Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:52

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ገቢው እንጅ ዋንጫው አያጓጓም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድል ከገቢው በላቀ ሁኔታ እንደማያጓጓቸው ታወቀ፡፡ ትልልቆቹ ክለቦች በምድብ ማጣርያው የሚኖራቸው ተሳትፎ የሚያስገኘው ገቢ ላይ ማነጣጠራቸውን የገለፁ ዘገባዎች በጥሎ ማለፉ ምእራፍ ከመቀጠል ይልቅ በየሊጋቸው ለሚያደርጉት የሻምፒዮናነት ትኩረት የመስጣት አዝማሚያ እየታየባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የውድድር ዘመኑ 5ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ሰሞኑን ሲደረጉ ለጥሎ ማለፍ ያለፉ 9 ክለቦች የተለዩ ሲሆን፤ 23 ክለቦች ለቀሩት 7 የጥሎ ማለፍ ቦታዎች በ6ኛው ዙር የመጨረሻ ግጥሚያዎች ውጤታማ ለመሆን ይቀርባሉ፡፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ እስከ 5ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ በተደረጉ 80 ጨዋታዎች ተደርገው 211 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን አንድ ግጥሚያ በአማካይ 2.64 ጎሎች ይገባበታል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ላይ የባየር ሙኒኩ ማርዮ ጎሜዝና የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ6 ጎሎቻቸው ተያይዘዋል፡፡ ከ6ኛው ዙር የመጨረሻ ማጣርያ በፊት የምድባቸው መሪ በመሆን ማለፋቸውን ያረጋገጡት ባየር ሙኒክ፤ ኢንተር ሚላን፤ ሪያል ማድሪድ፤ አርሰናልና ባርሴሎና ሲሆኑ በምድብ 8 ያለው ኤሲ ሚላን በሁለተኛ ደረጃ ማለፉን ሲያረጋግጥ ቤነፊካ ፤ ባየር ሌቨርኩዘንና ኤፒኦኤል የማለፍ ሰፊ እድል ይዘው የምድብ ማጠርያውን ማጠናቀቂያ ጨዋታዎች ይጠብቃሉ፡፡
ሪያል ማድሪድ በሬከርድ ውጤታማነት ወደ አስረኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ድል እየገሰገሰ መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም የቅርብ ተቀናቃኙ ባርሴሎና እና ባየር ሙኒክ እኩል ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሪያል ማድሪድ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ አያክስን ከረታ በ6 ጨዋታ ሙሉ 18 ነጥብ በመውሰድ አዲስ ሪከርድ ያስመዘግባል፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች በሪያል ማድሪድ የሞውሪንሆ ኤክስፐርመንቶች እየታዩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ቼልሲ፣ ማን ዩናይትድና ማን ሲቲ ህልውናቸው በመጨረሻው ጨዋታ መወሰኑ የእንግሊዝ ክለቦች ባለፉት 4 ዓመታት የነበራቸው የበላይነት እየደበዘዘ መምጣቱን አሳይቷል፡፡ ብቸኛው ተስፋ ለ12ኛ ተከታታይ ዓመት ምድብ ማጣርያውን ማለፍ የቻለው አርሰናል ብቻ ነው፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎችን ለማድረግ የበቁ ክለቦች በየጨዋታው 550ሺ ዩሮ የሚታሰብላቸው ሲሆን በተጨማሪ ለድል 800ሺ ዩሮ ለአቻ ውጤት ደግሞ 400ሺ ዶላር ያገኙባቸዋል፡፡ በምድብ ጨዋታዎች 6ቱንም የሚሸነፍ ክለብ ቢኖር እንኳን እስከ 7.2 ሚሊዮን ዩሮ ማግኘቱ ትልልቅ ክለቦች ወደ ዋንጫው የመገስገስ ፍላጎታቸው እንዲቀዘቅዝ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ገቢ ሌላ ክለቦች ከቲቪ ገንዘብ የሚያገኙት ድርሻም በምድብ ማጣርያው ምእራፍ ብቻ በቂ የገቢ እርካታ የሚፈጥር ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ለፍፃሜ የቀረቡት ሁለት ክለቦች ዋንጫውን የበላው ባርሴሎና 51 ሚሊዮን ዩሮ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ማን ዩናይትድ 52.3 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ባርሴሎና ሻምፒዮን ቢሆንም ከቲቪ ገቢ 25.9 ሚሊዮን ዶላር በመውሰድ ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው ማን ዩናይትድ ነው፡፡ ለፍፃሜ ያልደረሱት ሌሎች ክለቦች በሚገርም ሁኔታ ከቴሌቭዥን ገቢ ቼልሲ 44.5 ፣ ሻልካ 39.8፣ ሪያል ማድሪድ 39.3 ፣ ኢንተር ሚላን 38፣ ባየር ሙኒክ 32.6 እንዲሁም ቶትንሃም 31.1 ሚሊዮን ዩሮዎች አግኝተዋል፡፡ ይሄው ማራኪ ገቢ ታላላቅ ክለቦች ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከመድረሳቸው በፊት በምድብ ማጣርያው የሚያደርጉት ተሳትፎ ብቻ አተኩረው ለጥሎ ማለፉ ግድ ሳይኖራቸው በየአገራቸው ሊግ ለሚኖራቸው ስኬት ብቻ እንዲያነጣጥሩ ማድረጉን ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡

 

Read 2994 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 09:17