Saturday, 18 January 2014 11:34

እንደተመኘነው የአፍሪካ እግር ኳስ ቤተኛ እየሆንን ነው፤ የተፎካካሪነትና የዋንጫ ምኞታችንስ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ወደ የሚገኘው የኦሊቨርታምቦ አየር ማረፊያ የደረስነው ባለፈው ሃሙስ 9 ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ በበደሌ ስፔሻል የጉዟችን ሙሉ ወጭ ተሸፍኖ የቻን ውድድርን ለመዘገብ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናነው ጋዜጠኞች ከላይ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ለብሻለሁ፡፡ ከውስጥ የለበስኩት ቲሸርት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ማልያ ነው፡፡ የመግቢያ ቪዛዬን የመረመረው የኢምግሬሽን መኮንን አለባበሴን ሲያይ ዝም ማለት አልቻለም፡፡ ለምን ማሊያ እንዳቀላቀልኩ ሲጠይቀኝ፤ የሁለቱም አገራት ደጋፊ ነኝ አልኩት፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ ማጣርያው ካልቀናትና ከተሰናበተች፤ በሁለተኛ ደረጃ የምደግፈው አገር ደቡብ አፍሪካ ነው አልኩት፡፡

የኢምግሬሽን መኮንኑ ፓስፖርቴን እየመረመረ ደቡብ አፍሪካ ናይጄርያን ካሸነፈች ለዋንጫ ትደርሳለች አለኝ፡፡ እኔም፤ ኢትዮጵያ በሁለተኛው ጨዋታዋ ኮንጎ ብራዛቪልን ካሸነፈች ከምድብ የማለፍ እድል ይኖራታል አልኩት፡፡ የመልካም እድል ምኞት ተለዋውጠን ተለያየን፡፡ የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ወሳኝ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ትናንት እና ዛሬ ነበር የተደረጉት፡፡ ዋልያዎቹ በምድብ የመክፈቻ ጨዋታ በደረሰባቸው የ2ለ0 ሽንፈት ምክንያት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መከፈታቸውን ለመረዳት ብዙ አያስቸግርም፡፡ በዋና ከተማዋ ጆሃንስበርግ ውስጥ፣ ጄፒ ስትሪት አካባቢ የሚገኘው የጆበርግ መርካቶ ላይ ያጠላውን ድባብ መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በንግድ ስራ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱበት እና ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች በመምጣት እንደ መናሐርያ የሚገናኙበት የጆበርግ መርካቶ፤ ባለፈው ሃሙስ ከ10 ሰዓት በኋላ እንደልማዱ ጭር ሲል በአካባቢው ተዘዋውሬ የተመለከትኩት ሁኔታ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ባለሸንተረሩን፤ ወይንም ቢጫውን ካልሆነም አረንጓዴውን የዋልያዎቹ ማልያ የለበሰ ኢትዮጵያዊ እንደ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሰሞን አልነበረም፡፡ እንደውም በጆበርግ መርካቶ አካባቢ የሚታየው ከብሄራዊ ቡድን ጋር የተያያዘ ድባብ የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ርዝራዥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህን የዋልያዎቹ ማልያ በጆሃንስበርግ እስከ 140ራንድ መሸጡን ያሰታወሰው አንድ ነጋዴ ሰሞኑን በከተማዋ ለኢትዮጵያ እና ለደጋጋፊዎቿ ሲሸጥ የነበረው ማልያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለገበያ ቀርቦ ከነበረው የተረፈ መሆኑን ይናገራል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በ2010 እኤአ ላይ በዚያው አገር በተካሄደው19ኛው ዓለም ዋንጫ ወቅት ለውድድሩ ትኩረት የነበረውን የቩቩዜላ ጥሩንባ በማምረት እና በመቸርቸር እንዲሁም በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ማልያ በመሸጥ ከፍተኛ ገበያ ነበራቸው፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ መሳተፏን በድምቀት ያከበሩት እነዚህ ኢትዮጵያውን፤ በወቅቱ የዋልያን ማልያ በደቡብ አፍሪካ ስታድዬሞች በተለይም ብሄራዊ ቡድኑ በተጫወተባቸው ሁለት ከተሞች ሩስተንበርግ እና ኔልስፕሪት እንዲሁም በመናሐሪያቸው ጆሃንስበርግ ከተማ በመቸብቸብ እና በመልበስ የማልያውን ተወዳጅነት ጨምረውታል፡፡ ይሄው በደቡብ አፍሪካ ተመርቶ እና ለገበያ የቀረበው የዋሊያዎቹ ማልያ፤ ወደ ኢትዮጵያ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ወደ አውሮፓ ተልኮም ከፍተኛ ገበያ እንዳገኘ ተገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሰኞ እለት ዋልያዎቹ ከሊቢያ አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ የገጠማቸው የ2ለ0 ሽንፈት ያበሳጫቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ሲገባ ያደረግነው አቀባበል ከአፍሪካ ዋንጫው በተለየ የደመቀ ነበር ያለው ብሩክ የተባለ ወጣት፤ ያን ጊዜ እንበላዋለን ብለን ጨፈርን፤ አሁን ለቻን ሲመጡ ደግሞ ሁላችንም እናስብ የነበረው በሊቢያ እንዲሸነፉ ሳይሆን ለዋንጫ እንዲደርሱ ነው ብሏል፡፡ ያነጋገርኳቸው የጆሃን ስበርግ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በቻን የመክፈቻ ጨዋታ ዋልያዎቹ የነበራቸውን ብቃት አንገት ያስደፋል ብለው ገልፀውታል፡፡ አንዱ ወጣት ነጋዴ እንደውም ቡድኑ ከሊቢያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የነበረው ሁኔታ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን ያስመስለው ነበር ብሏል፡፡ ለሰላሣ አመታት ርቆን ስንመኘው ወደነበረው የአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ለመግባት መብቃታችን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ዋሊያዎቹ ለአህጉሪቱን የእግር ኳስ ዋንጫ ከሚፎካከሩ 16 ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን በመቻላቸው የህዝቡ ስሜት የቱን ያህል እንደተጠቀለለ አይተናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

ነገሩ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል አይደለም፡፡ በእንግድነት የረገጥነው አህጉራዊ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ነው፡፡ አለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከ መጨረሻው ዙር በስኬት በመጓዝ ከአስሩ ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን ችለናል፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ በአህጉራዊው የቻን ውድድር ውስጥ ገብተናል፡፡ አሁን ተራ ነገር ቢመስልም ለብዙ አመታት ስንናፍቀው የነበረ ነው አህጉራዊው የእግር ኳስ መድረክ፡፡ ነገር ግን ባዕድ ሆኖብን በነበረው መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆንን ብንመጣም በቂ አይደለም፡፡ በአህጉራዊው መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ የመሆን ምኞታችን ገና አልተነካም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ባለፈው 2 ዓመት ውስጥ ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንዱንም አላሸነፈም፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 አቻ ከወጡ በኋላ ፤ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከዛምቢያ ጋር አንድ ለአንድ አቻ፤ በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እና በናይጄርያ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሁለት ሽንፈት አስተናግደው ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ ልምዱ ተነስቶ በቻን ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበራቸው፡፡ - እስካሁን አልተሳካም እንጂ፡፡

በሊቢያው ጨዋታ አንዳንድ ደጋፊዎች አምበሉን ደጉ ደበበን ተበሳጭተውበት እንደነበር የገለፀው ታሪኩ የተባለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ፤ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተጫዋቹን ወቅታዊ አቋም በመረዳት ማሰለፍ እንዳልነበረበት እና በሱ ምትክ ሳላዲን በርጌቾን በማጫወት በቡድኑ ላይ የደረሰውን ሽንፈት እና በተጨዋቹ ላይ ያለ አግባብ የተፈጠረውን ትችት መከላከል ይችል ነበር ብሏል፡፡ ብሩክ የተባለው ኢትዮጵያዊ የደቡብ አፍሪካ ነዋሪ በበኩሉ በጨዋታው ላይ አዳነ ግርማ ከፍተኛ ድካም የገጠመው ያለቦታው በመሰለፉ ነው የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሩክ፤ ከሜዳ ውጭ ረዳት አሰልጣኝ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት እንዲህ አድርግ እዚያ ጋር ሸፍን በሚል በሚያዥጐደጉዱበት ትዕዛዝም ያደክማል በማለት ወቅሷል፡፡ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከሃዘናቸው ባሻገር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ወደፊት ብሄራዊ ቡድኑ በስብስቡ በወጣት ተጨዋቾች ተጠናክሮ ውጤት እንደሚያገኝ ስለሚያምኑ በደስታ መደገፋቸውን እንደማያቋርጡ ይገልጻሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን እንደገለፁት የሊቢያውን ጨዋታ ለመመልከት ስራቸውን ትተው ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ወደ ፍሪስቴት ስታድዬም በመጓዝ ጨዋታውን የታደሙ ቢሆንም በዋልያዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት አሳዝኖቸዋል፡፡ በምድብ 3 የተደለደሉት ዋልያዎቹ የመክፈቻ ጨዋታቸውን በፍሪ ስቴት ስቴድዬም ሲያደርጉ፤ ድጋፋችንን ለመስጠት እስከ 10 አውቶብስ ያህል ሆነን መጥተናል ብሏል - በደቡብ አፍሪካ አምስት አመት የሆነው ኢትዮጵያዊ በአጠቃላይ ለጨዋታው እስከ 8ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስታድዬም መግባታቸውን፤ የገለፀው ይሄው ኢትዮጵያዊ፤ የትኬት ዋጋ ከ50 እስከ 70 ራንድ መክፈላቸውን ተናግሯል፡፡ ከ100 እስከ 140 ብር ገደማ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ድጋፍ የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ሃይሎች ሳይቀሩ ተደስተዋል፡፡ የቻን ውድድር ድምቀት እናንተው ናችሁ በማለት የፀጥታ ጥበቃ ሃይሎች ኢትዮጵያውያን ሲያበረታቱ እንደነበሩና እንዳይ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው እና በነፃ ስታድዬምም እንዲገቡ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡድን በመሸነፉ የብዙዎቹ ስሜት ቢቀዘቅዝም ተስፋ ሳይቆርጡ ሁለተኛውን ጨዋታ ለመመልከት መጠባበቃቸው አልቀረም፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፍ መስጠታቸውም አያጠራጥርም፡፡ ዋልያዎቹ ኮንጎ ብራዛቪልን ማሸነፍ ከቻሉ ግን፤ የኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች ስሜት እንደገና ይሟሟቃሉ፡፡

ዋሊያዎቹ የፊታችን ሰኞ የምድባቸውን የመጨረሻ ጨዋታ ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ሲያደርጉ በርካታ ደጋፊዎች ስታድዬም እንደሚገቡም ይገመታል፡፡ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የነበረውን ጉዞ በንቃት መከታተላቸውን የሚናገሩት ኢትዮጵያውያን፤ ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካን በሜዳቸው ሁለት ለአንድ ባሸነፉበት ጊዜ በጆሃንስበርግ መርካቶ የነበረው ደስታ ወደር እንዳልነበረው ያስታውሳሉ፡፡ እዚህ በሰው አገር ከደስታችን ብዛት መንገድ ሁሉ ተዘግቶ በጭፈራ ደምቆ እንደነበር፤ ደቡብ አፍሪካውያኑን በማብሸቅ ከፍተኛ ድራማ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ታልፋለች በሚል ተስፋ ከናይጄርያ ጋር የተደረጉ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን እንደተከታተሉ ገልፀው፤ ኢትዮጵያ በመጀመርያው ጨዋታ በሜዳዋ መሸነፏን ሲያዩ ማዘናቸውንና የካላባሩ ጨዋታ ብዙም እንዳልሳባቸው ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ እለት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው እና ኢስትጌት በተባለው የገበያ ማዕከል ስንዘዋወር ቆይተን አንድ የስፖርት ትጥቆች ሱቅ ውስጥ ገባን፡፡

የተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ማልያዎች እየተመለከትኩ በነበረበት ጊዜ ነው አረንጓዴ ቱታ የለበሱ ተጨዋቾች ወደሱቁ የገቡት፡፡ የኮንጎው ብራዛቪል ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ አንዱን ወጣት ተጨዋች ንናግረው ስሞክር እኔ በእንግሊዝኛ እሱ በፈረንሳይኛ አልተግባባንም፡፡ በሬዲዮ የስፖርት 365 አዘጋጅና በኢንተርስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ዲያሬክተር ሁሴን አብዱልቀኒ ነው በፈረንሳይኛ ያግባባን፡፡ ኤሲ ሊዮፓርድስ በኮንጎ ብራዛቪል ትልቅ ክለብ እንደሆነ ወጣቱ ተጫዋች ገልፆ፤ በክለቡ የወጣቶች አካዳሚ ውስጥ እግር ኳስን ሰልጥኖ ዋናውን ቡድን በ21 ዓመቱ እንደተቀላቀለ ነገረኝ፡፡ ለኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ባለመመረጡ ቢያዝንም፤ ውድድሩን በጉጉት እየተከታተለው ነው፡፡ ከምድብ 3 የሚያልፉት እነማን ይሆናሉ ተብሎ ሲጠየቅ በሰጠን መልስ፤ ኢትዮጵያ እና ሊቢያ ጠንካራ ቡድኖች በመሆናቸው ከጋና ይልቅ እንፈራቸዋለን ብሏል፡፡ የኤሲ ሊዮፓርድሱ ተጨዋች ለስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ መጫወት እንደሚፈልግ ሲነግረኝ፤ የሚያስደንቅ ህልም አለህ ብዬ እንደሚያሳካው በመመኘት ተሰናበትኩት፡፡

Read 4184 times