Saturday, 18 January 2014 12:08

አዲስ አባ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ቀለበት አስሮ እንደያዘው
እንደደለለው ጋብቻ
ግብሩን ከቶ ሳላገኘው
ተጃጅዬ በስም ብቻ
በምኞት ህልም
በአጉል ተስፋ
እስትንፋሴ እየራቀ
አኗኗሬ እየከፋ
ውስጤ ላዬ እያደፈ
ብዙ አበቅቴ ተታለፈ፤
ቱር…ሳልል ብርር ….ሳልል
እዚህ እዚያ ሳላዳርስ
ጭብጥ ጥሬ እንኳ ይዤ
ባልጠግበውም ላመል ሳልቀምስ
ባይሞቀኝም እንዳይበርደኝ
ጐጆ ይዤ ጭስ ሳላጨስ
“እልፍ ካሉ - እ - ልፍ” እንዲሉ
ዞር ማለቱን ሰንፌ
እንዳኖሩት ግዑዝ ድንጋይ
ቀረሁብሽ ተወዝፌ፤
ውሃ እንደተጠማ ኩታ
ልዋጭ እንደሌለው ጨርቅ
ገምቼ ገልምቼ ስቼ
ከእድፌ ጋር ስጨቃጨቅ
ስትገፊኝ እምቢኝ እያልኩ .
ዛሬም አለሁ አንቺን ሳለቅ፤
አዲስ አባ
ውሃሽ በመዘውር አልፎ
ዙሪያ ገባሽን ቢሞላ
ለኔ በባሊ ነፍጐ
ለረጠበው እያደላ
“ዝናብ ቢዘንብ በባህሩ…”
ብሎ እንዳለው መምህሩ
ገበሬ እንኳ ዓመት ለፍቶ
ለጐተራሽ ቢዘረግፍ
እጀ ረጅሙ ደርሶ
አግበስብሶ ነው… እሚልፍ
እናም አዋጅ ልንገር ጐረቤት ሁሉ ይስማ
ርስቴን ለቀቅሁ ወጣሁ ወደ ሌላ ከተማ፡፡
አውላቸው ለማ   

Read 3430 times