Print this page
Saturday, 18 January 2014 11:38

570 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ፀደቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

         የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ 572 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ያፀደቀ ሲሆን ከዚህ ቀደም የወጡት ደረጃዎችም በአግባቡ እየተተገበሩ ስላልሆነ የማስፈፀም ሃላፊነት ያለበት ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታችን እንዲወጡ ኤጀንሲው ጠይቋል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ 10ሺህ ያህል ደረጃዎች ለማፅደቅ ቃል የገባው ኤጀንሲው ለብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤቱ 631 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አቅርቦ 572 ሲፀድቁ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን በተመለከተ ሊቀርብ የነበረውን ጨምሮ 59 ደረጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለጊዜው እንዲዘገዩ መደረጉን የኤጀንሲው የደረጃዎች ዝግጅት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ለገሰ ገብሬ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡ /በሰዎች ጤና እና አካል ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርቶችን በተመለከተ የሚወጡ ደረጃዎችን በማስፈፀም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊው፤ ንግድ ሚኒስቴር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በየዘርፉ የሚቀርቡ ደረጃዎች ሲገመገሙ ሰብሳቢ የሚሆነው የየዘርፉ አመራር መሆን አለበት የሚል አሰራር በመኖሩ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን በተመለከተ የቀረበው ደረጃ ያልፀደቀው ተወካዩ ባለመገኘታቸው መሆኑን የስራ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡ ብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን አድርጎ ካፀደቃቸው ደረጃዎች ውስጥ 309 አዲስ ሲሆኑ 33 የተከለሱ እንዲሁም 230 ነባር ደረጃዎችን ፈትሾ በማስቀጠል የፀደቁ መሆናቸውን አቶ ለገሰ ገልፀዋል፡፡ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ውጤቶች የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 131 ደረጃዎች፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ 211 የኢትዮጵያ ደረጃዎች፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 121 ደረጃዎች እንዲሁም በጤና፣በአካባቢና ደህንነት የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 109 የኢትዮጵያ ደረጃዎች የፀደቁ ሲሆን ደረጃዎቹን የሚመለከታቸው አካላት ተከታትለው የሚያስፈፅሙ ከሆነ፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የተጠቀሰ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የሃገሪቱ ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላሉም ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የአለማቀፉ የመስፈርት ተቋም (ISO) ሰርተፍኬትን ማግኘቱ ኤጀንሲው የሚሰጣቸው ደረጃዎች በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሚናው የላቀ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

Read 3079 times