Monday, 27 January 2014 08:40

አደገኛው ውሻ!

Written by  Äናስ ነማርያም
Rate this item
(7 votes)

አለሙ ገዳ እሳት የላሰ ደላላ ነው፡፡ አንደበተ ርዕቱ-አፈ ቅቤ፡፡ ልበ ምላጭ፡፡  ወደሚከራየው ቤት አቀናን፡፡ ከእርምጃውም ከምላሱም እየፈጠነ… “አሁንም ሌጣ ወንደላጤ ነህ! አግባ አግባ እንጂ…. እኔ ጣፋጭ የትዳር ሕይወትን አጣጥሜለሁ፡፡  ነገር ግን ምን ያደርጋል አምና ባለቤቴ ወደ ሳውዲ ተሰደደች “ባስና ሴት ጥለውኝ ሄዱ ብለህ አትዘን ከሳውዲ እየገቡ ነው” የሚል ጥቅስ አንብቤ ከዛሬ ነገ ትገባለች በሚል እየጠበኳት ነው፤ እንደመጣች ወዲያውኑ ቀብድ አስይዛታለሁ”
ግር ብሎኝ “ቀብድ አስይዛታለሁ” ስትል?­
“አስረግዛታለሁ ማለቴ ነው….ግን ምን ዋጋ አለው የሳውዲ ተመላሽ ሴቶች አብዛኛዎቹ አርግዘው ነው የሚመለሱት… ያ! ሁሉ የበረሃ… የባህር ላይ ጉዞ ለእርግዝና ነው እንዴ ያስብላል… ለነገሩ ንግስት ሳባ ያንን እልህ አስጨራሽ የእስራኤል ጉዞ አድርጋ አርግዛ አይደል የተመለሰችው” ሲል የነገር መአቱን እንደ ዶፍ አወረደው ….
“ወደ መካከለኛ ምስራቅ የሚደረጉ ጉዞዎች በእርግዝና የመጠናቀቅ እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ዛሬም ሆነ በዘመነ ሳባ ጥንትም…. እናም የሳውዲ ተመላሾች ዳፋ ቤት ኪራይን እሳት አደረገው  አንተ እድለኛ ነህ በ900 ብር …”
የአለሙ ገዳ ስለ ትዳሩ አቆራቆር…. የሚስቱ ስደት… የንግስት ሳባ ጉዞ… ዝባዝንኬ የቤት ኪራይ መናር ላይ ጉብ ለማለት ነው…  በዚህም ቢያንስ የ300 ብር ፈርቅ በእኔ ላይ ይይዛል…
“እየደረስን ነው… መታጠፊያው ላይ ያለው ቀይ በር ሰፊ ግቢ ነው … ባህር ዛፍ፣ ጽድ፣ በእንጆሪ ዛፎች የተዋበ ኤደን ገነት ግቢ ውስጥ ነው የማስገባህ …”
ደረስን፡፡ በሩ ላይ “ከአደገኛ ውሻ ተጠንቀቁ” የሚል በጉልህ ተፅፏል፡፡ ቅስሜ ስብር አለ፡፡ ውሻ ያለበት ግቢ መግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት፡፡ …. ውሻው ሁሌም በሰንሰለት እስር ላይ ነው፡፡ አይደርስብህም ….  አልፎ አልፎ ቅንጣቢ ስጋ ጣል ብታደርግለት ይላመድሃል…
ወደ ግቢው ዘለቅን፡፡ አለሙ ገዳ የደሰኮረው የእንጆሪ፣ የጽድ ዛፎች ግቢው ውስጥ ለመሃላ አይታዩም፡፡ ጉቱ መሳይ የደረቁ ባህር ዛፎች… በሞትና ሕይወት መካከል ጣር ላይ ያሉ የወየቡ ኮባዎች፣… አዛባ አዛባ የሚሸት የጠቆረ ውሃ ግቢውን አቋርጦ ያልፋል… ድንቄም ኤደን ገነት፡፡
ዋናው ቤት በረንዳ ላይ ወጠምሻ ጐረምሳ፣ ሴት ጭን መሐል ገብቶ ሹርባ እየተሰራ ነበር፡፡ “ቤት ለመከራየት ነው አይደል! አባዬን ልጥራው” ብሎ ብድግ አለ፡፡ አፍታም ሳይቆይ መለስ አለና “ይመጣል” ብሎን ወደ ሽሩባ ሰሪዋ ራመድ ሲል … ጭኗን ፈርከክ አደረገችው- ቀይ ጭኗ ላይ የእኔም የአለም ገዳ አይኖች እንደ ማስትሽ ተጣበቁ፡፡ ወጠምሻው እንደሶኬት ጭኖቿ መካከከል ተሰካ፡፡
አለሙ ገዳ በማንሾካሾክ ድምጽ “አይተሃታል ጭኗን በልቀጥ ስታደርገው…በልቃጣ ብልቅጥቅጥ… እሱም እንደ ሳንዱች ሄዶ ውትፍ! የዘቀጠ … አውቃታለሁ… አለሌ ሸርሙጣ ናት!
“ምን ታደርገዋለህ ሥራዋ ነው” አልኩት፡፡
“የምን ሥራ! ሥሪያ ነው የያዙት”
… ቤት አከራዩ አዛውንት ከእሳቸው ጋር አብራ ያረጀች የምትመስል መነጽራቸውን አውጥተው ደስ በማይል አተያይ አዩኝ- ማለትም ገላመጡኝ፡፡ ለወደፊቱ እንድፈራቸው ተጽእኖ ለመፍጠር ይሆን? የእዛኑ እለት ዕቃዬን አስገባሁ፡፡ ቀፎው አምፖል አልባ በመሆኑ ወጣ ብዬ አምፖል ገዝቼ ለመግጠም ወንበር ላይ እንደቆምኩ አከራዩ ወደ ክፍሌ ገባ፡፡ “ላላ አድርገህ ግጠመው- አጥብቀህ ከገጠምከው ያለውን ኃይል ሁሉ ምጥጥ አድርጐ ነው የሚበላው….”
ስንት ጉድ ይሰማል ሰዎች- ምንስ ተብሎ ይመለሳል፡፡ እኝህን ሰው መጠንቀቅ እንዳለብኝ እያሰብኩ ወደ እንቅልፍ…
ታህሣሥ 0 2ቀን 2006 ዓ.ም …
ትንሽ አመሻለሁ- በመጠኑ ለመቀማመስ፡፡ ወደ አራት ሰዓት በሩን ከፍቼ ስገባ ውሻው አንባረቀብኝ። የነጐድጓድ ያህል! የታሰረበት ስንሰለት ረዥም በመሆኑ ወደ እኔ ተወነጨፈ፡፡ ሰንሰለቱ ላለመበጠሱ ምን ዋስትና አለኝ፡፡ ወደ ክፍሌ ተወነጨፍኩ፡፡ በበሩ ሽንቁር ሳይ ወደል ጥቁር ውሻ!!
ታህሣሥ 03 ቀን 2006 ዓ.ም …
4፡30 ወደ ግቢ ገባሁ፡፡ ወደሉ ውሻ ጥግ ይዟል። ምንም ድምጽ አላሰማም፡፡ ክፍሌ ልደርስ ስል እየጮኸ ወደ እኔ ተወነጨፈ፡፡ ዱብ ዕዳ! ብርክ ያዘኝ። እንዴት በሬን ከፍቼ እንደገባሁ አላስታውስም። በድንጋጤ ቀልቤና ስካሬ ተገፈፈ፡፡ “ለምን አሳጥረው አያስሩትም” በረዥም ሰንሰለት የመታሰሩ ሚስጥር የተወሰነ ሜትሮች እንዳሻው እየተወነጨፈ፣ የሰውን ቆሌና ስካር ለመግፈፍ ይሆን? … ይህንን የሚያውቁት ሰይጣንና መሰሪው አከራይ ናቸው፡፡ እዚህ ሲዖል ግቢ ውስጥ ያስገባኝን የአለሙ ገዳ ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብኝ- ለአደገኛው ወደል ጥቁር ውሻ ቅንጥብጣቢ ስጋ ጣል ማድረግ…!
ታህሣሥ 04 ቀን 2006 ዓ.ም
4፡30 ከግሮሰሪ ወጣሁ፡፡ 5፡00 የፊት ለፊቱን በር ከፍቼ ገባሁ፡፡ ውሻው በጩኸት ተቀበለኝ፡፡ ቅንጣቢ ስጋ ወረወርኩለት፡፡ ስጋውን ትቶ “አንተን ነው መብላት የምፈልገው” በሚል ዓይነት ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ ወደ ክፍሌ ገብቼ በበሩ ቀዳዳ ሳየው ስጋውን ዋጥ ስልቅጥ ሲያደርግ አየሁት፡፡
ታህሣሥ 05…. የወረወርኩለትን ስጋ ትቶ እኔው ላይ ማላዘኑ እንደቀጠለ ነው …
ታህሣሥ 06… ሙዳ ሥጋ ወረወርኩለት- በስሱ ጮኸብኝ፡፡
ታህሣሣ 07… በውድቅት ሌሊት ነበር የገባሁት… የወረወርኩትን ሥጋ እና አጥንት ከመቆረጣጠም ውጪ አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡ “ተመስገን በመጨረሻ ተላመደኝ”
ታህሣሥ 08… ሙዳ ስጋ ወረወርኩለት፤ ስጋውን ከመብላት ውጪ ጸጥ ረጭ…!
ታህሣሥ 09 ቀን 2006 ዓ.ም …
ከምሽቱ 5፡00 ከግሮሰሪ ወጣሁ፡፡ 5፡30 የፊት ለፊቱን በር በሰረገላ ቁልፍ በመክፈት ላይ እያለሁ ለውሻው ምንም አለማያዜ ትዝ አለኝ፡፡ በሩን ከፍቼ ገባሁ፤ ወደ ክፍሌ ራመድ አልኩ… “ውሻው ይጮህብኝ ይሆን?” በሚል ስጋት ዞር ብዬ አየሁት- በለሃጭ ተዝረብርቧል፡፡ የሰረገላ መንቋቋት-ጂን! ጂን! የሚል የሰካራም ትንፋሽ /stimulus/ የውሻው ለሀጭ /Response/ የፖቭሎቭ ቲዎሪን በዛ ምሽት በአይኔ ለማየ በቃሁ፡፡ ውሻው አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም…
ከምሽቱ 5፡00፡፡ አራተኛ ደብል ጅን ላይ ስደርስ፣ ለውሻው ምንም ነገር ይዤ ላለመግባት ወሰንኩኝ። የጠጣሁት ጅን ድፍረት ሰጥቶኛል፡፡ ወደ ኋላ ዞር ሳልል በቀጥታ ወደ ክፍሌ ገባሁ- ውሻው አንዳችም ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 11… ከምሽቱ 5፡30 ገባሁ፡፡ ጢው ብዬ ሰክሬአለሁ፡፡ “ደቼ ብላ!” ብዬ ውሻውን ተሳድቤ ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡ ውሻው ድምጽ አላሰማም፡፡
ታህሣሥ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በውድቅት ሌሊት ነበር የገባሁት፡፡ እየተደነቃቀፍኩ ወደ ክፍሌ ስስገመገም ውሻው ግቢውን በጩኸት ቀውጢ አደረገው፡፡ ሰንሰለቱን ለመበጠስ ተውተረተረ። ጩኸቱ እንደ ነጐድጓድ ተስገመገመ፡፡ በፍጥነት ወደ ክፍሌ ገብቼ በሬን ጥርቅም አድርጌ ዘጋሁት። በመሐል ውሻው ጸጥ ረጭ አለ፡፡ በግማሽ ስካር እና እንቅልፍ መሐል ስለነበርኩ፣ በዚያች ቅጽበት ያሰብኩት ውሻው በምትሃት በሁለት እግሩ ተራምዶ በእጆቹ ያንኳኳ ነው የመሰለኝ፡፡ … በሩን አስከፍቶ ሊዘነጣጥለኝ.. ይመስገነው አከራዩ ነበር፡፡ ወቀሱኝ.. “ለምን እንዲህ ታመሻለህ? እኛንም ረበሽከን-በደረቅ ሌሊት በመግባትህ ነው ውሻው እንኳን ተበሳጭቶ የሚጮኸው”! የእኔ ማምሸት  ውሻውን የማበሳጨቱ ነገር እየገረመኝ ይቅርታ ጠየቅኋቸው፡፡ ከአከራዩም ሆነ ከውሻው ጋር ሰላም ለመፍጠር መላው ገብቶኛል።
ታህሣሥ 13 ቀን 2006…
ያለፋትን 4 ቀናት ለማካካስ ወፈር ያለ ሙዳ ስጋ ይዤ ገባሁ፡፡፡ በሩን በቀስታ ከፍቼ ውሻው ከመጮሁ በፊት በፍጥነት ሥጋውን ወረወርኩለት… ጮኸብኝ! ሰንሰለቱን ለመበጠስ እየታገለ አላዘነ፡፡ ስጋውን እልህ ይዞት አይበላ ይሆን? በሚል በበሬ ሽንቁር አይኔን ላኩኝ፡፡ ዋጥ ስልቅጥ እያደረገ ነው - “አፈር ብላ!” …
ታህሣሥ 14…. ሙዳ ስጋ ጣል ባደርግለትም ግቢውን በጩኸት ቀውጢ አደረገው፡፡
ታህሣሥ 15… ከቅንጥብጣቢ ሥጋ በተጨማሪ አጥንት ቀላቅዬ እነሆ ብለው እየጮኸ፣ እኔኑ ለመንከስ ከሰንሰለቱ ጋር ትንቅንቅ ያዘ….
ታህሣሥ 16… የወረወርኩለትን ሙዳ ሥጋ ከመሰልቀጥ ውጭ አንዳችም ድምጽ አላሰማም። በእኔ እና በውሻው መካከል የተፈጠረውን ሰላም ላለማደፍረስ ቃል ገባሁ፡፡
ታህሣሥ 17 ቀን 2006 ዓ/ም …
ጂን በቶኒክ እየተጐነጨሁ ነው፡፡ ስለዚያ ወደል ጥቁር ውሻ እየቆዘምኩ ነበር፡፡ እስከ መቼ ድረስ ከርሱን ስሞላ እኖራለሁ፡፡ ለአከራዩ ስሞታ ማቅረብ ትርጉም የለውም፡፡ “በውድቅት ስለምትገባ ተበሳጭቶ ነው የሚጮኸው”? የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡኝ …
… እንደገባሁ ቁራጭ ቅንጣቢ ሥጋ ወረወርኩለት። በፍጥነት ዋጥ ስልቅጥ አድርጐ አይኖቹን  አጉረጠረጠብኝ … እኔኑ ሊሰለቅጠኝ ይሆን ?
በመሰላቸት እየታከተኝ ወደ እንቅልፍ አለም… በዚያው ወደ ቅዠት ይሁን ሕልም …
መንገድ ጠርዝ ታክሲ እየጠበቅሁ፣ ባለ ዲኤክስ ሊፍት ሰጠን፤ ሶስት ሰዎች ገባን፡፡ ጉዞ ጀመርን። ሹፌሩ “እኔ ሊፍት ላለመስጠት ምዬ ነበረ… ለዚህ ያበቃኝ ደሞ አንዱን ሊፍት ሰጥቼው፣ ለውሻዬ እራት የገዛሁትን ግማሽ ኪሎ አጥንት ይዞብኝ ወርዶ ነው … ቤት ስደርስ ለውሻዬ ምን ልስጠው? ጾሙን አደረ” … ሁለቱ ወረዱ፡፡ ጉዞአችን ቀጠለ፡፡ ሹፌሩ ወደ እኔ ዞር አለና “የውሻዬን እራት የበላኸው አንተ ነህ! ያኔ አራቱን በልተህበታል! ዛሬ በተራው አንተኑ ይበላኸል!” የነዳጅ መስጫውን ረገጠው፡፡ መኪናዋ እንደ ጥይት ወደፊት ተተኮሰች፡፡ ብርግድ ብሎ በተከፈተ በር ገብታ ቀጥ ብላ ቆመች… እንዴት ከመኪናዋ እንደወረድኩ ሳላውቀው በዚያው ቅጽበት ወደል ጥቁር ውሻ ሰንሰለቱን በጥሶ ወደ እኔ ሲወነጨፍ… ጩኸት አሰምቼ ከእንቅልፌ ብንን አልኩ፡፡
በእውኔም ሆነ በሕልሜ ሕይወቴን ወደ ሰቅጣጭ ትራጀዲ የለወጠውን ወደል ጥቁር ውሻ ለመገላገል ስል በነገው ዕለት ቤቱን ለመልቀቅ ወስኛለሁ፡፡  

Read 4568 times