Sunday, 05 January 2014 00:00

አሰቃቂ የትዳር (ፍቅር) መቋጫዎች

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(31 votes)

በዚህ ጽሑፌ በፍቅር ተጀምረው በአሰቃቂ የግድያ ወንጀሎች የተቋጩ የትዳር (ፍቅር) ህይወቶችን ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ከፖሊስ የሰበሰብኳቸው መረጃዎች በርካታ ቢሆኑም ጥቂቶቹን ብቻ መርጬ ለማሳያነት አቅርቤአለሁ፡፡ አንባቢያን መረጃዎቹን አንብበው የራሳቸውን ግንዛቤ ይወስዳሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያም ባሻገር ግን በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር የማካሄድ ፍላጐቱ ላላቸው ባለሙያዎች እንደመነሻ ሊያገለግል ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ታሪኮቹ የቱንም ያህል አስከፊና አሳዛኝ ቢሆኑም ይፋ መሆናቸው በተለያየ መልኩ ጠቀሜታ እንጂ ጉዳት የላቸውም በሚል እንዲህ ተጠናቅረዋል፡፡  

በቅናት ባሏን ጋዝ አርከፍክፋ ያቃጠለች ሚስት…
“ከወንድ ጋር አየሁሽ” ብሎ ፍቅረኛውን በጩቤ የወጋ ወዳጅ--
የልጆቹ እናት ላይ 18 ጥይቶች አርከፍክፎ የገደለ ባል…

          በሸዋሮቢት ካራቆሬ ከተማ የተወለደችው ምንትዋብ ጌታቸው፤ በትውልድ አገሯና በአዲስ አበባ እስከ 9ኛ ክፍል ተምራለች፡፡ በ1989 ዓ.ም በ16 ዓመቷ ትዳር መስርታ አንድ ልጅ ብትወልድም ከባሏ ጋር መስማማት ባለመቻሏ ባገባች በሁለተኛ ዓመቷ ፍቺ ለመፈፀም ተገደደች፡፡
ሻይ አፍልታ እየነገደች ልጇን በማሳደግ ላይ ሳለች ነበር ሽታዬ ሙሉ ከተባለ ሰው ጋር እዛው ሸዋሮቢት የተዋወቀችው - ፍቺ ከፈፀመች ከሁለት ዓመት በኋላ፡፡ የትዳር ጥያቄ ሲያቀርብላት ግን በአንዴ በጄ አላለችውም፡፡ “ሌላ ለትዳር የጠየቀኝ ሰው አለ” በማለት አሻፈረኝ ብላ ነበር፡፡ በኋላ ግን “እህትሽ እኮ ፈቅዳለች” ብሎ በማግባባት የጋብቻ ጥያቄውን እንድትቀበል አደረጋት፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው። ከመጀመሪያ ባሏ የወለደችውን ልጇን ይዛ ኮተቤ አካባቢ ቤት በመከራየት አዲስ የትዳር ህይወት ጀመረች- ከአዲሱ ባለቤቷ ጋር፡፡ ብዙም ሳትቆይ ከሁለተኛ ባሏ ሁለተኛ ሴት ልጅ የወለደችው ምንትዋብ፤ በትዳሯ ግን ደስተኛ እንዳልነበረች ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ባሏ ሰክሮ እየገባ ይደበድባት ስለነበር በተደጋጋሚ ከቤት እየወጣች በሽምግልና ታርቃ መመለሷን ትናገራለች።
ሆኖም በዚህ መቀጠሉን ባለመፈለጓ፣ ልጆቿን ለእናቷ ሰጥታ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ወደ ኩዌት  ተጓዘች፡፡ ለዘጠኝ ወራት ያህል ከሰራች በኋላ ግን ችግር ገጠማት - ከኩዌት አሰሪዎቿ ሳይሆን ከአዲስ አበባ፡፡ ባለቤቷ “ሚስቴን አረብ አገር የላካችኋት እናንተ ናችሁ” በማለት ቤተሰቧን እንደሚበጠብጥና እንደሚያስፈራራ ስለሰማች፣ ሥራዋን ጥላ ወደ አገሯ መመለሷን ተናግራለች፡፡ ከዚያም ልጆቿን ከእናቷ ቤት አምጥታ  ከባሏ ጋር እንደገና መኖር ጀመረች፡፡ በኩዌት ሰርታ ባጠራቀመችው ከ20ሺ ብር በላይ ቤት ገዝታ  ከኪራይ ቤት ወጡ፡፡ በ2002 ዓ.ም ሁለተኛ ሴት ልጅ ደገሙ፡፡ ሆኖም ባለቤቷ ከእሷ በፊት ጐጃም ከነበረው ትዳሩ ሦስት ልጆች መውለዱን የሰማችው ምንትዋብ፤ “ለምን ደበቅኸኝ” በሚል ሰበብ ጭቅጭቅ ማንሳቷ አልቀረም፡፡ ባለቤቷ አንዱን ልጁን ክረምቱን አብሯቸው እንዲያሳልፍ ከጐጃም ማምጣቱ ደግሞ ጭቅጭቁን  አባባሰው፡፡ በመሃላቸው ሽማግሌዎች ገብተው፣ ሁለቱም ከሌላ የወለዱትን በውጭ እየረዱ በጋራ የወለዷቸውን አብረው እንዲያሳድጉ በመወሰናቸው ችግሩ በዚሁ እልባት አገኘ፡፡
ጥንዶቹ፤ የከፋ ጠብ ውስጥ የገቡት ሽታዬ የጤና እክል ገጥሞት ምንትዋብን ገንዘብ እንድትሰጠው በጠየቃት ጊዜ ነው፡፡ ሚስት ገንዘብ እንደሌላት ስትነግረው “ገንዘቡን ካላመጣሽ እዚህች ቤት አትገቢያትም” ብሎ እንደዛተባት ምንትዋብ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ገልፃለች፡፡ መጀመሪያ ላይ ወርቋን አስይዛ ገንዘቡን ከሰው ለመበደር አስባ እንደነበር ትናገራለች፡፡ በኋላ ግን ወደ ክፉ ሃሳብ ዞረች፡፡
ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ምንትዋብ ከጐረቤት በተዋሰችው መጥረቢያ፤ ባለቤቷን በተኛበት  ሁለት ጊዜ ጭንቅላቱ ላይ “እንካ ቅመስ” በማለት እንደገደለችው የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል። አሁን ምንትዋብ በከባድ ሰው የመግደል ወንጀል ተከስሳ፣ ፍርዷን በማረምያ ቤት ሆና በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ወታደር እዮብ ጌታቸው ናዝሬት ነው የተወለደው፤ በ1982 ዓ.ም፡፡ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ከተማረ በኋላ ሁርሶ ማሠልጠኛ በመግባት፣ ለሦስት ወር በእግረኛ ወታደርነት ሰልጥኖ በትግራይ ክልል ዲንሻ አካባቢ ተመድቦ መሥራት ጀመረ፡፡ በሀምሌ ወር አጋማሽ 2004 ዓ.ም ላይ ታሞ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ጦር ሀይሎች ሪፈራል ሆስፒታል የተላከ ሲሆን “ወባ አለብህ” ተብሎ በተመላላሽ ሲታከም ከቆየ በኋላ፣ ስላልተሻለው የአመት ዕረፍት ወስዶ አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡
በዚህ መሃል ነበር ከዚህ ቀደም አጠና ተራ አካባቢ በ200 ብር አብሯት ያደረውንና በሴተኛ አዳሪነት የምትተዳደረውን “ሰላማዊት” የተባለች ሴት ያገኘው፡፡ መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም ሌሊቱን አብረው ለማደር 200 ብር ሊከፍላት ተስማማ፡፡ እሷ መጠጥ ስለማትጠጣ አስፈቅዷት ሌላ ቦታ ሲጠጣ ይቆይና ከሌሊቱ 6፡00 ገደማ ወደ መኝታ ክፍሉ ይመለሳል፡፡ “ሰላማዊት” አኩርፋ እንደጠበቀችው የሚናገረው እዮብ፤ “ከሌላ ሴት ጋር ተኝተህ ነው የመጣኸው፤ ድሮም ወታደሮች ስትባሉ ሸርሙጦች ናችሁ” በማለት እንደሰደበችውና ተደባድበው መተኛታቸውን ተናግሯል፡፡ ከሌሊቱ 11፡00 ሰአት ላይ ትንሽ በረድ ብሎላታል በሚል ግንኙነት እንዲፈጽሙ ሲጠይቃት ግን የማታውን ዓይነት ስድብ ደግማ እንደሰደበችው የገለፀው ወታደር ኢዮብ፤ ይሄኔ ተናዶ አንገቷን አንቆ እንደገደላት ለፖሊስ የሰጠው ቃል ይጠቁማል፡፡ ወታደር ኢዮብ በከባድ ሰው የመግደል ወንጀል ተከስሶ፣ በማረምያ ቤት ፍርዱን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
በሰሜን ወሎ ላስታ ላሊበላ የተወለደው በሪሁን መብሬ፤ ወደ አዲስ አበባ የመጣው የአባቱን ሞት ተከትሎ  ከእናቱ ጋር ነበር - በ1997 ዓ.ም ፡፡ በ16 ዓመት የታዳጊነት ለጋ ዕድሜው ከአዲስ አበባ ጋር የተዋወቀው በሪሁን፤ ቀን እየሰራና ማታ እየተማረ እናቱንና እህቱን ይረዳ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ትዕግስት አበራ ከተባለች ወጣት ጋር ተዋወቀ፡፡ ለአራት አመታት በፍቅር ከቆዩ በኋላ ግን ትዕግስት አብራው በፍቅር  መቀጠል እንደትማፈልግ ነገረችው፡፡ በሪሁንም፤ “እኔ ወደ ክ/ሀገር እስክሄድ ድረስ ከማንም ወንድ ጋር እንዳላይሽ” ሲል እንዳስጠነቀቃት ለፖሊስ ከሰጠው ቃል መረዳት ተችሏል፡፡ ሆኖም ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም በቦሌ ክ/ከተማ  ልዩ ቦታው ጐሮ ገብርኤል በተባለ ስፍራ ከምሽቱ 1፡00 ሰአት ገደማ ላይ ሙልዬ ከተባለ ወንድ ጋር ቆማ ያያታል፡፡ ይሄኔ ነው ጠጋ በሎ “ከወንድ ጋር እንዳላይሽ ብዬ አልነበረም?” ሲል በኃይለቃል የጠየቃት፡፡  “ምን አገባህ!” ስትል እሷም በቁጣ እንደመለሰችለት በሪሁን ያስታውሳል፡፡ ወዲያው መለስ ይልናም አብሯት የቆመውን ሙሉዬ የተባለ ወጣት፤ “አብረሃት እንዳላይህ አላልኩህም” ብሎ ያፈጥበታል፡፡ “እኔ አይደለሁም የጠራኋት፤ እሷ ናት የጠራችኝ” በማለት ይመልሳል - ወጣቱ፡፡ በሪሁን እንደገና ወደ ትዕግስት ዞሮ “ከማንም ወንድ ጋር እንዳላይሽ አላልኩሽም ወይ?” ሲላት አሁንም ደግማ “አያገባህም!” ትለውና አብሯት የነበረውን ወጣት ጠርታ ይዛው ትሄዳለች፡፡
በሪሁን በድርጊቷ በግኖ ወደ ቤቱ በመሄድ፣ ከወሎ ያመጣውን ብረት ለበስ ስለት ይዞ እንደወጣ ይናገራል፡፡ ትዕግስትን ለብቻዋ አግኝቷት ሊያነጋግራት ቢሞክርም “አትንካኝ” በማለት እንዳመናጨቀችው  የገለፀው በሪሁን፤በያዘው ስለት ጡቷና ጀርባዋ ላይ ወግቶ ገድሏታል፤ የክስ መዝገቡ እንደሚጠቁመው፡፡  በሪሁን በፈፀመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሶ ፍርዱን እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ የተወለደው የወንደሰን ይልማ፤ በ1998 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ነበር ከሁለት ዓመት ፍቅረኛው ፍሬህይወት ታደሰ ጋር በቤተክርስቲያን ውስጥ ጋብቻውን  የፈፀመው፡፡
ሁለት ልጆች ወልደው በሠላም እየኖሩ ሳለ በመሃል በሚከሰቱ ጠቦች ባለቤቱ ከቤት እየወጣች ቤተሰቧ ጋር ትሄድ እንደነበር የሚናገረው የወንድወሰን፤ “በዚህም የተነሳ ታምሜ እተኛ ነበር” ሲል ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ጠባቸው እያየለ በመጣበት በ2003 ዓ.ም ግን ፍሬህይወት ቤተሰቧ ጋ አልነበረም የሄደችው፡፡ ቦሌ አካባቢ ቤት ተከራይታ ከሁለት ልጆቿ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ በተደጋጋሚ ሽምግልና ብልክባትም አሻፈረኝ አለች ይላል - የወንደሰን። ለአንድ ዓመት ተለያይተው ለየብቻ ቢኖሩም ታርቀው አብረው እንደሚኖሩ ተስፋ ያደርግ እንደነበረ የሚናገረው የወንደሰን፤ ባለቤቱ ግን የፍቺ ማመልከቻና የንብረት ማሳገጃ ወረቀት ከፍ/ቤት እንዳመጣችለት ይገልፃል።
በዚህ መሃል ልጆቹ ማየት እንዳልቻለ የሚያስታውሰው የወንደሰን፤ ለፍ/ቤት አመልክቶ ልጆቹን ቅዳሜ ቅዳሜ እንዲያያቸው ተወስኖለት ነበር፡፡ ልጆቹን ሲያገኛቸው ግን “ለምን መጣህ? አንተ አባታችን አይደለህም? አባታችን ጋሼ ነው” በማለት የጥላቻ ስሜት ያንፀባርቁበት እንደነበር ገልፆ በዚህም በእጅጉ ስሜቱ እንደተጐዳ ለፖሊስ ገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም በ10ሺህ ብር ከሰው ላይ በገዛው ክላሽ  የልጆቹ እናት ላይ 18 ጥይቶችን በማርከፍከፍ ህይወቷን ያጠፋ ሲሆን፤ ፍርዱን በማረምያ ቤት ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
በጐንደር አምባጊዮርጊስ የተወለደችው አማረች አቸናፊ፤ እናትና አባቷ ከሞቱ በኋላ ነበር በ14 ዓመቷ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሰው ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ መስራት የጀመረችው፡፡  በ2002 ዓ.ም ግን ፍቅረኛዋ ከነበረው ዳንኤል የተባለ ግለሰብ ጋር በአንድ ጐጆ ውስጥ የጋራ ኑሮ ይጀምራሉ፡፡ አማረች እንደምትለው፤ ፍቅረኛዋ አምሽቶ እየመጣና ከተለያዩ ሴቶች ጋር በስልክ እያወራ ያበሳጫት ነበር። የከፋ ነገር የተፈጠረው ግን ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ነበር፡፡ ከምሽቱ 4፡00 ላይ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የባሏን ድምፅ ሰምታ መውጣቷን የተናገረችው አማረች፤ ባለቤቷ ከጐረቤት ሴት ጋር ቆሞ ሲያወራ እንዳየችው ለፖሊስ ገልፃለች፡፡ ቤት ከገባም በኋላ ስልክ ደውሎ “ገብቻለሁ… አታስቢ” ብሎ ሲያወራ መስማቷንና  ይሄም በመካከላቸው የከረረ ጭቅጭቅ መፍጠሩን አስታወሳ፤ጐረቤቶቻቸው እሱን ጠርተው  “አትረብሹን” እንዳሉት ትናገራለች፡፡ በጐረቤቶቹ ንግግር የተበሳጨው ባለቤቷም፤ “አዋረድሽኝ” በማለት ልብሱን በፌስታል ሸክፎ ይተኛል። “ሁልጊዜም ጩቤ ከኪሱ ስለማይጠፋ ልብሱን የሰበሰበው ገድሎኝ ሊጠፋ ነው” የሚል ስጋት ያደረባት አማረች፤ ባለቤቷ እንቅልፍ እስኪወስደው ጠብቃ ሶስት ሊትር ጋዝ ሰውነቱ ላይ በማርከፍከፍ ክብሪት እንደለኮሰችበት ጠቁማ፤ ጭንቅላቱ አካባቢ እሳቱ ሲሰማው እንደነቃና “አድኑኝ” እያለ ሲሮጥ በዱላ ጭንቅላቱን ደጋግማ እንደመታችው ተናግራለች፡፡ ተጐጂው ባለቤቷ በየካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ቢያገኝም  ህይወቱ ሊተርፍ አልቻለም፡፡ አማረችም በማረሚያ ቤት ሆና ፍርዷን እየተጠባበቀች ነው፡፡  

Read 9206 times