Monday, 27 January 2014 08:04

ፍቅር ሳይሰቃይ አያሸንፍም

Written by 
Rate this item
(48 votes)

                 ባለፈው ሳምንት፣ “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ዝግጅት ላይ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ከድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ያቀረብን ሲሆን፤ ስላለፈው ዘመን ታሪክና ስለአዲሱ ትውልድ ፍላጎት ያለውን አስተሳሰብ መግለፁ ይታወሳል። ሁለተኛውን ክፍል እነሆ፡-
የአገሪቱን የሩቅና የቅርብ ጊዜ ታሪክ እየጠቀስክ፣ ታሪካዊ ሰዎችንም እያነሳህ የሰራሃቸው ዘፈኖች፣ ኢትዮጵያውያንን በፍቅር የሚያቀራርቡ ናቸው ብለህ ታምን ይሆናል። ነገር ግን፤ ብዙውን ጊዜ የምናየው ከዚህ የተለየ ነው። የተለያዩ ወገኖች ጎራ ለይተው፣ ታሪክን እየጠቀሱ ሲወዛገቡ ነው የምናየው። እንደማጥቂያ መሳሪያ ይጠቀሙበታል። የውዝግብ ማራገቢያ ከሚሆን፣ ቢቀር አይሻልም?    
ታሪክን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ታሪክ ጥቅም የለውም ማለትም አይደለም፡፡ ከታሪክ ውስጥ በአድናቆት አክብረን የምንወስደውና የምናሳድገው ነገር እንዳለ ሁሉ፣ ከታሪክ ውስጥ እንዳይደገም አድርገን የምናስተካክለውና የምናሻሽለው ነገር ይኖራል፡፡ ዛሬ በህይወት የሌሉ ሰዎች በጊዜያቸው ካሰቡት፤ ከተናገሩት፣ ከሰሩትና ከፈፀሙት ነገር የምንወርሰውና የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ነገር ግን፤ ሁሉንም ነገር መውረስ የለብንም። ከሞቱ ሰዎች ላይ፣ ህይወት ያለው መልካም ስራቸውን መውሰድ እንጂ፤ ከነሱ ጋር አብሯቸው የሞተ መጥፎ ነገርን ማውጣትና ማግዘፍ ምን ይጠቅመናል? በጎ በጎውን እንጂ፣ ክፉ ክፉውን ማጉላት ጥቅም የለውም።
በጨላለመው አቅጣጫ ላይ ካተኮርክና ከተጓዝክ ጨለማ ይውጥሃል፡፡ ወደ ብርሃናማው አቅጣጫ አተኩረህ ስትንቀሳቀስ ደግሞ፣ ትንሿ ጭላንጭ እንኳ እየፈካች እየሰፋች ትመጣለች፡፡ የወደድከው ነገር ወዳንተ ይመጣል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ አንተ ስትቅርበው ወዳንተ ይመጣል፡፡
ታሪክ አበላሽቷል ብለን የምናስበውንና ከብዙ አመታት በፊት የሞተውን ሰው እያነሳን፤ አፈር የተጫነው አፅሙ ላይ ክፉኛ እንጨክናለን። የሞተ ሰው ላይ እንዲያ ከጨከንን፣ በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጭካኔያችን ምን ሊሆን እንደሚችል ስታስበው ያስፈራል፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡
ከምንም በላይ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ፣ ለሚቀጥሉት ልጆች ማሰብ ያስፈለጋል፡፡ ሲሆን ሲሆን፣ ታላላቆቻችን የድሮ ቅሬታና አስወግደው፣ ‘አዲሱ ትውልድ የራሱን ታሪክ እንዲሰራ መልካም ነገር እናውርሰው’ ብለው ሲያስቡልን ብናይ እንወዳለን፡፡ ታላላቆቻችን ይህ ካልሆነላቸው፣ ቢያንስ ቢያንስ ብሩህ ዘመን እንዲፈጠር መመኘት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
ፈጣሪ ፍቅር ነው ስለሆነም ከፍቅር ማምለጥ አንችልም። የእለት ተእለት ኑሮ ላይ የማያግባቡን ጥቃቅን ነገሮች ይኖራሉ። ግን የጥላቻ አጥር አናድርጋቸው። ከፈጣሪ ጋር እንግባባለን የምንል ከሆነ፤ ፈጣሪ ሁሉንም የሚያቅፍ ስለሆነ፤ ሁላችንንም የሚያግባባ ፍቅር አለን ማለት ነው፡፡
ሰው መሆንን አሳንሰን፣ ታሪክንም አሳንሰን፣ ፈጣሪንም እንዲሁ ወደ እለታዊ ስሜት አውርደን፣ ወደ ፖለቲካ ንትርክ ደረጃ አጥብበን ማየታችንን ማቆም አለብን። የትኛው ሃይማኖት ነው ፍቅርን የማይሰብከው? የትኛው ሃይማኖት ነው እርቅን የማይደግፈው?
የገብረክርስቶስ ግጥም ላይ አንዲት ጥንቸል አለች፡፡ ጥንቸሏ ከመሬት ጋር የተዋዋለችው ብድር ነበረ፡፡ መሬት የተጠየቀችውን ሰጠች፡፡ ጥንቸሏ አቅም ስላላገኘች ይሁን ፍላጐት ስላጣች አይታወቅም፡፡ ቃሏን አላከበረችም፡፡ እና ለማምለጥ ትሮጣለች፡፡ አሁንም ትሮጣለች፡፡ ከመኖሪያዋ ከመሬት ነው ለማምለጥ የምትሮጠው፡፡ እኛስ እንዴት ነው ከፈጣሪ ፍቅር ለማምለጥ የምንሮጠው? ማን በዘረጋው መሬት ማን ባሰፋው ሰማይ ነው፤ ቂም እያወረስን አሳዳጅና ባለዕዳ ለመሆን የምንሞክረው? በታላላቆቻችን አለመግባባት ምክንያት የመጣ አውድ መሃል የተፈጠረ ትውልድ ሆነን፣ በፍቅርና በመግባባት መቀጠል ስንፈልግ እንዴት በክፉ ይታያል? እንዴት ታናናሾች ይህንን ለታላላቆች ይነግራሉ? እንዴት ታናናሾች ታላላቆችን ይሸከማሉ? ይሄ ከባድ ጥያቄ አለብን፡፡ በየአጋጣሚውና በሰበቡ በሚፈጠር ንትርክ ላይ ሳይሆን፤ ያንን ከባድ ጥያቄ ለመፍታት ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ታላላቆቻችንን፤ አለመግባባት እንዲወገድና ፍቅር እንዲሆን፣ አዲሱ ትውልድ በተስፋ አይን፣ አይናቸውን እየተመለከተ ይጠይቃቸዋል፡፡
እስቲ ተዋደዱ ይያያዝ እጃችሁ
አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ?
ቂምን ተሸክሞ አለመግባባትን የሙጢኝ ማለት ውጤቱ ምን እንደሆነ አብረን እያየነው፤ ለምን ወደሚቀጥሉት ልጆች እንዲሸጋገር እናደርጋለን? አንዳንዴ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቀና ትውልድ የድርሻውን እንዳይሞክር ማወክ፣ የፍቅር ሃሳቡንም ማፍረስ የለብንም፡፡ መድሃኒት አይገፊም፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፤ ረዥም ጊዜ ከተማመንበት በሽታ የሚያድነን፤ ፈውስ ነው፡፡
የድሮ ሰዎችን ትልቅ ታሪክና ጀግንነት እየጠቀስን የምንኮራ ከሆነ፤ በስህተታቸው ማፈርና የጥፋታቸው ባለዕዳ መሆን የግድ ነው፡፡ ሁለት ወዶ ይሆናል? ከወላጆቼና ከታላላቆቼ ያኛውን ትቼ ይህኛውን ብቻ ልውረስ ማለት ያስኬዳል?
በፍቅር ተገናኝተው ልጆችን ለማፍራት የበቁ ወላጆች፣ የአያቶችን አለመግባባትና ቂም አስታውሰው ሲለያዩ፤ ለልጆቻቸው የሚያወርሱትን አስበው፡፡
የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ላይ’ኮ አይተናል፡፡ ለዚህም አይደለም እንዴ፤ ዳህላክ ላይ ያለው ሰውዬ፤ ለተለያትና ለተለየችው ባለቤቱ፤ አለመግባባትና ፀብ በኛ ላይ ያቁም፤ ቅሬታን ለልጃችን አናውርሰው፤ ጥላቻንና ቂምን አናስተምረው የሚላት፡፡ ፍቅርንና መግባባትን ብናስተምረውና መልካም ችግኝ ብናደርገው፤ እኛን መልሶ የሚያቀራርብና የሚያስታርቅ ታላቅ ሰው ይሆናል ይላታል፡፡ አለመግባባት ሊያጋጥማቸው አይገባም ነበር በለን ታላላቆችን ሁሉ መውቀስ ስህተት የመሆኑን ያህል፤ አለመግባባትን ማውረስ ስህተት ነው፡፡ አለበለዚያማ፤ መሻሻልና ማደግ አይኖርም፡፡ እንደ ዳህላኩ ሰውዬ ታላላቆች ለአዲሱ ትውልድ መልካም ሲጨነቁ፣ ከወረሱት ቂም ይልቅ የሚያወርሱት ፍቅር እንደሚበልጥ አስበው መልካም ነገር ሲያስተምሩ፤ የታናናሾች እና የልጆች ስሜት ብሩህ፤ የአገሬው መልክና መንፈስ ያማረ ይሆናል፡፡ የአገር ታሪክ፣ ፖለቲካና መንግስትም ደግሞ፣ የአገሬውን ሕዝብ መምሰሉ የማይቀር ነው፡፡ በቅንነት የወደድከው ሳይመጣ አይቀርም፡፡ አዲሱ ትውልድ ቅን ስለሆነ፤ መልካም ዘመን፣ ድንቅ ታሪክ እየመጣ ነው፤ እድል እንስጠው፡፡
ወደ ፍቅር ጉዞ አይቆምም ብለሃል። ኮንሰርቶቹ ይዘጋጃሉ ማለት ነው?
የትውልድ ድምጽ፤ የትውልድ ራዕይ ነው። ራዕይ ደግሞ አስቀድሞ የተፈፀመ ነገር ግን አሁን የሚገለጥ ነው፡፡ ፍቅር እጅግ ሃያል ስለሆነም ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አገራችን በታሪክም በህዝብም ሰፊ ነች፡፡ አለመግባባት አይፈጠርም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ሰው፤ እንደተገነዘበውና እንዳወቀው መጠን፤ እንደመጣበትና እንደመረጠው መንገድ፤ በመሰለውና በኮረኮረው መጠን ያስባል፡፡ ይሄ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ፍቅር ይህንን ሰፊ ተፈጥሮ ስለሚያቅፍ፣ በየአጋጣሚው የሚያደነቃቅፍ ነገር ያጋጥመዋል ግን ይጓዛል፡፡
ወደ ፍቅር ጉዞ ተጀምሯል ትላለህ። ግን፣ ዙሪያችንን ስናየው፤ ብዙም ለውጥ የለም። በየምክንያቱ ግጭት፣ በየሰበቡ ውዝግብ ነው፤ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ...። ጉዞው ቢጀመር እንኳ ስንዝር መራመድ የሚችል አይመስልም።
ወደ ፍቅር የምትጓዘው መንገዱ ተመቻችቶ ሲዘጋጅ ብቻ አይደለም፡፡ መንገድ ከጠበበ እያሰፋህ መንገዱ ካልተመቸ እያስተካከልክ ነው የምትጓዘው። በአለም ደረጃም ልታስበው ትችላለህ፡፡ ከባድ አለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በየአገሩ ለጦር መሳሪያ የሚውለው ሃብት፣ ለጦርነት የሚወጣው የገንዘብ ሲታይ፣ ሰላምን ማጣጣም ወይም መፍትሔ ማግኘት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይነግርሃል። ፍቅር ያሸንፋል ሲባል፤ ክብደት የለውም ብሎ ለማቃለል አይደለም፡፡ ብዙ ነገር የመሸከም ሃይል ስላለው ነው። “ቀላል ይሆናል” የሚለው ዘፈንም’ኮ የተራራው ጫፍ እያለ ከባድነቱን ያሳያል፡፡
ደቂቀ ተስፋን ካየናት አርቀን
ነገ ሌላ ይሆናል ጥሩ ቀን
የተስፋ ጭላንጭሏ ማነስ፣ የተራራው አናት ርቀት፣ የመንገዱ አለመደላደልና አስቸጋሪነት ባይካድም፤ በብርሃን የተሞላው መስክና የተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ መጓዝ አለበት፡፡ ለምን ብትል፤ “ፍቅር ያሸንፋል” ካልን፤ “ለፍቅር እንሸነፋለን” ማለት ነው፡፡ ወደ ወደድከው ነገር ትጓዛለህ፡፡ ለፍቅር ብለህ፡፡
ሁላችንም አሸናፊ ለመሆን እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን አሸናፊነት ማለት የመጨረሻው ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ጉዞውም ጭምር ነው፡፡ “ገዳዩ፣ ገዳዩ” የሚሉ ብዙ ዘፈኖች አሉን፡፡ አሸናፊነን ለመግለጽ ነው፡፡ ግን መተውም ቢሆን የሚያሸንፉ አሉ፡፡ ኢየሱስ ይህንን ያስተማረን ይመስለኛል፡፡ ጥላቻን በይቅር ባይነት ድል በሚያደርግ ቀና የፍቅር መንገድ መጓዝ አሸናፊነት ነው፡፡ “ፍቅር ያሸንፋል” እና “ፍቅር አሸንፏል” ብሎ መናገር ልዩነት የለውም፡፡ ገና ከጅምሩ ጉዞው ውስጥ አሸናፊነት አለ፡፡
አንድ በጣም ስሜትን የሚነካ ታሪክ ላስታውስህ። በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል ለዘመናት ያላበራው ግጭት፣ ጥፋት እና ሃዘን አሁንም ከየእለቱ ዜና ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ነገሩ፤ የሙስሊሞች በዓል የሚከበርበት ቀን ላይ ያጋጠመ ነው፡፡ የታሪካቸው ቅርበት ያህል የብዙዎቹ ኑሮም ቅርብ ለቅርብ ነው፡፡ ከመንገዱ ወዲህ ፍልስጤኤማውያን፣ ከመንገዱ ወዲያ ደግሞ እስራኤላዊያን ይኖራሉ፡፡ ጥዋትም ከሰዓትም በኋላም ማዶ ለማዶ ይተያያሉ። ፋታ የሌለው ጥርጣሬ ግን በሰላም እንዲተያዩ አላደረጋቸውም፡፡
እና በዚያ የበዓል ቀን፤ አባት ለልጁ አዲስ ልብስ ገዝቶለታል፤ አዲስ መጫወቻም አምጥቶለታል፡ በተገዛለት መጫወቻ የተደሰተው ህፃን፣ አዲስ ልብሱን እንዳደረገ ከቤት ውጭ ይጫወታል፡፡ ቦታው ትንሽ ከፍ የለ ነው፡፡ ወደ ታች ብዙም ሳይርቅ የእስራኤላዊያን መንደር አለ፡፡
ከመሃል ባለው መንገድ ላይ ለጥበቃ የተመደቡ የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ይቃኛሉ። እና ከወታደሮቹ አንዱ፣ ከጉብታው አካባቢ የሰው እንቅስቃሴ ሲመለከት፤ አደጋ ተሰማው፡፡ የተነጣጠረ መሳሪያ ታየው፡፡ ሳይቀድመኝ ልቅደም ብሎ ይተኩሳል፡፡
አባቱ የገዙለትን ውሃ የሚረጭ ሽጉጥ ይዞ ሲጫወት የነበረው ህፃን በጥይት ተመታ፡፡ አባት የተኩስ ድምጽ ሰምቶ በድንጋጤ ከቤት ወጥቶ ይመጣል፡፡ ልጁ ወድቋል፡፡
የእስራኤል ወታደሮችም ተጠግተው አይተዋል፡፡ የተነጣጠረ መሣሪያ የመሰላቸው ነገር ውሃ የሚረጭ ሽጉጥ መሆኑን ሲያዩ ደነገጡ፡፡ ህፃን መጉዳታቸውን ሲያዩ አዘኑ፡፡
በአስቸኳይ ሄሊኮፕተር ተጠርቶ ልጁ ወደ ሆስፒታል እንዲወሰድ አደረጉ፡፡ ነገር ግን ወደ ሆስፒታል የተወሰደውን ህፃን ለማዳን ሃኪሞች ቢጣጣሩም አልተሳካላቸውም፤ ህይወቱ አለፈ፡፡ ይሄ አባት፣ ከዚያች ቅጽበት በኋላ ምን አይነት ሰው እንደሚሆን አስበው፡፡
በሀዘን የተመታው አባት፤ ሃኪሞቹን ጠየቃቸው። “የልጄ ልብ ንፁህ ነው ወይ” አላቸው፡፡ ያልጠበቁት ጥያቄ ነው፡፡ “አዎ ጤናማ ነው” አሉት፡፡
“እንግዲያውስ፣ በልብ ህመም ለሚሰቃዩ እስራኤላዊ ሕፃን አስተላልፉለት” አላቸው፡፡ ያልተለመደ በጣም አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ውስጥ ይበዛም ይነስ በጐ ነገር አለ፡፡ አደገኛነት ብቻ ሳይሆን ታላቅነትም የሚወለደው እንዲህ ካለ ጥልቅ ጉዳት ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍቅር ሳይሰቃይ አያሸንፍምና፡፡

Read 12844 times