Sunday, 19 January 2014 00:00

ተዋጊ፤ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሳይሆን፣ ሲመለስ ነው የሚወደሰው!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንድ ታዋቂ ደራሲ የእርሳሱ ታሪክ በሚል የጻፈው የአጭር አጭር መጣጥፍ እጅግ አስተማሪ ነውና ዛሬ ከትበነዋል፡፡ አንድ ልጅ፤ ሴት አያቱ ደብዳቤ ሲጽፉ አተኩሮ ይመለከታቸዋል፡፡ ብዙ ካያቸው በኋላ፤ “ስለ እኛ ታሪክ ነው የሚጽፉት? ስለኔ ነው?” አለና ጠየቃቸው፡፡ አያትየው፤ ደብዳቤ መጻፋቸውን አቆሙና ለልጅ ልጃቸው እንዲህ አሉት፡- “እርግጥ ነው ልጄ ስለ አንተ ነው የምጽፈው፡፡ ሆኖም ከጻፍኳቸው ቃላት ይልቅ ስለ እርሳሱ ማወቅ ያለብህ ነገር ነው እሚበልጠው፡፡ አንድ ቀን አንተም አድገህ እንደዚህ እንደምገለገልበት እርሳስ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ” በነገሩ እጅግ ተነክቶ፤ ልጁ እርሳሱን ትኩር ብሎ ተመለከተው፡፡ ሆኖም፤ ከሚያውቀው እርሳስ የተለየ ሆኖ አላገኘውም፡፡ “ይሄ ዱሮም የማውቀው እርሳስ አይደለም እንዴ? ምን የተለየ ተዓምር አለው? ሲል ጠየቃቸው። አያትየውም፤ “አየህ ልጄ፤ እሱ አንተ ነገሮችን የምታይበት ዓይን ጉዳይ ነው፡፡ እርሳስ አምስት ዓይነት ልዩ ጠባያት፤ አሉት፡፡ እነዚህን ልብ ካልክ፣ ምን ጊዜም በዓለም ላይ ሰላም ያለው ልጅ ትሆናለህ፡፡ “የመጀመሪያ ልዩ ጠባዩ፤ ትላልቅ ነገሮችን የመሥራት ክህሎት መኖሩ ነው፤ ሆኖም ምንም ዓይነት ልዩ ክህሎትና ችሎታ ቢኖርህ መንገድህን የሚመራ እጅ መኖሩን አትርሳ፡፡ ያን እጅ አምላክ እንለዋለን፡፡

እሱ ሁልጊዜ እንደ ፈቃዱ የሚመራን ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩ ጠባዩ፤ በምጽፍ ጊዜ አሁንም አሁንም መጻፌን አቁሜ ልቀርፀው ይገባኛል፡፡ ያም እርሳሱ ትንሽ እንዲያመው ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ከታመመ በኋላ የበለጠ የሰላ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንተም ህመምህንና ሀዘንህን እየተሸከምክ፣ እየቻልክ መኖርን ከተማርክ የተሻለ ሰው ትሆናለህ፡፡ ሦስተኛው ልዩ ጠባዩ፤ ድንገት የተሳሳተ ነገር ብንፅፍ በላዺስ ተጠቅመን ማጥፋት እንችላለን፡፡ ይሄ የሚያመለክተን አንድ የሠራነው ነገር ስህተት ሆኖ ሲገኝ ማረም መጥፎ አለመሆኑን ነው፡፡ ወደ ትክክሉ፣ ወደፍትሐዊው መንገድ ተቃንተን እንድንጓዝ ይረዳናልና! አራተኛው ልዩ ጠባዩ፤ የእርሳሱ የላይኛው የእንጨት ልባሱ ወይም ቅርፊቱ ሳይሆን ዋናው ከውስጡ ያለው ግራፋይት /እርሳሱ/ ነው ቁም ነገሩ፡፡ ይህ ራስህ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ልብ ማለት እንዳለብህ ትምህርት ይሰጥሃል፡፡ ዋናው የውስጣችን፣ የመሠረታችን ጉዳይ፤ ማለት ነው፡፡ አምስተኛውና የመጨረሻው ልዩ ነገር፤ እርሳስ ባለፈበት ሥፍራ ሁሉ ምልክት ወይም አሻራ ይተዋል፡፡ ልክ እንደ እርሳሱ ራስህን ቆጥረህ ብታስበው፤ እያንዳንዱ በህይወትህ እየሠራህ የምታልፈው ነገር ሁሉ ምልክት ይተዋል፡፡ ስለዚህ ያለፍክ ያገደምክባትን የሕይወት መንገድ ሁሉ አስተውል፡፡

                                                             * * *

ከአያት ከቅድመ አያት የወረስናቸውን ትምህርቶች በአግባቡና በቅጡ ሥራ ላይ ካዋልናቸው ከመሠረታዊ የኑሮ ግልጋሎታቸው ባሻገር አገርን ለማሻሻል የለውጥ አንጓ ይፈጥሩልናል፡፡ የራሳችንን ሰላም የምንፈጥረው ራሳችን ነን፡፡ የሚመራን እጅ/አምላክ እንዳለ ማሰብ ያለብን ራሳችን ነን፡፡ ህይወታችንን ማለትም እራሳችንን በየጊዜው መቅረጽ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ስናደርግም የየጊዜውን ህመም ተቋቁመን መሆን አለበት፡፡ ስህተትን አርሞ ወደ ፍትሐዊው መንገድ መጓዝ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ህይወት ከላይ ከላይ ስትታይ ብልጭልጯ ብዙ ነው፡፡ ብልጭልጯ ግን እንደእርሳሱ የተቀባ የእንጨት ቅርፊት ነው፡፡ ዋናው ውስጧ ነው፡፡ ቡጧ ነው፡፡ ውስጣችንን እናንብብ። አገራችንን እንወቅ፡፡ በውስጥ የሚከናወነውን እናጢን፤ እናውጠንጥን፡፡ ንፁህ ዜጋ በውስጡ የሚካሄደውን ክንዋኔ ሲያውቅ ራሱን ያውቃል፡፡ ቀጣይ መንገዱ ያውቃል፡፡ ለሀገሩ የሚበጀውን ያደርጋል፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ላይ የምንተወውን አሻራ ብናውቅ የአመት የአምስት ዓመቱን፣ የዘለቄታውንም አሻራ እናስተውላለን፡፡ አሻራችንን ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ ያም ሆኖ አንዳንዶች የሁሉን ተግባር አልፋና ኦሜጋ ራሳቸውን አድርገው ይፎክራሉ፡፡ “ሁሉ ያማረ በእኔ ነው፡፡ ሁሉን እምሠራ እኔ ነኝ፡፡ ከማንም የተሻልኩ ንፁሕ ነኝ፤ አልተሳሳትኩም፤” በማለት ይፎክራሉ፡፡ ይሄ በተራ ግንዛቤ እንኳ ሲታይ “የሚሠራ ይሳሳታልን” መርሳት ነው፡፡

“ክንፍ አለኝ፣ መልዐክ ነኝ ብለህ አትፎክር ትንኝም ክንፍ አላት፣ ባየር ለመብረር…” ይሉናል ብርሃኑ ድንቄ፡፡ የአደጉና አዳጊ፣ ትላልቅና ትናንሽ አገሮች አንዱ አንዱን የሚያይበት ዐይኑ መለያየቱ እንጂ እንከን አልባ ብሎ አገር የለም፡፡ የዓለም ገዢ ነን የሚሉት ኃያላንም ቢሆኑ፡፡ “ዓለም አቀፍ ዴሞክራቲክ ካፒታሊዝምም ቢሆን እንደዓለም አካላይ ኮሙኒዝም፤ አስተማማኝ ሥርዓት አለመሆኑን ልብ በሉ”፤ ይለናል ጆን ግሬይ፡፡ ዕምነት እምንጥልባቸውን ታላላቅ አገሮች በዲፕሎማሲያዊ ጥንቃቄ እንያዛቸው፡፡ እነሱም ለጥቅማቸው፣ እኛም ለጥቅማችን፤ እንበል። ሲያመሰግኑን “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ይሏታል”ን “እንዲህ እያልሽ ውቴልሺን ሽጪ” ማለትን እንልመድ፤ ቢያንስ በሆዳችን፡፡ ያለጥቅም እጅ የማይዘረጋበት ዘመን ነው፡፡ በተለይ ዕምነተ ካፒታሊዝማችን ያለዕውቀትና ከልኩ ያለፈ ሲሆን “የባለጌ ሃይማኖት ከጅማት ይጠናል” ነው እሚሆነው፡፡ ፓውሎ ኮሄሎ የተባለ ፀሐፊ፤ “አንዳንድ ታላላቅ መንግሥታት በሽብርተኝነት ላይ የሚካሄድ ጦርነት ባሉት ላይ፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ መንግሥት መፍጠሪያ ዘዴ አድርገው ይጠቀሙበታል” ሲል ይሟገታል፡፡

“እቺ ጠጋ ጠጋ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነች” እንደሚባለው ነው፤ ማለቱ ነው፡፡ “አንዱ ሲያለማ፣ ሌላው ያደለማ” በሆነበት የአገራችን ሁኔታ ውስጥ፤ ምሥጡን ከመዥገሩ፣ መወቴን ከአለሌ፣ ጨውን ከአሞሌ፣ ቱሪስትን ከፒስኮር፣ ህንዱን ከሳኒያን፣ ዶፉን ከወጨፎ፣ ጐረቤትን ከጐረቤት፣ ኔትዎርክን ከኖ-ወርክ…ለይተን ካልተጓዝን፣ የትም አንደርስም፡፡ እንወቅበት። ዛሬ “ከልጄ ለቅሶ፣ የጌታዬ ደቦ ይበልጣል” የሚል አድርባይ የበዛበት ጊዜ ነው፡፡ ለጥቅም የማይነቀል ባህር ዛፍ የለም፡፡ ባለጊዜን ማወደስ በየሥርዓቱ የሚታይ ክስተት ቢሆንም የከፋ ጊዜ ሲመጣ ባልሠራው የሚሞገስ፣ ባልፀዳበት ንፁህ የሚባል እየበዛ መሄዱ አንድም የአወዳሹን የፈጠጠ ደጅ ጠኒ አዕምሮ፣ አንድም የተወዳሹን ግብዝነት ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ በምንም መለኪያ አገር ገንቢ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ገና ሥራው ሳይሰራ በመፈክርና ይሄን ላደርግ ይህን ልፈጥር አቅጃለሁ በሚል ከፍ - ከፍ አርጉኝ ማለት፤ “ተዋጊ፤ ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሳይሆን፣ ሲመለስ ነው የሚወደሰው” የሚባለውን ተረት መዘንጋት ይሆናል!

Read 5161 times