Sunday, 19 January 2014 00:00

የአለም ዕዝነት

Written by  መሐመድ እድሪስ
Rate this item
(4 votes)

          ስለ አላህ መልእክተኛ አንዳንድ ነጥቦችን ለመግለጽ ዕድል በማግኘቴ ከፍተኛ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ ለአለም እዝነትና ብርሐን ሆነው ስለተላኩት የነብያት መደምደምያ ስለሆኑት ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) መግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ያቅሜን ያህል ሞክርያለሁ፡፡ ከአካላዊ ገጽታቸው ልጀምር፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ወደር አይገኝላቸውም፡፡ ገጽታቸው ውብ፣ ባህሪያቸው ያማረ ነበር፡፡ በርግጥ መልክና ፀባያቸውን በተሟላ መልኩ ማስቀመጥ ይከብደናል፡፡ ኢማም ቁርጡቢ እንዲህ ብለዋል:- “የአላህ መልዕክተኛ ውበት በተሟላ መልኩ አልተገለፀም፤ ምክንያቱም ውበትን ሁሉ ያካተተ ማንነታቸው በተሟላ መልኩ ቢገለጽ ኖሮ ሶሖቦች (ባልደረቦቻቸው) ገጽታቸውን ለማየት አቅም አይኖራቸውም ነበር፡፡ ሶሖቦች የአላህ መልክተኛ ዘወትር አብረዋቸው ቢሆኑም ከአናሳ ግብራቸው የተነሳ የመልእክተኛውን ውበት ብርሐን እስኪጠግቡ ያዩት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ አቡበከርና ዑመር ባሉበት የአንሷሮችና የሙሐጂሮች ስብስብ ነብዩ መሐመድ ሲመጡ ከአቡበከርና ከዑመር በስተቀር ሌሎች ሶሖቦች አንገታቸውን አቅንተው ሊያዩአቸው አይደፍሩም ነበር፡፡

ሁለቱ ግን ያዩአቸዋል፡፡ ፈገግታም ይለዋወጣሉ፡፡ (ቲርሚዚ) ግብጽን ያቀናው አሚር ቢን አልአስ በዕድሜው መጨረሻ ላይ ስለዚህ ነገር ሲያወጋ እንዲህ ብሏል:- “ከአላህ መልዕክተኛ ይበልጥ ተወዳጅና የተከበረ ሰው ከኔ ዘንድ አልነበረም፡፡ ለርሳቸው ካለኝ ክብር የተነሳ አይኔን ሞልቼ ላያቸው አልደፍርም፤ ገጽታቸውን እንዳብራራ ብጠየቅ እንኳን ይህን ማድረግ አልችልም፡፡ (ሙስሊም) የተባረከው የነብዩ ፊት በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች የስክነትና የመረጋጋት መንፈስ የሚያሰፍን እጅግ ውብና ንፁሕ ገጽታ ነበረው፡፡ ከአይሁድ የሐይማኖት ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበረው አብደላህ ቢን ሰላም፤ እስልምናን ከመቀበሉ በፊት የስደት ሐገር ከሆነችው መዲና እንደደረሰ የነብዩን፣ የተባረከ ፊት ባየ ጊዜ እንዲህ ለማለት ተገዷል:- “ይህ ፊት የሐሰተኛ ሰው ፊት አይደለም” (ቲርሚዚ ቢን ማጂህና አህመድ) የነብዩ ውበት፣ ግርማ ሞገስና የገጽታቸው ብርሐን ነብይነታቸውን የሚመሰክር ከመሆኑ የተነሳ የአላህ መልዕክተኛ ለመሆናቸው ሌላ ዋቤ ወይም ተዐምር አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ገጽታቸው፤ ትህትናን፣ ቆራጥነትን፣ ጽናትን እንዲሁም የላቀ አላማ የተሸከመ ህያው ነበር፡፡ የአዛኝነታቸውን ጥልቀት ለመግለጽማ ያስቸግራል፡፡ ነብዩ (ሰ.ወ) ፊታቸው የውበት ቋት ነበር። ንግግራቸው ይመስጣል፡፡

ገለጻቸው ያፈዛል። አንደበታቸው ርቱዕ ነው፡፡ አማረመዳቸው ይማርካል፡፡ ንግግራቸው ምክርና ጥበብ ብቻ ነበር። አሉባልታና ፍሬ አልባ ወግ አያውቁም፡፡ ትሁትና ልዝብ ነበሩ፡፡ ተንከትክተው አይስቁም፡፡ ሳቃቸው ፈገግታ ነበር፡፡ በድንገት ያያቸው ልቡ በፍርሃትና በአክብሮት ይመላል፡፡ የተላመዳቸው ደግሞ ከልቡ ይወዳቸዋል፡፡ ቸርነታቸው ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የበዛ ነበር፡፡ ጂቢር እንዲህ ሲሉ ይህን ዕውነታ ገልፀዋል። “የአላህ መልክተኛ አንዳች ነገር ተጠይቀው አይከለከሉም ነበር፡፡ (ሙስሊም) ንግግራቸው እውነተኛ ነው፡፡ ሲበዛ ብልህ ናቸው፡፡ በጥልቀትና በተከታታይ ያስባሉ፡፡ ዝምታቸው ረጅም ነው፡፡ ሲናገሩ ንግግርን ይሞላሉ። በጥቂት ቃላት ብዙ መልእክት የማስተላለፍ ክህሎት ነበራቸው፡፡ የአላህ መልዕክተኛ የጐረቤትን ሐቅ በመጠበቅ በኩል በጣም ጉጉ ነበሩ፡፡ እንዲህ ሲሉም ተናግረዋል:- “ጅብሪል (ገብርኤል) ስለጐረቤት የውርስ ባለመብት ያደርገዋል ብዬ እስካስብ ድረስ ኑዛዜ አስተላለፈልኝ፡፡ የጐረቤት መብት መጋፋት በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ አጮልቆ ሚስጥሩን መመልከት፣ በምግብ ሽታ ማወክ፣ የማይወደውን ድርጊት መፈፀም፡፡” ይህም በመሆኑ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል:- “ከአላህ ዘንድ መልካሙ ባልንጀራ፤ ለባልንጀራው መልካም የሆነው ነው፡፡

መልካሙ ጐረቤት ለጐረቤቱ መልካም የሆነው ነው፡፡ (ተርሚዚኑ) የአላህ መልዕክተኛ እዝነት፤ ለጦር ምርኮኞች ሳይቀር ተትረፍርፎአል፡፡ የሙስአብ ቢን ዑመይር ወንድም አቡ ዐዚዝ እንዲህ ሲል አውግቷል፤ “ከበድር ምርኮኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ አስተላለፉ:- “ምርኮኞችን በበጐ ሁኔታ ትይዙ ዘንድ አደራ እላችኋለሁ፡፡” የአላህ መልዕክተኛ ከርሳቸው መምጣት በፊት በአለም ላይ ሰፍኖ የነበረውን የባርያ አሳዳሪ ስርዓት በሂደትና ደረጃ በደረጃ የማስወገድ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ሰዎች ባሮቻቸውን ነጻ ይለቁ ዘንድ በየአጋጣሚው ያበረታቱ ነበር፡፡ ባርያን ነጻ መልቀቅ ትልቅ ዒባዳ (አላህን መፍራት) መሆኑን አስተምረዋል፡፡ በመሆኑም የነብዩ የቅርብ ወዳጅ አቡበከር፤ አብዛኛውን ገንዘባቸውን ያዋሉት ባሮችን እየገዙ ነጻ ለመልቀቅ ተግባር ነበር፡፡ መዕሩር ቢን ሰወይድ እንዲህ ሲሉ አውግተዋል:- “አቡዘርን በረበዛህ ውስጥ አገኘኋቸው። የሚያምር ልብስ ለብሰዋል፡፡ አገልጋያቸውም ተመሳሳይ ልብስ ለብሰዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጠየቅኳቸው፡፡ ተከታዩን ነገሩኝ፡፡ “አንድን ሰው ተሳደብኩ፡፡ እናቱን አስነወርኩበት፡፡ ነብዩም እንዲህ አሉኝ፡፡ “አቡ ዘር ሆይ፤ እናቱን ማነወርህ ተገቢ አይደለም፡፡ የጀህልያ ቅሪት ያለብህ ሰው ነህ። አልጋዮቻችሁ ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡

አላህ ወንድሙን ከስሩ ያደረገለት ሰው ከሚመገበው ይመግበው፡፡ ከሚለብሰው ያልብሰው፡፡ የማይችሉትንም ስራ አትዘዟቸው፡፡ ካዘዛችኋቸውም እርዷቸው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም) በጀህሊያ ዘመን (በድንቁርና ዘመን) ሴቶች ክብር አልባ አያያዝ ይያዙ ነበር፡፡ የጀህሊያ ሰዎች ሴቶቻቸውን ያለርህራሄ ከነህይወታቸው ይቀብሩ ነበር፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚደርስባቸውን መነወርንና ውግዘትን በመፍራት ነበር፡፡ ከአለት የጠጠረ ልባቸው ይህን ወንጀል ምንም ሳይመስለው ይፈጽማል፡፡ እንስት ስትወለድ ይሰማቸው የነበረውን የሐፍረት ስሜት አላህ እንዲህ በማለት በቁርዓን ውስጥ ገልጾታል:- “ከእነርሱ መካከል አንዱ በሴት ልጅ በተሰበረ ጊዜ ፊቱ በሐዘን ይጠቁራል፤ ቅስሙ ይሰበራል (አል - ነህል 58) በጀህልያ ዘመን ሴቶች ደረጃቸው ዝቅ ብሎ፣ ክብራቸው ተነክቶ፣ የሴሰኝነት ፍላጐት መወጫ ብቻ ነበሩ፡፡ ነብዩ እንዲህ ብለዋል:- ጀነት (ገነት) ከእናቶች እግር ስር ትገኛለች (አልነሳኢ) የአላህ መልዕክተኛ በጉዞ ላይ ነበሩ፡፡ አንጀሿህ የተባለ አገልጋያቸው አብሯቸው ነበር። የአላህ መልዕክተኛ በግመሎቹ ላይ የተሳፈሩ ሴቶች እንዳይንገላቱ ስጋት ገባቸው፡፡ ስለዚህ አገልጋያቸውን እንዲህ አሉት:- “አንጀሻህ ሆይ፤ ረጋ በል፤ ለነዚህ ስስ ብርጭቆዎች እዘንላቸው (በኻሪና አህመድ) በሌላ ሐዲስ እንዲህ ብለዋል፡፡

“ከዱንያ ውስጥ ሁለት ነገሮች ከኔ ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እነርሱም ሴትና ሽቶ ናቸው፡፡ ሶላት የአይኔ ማረፊያ ተደርጋለች” (ነሣኢና አሕመድ) “ሶስት ሴት ልጆች ወይም ሶስት እህቶች እንደዚሁም ሁለት ሴት ልጆች ወይም ሁለት እህቶች ኖረውት ተንከባክቦ ያሳደጋቸው፣ በነርሱ ጉዳይም አላህን የፈራ ጀነትን ያገኛል” ያሉት እኝህ ታላቅ ነብይ ናቸው፡፡ (ቲርሚዙ አቡ ዳውድና አህመድ) “ሁለት ሴት ልጆችን ለአካለ መጠን እስኪደርሱ ድረስ ተንከባክቦ ያሳደገ፣ እኔና እርሱ ጀነት ውስጥ እንደዚህ እንሆናለን” ብለዋል ጣቶቻቸውን አጠጋግተው እያሳዩ (ሙስሊምና ተርሚዝያ) የጀህሊያ ሰዎች ለእንስሳት አያዝኑም ነበር። በመጥፎ አያያዝ ይይዟቸዋል፡፡እንስሳትን እርስ በእርስ እያዋጉ እና እያጋደሉ ይዝናናሉ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ይህንን ድርጊት በመቃወም ከለከሉ፡፡ አቡ ዋቂድ ለይሲ እንዲህ ሲል አውግቷል:- “የመዲና ሰዎች የግመል ሻኛና የፍየል ላት ይወዱ ነበር፡፡ ከነህይወታቸው እየቆረጡ ይመገብዋቸው ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ ግን ይህንን ድርጊት እንዲህ በማለት ከለከሉ:- “እንስሳት በህይወት እያሉ ከአካላቸው የሚቆረጥ ስጋ ሁሉ በክት ነው (ተርሚዝይ አህመድ) ጆቢር እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ ፊቱ የተጠበሰ አንድ አህያ ተመለከቱና እንዲህ አሉ:- “ይህን ድርጊት አልከለከልኳችሁም ነበርን? ይህን የፈጸመውን ሰው አላህ ረገመው፡፡” የአላህ መልዕክተኛ መካን ለመቆጣጠር አስር ሺህ ሰራዊት ይዘው በዘመቱ ጊዜ መንገድ ላይ አንዲት እናት ውሻ፤ ተንጋላ ልጆችዋን ስታጠባ ተመለከቱ፡፡

እርሷንም ሆነ ልጆችዋን ወታደሮች እንዳያውኳቸው ይከለከል ዘንድ አንድ ሶሐባቸውን (ባልደረባቸውን) አዘዙት፡፡ (አልዋቂዲ) “አንደበት በሌላቸው እንስሳዎች ጉዳይ አላህን ፍሩ፡፡ በመልካም አያያዝ ጋልቧቸው፡፡ በመልካም አያያዝም ተመገብዋቸው (አቡ ዳውድ) ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) ከማረፋቸው በፊት የተናገሩትን ንግግር ቀንጨብ አድርጌ አቀርበዋለሁ። እጀምረዋለሁ እንጂ አልጨርሰውም፡፡ ምክንያቱም በቂ ጊዜና ቦታ ስለሌለኝ፡፡ “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ ንግግሬን አድምጡ፡፡ በዚህ ቦታ በተከታዩ አመት በምንም መልኩ ላንገናኝ እንችላለን፡፡ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አላህን እስክታገኙ ድረስ ይህ ቀንና ወር ብሩክ እንደሆነ ሁሉ ደማችሁና ገንዘባችሁም የተከበረ ነው፡፡ ፈጣሪያችሁን መገናኘታችሁ አይቀርም፡፡ የሰራችሁትን ድፍረትም ይጠይቃችኋል፡፡ በበኩሌ መልክቴን አድርሻለሁ። አደራ ያለበት ሰው ለባለንብረቱ ይመልስ፡፡ ወለድ (አራጣ) ውድቅ ነው፡፡ ግና ዋናው ገንዘባችሁ ወረታችሁ የናንተው ነው፡፡ አትበደሉም፤ አትበድሉም” ነብዩ መሐመድ (ሰ.አ.ወ) ያረፉ እለት የቅርብ ባልደረባቸውና ከሳቸውም በኋላ ኻሊፋ ሆነው የተሾሙት አቡበከር አልሰደቅ፤ ሰውን ሁሉ ሰብስበው እውነተኛው ነብይ ህይወታቸውን በሙሉ ያስተማሩትን ትምህርት እንዲህ ሲሉ ደግመውታል። “እናንተ ሰዎች ሆይ፤ መሐመድን ታመልኩ ከነበር መሐመድ ይሄው ሞቷል፡፡ አላህን የምታመልኩ ከሆነ ግን እሱ አይሞትም፡፡ ዘላለማዊ ነው፡፡”

Read 2270 times