Saturday, 28 December 2013 11:04

በድምፃዊት ሚካያ በኃይሉ ሕልፈት ብዙዎች አዝነዋል

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(21 votes)

“ሸማመተው” በሚለው አልበሟ ከፍተኛ እውቅናን ያገኘችው ድምፃዊት ሚካያ በኃይሉ፤ በ36 አመቷ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት አርፋለች፡፡ ድምፃዊቷ ብዙ መሥራት ስትችል ያለ ዕድሜዋ በማረፏ ብዙ አድናቂዎቿ አዝነዋል፡፡ ለሶስት ወራት በደም ሥር መቆጣትና በከፍተኛ የጨጓራ ህመም ስትሰቃይ የቆየችው ሚካያ፤ ለህክምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብታ ህይወቷ እንዳለፈ ታውቋል። በአዲስ አበባ የተወለደችው ሚካያ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ውስጥ የማስተርስ ድግሪዋን የመመረቂያ ፅሁፍ እየሰራች ነበር፡፡ በ2010 ኮራ የሙዚቃ ሽልማት ላይ ለእጩነት የደረሰችው ሚካያ፤ በባህልና ቋንቋ ላይ የሚያተኩር የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመስራት እየተንቀሳቀሰች እንደነበር ታውቋል፡፡ ድምፃዊቷ የአንዲት ሴት ልጅ እናት የነበረች ሲሆን የቀብር ስነስርዓቷ ባለፈው ረቡዕ በለቡ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል በሚካያ በኃይሉ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጆቿና ለአድናቂዎቿ መጽናናትን ይመኛል፡፡

Read 4888 times