮ ፤ ማሊ ከዚምባቡዌ እንዲሁም ነገ ጋቦን ከሊቢያ፤ ጋና ከዲሞክትራቲክ ኮንጎ ይጫወታሉ፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በዘንድሮው የቻን ውድድር ለሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖች በየደረጃው የሚከፋፈል 3.6 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ ከሩብ ፍፃሜው በፊት ይሄው የሽልማት ገንዘብ ይፋ የሆነው ለሻምፒዮናነት ጠንካራ ፉክክር እንዲደረግ ታስቦ እንደሆነ የገለፀው ካፍ ሻምፒዮኑ ብሄራዊ ቡድን 750ሺ ዶላር ከዋንጫው ሽልማት ጋር እንደሚያገኝ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ቻን ተብሎ በሚጠራው አህጉራዊ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈው የዋልያዎቹ ስብስብ ለትንሳዔው በታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች መስራት እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሶስት ከሊቢያ፤ ኮንጎ ብራዛቪልና ጋና ጋር ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ተሸንፎ፤ አንድም ጎል ሳያገባ 5 የግብ እዳ አስመዝግቦ በመጀመሪያው ዙር በመሰናበት ከትናንት በስቲያ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ዋልያዎቹ በቻን ተሳትፏቸው ደካማ አቋም ማሳየታቸው የብሄራዊ ቡድኑን የወደፊት ጉዞ መነጋገርያ አድርጎታል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጆሃንስበርግ ኦሊቨር ታምቦ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ብሄራዊ ቡድኑ ለቻን ውድድር ሲገባ ጥሩ አቀባበል አድርገውለት ነበር፡፡ ከውድድሩ በምድብ ማጣርያው ሲሰናበት ግን ምንም አይነት ሽኝት አላደረጉለትም፡፡  ቡድኑ ከቻን ተሰናብቶ ባለፈው ሐሙስ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል አዲስ አበባ ሲደርስም የፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ካደረጉት ቀዝቃዛ አቀባበል በቀር የተለየ ነገር አለገጠመውም፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች እና መላው ኢትዮጵያውያንም ሆነ እዚህ አገር ቤት ያሉ ወገኖች መላው በቻን የነበረው ደካማ ተሳትፎ የወደፊቱን የእግር ኳስ እድገት እንዳያጨልም ሰግተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርሆቦት ፕሮሞሽን አስተባባሪነት  የጉዟቸው  ሙሉ ወጭ ተሸፍኖ የቻን ውድድርን ለመዘገብ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት ጋዜጠኞች በደሌ ስፔሻል በፈጠረላቸው እድል መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ በደሌ ስፔሻል ከ600ሺ ብር በላይ ወጭ  አድርጎ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ  ያደረገላቸው የስፖርት ጋዜጠኞች ከአዲስ አድማስ፤ ከሪፖርተር፤ ከኢንተር ስፖርት ፤ ከሊግ ስፖርት እንዲሁም ከኢትዮ ፉትቦል ድረገፅ  የተወከሉ ናቸው፡፡  
በአህጉራዊ ውድድሩ በቀጥታ መረጃ የሚያገኙበትን እድል በመፍጠር፤ ከውድድሩ በተያያዘ የተለያዩ ልምዶችን እንዲቀስሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና የሙያ ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ በማገዝ ኩባንያው ላደረገው ድጋፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ምስጋናቸውን ገልፀዋል።  የስፖርት ጋዜጠኞቹ፤ በደቡብ አፍሪካ ሁለት ከተሞች ጆሃንስበርግና ብሎምፎንቴን ለ8 ቀናት ቆይታ ነበራቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብሎምፎንቴን በሚገኘው ፍሪስቴት ስታድዬም በምድቡ  ከኮንጎ እና ከጋና ብሄራዊ ቡድን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች 900 ኪሎሜትር የደርሶ መልስ ጉዞ በማድረግ በቀጥታ ተከታትለዋል፡፡ በጆሃንስበርግ ከተማ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በመገናኘት በእግር ኳሱ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ምክክር አድርገዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ስታድዬሞችን በመመልከትና ታዋቂ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራን ጐብኝተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ምን ይላሉ? ፌደሬሽኑስ?
ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ በቻን የምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታው ብሄራዊ ቡድኑ በሊቢያ  2ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ደስተኞች አልነበሩም፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ወደ ብሎምፎንቴን በመምጣት ድጋፍ ለመስጠት የተቸገሩትም የቡድኑ ብቃት ያልጠበቁት ሆኖባቸው ነው፡፡ በዋልያዎቹ የምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታ በፍሪስቴት ስታድዬም የተገኙ ኢትዮጵያውያን በስምንት አውቶብሶች ተጉዘው ብሎምፎንቴን የገቡ ነበሩ፡፡ እስከ ስምንት ሺ ይደርሳሉ፡፡ ከኮንጎ በተደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ግን ይህ ሁኔታ ተቀዛቀዘ፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩበት ጆሀንስበርግና ሌሎች ከተሞች ብሎምፎንቴን የመጡት በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከጋና ጋር በተደረገው የምድቡ መጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ቡድኑን ለመደገፍ ፍሪስቴት ስታድዬም የተገኙት በከተማዋ የሚኖሩት ሲሆኑ ከሌሎች ግዛቶች የመጡት በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቻን ውድድር በምድብ ማጣርያው ከተሰናበተ በኋላ በተለያዩ በደቡብ አፍሪካ እየሰሩ  የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን በዋልያዎቹ አጨዋወት የተመለከቱት የብቃት ችግር፤ የወኔ መቀዝቀዝ እና ያለጎል የደረሰው ተከታታይ ሽንፈት አንገታቸውን አስደፍቷል፡፡ መከፋታቸውንም በተለያዩ መንገዶች ገልፀውታል፡፡ በአሰልጣኙ ብቃት እና ተጨዋቾችን የመቀየር ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያላቸውም ብዙዎች ነበሩ፡፡ በአጥቂ በተከላካይ መስመር ተሰላፊ የሆኑ ተጨዋቾች ባሳዩት አቋም ተናድደው ተጨዋቾቹን ያወገዙም ጥቂት አይደሉም፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዋልያዎቹ ባስመዘገቡት ውጤት ተነሳስቶ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተመልሶ እንዳያሽቆለቁል በመስጋት የተለያዩ ሃሳቦችን አንፀባርቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የ2014 የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጉዞውን ከ2 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ከጀመረበት  ጨዋታ አንስቶ የሚገርም ድጋፍ እየሰጡ ነበር፡፡ ከቻን ውድድር የምድብ መጨረሻ ጨዋታ በኋላ ግን ድጋፉ ወደ ብስጭት እና ተስፋ መቁረጥ ተቀይሯል፡፡ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ በነበራቸው ጉዞ በዚያው አገር በተለያዩ ግዛቶች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለድጋፍ በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የነበረው ወጣት ፅኡመልሳን ውብሸት ይባላል፡፡ የቀበናው ልጅ  ፅዑመ በደቡብ አፍሪካ መኖር ከጀመረ ከ14 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡  
ይህ ማለት ከእግር ኳስ በተያያዘ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለድጋፍ በማስተባበርና የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ታዋቂ ሆኗል። ‹ብሄራዊ ቡድናችን በደቡብ አፍሪካ በተለያዩ ውድድሮች ሲያሸንፍ ለማየት ባንታደልም በነበረው ጉዞ ያን ያህል አናዝንም›› ይላል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋልያዎቹ ከዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያና ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በቻን በተሻለ ጥንካሬና ብቃት የሚመጡበትን ቀን በተስፋ ሲጠባበቁ እንደነበር ያስታወሰው ፅዑመ፤በቻን ውድድር ብሄራዊ ቡድኑ ከምድቡ በጊዜ ሲሰናበት ደንግጠናል ብሏል፡፡ “ዋልያዎቹ በቻን ተሳትፏቸው መልካም ውጤት ይኖራቸዋል ብለን ስንጠብቅ በተጋጣሚዎቻቸው ብልጫ ተወስዶባቸው እና ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ስንመለከት ምን ጎደላቸው ብለን ግራ ተጋብተን ነበር ያለው ፅዑመ፤ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ከማንኛውም አገር የሚስተካከል አቅም እንዳላት እናምናለን፤ በስፖርቱ የሚገኝ ውጤት ለሁላችንም ኩራት ነበር፡፡ የአገራችንን ገፅታ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ይገባናል፡፡ ስለዚህ ለወደፊቱ መሰረታዊ የእድገት ስራዎች ለውጥ ማየት እፈልጋለሁ” ብሏል፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በታዳጊ ፕሮጀክት በመስራት እና የተለያዩ አዝናኝ የእግር ኳስ ውድድሮችን በማዘጋጀት የሚታወቀውና አሁን በደቡብ አፍሪካ በንግድ ስራ የተሰማራው አቶ ኤልያስም ለወደፊቱ ምን መደረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጥቷል፡፡  በበኩሉ የኢትዮጵያ ቡድን በአለምአቀፍና በአህጉራዊ ደረጃ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ብቁ ተፎካካሪ እንዲሆን በወጣቶች እና በታዳጊዎች የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች በስፋት መስራት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነም ይመክራል፡፡ በአመራር ላይ የሚገኘው የእግር ኳስ ፌደሬሽን  በረጅም ጊዜ እቅድ የሚሰራበትን ስትራቴጂ በመቀየስ እና ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶችን በመቅረፅ መስራት አለበት ብሎ አስተያየት ሰጥቶናል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አቅጣጫ ትኩረት በማድረግ ከ15 እና ከ17 አመት በታች በሚደረጉ አህጉራዊ ውድድር በመሳተፍ ካልሰራች በዋና ብሄራዊ ቡድን ዘላቂ የሆነ ብቃት እና ውጤታማነት ለማግኘት ይከብዳታልም ብሏል፡፡  
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ማናጀር የሆኑት አቶ ሳምሶን ጌታቸው ይህን አስመልክቶ በሰጡን አስተያየት፤ በአገሪቱ ከ15 ዓመት በታች ላለው የታዳጊ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚሆን የአምስት አመት የገንዘብ ድጋፍ ከኮካ ኮላ ኩባንያ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚሁ ተግባር ከኮካ ኮላ በየአመቱ የሚሰጠውን የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በየክልሉ በሚደረጉ የታዳጊዎች ውድድር ላይ በመበጀት እንዲሠራ ታስቦ ለፌዴራል ስፖርት ኮምሽን የፕሮጀክት ስምምነቱ እንደቀረበ እና ለተግባራዊነቱ የኮሚሽኑ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከ17 ዓመት በታች ባሉ ወጣቶች ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየሰራ እንደሆነ የሚናገሩት  የፌዴሬሽኑ የውድድር እና ስነስርዓት ዲያሬክቶሬት አቶ ተድላ ዳኛቸው ናቸው፡፡  በ11 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድርን ለማስጀመር  ዝግጅቱን ጨርሰናል ያሉት አቶ ተድላ፤  የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ሁሉም ክለቦች ተገቢውን የእድሜ ምርመራ አድርገው በውድድሩ እንዲሳተፉ መመሪያ ተሰጥቶ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የጌታነህ ምክር
ጌታነህ ከበደ በጆሃንስበርጉ ቢድቬስት ዊትስ ዩንቨርሲቲ ክለብ መጫወት ከጀመረ ሁለት ወራት ሆኖታል፡፡ አጥቂው ጌታነህ ከበደ ለዚሁ ክለብ 5 ጐሎችን በማስቆጠር በደቡብ አፍሪካ ሚዲያ ተደንቋል፡፡ ዋልያዎቹ ከሊቢያ አቻቸው ጋር በፍሪስቴት ስታዲየም ያደረጉትን ጨዋታ እንደተመለከተ የነገረን ጌታነህ ቡድኑ የግብ አጋጣሚዎች ሊጠቀም ባለመቻሉ ለሽንፈት እንደሚጋለጥ ይናገራል፡፡ ጌታነህ ከበደ በደቡብ አፍሪካው ክለብ መጫወት ከጀመረ በኋላ ብዙ ለውጥ ይታይበታል የሚታየውን የአካል ብቃት ችግር እያለፈው እንደሆነ ታዝበናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ያለባቸው የአካል ብቃት ችግር በጂም በሚደረጉ ልምምዶች እና ስልጠናዎች ሊስተካከል እንደሚችል በጌታነህ ከበደ መለወጥ አረጋግጠናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቻን ውድድር ከምድብ ማጣርያ በጊዜ መሰናበቱ እንዳስከፋው የገለፀልን ጌታነህ ፤ የአገራችን ክለቦች በአደረጃጀታቸው ፕሮፌሽናል ደረጃዎችን በማሟላት ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው፤ በባላሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተው መሰረታዊ የስልጠና መሰረተልማቶች ማስፋፋት እንዳለባቸው እና በታዳጊ ፕሮጀክቶች በስፋት መሰራት እንደሚያስፈልግ ምክሩንም ለግሷል፡፡

የሰውነት ቢሻው መጨረሻ
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብሄራዊ ቡድናቸው የመጨረሻውን የምድብ 3 ጨዋታ ከጋና አቻው አድርጎ 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ  ከአምበሉ አዳነ ግርማ ጋር በፍሪስቴት ስቴት ስታድዬም የፕሬስ ኮንፍረንስ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ  ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ ከኮንጎ እና ከጋና ጋር በተደረጉ ሁለት ግጥሚያዎች ዋልያዎቹን በአምበልነት የመራው አዳነ ግርማ ቡድኑ ስለነበረው የጎል ማግባት ችግር ሲጠየቅ ‹‹በመከላከል ረገድ እንደ ቡድን ጥሩ ብንቀሳቀስም፤ በማጥቃት ጨዋታ ላይ በቡድን አለመስራታችን ዋጋ አስከፍሎናል›› ሲል ተናግሯል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ብሄራዊ ቡድናቸው በቻን ላይ በነበረው ተሳትፎ ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲናገሩ፤ ከውድድሩ ብዙ ትምህርት እና ልምድ ማግኘታቸውን ገልፀዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቀጣይ ጉዞ እና በዋና አሰልጣኝነት ስለመቀጠላቸው ወይም ስለመልቀቃቸው ከስፖርት አድማስ ግልፅ ማብራርያ እንዲሰጡም ተጠይቀው ነበር፡፡ በምላሻቸው ‹‹ብሄራዊ ቡድኑን ማሰልጠኔ አብቅቷል ብዬ አልተናገርኩም። አሉባልታው ከየት እንደመጣ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ያለኝ ብቸኛ ሙያ ነው፡፡ ካለሰለጠንኩ ምን ልሰራ እንደምችል አላውቅም፡፡ የእኔ አላማ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በመቀጠል እግር ኳሱን በማሻሻል ለመስራት ነው፡፡ እግር ኳስ በስህተት የተሞላ ነው። ቡድናችን በማጥቃት እና በመከላከል ያሉበት መሰረታዊ ችግሮች ዋጋ አስከፍለውታል። ከቻን በኋላ ስራችንን የምንቀጥለው ለብሄራዊ ቡድኑ ተተኪ የሚሆኑ ወጣት እና ተሰጥኦ የያላቸውን ተጨዋቾች በማፈላለግ ተግባራት ላይ በማተኮር ነው፡፡
በአጠቃላይ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሙያዬ እንደመሆኑ ስራዬን አቆማለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ግን አይታወቅም፤ ስራዬን እንድለቅ የሚያደርግ አስገዳች ሁኔታ እና ተፅእኖ ካልተፈጠረ በቀር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቡድናቸውን ለቻን ውድድር እንዴት እንዳዘጋጁ፤ ከውድድሩ ምን እንደተማሩ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም በጋዜጣዊ መግለጫው ምላሽ እንዲሰጡባቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችም  ጠይቀዋቸዋል፡፡ ‹‹የተዘጋጀነዉ ለ15ቀናት ነው፡፡
የአካል ብቃት ልምምድ ለማድረግ በቂ ግዜ ባይኖረንም  ሁሉንም ስራ አሰርቻለሁ፡፡ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ከማድረግ ባሻገር በዝግጅታችን የነበረው የማቀናጀት ስራ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ በቻን ተሳትፎ የኛ ተጫዋቾች ከሌሎች ሀገር ተጫዋቾች በተለየ የሚጎድሏቸውን ብቃቶች ታዝብያለሁ፡፡ በእኛ  እና በሌሎች  ተጫዋቾች ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ባይኖሩም በሊግ ተጫዋቾች መሀል ያለዉን ልዩነት በሚገባ ተመልክቻለሁ›› በማለት ሰውነት ቢሻው የቻን ውድድርን ተሰናብተዋል፡፡

Read 2793 times