Saturday, 18 January 2014 11:53

የአውራው ፓርቲ “ብዥታዎች” በዝተዋል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(22 votes)

የኒዮሊበራሊዝም ኃይሎች በአሸባሪነት ተፈርጀዋል እንዴ?
የኢኮኖሚ ዕድገቱን መካድ “ከሃዲነት” ነው!
“የመንግስት ሚዲያዎች በባህርያቸው የአውራው ፓርቲ ልሳን ሆነዋል”

<እውነቱን ለመናገር በአሁኑ ወቅት “ማጥራት” የሚፈልጉ “ብዥታዎች” እንደ ጉድ ተበራክተዋል (የቃላቱ ኮፒራይት የኢህአዴግ መሆኑ ልብ ይባልልኝ!) እናላችሁ ….. የዛሬ ፖለቲካዊ ወጌ በእነዚህ “ብዥታዎች” ዙርያ ያጠነጥናል፡፡ (ብዥታዎች ሳይጠሩ ልማትም ዲሞክራሲም ቅዠት ነው!) በነገራችሁ ላይ… ያለማንም ስፖንሰርሺፕ ባካሄድኩት መጠነኛ ጥናት፤ ብዥታዎቹ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ሳይል በሁሉም ላይ የሚታዩ መሆናቸውን ያረጋገጥኩ ሲሆን ብዥታዎቹን በመፍጠር ረገድ ግን አውራው ፓርቲና የመንግስት ሚዲያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ (የእኔ ሳይሆን የጥናቱ ውጤት ነው!) አሁን በቀጥታ ወደ “ብዥታዎቹ” እንግባ፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ ሰማያዊ ፓርቲ “የምናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥልኝ አልፈቅድም” ማለቱን አንብቤ ቆራጥነቱን አድንቄለታለሁ፡፡ እዚሁ ቆራጥነት ውስጥ ግን ያሸመቀ “ብዥታ” አስተውያለሁ። ብዥታውን የፈጠረው ኢህአዴግ ቢሆንም። ነገርዬው…. ኢቴቪ በቅርቡ ካስተላለፈው የሽብርተኝነት ዶክመንተሪ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው ተብሏል፡፡ /ፓርቲው ነው ያለው!/ እኔ የምለው ግን …ኢቴቪ በቅርቡ ለግሉ ሴክተር ያቀረበውን “ዶክመንተሪ ፊልሞች በጋራ እንስራ” የሚል ፕሮፖዛል ወይም የግብዣ ጥሪ ሰምታችኋል? (አቅሙና ፍላጐቱ ያላችሁ እንዳያመልጣችሁ ብዬ ነው!) ግን የ“ሰው ለሰው” ዓይነት ድራማ እንዳይመስላችሁ፡፡

በአብዛኛው ለውዝግብና ለፍ/ቤት ማስረጃነት የሚቀርቡ ዶክመንተሪ ፊልሞች ናቸው፡፡ (ማዝናናትና ትግል ለየቅል ናቸው!) እኔ መጀመሪያ ግብዣውን እንደሰማሁ “አደጋ አለው!” ብዬ ነበር፡፡ በኋላ ረጋ ብዬ ሳስበው ግን የወደደ የሚገባበት ስለሆነ ችግር የለውም ብዬ ተፅናናሁ፡፡ (የቱ ነበር ክስ የቀረበበት ዶክመንታሪ?) ለዚህ ነው መሰለኝ የኢቴቪን ግብዣ እንደሰማሁ “አደጋ አለው!” ያልኩት፡፡ ያለዚያማ ኢቴቪ ያለበትን የአቅም ውሱንነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ ከግል ሴክተሩ ጋር ለመስራት ያቀረበው ሃሳብ ወርቅ እኮ ነው፡፡ (ኧረ እንደውም ዘግይቷል!) እዚህ ጋ ግን አንዲት “ብዥታ” ጥርተን ማለፍ ይኖርብናል፡፡ ዶክመንታሪውን ከኢቴቪ ጋር ለመስራት የኢህአዴግ ደጋፊ፣ አባል፣ ምናምን መሆን ያስፈልጋል እንዴ? (መጥራት ያለበት “ብዥታ” ስለሆነ ነው!) አያችሁ …. ብዙዎቹ የኢቴቪ ዶክመንታሪዎች የአውራውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ውሣኔና አቋምን የሚያንፀባርቁ ስለሆኑ አውቀን እንድንገባበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ …. ኢቴቪ በሚዲያ ዳሰሳ ፕሮግራሙ የግሉን ፕሬስ ጋዜጠኞች እየጋበዘ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማወያየቱን ወድጄለታለሁ፡፡

(ከመራራቅ መቀራረብ፣ ከመነቃቀፍ መወያየት ይሻላል!) አያችሁ…የእኔን ነገር! ሳላውቀው እኮ ሌላ አጀንዳ ውስጥ ራሴን ዶልኩት፡፡ (የእኛው ጉዳይ ስለሆነ አትታዘቡኝ!) ሰማያዊ ፓርቲ “የምናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥልኝ አልፈቅድም” ብሏል ብዬ ነበር - ባለፈው ሳምንት። ፓርቲው ይሄን ያለው በኢቴቪ በቀረበው ዶክመንታሪ ላይ ከ “ኢሳት” ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ጠቅሶ ነው። ማስጠንቀቂያው የመንግስት ባለስልጣኖችን ዝም ብሎ ማለፉ ያስቆጣው ይመስላል - ፓርቲው፡፡ (“የመንግስት ባለስልጣኖችም ለኢሳት ቃለምልልስ ሰጥተዋል” ባይ ነው!) “ኢሳት” በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ድርጅቶች አንዱ በሆነው ግንቦት 7 ድጋፍ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ በዶክመንተሪው ላይ ቢገለጽም ሰማያዊ ፓርቲ ግን አጣጥሎታል (ውሃ አያነሳም ብሎ!) አሸባሪዎችን የመፈረጅ ብቸኛ ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው ያለው ፓርቲው፤ “እስካሁን ም/ቤቱ በአሸባሪነት ስላልፈረጀው በጣቢያው ቃለምልልስ ማድረጌን፣ ፕሮግራሜን ማስተዋወቄን፣ የአባላቶቼን ቁጥር ማሳደጌን እቀጥላለሁ” ብሏል፡፡ (በቁርጠኝነት!) ይሄውላችሁ… “መጥራት” የሚያስፈልገው “ብዥታ” ማለት እንዲህ ያለው ነው፡፡

“ኢሳት አሸባሪ ነው አይደለም?” የሚለው “ያልጠራ ብዥታ” በመሆኑ የውዝግብ መነሻ ሆኗል፡፡ እኔ የምላችሁ…በዶክመንታሪው እንደተገለፀው በኢሳት ቃለምልልስ ማድረግ ከአሸባሪ ጋር እንደመተባበር የሚቆጠር ከሆነ፣ ኢሳትን መመልከትስ? ይሄን ለመግለጽ ሌላ ዶክመንታሪ መስራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በአጭሩና በግልጽ መናገር በቂ ነው፡፡ (ህጉን ተከትሎ ማለቴ ነው!) አሁን ደግሞ ወደ ሌሎች ብዥታዎች እንለፍ። “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ባለፈው ረቡዕ በፊት ለፊት ገፁ ላይ ያወጣውን ዜና አይታችሁልኛል? “መጽሔቶቹ በብዙ ባህሪያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” ይላል፤ የጥናት ሰነድ በመጥቀስ የወጣው ዘገባ፡፡ ጥናቱን ያሰሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደሆኑ የገለፀው ዘገባው፤ ጥናቱ የተካሄደው በሰባት የግል መጽሔቶች ላይ መሆኑን በመጠቆም ዘርዝሯቸዋል፡፡ ይሄን የጥናት ሪፖርት ያመጣሁት መጥራት ባለባቸው በርካታ “ብዥታዎች” የተሞላ በመሆኑ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡

(ፖለቲካዊ አቋም ልይዝበት እንዳይመስላችሁ!) እንግዲህ ሁለቱ የመንግስት ተቋማት ከመስከረም እስከ ህዳር መጨረሻ ድረስ (ለ3 ወራት ማለት ነው!) ስለመጽሔቶቹ እንዲጠናላቸው የፈለጉት ምን መሰላችሁ? መጽሔቶቹ በህትመቶቻቸው ያነሷቸው ስድስት ርዕሰ ጉዳዮችን ነው፡፡ (ማን ይሆን ያጠናው?) በሌላ አነጋገር የአዝማሚያ ጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ያተኮሩት… ሀ) የመንግስት ኃላፊዎችን የግል ስብዕና የሚነኩ ለ) የአመጽ ጥሪዎችን የሚጠሩ ሐ) ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ መ) የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ሠ) የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚክዱ ረ) ህገመንግስቱን የሚያጣጥሉ… በሚሉት ዙሪያ ነው፡፡ እናም እነዚህን ሲያጠኑና ሲያስተነትኑ ቆይተው ነው “መጽሔቶቹ በብዙ ባህሪያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” የሚለው ድምዳሜ ላይ የደረሱት፡፡

(አይ “ብዥታ”!) በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ይሄን ጉዳይ ያነሳሁበት ምክንያት አንዳችም “ብዥታ” እንዲፈጥር አልፈልግም፡፡ (ብዥታን ለማጥራት ብዥታ መፍጠር ተገቢ አይደለም!) እናም… የፕሬስ ድርጅትና ኢዜአ ለሶስት ወር ውድ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተውና ከስክሰው የግል ፕሬሱ ላይ (ጋዜጦችን ባይመለክትም!) ጥናት በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ (ምስጋናው ጥናቱ ፋይዳ እንዳለው አይጠቁምም!) በነገራችሁ ላይ የመጽሔቶቹ አዘጋጆችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የጥናት ሪፖርቱን በጽኑ ተቃውመውታል፡፡ (አደራ አንተስ እንዳትሉኝ!) የእኔ ዓላማ ለጊዜው ብዥታዎችን መንቀስ ብቻ ነው፡፡ በጥናቱ ውስጥ ሳይገቡኝ ዝም ብለው የገረሙኝ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ መጥቀስ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ከአመጽና ሽብርተኝነት ጋር የተያያዙትን ትቼ ገራገሮቹን ብቻ አነሳለሁ፡፡ (ብዥታን ለማስቀረት እኮ ነው!) አሁን ለምሳሌ “የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚክዱ ዘገባዎች” የሚለው ነገር አሁንም ድረስ (ሳምንት ሙሉ ማለት ነው!) ይገርመኛል እንጂ ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ (በብዥታ የተሞላ ነዋ!) መንግስት ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤአለሁ ሲል ቆይቷል፡፡ መጽሔቶቹ ደግሞ ይሄ የመንግስት ቃል አላሳመናቸውም (ዕድገትን በቃል ማሳመን ከባድ ነው!) እናም ዕድገት የለም ብለው ፃፉ፤ ዘገቡ፡፡ ምንድነው ችግሩ? ያላመኑበትን መግለጽ ሃጢያት ወይም ክህደት ሊሆን አይችልም፡፡

(“ዕድገቱን በግድ እመኑ” ይባላል እንዴ?!) ለዚህ እኮ መድሃኒቱ ሌላ ሳይሆን አለ የተባለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ወዳላመኑት ወገኖች ማዳረስ ነው፡፡ ( “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን ናቸው” ለዕድገት አይሰራም!) እናም… የግል ሚዲያዎች መንግስት የሚገልፀውን የኢኮኖሚ ዕድገት አልተቀበሉም ማለት ሌላ አንደምታ ያለው ነው የመሰለኝ (በጥናቱ መሰረት!) አንደምታው በግልጽ ይነገረን። ይከሰሳሉ? በአሸባሪነት ይፈረጃሉ? ይዘጋሉ? ወይስ ምን? መጥራት ያለበት “ብዥታ” ነው። በዚህ ጥናት ውስጥ ሌላው ሳይገባኝ የገረመኝ ደግሞ “የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ” በሚል የቀረበው ነው፡፡ ያጨለሙት በብዕር ነው በትጥቅ ትግል? በመፃፍ ነው ጦርነት በመክፈት? በሃሳብ ነው በሃይል? ነገርዬው አልጠራም!! በነገራችሁ ላይ የፕሬስ ድርጅትና ኢዜአ ይሄ ጉዳይ እንዴት እንዳሳሰባቸውና የጥናት ትኩረት እንዳደረጉት ፈጽሞ አልገባኝም፡፡ የግል መጽሔቶቹ የፖለቲካ ስርዓቱን “አጨልመውታል” ብለው ካሰቡ እኮ እነሱም በሚዲያቸው “ማፍካት” ይችላሉ፡፡ (የሚዲያ ችግር የለባቸውማ!) ከሁሉም ግን የጠጠረብኝና በ“ብዥታ” የተሞላው የቱ መሰላችሁ? ሁሉም መጽሔቶች የጋራ የመረጃ ምንጮች ይከተላሉ ተብሎ “የኒኦሊበራል አክራሪ ኃይሎች፣ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች…” በሚል የተጠቀሰው ነው፡፡

እውነቴን እኮ ነው… ይሄ ኒኦሊበራል የሚለው ነገር ላይ ፈጽሞ የተግባባን አይመስለኝም። ከቃሉ ፍቺ ውጭ የተሰጠው አዲስ ብያኔ ካለ ይነገረን እንጂ አልሆነም፡፡ (እንደ ባቢሎን ግንብ ሆንን እኮ!) እኔማ ምን አስብ ነበር መሰላችሁ? ኢህአዴግ የኒኦሊበራል ኃይሎች ምናምን ሲል…ከተቃዋሚዎች ጋር ለመበሻሸቂያ እንጂ የምሩን አይመስለኝም ነበር፡፡ (በጥናት ውጤቱ ተገለጠልኝ!) እናላችሁ የኒኦሊበራል ሃይሎች አሸባሪ ተብለው ተፈርጀው እንደሆነ በግልጽ ይነገረን (ብዥታው እንዲጠራ!) በነገራችሁ ላይ… የጥናት ውጤቱ በመጽሔቶቹ ላይ የደረሰበት ድምዳሜም እኮ “ብዥታ” የሞላበት ነው፡፡ “መጽሔቶቹ በብዙ ባህሪያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? ለማንኛውም ግን በኢህአዴግ ሳቢያ የሚፈጠሩ በርካታ “ብዥታዎች” በጊዜ ካልጠሩ ለአደጋ ያጋልጡናል (ጐጂ ልማድም ናቸው!) እኔም እንግዲህ የበኩሌን አንዲት “ብዥታ” ጣል አድርጌ ልሰናበት፡፡ (ለሙከራ ያህል እኮ ነው!) “የመንግስት ሚዲያዎች በብዙ ባህሪያቸው የአውራው ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” (ለአቅመ “ብዥታ” በቅቶ ይሆን?)

Read 4347 times