Saturday, 18 January 2014 12:08

ግጥሞቻችንን እንዴት እንታደጋቸው?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

“ግጥም እግሮቹ ሳይጠኑ ወረቀት ላይ አይራመድ”

ስለዘመናችን ስናስብ፣ ዘመኑ ስላበቀላቸው ግጥሞች ስናሰላስል ሣቅ ይርቀናል፣አይናችን እንባ ያቀርራል፡፡ ግጥም ታላቅ ጥበብ መሆኑን ታላላቅ የዓለማችን ጠቢባን በብርቱ ብዕራቸው ድርሣን ሞልተው ቢያልፉም ብዙዎች ግን እንደፌንጣ እየዘለሉ አጉድፈውታል፡፡ በኛ ሀገር የግጥም ነገር መላቅጡን እያጣ መምጣቱን ደጋግሜ መለፈፌ ይታወቃል፡፡ “ግጥም ሞቷል” ብሎ አንድ የተባ ብዕር ያለው ጋዜጠኛ ከጻፈ በኋላ፣ ነገሩ እውነት እየሆነ መምጣቱ ሲገርመን አሁን ደግሞ አስከሬኑን ለመጎተት ልባቸው የጠና ምድሩን ሞልተውት እያየን ነው፡፡ ለአቅመ ንባብ ያልበቁትን ግጥሞች በወረቀት ገንዘው ሲያቀርቡ፣ በየአዳራሹ ውስጥ ለማስመረቅ ሳይሆን ለማስቀበር እንደነፍስ አባት ለፍትሀት የሚወዛወዙ ከየሙያው ዘርፉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲዋ መምህርት ሊዎራሮ ስፔየር፤ ግጥም እግሮቹ ሣይጠኑ ወረቀት ላይ አይራመድ ትላለች፡፡ ታላቁ የግጥም ምሁርና ተመራማሪ ሂሊየር ደግሞ ግጥማችሁን ደጋግማችሁ አብስሉት ይላል፡፡ እንግሊዛዊው ገጣሚና የዩኒቨርስቲ ምሁር ሮበርት ፍሮስትም፤ “ግጥም በዘይቤያዊ ቃላት ካልተከሸነ አይን አይገባም፤ ልብም አይደርስ” ይላል፡፡

የእኛ ሀገር ዋና ዋና ችግሮች አሁን የተጠቀሱት ይመስሉኛል፡፡ ጥሩ የምንላቸው እንኳ ዘመን የማይሻገሩ፣ ፈንጠዝያ ፈጣሪ የምጣድ ላይ ተልባዎች ሆነዋል፡፡ አንዴ ዘልለው መሬት የሚቀሩም አሉ። አንዳንዶቹም አክንባሎ እንዳልተከደነ እንጀራ መስለው አይን አውጥተው አይን ሳይጠቅሱ የሚቀሩ እንጥልጥሎች ሆነዋል፡፡ ለዚሁ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ደግሞ የእኛ ግብዝነትና አስመሳይነት ይመስለኛል፡፡ የግጥሙንና የገጣሚውን ትክክለኛ አቅምና ብቃት ከመናገር ይልቅ ተለሳልሰን ርካሽ ውዴታና ውዳሴ መቀበል እንመርጣለን፡፡ እጅግ የምወዳቸውና የማከብራቸው የግጥም ጓዳ ፈታሽ ለውረንስ ፔረኒ ግን በዓለማችን ላይ ማን በየትኛው ደረጃ እንደሚቀመጥ በስም ለይተው እስከ መጻፍ ደፍረዋል፡፡ ሂሊየርም ቢሆኑ ሎንግፌሎውን ሲያደንቁ፣ ዲከንሰንን ሲያወድሱ፣ አላንፖን ሲገመግሙ ድክመቱን እየጠቆሙ ነው - መረጃ እየጠቀሱ፡፡ ለምሣሌ የአሜሪካን የ19ኛው ክፍለ ዘመን አራት ምርጥ ገጣሚያን ይደረድሩና አንዱ ግን ወደ ሃያኛው ክፍለ ዘመን መሻገር እንዳቃተው ይጠቁማሉ - ያውም ኤመርሰንን! እኛ ግን ለዚህ አልታደልንም፣ እየዋሸን፣ እያስመሠልን የሀገራችንን ጥበብ እንቀጫለን። ለዚያውም አስተያየት ስንሰጥ “በኔ አመለካከት” እያልን ነው፡፡ የእኛ አመለካከት ስሜት ነው። ለራሳችን ማጣጣሚያ ብቻ የሚሆን ነው። ስለ ግጥም የተጻፉ በርካታ መጽሐፈት እያሉ፣ ለምን በስሜት መዳኘትና ማሣሣት እንዳማረን ባላውቅም፣ አዝናለሁ! ….ፍቅር ካለን በቅጡ መገምገም ነው፡፡

ለምሣሌ ባለፈው ሰሞን አንድ ነጋዴና ሌላ አትሌት የግጥም መጽሐፍ ላይ አስተያየት እንደሰጡ ጠቁሜ ነበር፡፡ ጥፋቱ ግን የነርሱ አይደለም፡፡ የአስተያየት ጠያቂዎቹ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ከየትኛውም የጥበብ ዘርፍ በእኛ አገር ሁሉም ተነስቶ እንደፈለገ የሚፈነጭበት የግጥም ሠፈር ብቻ ነው፡፡ በተለይ አጫጭር ግጥም የሚለውን ሰበብ ተጠቅሞ እንደልቡ ያልሆነበት የለም፡፡ አንብበናል የሚሉትን ሰዎች እንጀራቸውን ሲያሣድዱ ጥበቡ ገደል ይገባ ብለው ትተውት “ሃይ!” የሚል ጠፍቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በጓደኝነትና በቡድን የማይረባውን ሥራ ከፍ ከፍ ለማድረግ ሲሞክር ይታያል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ካነበብኳቸው የግጥም መጽሐፍት ሁለንተናዊ የግጥም አላባውያንን ያሟሉና ብቃት ያላቸው መጽሐፍ አሥር እንኳ አይሞሉም፡፡ አንዳንዶቹ ለጊዜው ቢጣፍጡም እንደእለት መና ለአንድ ቀን ጣፍጠው በማግስቱ ትዝ የማይሉና የሚረሱ ናቸው። ምናልባት በቋንቋ ልቀትና በአሠኛኘት፣ በሥርዐተ-ነጥብ፣ በዜማና ምት ከፍ ያሉ ናቸው የምንላቸው የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ የታገል ሰይፉ (የመጨረሻ መጽሐፍ) የዮሐንስ ሞላ ጥቂቱ ናቸው። ለምሣሌ በቅርብ ከታተሙት “ቀብድ የበላች ሀገር” በቋንቋው የተሻለ ስፍራ የያዘ ነው። እንደዚሁ የላቀ ሃሣብ ይዘው እንደ ዱባ ሀረግ ሃሣብ መሸከም የሚችል ቃላት አጥተው መሬት ለመሬት የሚሳቡም አሉ፡፡ ሰሞኑን ከታተሙት የግጥም መፃሕፍት… የገጣሚ አብርሃም ስዩም መድበል ጥሩ አተያይ፣ ሩቅ ያለ ሕልም በውስጧ ይዛለች ለማለት ያስደፍራል፡፡

ደግሞ በሌላ በኩል የዜማ ስብራት፣ የአሠኛኘት ልልነት ይታይባታል… ቢሆንም ብሩህ ተስፋ ያረገዘች መፅሃፍ ናት፡፡ እስቲ ጥቂት ግጥሞች እንይ… መርሺያ የለኝምና! እርሽኝ አታስታውሽኝ እስከ መፈጠሬ! እርሳኝ ግን አትበይኝ እባክሽን ፍቅሬ! ይህች “መንቶ” ግጥም ትልቅ ሃሣብ፣ ጥልቅ ስሜት ተሸክማለች፡፡ ግዙፍም ናት፡፡ “ያገር ነሽ!” በሚል ስንኝ የተቋጠረለትን ግጥም ደግሞ እንያት፡፡ የሕዝብ ቅኝት ናት የሕዝብ ሁሉ ዜማ፣ የኔ ነሽ አይሆን መቼም ቢሆን ስሟ! እንደባቲ ቅኝት ደግሞ እንደ ትዝታ ማንም ይቃኛታል ሲመሽ ወደ ማታ! ትራፊክ የለበት መንገድ ሚቆጣጠር ፈቃድ አይጠይቅም እሷን ለመዘወር ልቤን ወስዳው ነበር ድንገት እንዳየኋት ያገር ብትሆንብኝ አፍቅሬ ሸሸኋት!! ይህች ግጥም በጭብጥዋ የዘመናችን ችግር ናት፡፡ አንድ ሰው ልቡን ስንት ቦታ እንደሚቸረችር መቁጠር ያዳግታል፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ሴቶች ይወራል እንጂ የወንዱ ይብሣል፣ ባህላችን ግን ብልግናን ለወንድ የፈቀደ ስለሆነ ሴቶች ላይ ጥቂቱ ይገዝፋል። ይህንን አሮጌ ባህል መዋጋትና ማስወገድ የጥበቡ ዓለም ሰዎች ይመስለኛል፡፡ “አንድ እኩል” የሚለው ግጥምም እንዲህ ይላል፡- በሎሚ ጋጋታ … አነጣጠርኩና ደረቷን ብመታ፣ እኔም አላመለጥኩ ደረቴ ተመታ፣ ከባሏ ጠመንጃ በተሳበ ቃታ!! ሃሣቡ ጥሩ፣ አተያዩ የተለየ ነበር፡፡

ግን ቤት መምቻውና መድፊያው ሥሩ አንድ ግስ ነው፡፡ ሀብትን ማን ይጠላል? የሚለው ግጥም፡- ያማረ መኝታ የተንደላቀቀ የማይቆጠር ሃብት ስፍሩ ያልታወቀ ጮማና ወይን ጠጅ እንኳንስ ቀምሰውት ሲያዩት የሚያስጐመጅ ይህን ሁሉ ሰጥቶ ፍላጐት ከማጣ ቁርበት የለበሰ የጭቃ መደብ ላይ ድንጋይ ተንተርሼ ጣሪያ ሆኖኝ ሰማይ አንድ ቅርጫት ሙሉ ቦሎቄ ከክቼ እየፈሳሁ ልደር ጧ ብዬ ተኝቼ ግጥሙ እርካታ በገንዘብና ምቾት እንደማይገኙ ይተርካል፡፡ በቁሳዊ ነገር ጥሩ እንቅልፍ፣ ዘንባባ የተጐዘጐዘበት ሕይወት እንደማይመጣ ያሣያል። ርዕሰ ጉዳዩ የዘመኑ የሥነ ልቡና ምሁራን መከራከራያና ጥያቄም ነው፡፡ አብርሃም ጥሩ አይቶታል፣…. ቤት ለመምታት ሲል ግን አራተኛውን ስንኝ ለጥጦ ውበት አሣጥቶታል እንጂ፡፡ የአብርሃም ግጥሞችን ስቃኝ አርታኢ ቢኖረው ኖሮ ያሰኙኝ ግጥሞች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ግጥሙን ያነበበለትና አስተያየት የሰጠው አርቲስት “ስሞት አትቅበሪኝ” ከሚለው ግጥም ላይ የመጨረሻዎቹን ስድስት ስንኞች ማስወገድ ነበረበት፡፡ ግጥሙን ከወገብ በላይ ጠንካራ፣ ከወገብ በታች እግሮቹን የሚጐትት ሽባ አድርጐታል፡፡ ይልቅ፡- ተስማሚ በቃሌ ፍቅሬ እሺ በይኛ፣ ሞቼም አልለይሽ አብሬሽ ልተኛ --- ብሎ ቢያቆም ሙሉና የፈረጠመ ውበት በነበረው፡፡ የዘመን ጣር የሚለው ግጥር ላይ ጳጉሜን “ዘመን” ብሎ በዚያው አንድ መስመር “ዘመናት” ሲል የሁለትዮሹን ሥብራት ማቅናት ይቻል ነበር፡፡

ገጽ 8 ላይ ያለው “ነበር” በሚል ርዕስ የተጻፈ ግጥም፣ ከሠናይት አበራ “የጨረቃ ሳቆች” መድበል ገጽ 15 ላይ ካለው “እባብ የሞት ምግብ” ጋር ተመሳሳይነቱን ልብ ይሏል፡፡ እስቲ እናስተያያቸው፡- እባብ የሞት ምግብ አዳምና ሄዋን ቻይናዊ በሆኑ የሩቅ ምስራቅ ሰዎች ጃፓን በነበሩ ይቺን ፍሬ ብሏት ብሎ የነገራት ይሆን ነበር ሾርባ ከእፀበለስ በፊት፡፡ ይህ ግጥም በ1996 ዓ.ም የታተመ ነው፡፡ “ነበር” ሕንዳዊ ነው አዳም አባቴ! ማለቴ፤ አዳም ቻይናዊ ሆኖ ቢፈጠር በለሱን ትቶ እባቡን ከትፎ ይበላው ነበር፡፡ ይህ መመሣሠል አንዳንዴ ሣይታወቅ፣ በአአምሮ ውስጥ ቆይቶ ከራስ ሃሣብ ጋር ሊፈስ ስለሚችል ያጋጥማል ብሎ መጠበቅ ይቻላል፡፡ ግን ይህንን አርታኢ ሊያስታውሰውና ሊያቀናው ይችላል፡፡ ግን በአጠቃላይ ግጥም፣ የብዙ ነገሮች ቅንብርና የብዙ መዋቅር ውጤት እንጂ እንደ ኦ ሔነሪ ልቦለዶች ያልታሰቡ ነገሮችን ብቅ ማድረግ ብቻ አይደለም። የላቀ ቋንቋ ለግጥም የግድ ነው። እንደፍጥርጥሩ ካላልን በስተቀር ኦና ቃላትን መደርደር ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው የአብርሃም ስዩም “ወደ ብርሃን የተሰኘ” መጽሐፍ ግን ብዙ ውበት፣ ጥሩ አተያይ የተስተዋለበት ነው፡፡ የአሠኛኘት ጥንካሬ ለማግኘት ግን ንባብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እጅግ ለተሻለ ሥራ የሚጠበቅ ወጣት መሆኑን ከሥራዎቹ ማየት ይቻላል፡፡ ግን ሳያነቡ መጻፍ በጐ አይመስለኝም፡፡ አቅምን በንባብ ማገዝ ለሁሉም ወጣት ገጣሚያን ፍቱን መድሃኒት ነው። የግጥማችንን ሬሳ ከመጐተት ያድናልና፡፡ አብርሃም በርታ…. ጥሩ ሃሣብ፣ጥሩ ድፍረት ይዘሃል፡፡

የፍልስፍና ጥያቄዎችህም የሚያመራምሩ ናቸው፡፡ ሌላው በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለው መጽሐፍ የቴዎድሮስ ሞገስ “የኔው እኔ” የተባሉ የግጥሞችና ጭውውቶች መድበል ነው፡፡ መጽሐፉ ፀሐፌ ተውኔት ኃይሉ ፀጋዬ የጀርባ አስተያየት ሰጥቶበታል። መድበሉ በአሠኛኘትና በዜማና ምት ጣዕም ፈቀቅ ያሉ ግጥሞችን ያካተተ ነው፡፡ እንደጉሽ ጠላ እንትፍትፍ የሚያሰኙ ግሣንግሶች የሉበትም። ጥቂት ቢሆኑም ጥልል ያሉ ግጥሞች ይዟል፡፡ ለምሣሌ “ጥበብ” የሚለው ግጥሙን እንይ፡- ውርጭ የመታው ጥጥ ፈርቅጠው በወጥ አባዝተውት በቅጥ በብሳና ደጋን ብን አርገው ሳይነድፉት፣ በ ከማን አንሼ እኔ ከማን ብሼ ከእነ እድፍ ጉድፍ አሸምነው ጥበብ ጥልፍ ቢያስጠልፉት፣ እንኳን ልብ ሰርቆ ስም በሩቅ ሊያስጠራ ቢለብሱትም አይሞቅ ቢያጥቡትም አይጠራ፡፡ ጥበብን ትንሽ ለየት ባለና ከሀገራችን የሸማ ሥራ ጥበብ ጋር አዛምዶ ወይም አነጻጽሮ ተምሣሌታዊ በሆነ መንገድ አቅርቦታል፡፡ የነቶሎ ቶሎ ቤት ካደረጉት ደግመው ሊያበጁት አይችሉም፡፡ ሊያቀኑት አይቀልልም ይላሉ፡፡ “እንኳን ትርፍ ሊያገኝ” የሚለው ግጥም እንዲህ ተጽፏል፡- እንደ ዕድሉ እንደገዱ ጠመመም ተቃና የሕይወት መንገዱ እንደተጻፈለት መኖር ላይቀርለት ቅናት ሎሌው አርጐት አጉል ሲያቀናጣው እንኳን ትርፍ ሊያገኝ ያለውን ሊያሳጣው አምጦ ላይወልደው ወይ ነጥቆ ላይወስደው የባልንጀራውን አጥብቆ አስወደደው፡፡

የተሻለ ርዕስ ሊመርጥለት ሲችል ለምን ይህን እንዳደረገው ባይገባኝም፣ ቅናትን ትርፍ የለሽ አድርጐ የሚጐሽም ግጥም ነው፡፡ የጠለቀ ሃሣብ የተደበቀ ዓይን የለውም፣ ያው በኛው አይን ነው ያየው፡፡ ገጣሚ ግን የማይታይ አይን አለው ብለን እናምናለን፡፡ ሌላው “የእኔው እኔ” መድበል ግጥሞች ፀባይ ባብዛኛው የግጥሙ ተራኪ ተቺ መሆኑ ነው- አውጋዥ ነው፡፡ “ሰው መሳይ” እንዲህ ይላል፡- ሰው ሲል የሰማውን ደጋግሞ ዘማሪ ልብስ ተማሪ በቁም ከፈን እንደቃሪያ ተሰንጐ ሳመኝ ስሙኝ ይላል ሰው መሳይ በሸንጐ “ቅቤ እንኳንስ ሆዱን” የሚለውም ግጥም ተራኪው ሌላኛውን ወገን የሚተችበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከላይ እንዳልኩት ጥሩ የተገመዱ ሰንኞች አሉት፣ ሀዲዱ ግን በአብዛኛው ወደ አንድ አቅጣጫ ያመራል፡፡ ቋንቋው የላቀ ባይባልም አሁን ከምናያቸው አብዛኞቹ ግጥሞች የተሻለ ነው፡፡ የሃሣብ ልቀት ግን ያንሰዋል፡፡ ቢሆንም አንዴ ተነብቦ የሚጣል አይደለም፡፡ ጥሩ ነገሮች አሉት፡፡

Read 2586 times