Sunday, 19 January 2014 00:00

“ሰላም” ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ ሁለት ጠንካራ ጐራ አሠባስባለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የአገሪቱን ፓርቲዎች ለውይይት ጋብዟል

በሀገራችን የሚገኙትን በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማሠባሠብ ሁለት ጠንካራ ጐራዎች ለመፍጠር ማቀዱን የገለፀው “መግባባት፣ አንድነትና ሠላም ማህበር” (ሰላም) በዛሬው እለት በሚያደርገው ስብሰባ ይሄን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ገለፀ፡፡ ማህበሩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በዛሬው እለት ለግማሽ ቀን በአዲስ ቪው ሆቴል በሚያደርገው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ላይ በአገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ጋብዟል፡፡ “በዚህች ሀገር ፖለቲካ ውስጥ ሁሉም በደል አድርሷል” ያሉት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ፤ ይህን በደል የሚፍቅ የይቅር ባይነት ልብ እንዲፈጠር የሁሉንም ትውልድ ብሩህ ተስፋ ማለምለም ይገባል ብለዋል፡፡ ማህበሩ ይህንን እውን ለማድረግም ሁሉንም አካላት እንደሚያወያይ ገልፀዋል፡፡ “ሀገርን ከመከፋፈልና ከመመዝበር ለማትረፍ፣ ከጥላቻ ፖለቲካ በፀዳ መልኩ ቂም በቀልን አስወግደው ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርጉ ዳግማዊ ቴዎድሮሶችንና የይቅርታና የነጻነት አባት ዳግማዊ ኔልሠን ማንዴላን የሚተኩ ቁርጠኛ አፍሪካውያን መሪዎችን ለማፍራት በርትቼ እሠራለሁ” ብሏል - ማህበሩ፡፡ አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫ ከማውጣት ባለፈ የህዝብን መብትና ነፃነት የማሳወቅና የማስከበር አቅማቸው አናሣ ነው ያለው ማህበሩ፤ ገዥው ፓርቲም ይህን ድክመታቸውን በመገንዘቡ በተቃዋሚዎችና በሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ውስጥ ሠርጐ በመግባት የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው ብሏል፡፡

Read 2336 times