Monday, 27 January 2014 08:09

“ኢትዮጵያ ቀሚስ የለበሰች ‘ለት”

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

በቅርቡ ለዕይታ የበቃውን ቀሚስ የለበስኩ ‘ለት የተሰኘ ‹‹ፊልም›› ከጓደኞቼ ጋር አይተን ስንወጣ በጭብጡ ብዙ ተወያየን፡፡ ለጥበብ እንዲህ መወያየት ምንኛ መታደል ነው፡፡ ከውይይትም ባሻገር ፊልሙን የሰሩትን ባለሙያዎች ልናደንቅና ስለፊልሙ የተሰማንን በጽሑፍ  ልናስቀምጥ ወደድን፡፡
ፊልሙ ሲጀምር ያልተለመደና ቀላል የሚመስል፣ ነገር ግን መሰረታዊ የሆነ ለውጥ አስተውለናል፡፡ የፊልሙ አቅራቢ፣ አዘጋጅ፣ ደራሲ፣ ስምና የስራ ድርሻ ቁልጭ ባለ አማርኛ ቀርቧል፡፡ በአብዛኞቹ ፊልሞቻችን እነዚህ ነገሮች በእንግሊዝኛ እንደሚቀርቡ ልብ ይሏል፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪያችን እጅጉን ወደኋላ እንደቀረ አንክድም፡፡  ከመቶ አመታት በላይ ታሪክ ቢኖረውም ወደ ኋላ 100 አመት መጐተቱን ብንናገር ጨለምተኛ አያስብለንም፡፡  ወደ ኋላ የመቅረታችንን ምክንያት፣ ብንነጋገርበት፣ ብናውቀውና ውሉን ብንፈታው፤ በዕምቅ የታሪክ ሃብትና የጥበብ ክምችታችን ተጠቅመን በፊልም ዘርፍ ዓለምን ማስደመም እንችላለን፡፡
ፊልሙ ተጀመረ… እየታየ ነው፡፡
ወጣ ገባ እያለ የሚፈሰው ታሪክ፤ የፊልሙን ገጸ- ባሕርያት ከጭብጡ አንፃር በቅጡ እንዳንፈትሻቸው፣ አድርጐናል፡፡ ለምን ቢሉ? የተቆራረጡ ትዕይንቶች (ሲኖች) በጣም በዝተዋል፡፡
አንደኛው ጓደኛችን “እኔ ፊልሙን የወደድኩት ሙሉአለም እና ሰራዊት ባለመኖራቸው ነው” ብሎ የተለመደ አስቂኝ ትዝብቱን ጣል አደረገልን፡፡ ይሄ ጓደኛችን እንዲህ ያለው ሁለቱ አርቲስቶች ላይ የግል ጥላቻ ኖሮበት አይደለም፡፡ ፊልሙ እንደነሱ ያሉ ለዓመታት  ገንነው የዘለቁ ባለሙያዎች ሳይሳተፉበት፣ አሪፍ ሆኖ መሰራቱን ለማድነቅ ነው፡፡  በእርግጥም አዳዲስ እና ወጣት ፊቶች ማየት በራሱ ዕድልም ድልም ነው፡፡ በአንድ ብቻ እንዳይቀሩብን እንጂ!?
በፊልሙ ወደተሳተፉት ተዋንያን እንምጣ። የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት ኘሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በፊልሙ ውስጥ መሳተፋቸው ለጥበቡ ያላቸውን ክብር ቢያሳይም የተሰጣቸውን ሚና በብቃት ተጫውተውታል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕርይ ሳምራዊት/ዘሪቱ፤ በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ የምታልፍ ጠንካራ ሴት ሆና ብትቀረጽም  ያንን ስሜት በትክክል አንፀባርቃለች ለማለት ያዳግታል።  ዘሪቱ በከፍተኛ ዝምታ ውስጥ ሆና የዝምታዋን ጥንካሬ፤ ውበትና ሕይወት አላሳየችንም፡፡ ስሜት… ህይወት… እስትንፋስ…ያንሳታል፡፡ ነገሮችን አመዛዝና ከፍተኛ የሕይወት ውሳኔ የምትሰጥ ገጸ-ባሕርይ መሆኗን በብቃት አላሳየችንም፡፡ ስሜቷን ልታጋባብን አልቻለችም፡፡
ሔኖክ አየለ፤ መጀመሪያ ላይ  አስተማሪ ገጸ ባህርይ ተላብሶ ቢተውንም  በፊልሙ መገባደጃ ላይ ግን ድራሹ ይጠፋል፡፡ የገባበት አይታወቅም፡፡ በፊልሙ ውስጥ ለምን ተወለደ…? ለምንስ ድንገት ፊልሙ ሳያልቅ ጠፋ? የትስ ነው የገባው? አይዳ የተሰጣትን ገፀ ባህርይ ውብ አድርጋ ተጫውተዋለች፡፡ መሳይም ግሩም ነው፡፡ የሳምራዊት ጸሎት ጠንካራ ነበር! ሳምራዊት እና ዲበኩሉ፤ ከምትጠልቀዋ ፀሐይ ስር፣ መኪና ተደግፈው የሚታየው ትዕይንት  እጅግ ማራኪ ነው፡፡ ተመስገን ለተፈጥሮአችንና ዘመኑ ለፈጠረው ቴክኖሎጂ! በካሜራ ጥበብ  ይሄን ያህል ለውጥና መሻሻል ማየትም መታደል ነው፡፡ (ገና ብዙ ቢቀርም)
በዚህ ፊልም ተመልካቹ ሳይወድ በግድ ከ1 ሰዓት በላይ በዝምታ እንዲታደም መደረጉን ብዙዎች የወደዱት አይመስልም፡፡ ሳቅ የለም፤ ጭብጨባ የለም፡፡ ዝም ብሎ መመልከት ብቻ፡፡ ዝም ብሎ ማሰብ ብቻ፡፡ ዝም ብሎ መጠየቅ ብቻ፡፡ ዝም ብሎ መመራመር ብቻ፡፡ እንዲህ ነው የሚያደርገው የእነዘሪቱ ፊልም!
እርግጥ ነው በዘመነኛ አገራዊ ፊልሞቻችን  እንዲህ ዝም ብለን እያዳመጥን፤ እያሰብን… ሳንስቅ፣ ሳናጨበጭብ ፊልም አይቶ መጨረስ አልተለመደም፡፡ ለማሰብና ለመመራመር የሚገፋፉ ፊልም ሲኖር አይደል፡፡ ግን ለየትኛው ነው ክብርና ዋጋ የምንሰጠው? የፊልሙ ዋና ጭብጥም “ክብር ለማን እንስጥ” የሚል ነው፡፡
የሁሉንም የልብ ትርታ ማወቅ ባልችልም ለኔ እና ለወዳጆቼ ግን ከፊልሙ ያገኘነው መልዕክት ወደር የለሽ ነው፡፡ በተለይ የፊልሙ መጨረሻ አካባቢ ከመቀመጫ አስነስቶ የሚያስጨበጭብ ታላቅ መልዕክት ይተላለፋል፡፡  ፊልሙ ሲታይ ማንም ያጨበጨበ ባይኖርም፤ አንዳንዱ ቤቱ ሄዶ የሚያጨበጭብ ይመስለናል፡፡ አሊያም ዘመንን ተሻግሮ፤ ‹‹ለሰው ክብር ዋጋ›› የሚሰጥ ትውልድ ሲፈጠር በደንብ የሚጨበጨብለት ፊልም እንደሆነ የእነዘሪቱ ፊልም በሁሉም ነገር የበቃና የተሳካለት ነው ሊባል አይችልም፡፡ ግን በፊልም ዘርፍ ብሩህ ዘመን እየመጣ እንደሆነ አመላካች ነው - በፍቅርና በትጋት ከተሰራ፡፡
የጥበብ ስራ በተለይ ፊልም ተሰርቶ ሲጠናቀቅ፣ በዘርፉ ባለሙያዎች ሊፈተሽና አስተያየት ሊሰጥበት እንደሚገባው አያከራክረንም - ለተመልካች ከመቅረቡ በፊት፡፡  እነ ዘሪቱ ይህን አድርገው ይሆን?
በሕይወት ዘመናችን አንድ ጊዜ የሰራነው ስሕተት ምን ዋጋ አስከፈለን? ስህተቱን ከመስራታችን በፊት ምን ያህል ተጠነቀቅን? ስህተቱን ከሰራን በኋላስ ምን አይነት መፍትሔ ወሰድን? ከስህተታችንስ ምን ተማርን? ከፍተኛ መስዋዕትነት፣ዋጋ እና ክብር ሊሰጥ የሚገባው ለማን ነው? ለምንስ ነው?…. እነዚህን ሃሳቦች በውስጣችን ይቀሰቅሳል - ፊልሙ፡፡
የሰው መንፈስ በኦና ምድር እየተንሳፈፈች በምትገኝበት ዘመን፤ የሰው ክብር ዋጋ-ቢስ በሆነበት በዛሬው ጊዜ፣ ከንዋይ በልጦ ሊዘከር የሚችል ምንድን ነው?... የሚል ጥያቄም ይፈጥርብናል፡፡
ጥያቄና ፍተሻውን ወደ አገር ደረጃም ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ቀሚስ የለበሰች ዕለት›› ምን አይነት ስህተት ሰራች…? ምን አይነት ውሳኔስ ወሰነች…? ምን አይነት መፍትሔ አማጠች…?  ውሳኔዋ የሰውን ክብር አመጣ ወይስ አሳጣ? በተደጋጋሚ ቀሚስ መልበስ… በተደጋጋሚ ስህተት መስራት… እናም… ከስህተት አለመማር… ግን በጥበብ ከስህተት መቆጠብ እንችላለን፡፡ በጥበብ ከስህተት መማር እንችላለን፡፡ የእነዘሪቱ ፊልም ይሄን ያስተምረናል፡፡ ወደነዋል፤ አድንቀነዋል፡፡ በርቱም ብለናል - ባለሙያዎቹን፡፡

Read 2008 times