Sunday, 19 January 2014 00:00

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም የ50 ዓመታት ጉዞ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ሙዚየሙ ያለበት ግቢ በዲሞክራሲ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል”

ሰዓሊ ግርማ ቡልቲ እና ሰዓሊ ቅድስት ብርሃኔ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም አራት ስዕሎችን በስጦታ አበርክተዋል፡፡ በዕለቱ የሙዚየሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደገለፁት፤ ተቋሙ ባለፉት 50 ዓመታት ለባህላዊ ስዕሎች ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ ሥራዎችን ያሰባሰበ ሲሆን አሁን ደግሞ ዘመናዊ ስዕሎችን ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡ ስለ ሙዚየሙ አመሠራረትና የሥራ ሂደት የሙዚየሙ ኃላፊ ከሆኑት ከዶ/ር ሀሰን ሰኢድ ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አመሠራረት ታሪክ ምን ይመስላል? ሙዚየሙ እንዲቋቋም የመጀመሪያውን መሠረታዊ ሥራ የሰሩት የፖላንድ ተወላጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ናቸው፡፡ አይሁዳዊነት ስላላቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ካናዳ ሄደው በመማር ላይ ሳሉ ተጋብዘው ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡

ፕሮፌሰሩ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ላይብረሪ እንዲያደራጁ ተጋብዘው በመጡበት ወቅት፤ በ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ያዩዋቸው ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ክፍለ ሀገራትና ብሔረሰቦች የተውጣጡ መሆኑ አስገርሟቸው ስለነበር፣ ተማሪዎቹ ባህላቸውን የሚወክል ቁሳቁስ እንዲያመጡ እየጠየቁ ቅርስ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ በ1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም በ6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ግቢ ሲቋቋም ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ያሰባሰቧቸው ቅርሶች ወደዚህ መጡ፡፡ ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ኢትኖሎጂ ሶሳይቲ መስራችም ናቸው፡፡ የሶሳይቲውን ጆርናልም ያዘጋጁ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ሲሆኑ ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ ፀሐፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ተቋሙ በሁለቱ ሰዎች እየተመራ እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡ የተመሠረተበት ዓላማ ምን ነበር? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጥናት ርዕሰ ጉዳዩ በማድረግ ነው የተነሳው፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ጥናት ምንድን ነው? ብለው የሚጠይቁ ሰዎች አሉ። የተቋሙ መሥራቾች ሲጀምሩ እንዳመኑበትና ዛሬም ብዙዎቻችን እንደምንስማማበት ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የተለያየ ባሕልና አመለካከት ያላቸው ብሔረሰቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩበት አገር ናት፡፡ የዚህን ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት … ማጥናት ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ገናና ስልጣኔ ታይቶ የከሰመባት ምድር ናት፤ ይህ በራሱ ለጥናት ይጋብዛል፡፡

ልክ ሲሪዮሎጂ፣ ኤጀፕቶሎጂ እንደሚባለው የኢትዮጵያም ጥናት ያስፈልጋል በሚል ዓላማ ነው የተቋቋመው፡፡ ሙዚየሙ ምን ስብስቦችን ይዞ ነው ሥራ የጀመረው? የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ከተመሠረተ በኋላ እንቅስቃሴው ሁሉ እንደ ብሔራዊ ሙዚየም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ስታንስላቭ ሆይናይስኪ የማይሰበስቡት ነገር አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያን ይገልፃሉ የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ከመሰብሰብ ወደ ኋላ አላሉም ነበር፡፡ ቆርኪ፣ የመኪና ታርጋ ሁሉ ይሰበስቡ ነበር፡፡ ቅርስ ማሰባሰቡ በጀመረው መልኩ ነው የቀጠለው? የመጀመሪያው ቅርስ ማሰባሰብ ሥራ በፍላጎትና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ አሁን አኩዚሽን ፖሊሲ መከተል አስፈልጎናል፡፡ ሙዚየሙ 13 ሺህ የሚደርሱ ታሪካዊ ስብስቦች አሉት፡፡ የተበላሸ ቅርስ መጠገኛ ላቦራቶሪ ግን የለውም፡፡ በፖሊሲ መመራታችን የቅድመ አደጋ ጥንቃቄ ላይ በሚገባ እንድንሰራ ይረዳናል፡፡ ሁሉም ሙዚየሞች የሚመሩበት ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትና ዓላማ የሙዚዮሎጂ ኮርስ በዩኒቨርስቲው ግቢ ከ2006 እ.ኤ.አ ጀምሮ ማስተማር ስለጀመርን ትምህርቱን ያገኙ ባለሙያዎች በተለያዩ ሙዚየሞች በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሙዚየም ጥናት ኮርሱ ምን ላይ ያተኩራል? የሙዚየምን ሳይንስ ነው የምናስተምረው፡፡ አንድ ሙዚየም ጥራት ያለው ስብስብ እንዲኖረው ከተፈለገ የሚመራበት ፖሊሲ ያስፈልገዋል፡፡ ብሔራዊ የፖስታ ወይም የቡና ሙዚየም አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው ትኩረት ያደረጉት፡፡ ሙዚየሞች በማንኛውም አካል ሲቋቋሙ በምን ጉዳይ፣ ለምን ዓላማ … እንደሚቋቋሙ ግልጽ አድርገው እንዲነሱ የሙዚዮሎጂ ትምህርት ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ ሁሉንም አማረን ብሎ ማከማቸት ቅርስ መሰብሰብ ሳይሆን ማበላሸት ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሙዚየም ባለሙያ ጥንታዊ ቅርስ ስላገኘ ብቻ ወደ ሙዚየሙ ማስገባት የለበትም። ለቅርሱ ተገቢ የሆነ ማስቀመጫ አለኝ ወይ? ቅርሱ ቢበላሽ የሚጠገንበት ላቦራቶሪና ባለሙያ ይገኛል? ብሎ ቀድሞ ሳያስብበት ቅርሱን ሙዚየም ቢያስገባ ቅርሱ ተጠብቋል ማለት አይደለም፡፡ የሙዚዮሎጂ ጥናት በቅርስነት ተመዝግበው የተቀመጡትን ቅርሶች በልዩ ጥንቃቄ እንዲያዙ ያግዛል፣ በተቃራኒው ቅርስ ከማግበስበስ እንድንቆጠብም ይረዳናል፡፡

አሰራራችን ሳይንሳዊ ከሆነ የዲስፕሌይ መርህንም እንድንከተል ያስገድደናል፡፡ መርሁ መረጃ የሌለውን ቅርስ ለእይታ አታቅርብ ይላል። ለእይታ ባቀረብከው ነገር ልታስተምር ነውና ቅርሱ የማን እንደነበር፣ ከየት እንደተገኘ፣ ለምን አገልግሎት ይውል እንደነበር፣ መሠረታዊ ምላሾችን ሳታስቀምጥ አታወጣውም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቅርሱ ለእይታ ቢቀርብ ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ከሆነና የሥነ ጥበብ ዋጋና ደረጃውም ከተጎዳ ለእይታ እንዲቀርብ አይበረታታም፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም ቅርሶች ሁሉም መረጃ አላቸው? እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሙዚየሙ የማይሰበስበው ነገር አልነበረም፡፡ ከንጉሳዊያን ቤተሰብ፣ ከቤተክርስቲያናት፣ ትግራይና ጎጃምን ከመሳሰሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባህልና ቅርስን የሚያመለክቱ በርካታ ነገሮች ተሰብስበዋል፡፡ ቅርሶቹ ዝርዝር መረጃ ያላቸውም የሌላቸውም ይገኙበታል፡፡ የእኛ ሙዚየም ቤተ መንግሥት ሆኖ ያገለገለ ቤት በመሆኑ የተነሳ ከቤተመንግሥት የመጡ ስብስቦች አሉን፣ ግን ሙሉ መረጃ የሌላቸው ቅርሶችም አሉን፡፡

ይህ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ሰሀንን ሰሀን ከማለት ውጭ መቼ ተሰራ? ማን ነበር የሚገለገልበት? ከየት አገር ተሰርቶ መጣ? በግዢ ነው በስጦታ የተገኘው? … ለሚለው ጥያቄ መረጃ የሌላቸው አልባሳት፣ ቦርሳዎች፣ ጫማዎች … አሉ፡፡ የመረጃ እጥረቱን ለመሙላት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ከላይ እንዳልኩት የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ፍቅር ባሳደረባቸው ሰዎች ስለነበር፤ ያንን መነሻ በማድረግ ያለ ገደብና ምርጫ ብዙ ነገር ሰብስቧል። የአፄ ኃይለሥላሴና የቤተሰባቸው መገልገያዎች፣ የከፋው ንጉሥ ባህላዊ ዘውድ፣ አርበኞች ተገልግለውበታል የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች … የመሳሰሉ በርካታና የተለያዩ ስብስቦች ይገኛሉ። ቅርሶቹ በዚያን ዘመን በዚህ መልኩ ባይሰባሰቡ የመሰረቅና የመጥፋት አደጋ ሊያገኛቸው ይችል ነበር፡፡ ይህ በጥሩ ጎኑ ቢነሳም የቤተመንግሥቱ፣ የሕብረተሰቡ፣ የጦር ሚኒስትሩ፣ የየክፍለ ሀገሩ … ቅርሶች ራሳቸውን በቻሉ ተቋማት አለመሰብሰባቸው የመረጃ እጥረት አስከትሏል፡፡ እንዲህም ሆኖ 13ሺውንም ቅርሶች የመዘገብንበት አክሴሽን ካርድ አለ፡፡ አንድ ሰው ጤና ጣቢያ ሲሄድ እንደሚሰጠው ካርድ እያንዳንዱ ቅርስም የራሱ የሆነ መለያ ቁጥር ያለው ካርድ አለ፡፡ የቅርሱ ሥም፣ የተሰራበት ቦታ፣ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት፣ የተገኘበት አካባቢ፣ ውፍረቱ፣ ቅጥነቱ፣ ክብደቱ፣ የደህንነት ደረጃውና ፎቶውን ጭምር ይዟል፡፡ በካርድ ብቻ ሳይሆን በካታሎግ የተመዘገቡ ቅርሶችም አሉ፡፡ የሙዚየሙ ዋነኛ ተግባርም የቅርሶቹን መረጃ ማሟላት፣ መጠበቅ፣ ማናፈስ፣ ቀጣይ ዕድሜያቸው የሚረዝምበትን አሰራር መከተል፣ ለጥፋትና ስርቆት እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ለጥናትና ምርምር ምቹ እንዲሆኑ ማመቻቸትና ሥነ ጥበባዊ ዋጋቸውን መጠበቅ ነው፡፡

የሙዚየሙ አደረጃጀት ምን ይመስላል? ሙዚየሙ ያለበት ግቢ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ግቢው ከቤተ መንግሥት ወደ ዩኒቨርስቲ የተለወጠበትንና ዩኒቨርስቲ ከሆነ በኋላ በአገር ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሂደቶችን በማሳየት ነው የሙዚየሙ አደረጃጀት የተዋቀረው፡፡ በመቀጠል ከልጅነት እስከ ሞት የሚል ክፍል አለ፡፡ በዚህ ውስጥ የልጆች ጨዋታ፣ ትምህርት፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሞትና ሐውልቶችን ማሳያዎች አሉ፡፡ የንጉሱና የእቴጌይቱ እልፍኝ ሌላው ክፍል ነው፡፡ ለጥናትና ምርምር የሚረዱ በርካታ ስብስቦች ያሉበት ይህ ክፍል፣ ከአፄ ምኒልክ ጊዜ ጀምሮ በአገራችን የታተሙ ቴምብሮች ይገኙበታል፡፡ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ክፍል ሌላኛው አደረጃጀት ነው፡፡ የክር፣ የትንፋሽ፣ የምት … ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ይገኙበታል፡፡ የሙዚየሙ ሌላኛው አካል አርት ጋለሪው ሲሆን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክን መሠረት ያደረጉ ስዕሎች አሉበት፡፡ የመስቀል ስብስቦች ሌላኛው የሙዚየሙ አካል ነው፡፡

በንጉሡና በእቴጌይቱ መኝታ ክፍል ስላሉት አልባሳት ምን መረጃ አላችሁ? የንጉሥ ኃይለሥላሴና የእቴጌ መነን አልባሳት መሆናቸውን እርግጠኛ የሆንባቸው ስብስቦች አሉን፡፡ ማን ይገለገልባቸው እንደነበረ ባይታወቅም ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች፣ ሊቀመኳስ … መሰል ማዕረግ አመልካች አልባሳትም አሉ፡፡ በአልባሳቱ ላይ የሚታዩት የሙካሽ ሥራ፣ የብረታ ብረት ጌጦችና ፈርጦች ምንነት የተጠኑም ያልተጠኑም ይገኙበታል። በሙካሽ የሚገለጽ የማዕረግ ዓይነት፣ ሙካሽ የት ይሰራ እንደነበር፣ ማቴሪያሉ ከየት እንደሚመጣ፣ የሙካሽ ሥራ ዕውቀት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደጀመረ … የመመረቂያ ጽሑፍ ተሰርቶበታል። እኛም ጥናቱን ኮፒ አድርገን የሙዚየማችን አካል አድርገነዋል፡፡ በአልባሳቱ ላይ የሚገኙት የብረታ ብረት ጌጣ ጌጦች “ጋሻ ጉብ ጉብ” የሚባለው ቅርጽ ያላቸውና ከአንድ ወርክ ሾፕ የወጡ መሆኑን አስረግጦ መናገር የሚቻል የጥበብ ሥራ ናቸው፡፡ የት ይሰሩ እንደነበር፣ ከምን ማዕድናት እንደተሰሩ ገና መጠናት ያለበት ነው፡፡ ከአልባሳቱ ቁልፎች ጋር በተያያዘ የተሰራ ምንም ጥናት የለም፡፡ አንጥረኝነትን የምናደንቅበት አቅም ስላልነበረን ዛሬ ላለብን የመረጃ እጥረት አንዱ ምክንያት ሆኗል እንጂ፤ ኢትዮጵያዊያኑ አንጥረኞች “ቡዳ” እየተባሉም ቢሆን ብዙ ነገር መሥራታቸውን የሚያሳዩ በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ ሙዚየሙ የታዋቂ ሰዎችን አልባሳትና የግል መገልገያ ቁሳቁስ እየተቀበለ ማስቀመጡን ቀጥሎበታል፡፡

ይህ አሰራር ሙዚየሞች በተወሰነ ነገር ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው ከሚለው ጋር አይጋጭም ? አሁን እየሰበሰብን ያለውን ብቻ ሳይሆን 13ሺውንም ስብስቦች በፊት ከሚገኙበት በተሻለ ሁኔታ በየርዕሰ ጉዳዩ ከፋፍለን በመመደብ ለእይታ የማቅረብ እቅድ አለን፡፡ የዩኒቨርስቲው አዲሱ የአስተዳደር ሕንፃ ግንባታው አልቆ ሥራ ሲጀምር፣ በመኮንን አዳራሽ ያሉ በርካታ ክፍሎች ስለሚለቀቁ፣ እነዚህን የሙዚየሙ አካል የማድረግ እቅድ አለ፡፡ በእቅዳችን መሠረት ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም የሕፃናት ክፍል ከነመዝናኛው፣ የአርበኞች ክፍል፣ የደራሲያን ክፍል፣ የባህላዊ ሸክላ ሥራና የአንጥረኞች ክፍል፣ የዘመናዊ ሰዓሊያን ክፍል ይኖሩታል፡፡ ይህንን እቅድና ዓላማ ምክንያት በማድረግም የተለያዩ የአርበኛ፣ የሚሊተሪና ታዋቂ ሰዎች ታሪካዊ ስብስቦችን ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለን አስቀምጠናል፡፡

እነዚህ ስብስቦች ሙሉ መረጃ ያላቸው ናቸው። በዚህ መልኩ የታዋቂ ሰዎችን አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስ፣ መፃሕፍት ከሰጡን መሐል የፀጋዬ ገ/መድህን፣ የመንግሥቱ ለማ፣ የከበደ ሚካኤል፣ የሀዲስ አለማየሁ፣ የማሞ ውድነህ፣ የጳውሎስ ኞኞ ቤተሰቦች ይገኙበታል፡፡ በመጨረሻ የሚያነሱት ነገር ካለ … ሙዚየሞችን በተመለከተ በአገራችን መስተካከል ያለባቸው ብዙ አሰራሮች አሉ፡፡ አገራችን የሙዚየሞች ዓለም አቀፍ ስምምነትን በ1978 ዓ.ም ፈርማለች፡፡ ስምምነቱ ቅርሶች ወደተገኙበት ምንጭ እንዲመለሱ ያሳስባል፡፡ በውጭ አገራት ያሉ ቅርሶቻችን እንዲመለሱልን የምንጠይቀው በዚህ ምክንያት ነው። ስምምነቱ በአገር ውስጥም ከመገኛቸው ርቀው የሚገኙት ወደ ነበሩበት ይመለሱ ስለሚል በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራ መስራት ያለብን ይመስለኛል፡፡

Read 3066 times