Saturday, 28 December 2013 12:06

ቅኔን ሳያውቁ ቅኔን መፍታት ታላቅ ድፍረት!

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሸራ
Rate this item
(15 votes)

በኢትዮጵያ እንደ አበባ ከፈኩት ጥበባት ውስጥ አንዱና በሌላው አገር የሌለው የግዕዝ ቅኔ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ፣ በግዕዝ ተገጥሞ የሚቀርብ ሥራ ቅኔ መሰኘቱ የረቀቀና የመጠቀ ሐሳብ እጥፍ ድርብና መንታ ፍልስፍና ስለሚተላለፍበት ነው፡፡ ይህም ማለት ቅኔ የራሱ መነሻ ሰበብ፣ መድረሻ ምኩራብ አለው ማለት ነው፤ ትንሲቱ ብዙ ነው፡፡
ከጥንት ዘመን ጀምሮ ቅኔያት ከታላላቅ ሊቃውንት አእምሮ እንደግዮን ምንጭ እየፈለቁ ሲፈስሱ ኖረዋል። “ይበል እሰየው” እየተሰኙ በመደነቅም  ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል  ሲተላለፉ ኖረዋል። የተወሰኑትም እየተንባጠቡና እየነጠቡ ጠፍተዋል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ታላቅ ቅርስና የአዕምሮ ፈጠራ የተቆረቆሩ ጥቂት ለባውያን ቅኔያትን ለማሳተም ጥረት አድርገዋል። ለቅኔ ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ከአሰባሰቡ የውጭ ሀገርና የአገር ውስጥ ምሁራንና ሊቃውንት መካከል ጣልያናዊው ኢኞሲዮ ጉይዲ (1901 ቅኔ ኦ .ኢኒ አቢሲኒ) በሚለው መጽሐፉ 44 ቅኔያትን፣ ፈረንሳዊው አንቶን ዲ አባዲዩ (1908 ልዳ ከልታ ዲ ቅኔ ኤም ኤስ) 86 ቅኔዎችን፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር (1951 የዐባይ ውሃ ልማት መጀመሪያ መሠረት) 79 የቅኔ ፈጠራዎችን፣ አለቃ ይኹኖ አምላክ ገብረ ሥላሴ/1958 የጥንት ቅኔዎች/ 22 ቅኔዎችንና በትክክል የትርጉም ይትበሃሉን ጠብቀው ወደ አማርኛ የተረጐሙ/ ይሄይስ ወርቄ 1960 ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት አዕማደ ምሥጢራት/ 79 ቅኔዎችን በአግባቡና በጥልቀት የተረጐሙ፣ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማርያም ወርቅነህ  (1963 ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት) 107 ቅኔዎችን፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ (1963 -1984 መጽሐፍ ቅኔ ዝክረ ሊቃውንት) 2829 ቅኔዎችን ያለ ትርጓሜ፣ አቅርበውልናል፡፡ ከፍያለው መራሂ (ቀሲስ) 2006 እ.ኤ.አ The meaning of quine; the river life) 31፣ ቋንቋዎች አካዳሚ (1980፣1984፣1955) በሦስት ክፍል 1143 ቅኔያትን የግዕዝ ቅኔያት፤ ከእነተርጉማቸውና ትንታኔያቸው፣ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑልና ቀሲስ ከፍያለው መራሒ (1992 ትርጓሜ ቅኔ ፈለገ ሕይወት) 120 የቅኔ ድርሰቶችን፣  ታደለ ገድሌ (1997 ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ) 47 ቅኔዎችን ወደ አማርኛ በመመለስ፣ ብርሃኑ ድንቄ /1997 አልቦዘመድ/ 10 ቅኔያትን፣ ያሬድ ሽፈራው ሊቀሊቃውንት (2002 መጽሐፈ ግስ ወሰዋሰው መርኖ መጻሕፍት) የራሳቸውን 213 ያለ ትርጉም፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ኤስድሮስ (2002 የመምህር አካለወልድ የሕይወት ታሪክና ቅኔዎቻቸው) 184 ቅኔዎችን ወደ አማርኛ በመቀየር፣ ዕደ ማርያም ጸጋ ተሻለ/2003 የሊቀ ካህናት ጸጋ ተሻለ የሕይወት ታሪክ) 28 ቅኔያዊ ፈጠራዎችን ወደ አማርኛ በመቀየር አሰባስበው አቅርበውልናል፡፡
አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ (1951 የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ዩኩኖ አምላክ እስከ ዓፄ ልብነ ድንግል) 25 የዓፄ ናዖድ የቅኔ ድርሰቶችን ከገድለ ፋሲለደስ ውስጥ አሰባስበው ሲያሳትሙ፣ አለቃ ዕንባቆም ቃለ ወልድ 33 የግዕዝ ቅኔያትን (ያልታተሙ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ሰንደውልናል፡፡
ዓለማየሁ ሞገስ (1961 ሁለት ወር በዋሸራ) 1976 የዋሸራ ቅኔዎችን አሰባስበውና ጽፈው አስቀምጠውልናል። ቅኔያቱ ገና አልተተረጎሙም፣ አልተተነተኑምም፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎች ከኢኛሲዮ ጉይዲና አንቶን ዲ.አባዲ በስተቀር እንዲሁም አቶ ተክለዳዊት መኩሪያ (መሠረታዊ የቅኔ ዕውቀት ግንዛቤ እንደነበራቸው ብቻ ተገንዝቤያለሁ) ሌሎች ቅኔ ቤት ገብተው ግስ የገሠሡ፤ በተለይም እንደነ መምህር አካለወልድ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አድማሱ ጀምበሬ፣ ይኄይስ ወርቄ፣ ይኩኖ አምላክ ገብረ ሥላሴ፣ ዓለማየሁ ሞገስ፣ ያሬድ ሺፈራው የመሳሰሉት በዕውቀት ሠገነት ላይ ወጥተው የሚቀመጡ ሊቃውንት መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡
“ላይፈቱ አይተርቱ” እንዲሉ ይህንን ሁሉ የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሰሞኑን በታላቁ የቅኔ ፈላስፋ በተዋነይ ዘጎንጅ ስም አንድ መጽሐፈ-ቅኔ ታትሞ በማየቴ ነው፡፡ መጽሐፉን ማየት ብቻ ሳይሆን የገዛሁበት ትንሲቱም እንዲህ ነው፡፡
ሰሞኑን ከዋሸራ ማርያም ተነሥቼ ወደ ባሕር ዳር የምሔድበት ጉዳይ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ባሕርዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ለጸሎት እንደቆምኩ አንድ መጽሐፍ አዝዋሪ የታላቁን የቅኔ ፈላስፋ የተዋነይን ስም የያዘ መጽሐፍ አሳየኝ፡፡ ወዲያው ከጸሎቴ ተናጠብኩና መጽሐፉን ተቀብዬ በዓይነ ገመድ አየት አየት አደረግሁት፡፡ የዋሸራ ሰው ደግሞ ከገንዘብ ይልቅ ለቅኔ ስሱ ስለሆነ ዋጋው ስንት ነው? ብዬ መጽሐፍ አዝዋሪውን ጠየቅሁት፡፡
“ዋጋው ከጀርባው ላይ አለ፤ 100 ብር” አለኝ። የመጽሐፉ ወረቀት ከግማሽ በላይ ባዶ ነው፡፡ ትናንሽ መስመር ያላቸው ቅኔዎች (ለምሳሌ አንዲት ባለ ሁለት ቤት ጉባዔ ቃና ቅኔ በአንድ ገጽ ላይ ሠፍራ ሌላው ወረቀት ባዶ ነው፡፡ በሚቀጥለው ገጽ ግን አቶ ኤፍሬም የቅኔያቱን ሰማዊ ፍች ወደ ግጥም ቀይሮ፣ ከባለ ቅኔው እሳቤ ውጭ ቃላት ደርድሮ ገጹን ለመሙላት ሞክሯል፡፡
የመጽሐፉ ርእስ “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሊቃውንት” ይላል፡፡ አሳታሚው “ሻማ ቡክስ” ነው። የመጽሐፉ ገጽ 190 ሲሆን ቅኔያቱ ሁለት ሦስት እየሆኑ በየገጹ ቢስተናገዱ ኖሮ፣ መጽሐፉ ከ50 እና 60 ገጽ አይበልጥም ነበር፡፡ ስለዚህ አንባቢው ለዚህ መጽሐፍ 100 ብር የሚከፍለው ለባዶው ወረቀት ጭምር ነው፡፡
አቶ ኤፍሬም ሥዩም የተለመዱ ቅኔዎችን ከተለያዩ መጻሕፍት ቀንጭቦ 24 ጉባዔ ቃናዎችን፣ 6 ዘአምላኪየዎችን፣ 2 ሚበዝጐዎችን፣ 10ዋዜማዎችን፣ 10 ሥላሴዎችን፣ 1 ዘይዕዜ፣ 1 ሣህልከ፣ 1 ኩልክሙ፣ 13 መወድሶችን፣ 5 ክብር ይዕቲዎችን፣ 2 ዕጣነ ሞገሮችን፣ 2 አርኬዎችን፣ 1 ምስጋና /የያሬድ/፣ 1 ደረጃ ያልሰጠውና የሌለው (ግን የድሮ ባለ ሦስት ቤት ክብር ይዕቲ)፣ 2 ጥቅሶችን፣ በድምሩ የአቶ  በላይ መኮንንን ቅኔ ጨምሮ 83 ቅኔዎችን አሳትሟል፡፡ ማሳተም ብቻ ሳይሆን የቅኔዎችን ሰማዊ ትርጉም ወስዶ በራሱ መንገድ ወደ አማርኛ ግጥም ቀይሯቸዋል፡፡ ኤፍሬም አንዷን ባለ ሁለት ቤት ጉባዔ ቃና ዘተዋነይ (ገጽ 60) ከተዋነይ መንፈስና ዕሳቤ ውጭ በ3 ገጽ ግጥም ጽፎባታል፡፡ እዚህ ላይ የምናስተውለው የባለቅኔዎችን የመጠቀና የረቀቀ ምሥጢር ሳይሆን የኤፍሬምን ፈንታዚያ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በነጻና በውርስ ትርጉም ስም በቅኔ ጥበብ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ቅኔ ደግሞ የወሸነኔ ስሜት መግለጫና መቀለጃ አይደለም፡፡ የቅኔ ይትበሀሉንና ሊቃውንቱንም መናቅ ነው፡፡ ለቅኔ ዋናው ተፈላጊ ነገርኮ ወርቁ ውስጠቱና ማሩ ነው፡፡ ሰሙ፣ ሰፈፉ፣ ገለባው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ገጽ 64 የቅኔ ቁጥር 21 “ሙሴ በታቦር እመ ትሬዒ ደመና፡፡ ኢይሞሰልከ እስኩ ዘይወርድ መና፡፡ ርዒተ መና ጥዑም አምጣና ተርፈ በሊና፡፡” የሚለውን ቅኔ፣ ኤፍሬም በመሰለው ግጥም ቢያደርገውም የራሱ ምሥጢር አለው፡፡ እና ምሥጢራትን፣ ወርቃዊ መልዕክቶችን ኤፍሬም ለምን አላነጠራቸውም? ግልጽ ነው፡፡ ራሱም እንዳለው ቅኔ ቤት ገብቶ ግስ አልገሰሰም፣ ተነሽና ወዳቂውን፣ ሩቅና ቅርቡን፣ ነጠላና ብዙውን፣ ረቂቁንና ግዑዙን፣ ጨለማና ብርሃኑን፣ ሰያፉን፣ አንቀጹን፣ ባለቤቱን፣ አቀባዩን፣ ዘርፍን አያያዙን፣ ዋዌውን፣ ገቢር ተገብሮውን፣ መዳቡን፣ ዕርባ ቅምሩን፣ ዕርባ ግሱን፣ ክረምትና በጋውን፣ ተባእቱንና አንስቱን፣ ዕፀዋቱን፣ አዝዕርቱን፣ ጠሉን እነ ራምኖንን፣ እነ ጳውቄናን … አልተማረም፡፡
ቅኔ ደግሞ በጨለማ የሚገቡበት፣ በነጻ ወይም በውርስ ትርጉም ስም የሚፏልሉበት ጥበብ አይደለም። ቅኔ ያልቆጠረ፣ ቅኔ ያልነገረ ሰው በድፍረት ዐደባባይ የወጣበት ዘመን ቢኖር ይህ ያለንበት ጊዜ ነው፡፡ የቅኔ ምሥጢሩ እንጂ መንፈሱ አይወረስም፡፡ ሰም በቅኔው ዙሪያ ለመሽከርከር የሚያጅብ ሚዜ እንጂ ዋናው ሙሽራው ወርቁ ነው፡፡ ሁለቱ አይለያዩም፡፡ አንዱ ከአንደኛው ተነጥሎ ቢቀርብ አይደምቅምም አያምርም። እሳት የሚጫረው ዐመዱ ተገልጦ ነው፡፡
ቅኔ በስማበለው አይታወቅም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ቤተልሔም አካባቢ የሚንገላወደው ሰሞነኛና አማርኛ ግጥም መግጠምና ቃላት መደርደር፣ መደረት የቻለ ሁሉ ባለቅኔ ይሆን ነበር፡፡ ለመሆኑ ነጻ ወይንም ውርስ ትርጉም ማለት ምን ማለት ነው? በእኔ ትሑት አረዳድ ነጻ ወይንም ውርስ ትርጉም የሚባለው በአንድ የውጭ አገር ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ተመሥርቶ የተሠራን የጥበብ ሥራ ወደ አገርኛ ቋንቋ ሲመለስ/ሲተረጐም/የአገራዊ ባህልን፣ አኗኗርን፣ ታሪክንና፣ ለዛን እንዲመስል ተደርጐ መተርጐም ይመስለኛል። ይኸውም አገሬውን እንዲመስል፣ የራሳችን መስሎ እንዲሰማንና እንዲገባን ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ነገር ግን ቅኔ የራሳችን ሀብትና ትውፊት እንደመሆኑ ይትበሃሉን ጠብቀን ሰም፣ ወርቅ፣ ምሥጢር ብለን መፍታት ሲገባን ውርስ ትርጉም እንጠቀም ዘንድ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ኤፍሬምም ቢሆን የውጭ አገር ዜጋ አይመስለኝም፡፡
በእርግጥ ለቅኔና ለሊቃውንቱ አክብሮትና ፍቅር ሰጥቶ፣ ይህንን ሥራ በድፍረትም ቢሆን መሞከሩ ያስመሰግነዋል፡፡ ቢሆንም እርሱ ያለው ስሜቱ እንጂ ዕውቀቱ ስላልሆነ ቅኔን ደፍሮ ይኸ ሰሙ፣ ይኸ ወርቁ፣ እያለ ባለመተንተኑ አልፈርድበትም፡፡ በእኔ አስተያየት የመጽሐፉ ትልቁ ጉድለት የሚመስለኝ የታላቁን ፈላስፋ የተዋነይን ስም ይዞ፣ ስለተዋነይ የሕይወት ታሪክና ሥራ በጥቂቱም ቢሆን አለማተቱ ነው፡፡ ብዙ ሰው ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚለውን ርእስ ሲመለከት የበርካታ ነገሥታት ቅኔዎች የተካተቱበት ሊመስለው ይችላል፡፡
ግን በመጽሐፉ ውጥ የምናገኘው ባለቅኔ ንጉሥ እስክንድር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ያው የተለመደው ከተዋነይ ጋር ገጥሞ የዘረፈው ሥላሴ ቅኔ ነው። ይልቅስ እውነቱ በተዋነይና በነገሥታት ስም ገበያ ፍለጋ ነው፡፡ ሥራው መክሊት እንጂ እውቀት ፍለጋ አይመስልም፡፡
በብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ውስጥ የትላንቶቹ እነ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ አድማሱ ጀንበሬ፣ አራት ዓይና ጐሹና ሌሎች ተጠቅሰዋል፡፡ እና እነዚህ ሊቃውንት ለአቶ ኤፍሬም የብሉይ ዘመን ሰዎች መሆናቸው ነው? አቶ ኤፍሬም የብሉይ ዘመንን ቀመር ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ከዚህ እስከዚህ የብሉይ፣ ከዚህ እስከዚህ የአዲሱ ዘመን ቅኔ ነው ብሎ፡፡ በአቶ ኤፍሬም ሥዩም ሥራ ላይ በእጅጉ ያሳፈረኝ ደግሞ የአቶ በላይ መኮንን ምሥክርነት ነው፡፡ አቶ የምለው “ሊቀ ህሩያን” የተሰኘውን ማዕረግ የትኛው ሕጋዊ አካል እንደሰጠው ስለማላውቅ ነው፡፡ ለእኔ ራስን ከፍ አድርጐ ከማየት የመነጨ ሲመተ ርእስ ይመስለኛል፡፡
አቶ በላይ “ቅድመ መቅድም” በሚለው የመጽሐፉ ክፍል፣ ኤፍሬምን የጠቀመ መስሎት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኛቸውን ዲግሪዎች ጨምሮ ስለራሱ ማንነት ነግሮናል፡፡ ኤፍሬም “የቅድመ መቅድም” ቦታ ሰጥቶት የመሠከረለት ይመስላል፡፡ ቅድመ መቅድም ደግሞ ሌላ መቅድም ሲኖር ነው የሚፃፈው፡፡ የኤፍሬም ግን “መግቢያ” ነው የሚለው፡፡
አቶ በላይ ለራሱ ያህል ቅኔ ቢዶገዱግ እንጂ ለሰው የሚተርፍ ዕውቀት ያለው አይመስለኝም። አቶ በላይ እውነተኛው ቅኔ አዋቂ ቢሆን ኖሮ፣ ቅኔ በወረቀት ላይ እንደ ግጥም እየጻፈ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አያነብም ነበር፡፡ ቅኔ በቃል ይዘረፋል እንጂ ተጽፎ አይነበብም፤ ነውር ነው፡፡ ይህንን ምን ዓይነት የቅኔ መምህር እንዳስተማረው አላውቅም። አቶ በላይ አቶ ኤፍሬምን “ይበል የተባለለት ባለ ቅኔ ነው” (ተዋነይ ገጽ 2) እያለ ያዳነ መስሎ ከሚገድለው፣ ስሕተቱን አርሞና በበለጠ አውቆ እንዳይገኝ ከሚያደርገው፣ ቀድሞ ነገር ራሱ ወደ ቅኔ ቤት ሄዶ ቅኔውን ቢያለዝብና ቢቀጽል ይሻላል፡፡ ያኔ እግረ መንገዱን ኤፍሬምንም መቋሚያ አስይዞ ቢያስከትለው አይከፋም፡፡ ወደ ዋሸራ ከመጣም እንቀበለዋለን፡፡
ከንቱ ሙገሳ ሰውን አያሳድገውም፡፡ አንድ ጋትም ወደፊት አያራምደውም፡፡ አቶ በላይ በቅኔው ዘርፍ የበቃሁ ነኝ ካለ ትውልዱን ማስተማር፣ መንገድ ለጠፋው መንገድ ማሳየት ይገባል እንጂ “ስማ ምሥክሬ” ብሎ መፎከር የለበትም፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዲሉ፡፡ ድፍረት ደግሞ ግብዝነት ይመስለኛል፡፡ መድፈር የደቦ ሥራ የሆነውን እንደዐባይ ዓይነቱን እንጂ በረቀቀና በመጠቀ የግለሰብ ፈጠራ ላይ የተመሠረተውን የግዕዝ ቅኔን አይደለም፡፡ “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ጠፋ” እንደሚባለው፣ የኢትዮጵያ የቅኔ ሊቃውንት ሞተው ሳያልቁ በቁማቸው አራሙቻ ማልበስ አይገባም፡፡
ይህ ድርጊት ባለ ቅኔዎችን መናቅና ክብር ማሳጣት ነው፡፡ በቅኔ አዋቂነታቸው የመጠቁና የረቀቁ የቅኔ ፈላስፋዎችን ሥራ ማዋረድ ነው። የቆየውንና ነባሩን የቅኔ ቅርስ ማበላሸት ነው። የባለ ቅኔዎቹ ስምም በአግባቡ አልተጠቀሰም፡፡ ለምሳሌ በገፅ 164 ላይ የተጠቀሰው ጉባዔ ቃና የሊቁ መሪጌታ ስመኝ ሆኖ ሳለ፣ ተርጓሚው በአግባቡ አልጠቀሳቸውም፡፡ በአጠቃላይ የተደነቁት ሊቃውንት ቅኔ ግዕዙንም፣ የቅኔውን ምንነትም በማያውቅ ሰው ሊፈታ አይችልም፡፡ ይህ አንባቢንም ቲፎዞንም ማደናገር ነው። ምክንያቱም የአሁን ዘመን ሥራ የሚሠራው በቲፎዞ ስለሆነ ነው፡፡  መካሪውን፣ መሥካሪውን፣ ተመካሪውንም ያስነቅፋል፡፡
ለማንኛውም አስተያየቴን በጥበቡ አባአጋር መወድስ ቅኔ ላጠቃልለው፡፡
መወድስ
የመስከረም በሬ ዲያቆን ደርሶ የሚያገሳ፣
ሙጃ መክፈልት እስመ ለከርሱ ሰጠጦ፣
ወለድማሁ ዐቢይ ፀዊረ ጋዘና መለጦ፣
መሪር ልሳነዚአሁ እስመ ኮነ ግብጦ፡፡
ወቃለ መምህር ለእመ ሰምአ
ፈሪ ዲያቆን በረዊጽ ያመልጦ፡፡
ለዲያቆን ሂ ፀረ ተማሪ እንተ ያገንብጥ ቂጦ፤
ኤርትራ ቤተልሔም ከመፈርአን ትውህጦ፡፡
እመኒ ነጻረ ዓይነዚአሁ ገልብጦ፡፡
መክፈልት ጋለሞታ ለልበዚአሁ ትመስጦ፡፡


Read 9235 times