Monday, 27 January 2014 07:54

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ተኩስ ለማቆም ተፈራረሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አደራዳሪው አምባሳደር ስዩም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ይቆጣጠራሉ
በመንግስት የታሰሩ ተቃዋሚዎች ይለቀቃሉ ተብሏል


የደቡብ ሱዳንን ገዢ ፓርቲ ለሁለት በመሰንጠቅ፣ አንጋፋ መሪዎች በሁለት ጐራ የሚያካሂዱትን ጦርነት ለመሸምገል በአካባቢው አገራት ይሁንታ የተመደቡት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ ሁለቱ ባላንጣዎች ተኩስ እንዲያቆሙ በማስማማት ሐሙስ ማታ አፈራረሙ፡፡
በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከስልጣን የተባረሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ካካሄዱ በኋላ፣ መንግስት አፈንጋጭ የገዢው ፓርቲ አመራሮችንና ባለስልጣናትን ያሰረ ሲሆን አፈንጋጮቹ በበኩላቸው፤ በወታደራዊ ጥቃት በርካታ ከተሞችና የነዳጅ ማውጫ ቦታዎች ላይ መዝመታቸው ይታወቃል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የኢጋድ አባል አገራት፣ አምባሳደር ስዩም መስፍንን ከቻይና በመጥራትና ሁለት ተጨማሪ ልዑካንን በማከል ተቀናቃኝ የደቡብ ሱዳን ባላንጦችን እንዲሸመግሉ ቢመድብም፣ ተቀናቃኞቹ ያቀረቡት የድርድር ቅድመ ሁኔታ ፈታኝ ሆኖባቸው እንደቆየ ተነግሯል። ድርድሩ ያለ ውጤት ሊራዘም ይችላል ተብሎ ቢገመትም ፤ መንግስት ለሰላም ድርድር ሲል ተቃዋሚዎችን ከእስር እንዲለቅ፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ በሃይል ስልጣን ለመያዝ ከመሞከር እንዲቆጠቡ በማሳመን ሐሙስ እለት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ተደርጓል፡፡
ተቀናቃኞቹ ወገኖች ከወታደራዊ ጥቃትና ከፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመቆጠብ የተፈራረሙትን ስምምነት ማክበራቸውን ለመቆጣጠር አምባሳደር ስዩም እና ሁለቱ ተጨማሪ የኢጋድ ልዑኮች ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ አስቸጋሪ ሃላፊነት በተጨማሪ፤ ተቀናቃኞቹ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ለመድረስ የሚያካሂዱት የሰላም ድርድር ብዙ ፈተናዎች ስለሚጠብቁት፤ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ይቆያል ተብሏል፡፡
በሚቀጥለው ሣምንት በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም በግብርናና በምግብ ዋስትና ዙሪያ እንዲያተኩር ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ የጉባኤው ትኩረት ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የፀጥታ አደጋዎች ይዞራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሃይማኖት ጋር የተነካካው የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ቀውስ እና የእርስ በርስ ግጭት ሰሞኑን ረገብ ያለ ቢመስልም አገሪቱ አሁንም ከቀውስ አልወጣችም፡፡ የዋና ከተማዋ የባንጉዊይ ከንቲባ የአገሪቱ ኘሬዚዳንት እንዲሆኑ ተመርጠው ስልጣን ቢረከቡም የፀጥታ ሁኔታው አሁንም እንዳልተረጋጋና አፋጣኝ ሁነኛ መፍትሄ ካልተገኘ ግጭቱ ወደ እርስ በርስ እልቂት ሊያመራ እንደሚችል ከአገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡
ከመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞ የአፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፤ በሠላምና መረጋጋት ችግሮች ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሃሣቦችን ለመሪዎቹ ጉባኤ ያቀርባል፡፡
በህብረቱ ጉባኤ ላይም ሆነ ጣና ላይ እየተካሄደ ባለው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ግብጽ አትሳተፍም። የመሀመድ ሙርሲን መንግስት ተክቶ ያለው ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን በህዝብ ለተመረጠው መንግስት እስኪያስረክብ ድረስ ግብጽ በአፍሪካ ህብረት እንዳትሳተፍ ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡

Read 1787 times