Saturday, 11 January 2014 10:55

ያልወጋ ቀንድ ከጆሮ ይቆጠራል!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ እረኛ ከብቶቹን ወደ ቤቱ እየነዳ ሳለ ወደ በረታቸው መቃረባቸውን በማሰብ ለመዝናናት ወደኋላ ይቀራል፡፡ ሳያስበው ግን በድንገት አንድ ተኩላ ይመጣበታል፡፡ ሮጦ በማያመልጥበት ርቀት ላይ በመሆኑ ባለበት ቆሞ ይቀራል፡፡ ተኩላውም፤ “እንዴት ብትደፍረኝ ነው፤ በእኔ ግዛት፣ በዚህ ምሽት፣ ያለ ፍርሃት እየተዝናናህ ያገኘሁህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ እረኛውም፤ “አያ ተኩላ፤ ብዙ ጊዜ ከብቶቼን እየነዳሁ ስሄድ ታየኛለህ፡፡ እስከዛሬም በጠላትነት ተያይተን አናውቅም፡፡ ስለዚህ በድፍረት ሳይሆን በፍቅር ተሳስበን እንተላለፋለን እንጂ በክፉ አንተያይም በሚል እሳቤ ነው ዘና ብዬ ወደ ቤቴ የምሄደው” አለው፡፡ ተኩላም፤ ነገር ፈልጐ ልጁን መብላት አስቦ ኖሮ፤ “በጭራሽ የንቀት ነው፡፡ ምናልባትም ውሾችህንና ጌታህን ተማምነህ ይሆናል፡፡ ማናቸውንም እንደማልፈራቸው ዛሬ አሳይሃለሁ!” እረኛው በሌላ መንገድ ሊያሸንፈው እንደማይችል ተገንዝቦ፤ “አያ ተኩላ፤ እራትህ ልሆን እንደምችል አውቄያለሁ፡፡

ላመልጥህም እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ውሾቼም ሆኑ ጌታዬ እንደማያድኑኝም ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስለዚህ አንድ ውለታ ብቻ ዋልልኝ፡፡ ከእንግዲህ ዕድሜዬ በጣም አጭር ናትና ተደስቼ እንድሞት ዕድል ሰጠኝ፡፡” ተኩላውም፤ ልጁ ለመበላት ዝግጁ መሆኑ ደስ አለውና፤ “ከመበላትህ በፊት የሚያስደስትህ ምን እንደሆነ ንገረኝና በቀላሉ ላደርገው የምችለው ነገር ከሆነ አደርግልሃለሁ” አለ፡፡ እረኛውም፤ “እባክህ ዋሽንት ንፋልኝ፡፡ ጥሩ ዜማ ሰምቼ ለመሞት እፈልጋለሁ” ሲል ለመነው፡፡ አያ ተኩላም ከእራት በፊት ሙዚቃ መጫወት የሚከፋ ነገር አይደለም ብሎ በማሰብ የእረኛውን ዋሽንት ተቀብሎ መጫወት ጀመረ፡፡ እረኛውም መደነስ ቀጠለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የዋሽንቱን ድምጽ የሰሙ ውሾች፤ “በጭለማ ዋሽንት ማን ሊጫወት ይችላል? ከየት በኩል ነው ድምፁ የሚመጣው?” ተባባሉና ሙዚቃውን ወደሰሙበት አቅጣጫ ሲመጡ፤ አያ ተኩላ ዋሽንት ይጫወታል፡፡ ትንሹ እረኛ ይደንሳል፡፡ ሳያመነቱ ተኩላውን ለመያዝ እየሮጡ መጡበት፡፡ ተኩላው ዋሽንቱን ወርውሮ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ እየሮጠ ሳለ ግን ወደ ልጁ ዘወር ብሎ፤ “ዋና ሥራዬ ልኳንዳ ቤት ነው፡፡ ያገኘሁትን ሥጋ አርጄ መብላት ሲገባኝ እኔን ብሎ ሙዚቃ ተጨዋች! ዋጋዬን አገኘሁ!” እያለ ሩጫውን ቀጠለ፡፡

                                                             * * *

ያለሙያ መግባት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አገኘን የምንለውን ድል በአግባቡ ካልተጠቀምንበትና በዚያ ተኩራርተን ትርፍ መንገድ እንሂድ ካልን የጥፋተኝነታችንን ያህል ኪሣራውን መክፈል ግዴታችን ይሆናል፡፡ ፖለቲከኛው ባለሙያው ሥራ ውስጥ ተሸብልቆ ከገባ፣ ባለሙያ ባንድ ጀንበር ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ ከተፈጠመ፤ ጉዟችን የእውር የድንብር ነው የሚሆነው፡፡ በእጃችን ያለውን ሙያ ትተን የማያገባን ሥር ውስጥ ገብተን መቧቸር ከሁለት ያጣ ያደርገናል። የሰለጠንበት ሙያ ሌላ፤ የምንሠራው ሥራ ሌላ ከሆነ፤ ከሁለት ያጣ እንሆናለን፡፡ የራሳችንንም ሥራ አልሠራን፤ ሌሎችም ሥራ እንዳይሠሩ አደረግን፡፡ የሀገራችን አንዱ ችግር ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመቀመጡ ነው (The right man at the right place እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ)፡፡ ወይ በዘመድ፣ ወይ በታሪክ አጋጣሚ፣ አሊያም በዕድል ያለሙያችን የተቀመጥንበት ቦታ ከልማቱ ጥፋቱ ይበዛል፡፡ ሁሉ በጄ፣ ሁሉ በደጄ ማለታችን አይቀርምና ከእኛ በላይ የሚያውቅን ሰው አላግባብ ማጐሳቆላችን፣ “እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ፣ እኔ ያልኩትን ብቻ ፈጽሙ” ወደሚል ግትርነት ማዘንበላችን አይቀሬ ነው፡፡

“ወዳጄ እጅግ ብዙ ምክር ያዳምጣል፡፡ የማታ ማታ የሚሰማው ግን የራሱን ልቦና ነው” ይለናል ደራሲ፡፡ ያ ደግሞ ለለውጥ አያመችም፡፡ “እግዚአብሔር ሲምር ምክር ያስተምር” የሚለውን ያስዘነጋልና፡፡ የጋራ አገር እንዳለን እንዲሰማን ያስፈልጋል፡፡ በጋራ እንደግ ብሎ ልብን መክፈት ያስፈልጋል፡፡ አገር ጥቂቶች የሚለፉባት ሌሎች የሚያፌዙባት እንዳልሆነች መገንዘብ ይገባል፡፡ ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን “የአገሬ ሰው አብረን ወደላይ እንደግ ሲሉት፤ አሸብልቆ ወደታች ወደመሬት ማጐንቆል ይወዳል!” ይለናል፡፡ ቀጥሎም፤ “አንድም መንግሥት ማለት የአገሩ አዕምሮ እንጂ የልቡ ሮሮ አይደለም” ይለናል፡፡ ሀገራችንን በጋራ ዐይን እንያት፡፡ “ወዳጄ ልቤ ሆዬ የእኔ መከራ ያንተ መከራ አይደለምን?” እንባባል፡፡ (ብላቴን ጌታ ህሩይ እንዳሉት) የሀገርን አንድነት፣ የሀገርን ኢኮኖሚ፣ የሀገርን ባህል፤ ተጠንቅቆ ጠብቆ በቅጥ በቅጡ ለማቆየት፤ በፍቅርና በመተሳሰብ እንጂ “የራቀውን በመድፍ፣ የቀረበውን በሰይፍ” የምንልበት የምንበቃቀልበት፣ የምንጠፋፋበት ዓይነቱ ዘዴ፤ ቢያንስ ዘመናዊ አይደለም፡፡ “ጀግናን ዘገንኩና አፈር ብዬ ተውኩት”፣ እንዳለች ዕድሜዋን ትገፋለች አሉ የጐበዝ አገር እናት፡፡ ዛሬ፤ በዕውቀት ብርሃን የተጋ ዜጋ ያስፈልገናል፡፡

ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአተካሮና የውሃ ወቀጣ ባህልን ዘሎ ማሰብ የሚችል አዕምሮ ብቻ ነው የመፍጠር ክህሎትን የሚቀዳጅ፡፡ ነፃ አዕምሮ ነፃ አስተያየትን ይወልዳል፡፡ ማርክ ትዌን፤ “በእኛ አገር በእግዚሃር ደግነት ሦስት ወደር የሌላቸው ነገሮች ተሰጥተውናል:- የመናገር ነፃነት፣ የሀሳብ ነፃነት እና ሁለቱንም በተግባር ያለማዋል ኩራት” ይለናል። ስለማንነት ሲናገርም “ቦስተን ውስጥ ምን ያህል ዕውቀት አለው? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ኒውዮርክ ውስጥ ምን ያህል ዋጋ አለው? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ፊላዴልፊያ ውስጥ ወላጆቹ እነማናቸው? ተብሎ ይጠየቃል” ይላል፡፡ የትኛውን ነን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በተግባር የማንፈጽመውን አዋጅ ማወጅ፣ የማንከውነውን መመሪያ ማውጣት፣ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ ፖለቲካ ማውራት፣ የሩቁን ትተን የዕለት የዕለቱን ብቻ እያወራን በአየር ላይ መኖር፤ “ያልወጋ ቀንድ ከጆሮ ይቆጠራል” የሚለው ትርጓሜ ነው የምንሆነው፡፡ መሠረት ያለው፣ ዕውቀትን የተንተራሰ ከወሬ ያለፈ ህብረተሰብ ለመገንባት ጥረት እናድርግ፡፡

Read 4257 times