Saturday, 11 January 2014 11:56

ክፍል ሦስት ከባለፈው እትም የቀጠለ………… የግል ንግድ ተቋማት ማህበራዊ ሃላፊነትና የህጻናት ጥቅም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

        ሶስተኛው መርህ የንግድ ተቋማት ለወጣት ሰራተኞች፣ ለወላጆች እንዲሁም ለተንከባካቢዎቻቸው ምቹ የሆነና አቅምን ያገናዘበ የስራ አከባቢን መፍጠር እንዳለባቸው ያትታል፡፡ ሰነዱ እንደሚያስረዳው ወጣት ሰራተኞች ስንል በህግ ለስራ ከተፈቀደው ዝቅተኛ የእድሜ ወሰን(14 አመት) የዘለሉና በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ነው ፡፡ የእነዚህ ወጣት ሰራተኞች ስራ ወይም የስራ ሁኔታ አደገኛ በሚሆንበት ጊዜም ከጉልበት ብዝበዛ ጋር ሊዛመድ የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ መርሁ በተለይም ለነዚህ ወጣት ሰራተኞች የመስራት ፣ከአደጋ ነጻ የሆነ የስራ አከባቢ የማግኘት፣ጾታን ያማከሉ የውሃና የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን ማግኘት ላይ አትኩሮት በመስጠት እንዲሰራ ግፊት ያደርጋል ስለዚህም የንግድ ተቋማቱ የእነዚህ ወጣት ሰራተኞች ጥቅም ከግምት በማስገባት ይህን ጉዳይ የሚያሥተዳድር መመሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳል፡፡በተጨማሪም የንግድ ተቋማቱ የወጣት ሰራተኞችን ጤና ማህበራዊ ደህንነት እንዲሁም ተከታታየይነት ያለው አቅም ግንባታን ያማከለ ምቹ የስራ ሄኔታና መፍጠር እንዳለባቸው ሃላፊነት ይሰጣል፡፡በተጨማሪም እነዚሁ ተቋማት ላረገዙ& ጡት ለሚያጠቡ እናቶች፣ለተንከባካቢዎች እንዲሁም ለስደተኛ ሰራተኞች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡

አራተኛው መርህ የሚያተኩረው የንግድ ተቋማቱ በሚያከናዉኗቸው እንቅስቃሴዎች እና በአቅርቦታቸው የህጻናትን ደህንነትና ጥበቃን የማረጋገጥ ሃላፊነት እንዳለባቸው ያትታል፡፡ መርሁ የህጻናት እንዲሁም የወጣት ሰራተኞችን ጥቃትና ብዝበዛን ብሎም ደህንነታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በመከላለክለና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ማካተትን እንዲሁም አግባብነት ያለው እርምጃ ስለመውሰዳቸው የማረጋገጥ ሃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡ በተጨማሪም መርሁ የንግድ ተቋማት የህጻናትን ደህንነትን አስመልክቶ በዘላቂነት ሊተዳደሩበት የሚገባ ፖሊሲ ሊኖራቸው እንደሚገባና በሰነዱ ላይም ቀጣይነት ያለው ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ሊሎች ተመሳሳይ ተቋማትም ይህን መመሪያ እንዲያካትቱ ማበረታታትና ተነሳሽነትን መፍጠር እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ የንግድ ተቋማቱ የሚያመርቷቸው ምርቶችና የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከህጻናት ጥቅሞች ጋር የማይጻረሩ እንዲያውም ደጋፊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚለው የአምስተኛው መርህ ዋነኛ መልእክት ነው ፡፡

በመርሁ መሰረትም ህጻናት ሊጠቀሙበት ብሎም ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ማንኛውም ምርቶችና አገልግሎቶች የአለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ጥራታቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው፣ደህንነታቸው የተጠበቀ ስለመሆኑና ምንም አይነት የአካል፣የአእምሮና ሞራላዊ ጉዳት ላለማስከተላቸው ቅድሚያ መረጋገጥ እንዳለበት ይገልጻል፡፡በተጨማሪም የንግድ ተቋማቱ የሚያመርቷቸው ምርቶች ወይም የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ለህጻናት ጥቃትና ብዝበዛ መሳሪያነት እንዳይውል ለመከላከል የራሳቸውን ጥረት የማድረግን ሃላፊነት ያስረዳል፡፡በዚህ መርህ መሰረት የንግድ ተቋማት ሃላፊነት የሚያጠነጥነው የምርትና አገልግሎታቸውን አቅርቦትና ስርጭት ተደራሽነት በማስፋት የህጻናት ጥቅሞች ማስጠበቅ ነው፡፡

Read 1535 times