Saturday, 11 January 2014 11:14

የአውራምባ የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(4 votes)

ሴት የወንድ ሥራ ብትሠራ ያባቷ ሥራ ነው፡፡ ወንድ የሴትን ሥራ ቢሠራ የእናቱ ሥራ ነው!! የጠብ ምንጭን ማስወገድ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ጠብን አስወግደን ምድራዊ ገነትን ፈጥረን መሄድ አለብን (በማህል ልጁዋ መጣና እሱን እስክትሸኝ ታገስኩ፡፡) በተለይ በ80 ዓ.ም ደርግና ኢህአዴግ ተፋጠው ባሉበት ወቅት እኛን ኢህአዴጐች ናቸው ብለው ያስወሩ ነበር፡፡ ወደ ደቡብ ስደት እንድናደርግ ተገደድን፡፡ የሚበላ በሌለበት በዓላማችን ፀንተን ቆየን፡፡ ከዚያ ተመልሰን የዙምራን አስተሳሰብ እየሠራነው እየኖርነውና እንገኛለን፡፡ “ዱሮ በምን መለኪያ ነበር የሚረዳቸው?” አልኳት። “ደካሞችን በሚረዳ ጊዜ የሚረዳቸው የሌላቸውና የመሥራት አቅም የሌላቸው ሰዎች ይመስለኛል፡፡ ህፃን ሽማግሌ ይመርጣል፡፡” “በሳቸው አቅም ሁሉን ያዳርስ ነበር?” “እኔ እንጃ” ኑሩ ተቀበላት፡፡ “በግምት ስንት ችግርተኛ አለ ብሎ አጥንቶ ይመስለኛል፡፡

ሁሉን እኩል ለማድረግ መጣጣር፡፡ ከራሱ ውጪ ቸገረን የሚል ሰው ሲመጣ መስጠት ነው፡፡ ይመልሱልኛል ብሎ አይደለም ዝም ብሎ መስጠት ነው፡፡ እነሱ መመለስ ያስባሉ እሱ መስጠት ብቻ ነው ማገዝ መነሻ ለሌላቸው፣ አቅም የሌላቸው” “ትምህርት አለው እንዴ ዙምራ?” “የለውም፡፡ ሲፈርም እንኳ ተንቀጥቅጦ ነው የሚፈርመው፡፡ መሠረተ ትምህርት መማር አለባችሁ በተባለ ጊዜ ለአንዲት ቀን ገብቼ ነበር ይላል፡፡ አንዲት ቀን በገባበት ትምህርት ግን ይሄንን ማንበብ ችሏል አይፈጥንም እንጂ፡፡” የቤተሰቡ ሁኔታስ? ብላቸው፤ “ሀብታሞች ናቸው። ዕውቀት ነው እንጂ ያጣችሁት፤ ለብዙ ትተርፉ ነበር ይላቸው ነበር፡፡ “ቤተሰቦቹ የዳሩለት ልጅ ከአስተሳሰቡ ጋር የምትጣጣመውን ፈልገው አግኝተው ነው? መቼም እንዳሁኑ ዘመን ጠበሳ ምናምን የለም ብዬ ነው?” አልኳቸው፡፡ “ወደሱው እየተንደረደርኩልህ ነው፡፡ መቼም ዙምራ ከብዙ ሴቶች ጋር ተፈናቅሏል፡፡ ለምን? በአስተሳሰቡ። ሚስትየዋ፤ “የሰጠነውን ገንዘብ መቀበል አለብን” ትላለች፡፡

እኔ፣ ችግራቸውን ላስወግድ እንጂ ልቀበል አልሰጠኋቸውም” ይላል፡፡ በዚህ አልተስማሙም፡፡ ይሄኔ እሱ፤ የኔና የሷ ፍላጐት ተለያይቷልና መለያየት አለብን፤ ይላል፡፡ ራሴን ችዬ ልቀጥል ይላል፡፡ ሲወጣ ደግሞ ለራሱ ለዕለት ጉርስ የምትበቃውን ይወስዳል እንጂ ሀብቱን ትቶ ነው የሚወጣው፡፡ ደስ የሚልሽን ህይወት ምሪ ይላታል፡፡ የዛሬይቱ ስድስተኛ ሚስቱ ናት ይመስለኛል፡፡ አይደል? አላት፡፡ አዎን ስድስተኛው ናት አለች ጥሩ ሰው በማረጋገጥ፡፡” “ህፃናቱ፣ ልጆቹ ላይ ተፅዕኖ የለውም?” “አለው፡፡ ግን ይሄኛው ሚዛን ስለደፋበት ነው፡፡ ግን ምንም ላደርግ አልችልም ይላል፡፡ እንደሌላው ሆኜ ለመኖር ብችል ብዬ አስበዋለሁ፡፡ ግን አስተሳሰቤ እሺ አይለኝም አለ፡፡ ተመልሼ እዛው እገባለሁ፡፡ “ከዚያ ሃሳብ ቢላቀቅና ለውጥ ቢቀበል አይችልም ማለት ነው? ለምን አይችልም?” “የተፈጥሮ ነገር ይመስለኛል አይችልም፡፡ ላስለቅቅ ብዬ መላቀቅ አልቻልኩም፡፡ እውስጤ ያለው ነገር እንደ እሳት ነው የሚበላኝ - ያንን ባስብ፡፡ ወስኜ አያስችለኝም። ተመልሼ እዛው ነኝ፡፡ እኔ እማላውቀው የተፈጥሮ ነገር አለብኝ ማለት ነው፡፡” “ሁሉን ነገር ለተፈጥሮ ከሰጠነው እኛም የተሰጠንን የማሰብ አቅም ገደብነው ማለት አይደለም ወይ? በዓለም የታወቁት ፈላስፎች ከዓለም ዓለም እየዞሩ ፍልስፍናቸውን ይናገራሉ፡፡

እዚህ ግን የታጠረ ይመስለኛል፡፡ ለማስተማር ሲሄዱኮ ተምረውም ነው የሚመጡት፡፡ በመስተጋብሩ ለውጥ ይመጣል፡፡ ይሄ ማህበረሰብ የተገፋ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ባካባቢያችሁ ባለው ገበሬ ላይ በቂ ተጽእኖ አሳድሯችኋል?” “በአብዛኛው አሳድሯል፡፡ በተማረው ክፍል ላይ አዎ አሳድሯል፡፡ ወደተግባር ለመለወጥ ግን ሌላ step ነው፡፡ ግማሹ ጠያቂ ነው፣ ግማሹ እንቅፋት ነው ግማሹ ይጠላዋል” “ሃይማኖት ካላጠረህ፤ የተወሰነ ዕምነት - እንበል ኮሙኒዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም ካልያዘህ፣ ነፃ አስተሳሰብ ካለህ፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ማለት የዱሮውን ማፍረስ ሳይሆን የዱሮውን ማሳደግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ማሳደግ መቻል ነበረበት፡፡ ለማሳደግ ደግሞ ያካባቢ Interaction የሌሎች ግብዓት ያስፈልጋል፡፡ ያ እንዴት አልሆነም?” አልኩት፡፡ ወደ ጥሩ ሰው ዞሬም፤ “እያየሁ ሲሆን የሆነውን ነው የምትነግሪኝ፤ አሁን ግን የምታስቢውን ነው የምትነግሪኝ- audiovisual መሆኑ ነው…ማህበረሰቡ ሚስት መፍታትን እንዴት ነው እሚያየው?” ለምሳሌ ከእናንተ ውጪ ያለው ህዝብ፣ ሰው ሚስቱን ከፈታ Irresponsibility ነው ኃላፊነት የጐደለው ተግባር ሆኖ ነው የሚታሰበው፡፡

ችግር አለበት፡፡ ይሄን ቀንሰሽ መደብደብ፣ ማሰቃየት፣ ገንዘብ አለመስጠት፣ ልጆች መበደል ወዘተ አለ ማለት ነው ይባላል፡፡ የብዙዎች አስተሳሰብ ባልየው ጥሩ ባይሆን ነው የሚል ነው… 1ኛ) ማህበረሰቡ መፍታትን እንዴት ያየዋል? 2ኛ/ የተፈቱትን ሴቶች ማግኘት እችላለሁ ወይ? ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ? “አትችልም” አለች ጥሩ ሰው፡፡ “አይ ትችላለህ” አለኝ ኑሩ፡፡ “የዙምራን እኮ አደለም የሚለው ማንኛዋንም የተፈታች ሴት ነው” አለ፡፡ የዙምራን ሚስቶች ግን ማግኘት አይቻልም ማለት ነው ይመስለኛል አንድምታው፡፡ “እንደመተዳደሪያ ህግ ያስቀመጥነው ጠቅለል ያለ የጋብቻ ደንብ አለን፡፡ ማነጋገር ትችላለህ… መፋታት ትችላለች ይላል ደንቡ” (ጥሩ ሰው ወጣ አለች) ኑሩ ቀጠለ:- “ጋብቻ፣ የሁለት ፆታዎች ነፃ ስምምነት ነው፡፡ ከሌሎች ረቀቅ ያለ አስተሳሰብ የሚሻ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ የመጀመሪያ ጋብቻ ከ20 ዓመት ዕድሜ በላይ እንዲሆን ይመከራል፡፡ በዚያ ዕድሜ ክልል አርቆ የማሰብ፣ ጠለቅ ብሎ የማሰብ፣ ግልጽ አድርጐ ሁኔታዎችን ማሰብ ያስችላል የሚል አስተሳሰብ አለን፡፡ በጣም ክቡር ነገር ነው፡፡ በቀልድ እሚጀመር፣ በቀልድ እሚፈርስ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ለአንድ የፀና ይሆናል፡፡ ህጉ አለ፡፡ በሥራም አብረን ነው፡፡ ባህሪያችንን መተዋወቅ አለብን፡፡ ይሄን አስተሳስረን እኔና እሷ እንወስናለን፡፡ ባህሪ፣ ቁምነገር፣ ሥራ ወዳድነት ሊሆን ይችላል ያግባባን፡፡ ሌላም ሌላም የውስጥ መመዘኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ለናት አባታችን መግባባታችንን እንነግራቸዋለን፡፡ የማህበረሰቡ ጋብቻ መመዝገቢያ አጀንዳ አለ፡፡ እዚያ ላይ መመዝገብ አለበት ህጋዊ ለማድረግ፡፡” (ማዘጋጃ ቤት መሆኑ ነው) ለጋብቻ ወጪ ይውጣ ተብሎ አይመከርም፡፡ ከኢኮኖሚ አኳያ ወላጆች ጐጆ መውጪያ ቢሰጡ ነው እምንመርጠው፡፡ ያም ሆኖ ኑሮአቸው ሁሌ ጭቅጭቅ የሚሆን ከሆነ ህይወታቸው የተሳቀቀ ሊሆን ነው፡፡ ወይ ደሞ መካንነት፣ አሊያም የጤና ችግር ከተከሰተ፤ በግልጽ ጋብቻው በይፋ የተቋረጠ መሆኑን ማህበረሰቡ ያውቃል።

መዝገቡ ላይ ምልክት ይደረግበታል፡፡ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አለ መጀመሪያ ባለትዳሮቹ ይወያያሉ፤ ካልተቻለ ካካባቢው ሰው ይመክራቸዋል፣ በጣም ከከረረ ኮሚቴው ያየዋል፤ አስተያየት ይሰጥበታል፡፡ ልጆችም ያንን ዓይተው ክፉ ይማራሉ፡፡ ኮሚቴው ለማህበረሰቡ ሂደቱን ያስረዳል። አስተያየት ስጡ ይላል፡፡ አንድ ዕድል ይሰጣል። ካልሆነ ይፋታሉ፡፡ “አንተ አግብተሃል? ወልደሃል?” “ወደ አምስት አሉኝ” “ለዚህ ማህበረሰብ 5 አይበዛም ወይስ ብዙ ተባዙ ነው?” “በእርግጥ፤ አቅም አገናዝቦ መሄድ ያስፈልጋል ይሄ ይበዛል” “አንቺስ?” “ሶስት አሉኝ” “ይማራሉ?” “አዎ” “ትምህርት ቤት ገብተው ኮሌጅ ጨርሰው ሲያበቁ ግንኙነታችሁ እንዴት ይሆናል? ያ ህብረተሰብ ሌላ ይሄኛው ሌላ? የብዙዎቹ ገጠመኝ ሰፊ ልዩነት መኖሩን ነው ያዩት፡፡ አብዛኛው ሌላ ሳይጨምሩ የራሳቸውን ይዘው የመምጣት ፍላጐት አላቸው፡፡ ልጅነት አለ፡፡ ጉልበት፣ በስሜታዊነት መተዳደር ነው በአብዛኛው እሚታየው፡፡” “ውጪውስ አገር?” “እንደዛ አላጋጠመንም” “የተረፈ ምርትስ ነገር አያሳስባችሁም? ሀብት እየበዛ ሲሄድ ነው እኩልነትና ፍትሀዊነት እየጠፋ እሚሄደው ይባላል? ወደ ፋብሪካ ሲለወጥ፣ ወደ ትላልቅ እርሻ ስትገቡ፣ ገበያችሁ ወደ ፋብሪካ ሲለወጥ፣ ወደ ትላልቅ እርሻ ስትገቡ፣ ገበያችሁ ሲሰፋ ምናልባት የሀብት ክፍፍል በዛ ደረጃ አላጋጠማችሁም ይሆናል፡፡” “ያጋጥማል፡፡ ብቻችንን ስንኖርና አሁን ከሰው ጋር መኖር ስንጀምር፤ ምን ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡ አዕምሮንም ለመለወጥም ሆነ ለማጠፍ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

እሚመጣው ነገር ነው ይዞት የሚመጣው፡፡ ያው ባህርዳርም አገራችን ነው፡፡ ቅርንጫፍም እየከፈትንበት ነው፡፡ የሁለቱ ቦታዎች አስተሳሰብ በጣም ይለያያል፡፡ እዚህ አካባቢኮ ወድቆ የተገኘ ንብረት ተጠብቆ የሚቀመጥበት ነው፡፡ እዛ አካባቢ ደሞ እሌላው ኪስ ገብቶ ይዞ እሚኬድበት ቦታ ነው፡፡ ሁለቱን ማዋሃድ በጣም አድካሚ ነው በበቀል ከመፍታት አስተማሪ በሆነ ሲስተም መፍታት ነው - ማሳየት መማማር ያሻል፡፡ እንደሁኔታው ለመለወጥ መሞከር ነው እንጂ ሁልጊዜ እንደደሴት ተቀምጦ የሚመጣው ለውጥ ለውጥ አይባልም” “በሉ አሁን መሬቱ ላይ ያለውን ሁኔታ ደሞ እንይ ውሰዱኝ” አልኳቸው፡፡ “የምናገኘው ገቢ ከቱሪስት የመግቢያ ዋጋም፣ ከፈተላም፣ ከኢንተርኔትም የሚገኘው ከኮኦፕሬቲቩ ሳይቀላቀል ለኮሙኒቲው ገቢ ነው እሚሆነው፡፡ ቀለብ፣ ልብስ፣ ንጽሕና መጠበቂያ ባካባቢ ያሉ ሰዎችን እንዳቅማችን የምንረዳበትን ሁኔታ እሚያመቻች ኮሚቴ አለ፡፡ መጽሔቱ ላይ አለልህ፡፡ ከኑሩና ከጥሩ ሰው ጋር ያረኩትን ቆይታ አበቃሁ። በጠቅላላው ያካባቢውን መኖሪያ ቤትና አኗኗር፣ የማረፊያና ዘመናዊ ቤርጐ ሽንት ቤት፣ ጐብኝቼ ወደ ባህር ዳር ልመለስ ሳስብ፤ ጥሩ ሰው “ዙምራ መጥቷል አግኝው” አለችኝ፡፡ መጀመሪያ ወደገባሁበት መጠነኛ አዳራሽ ሄድን። ዙምራን ቁጭ ብዬ መጠበቅ ያዝኩ፡፡

Read 2962 times