Saturday, 28 December 2013 10:51

የ“ኢትዮ ምህዳር” ዋና አዘጋጅ እንደገና ተከሰሰ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮ ምህዳር ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ፤ ከንግድ አሰራርና ሸማቾች ባለስልጣን ጋር በተገናኘ ሐሙስ እለት ማዕከላዊ ምርመራ ድረስ ተጠርቶ ቃል እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በባለስልጣኑ ለፖሊስ ያመለከተው፣ ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም “የንግድ አሰራርና ሸማቾች ባለስልጣን ቅሬታ ቀረበበት” በሚል ርእስ በጋዜጣው ላይ ባወጣው ዜና ሳቢያ እንደሆነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ተናግሯል፡፡ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ቢሯችን ድረስ መጥተው የዜና ጥቆማ ሲሰጡን፤ መስሪያ ቤቱ ዘመድ አዝማድ በሙስና የሚሰባሰቡበት ሆኗል በማለት የጽሑፍና የቃል መረጃ አቅርበውልናል የሚለው ጋዜጠኛ ጌታቸው፤ ጋዜጠኛ ልከን ስራ አስኪያጁን ለማነጋገር ብንሞክርም ሳይሳካ ወደ ህዝብ ግንኙነት ክፍል እንድንሄድ ነው የነገረን ብሏል፡፡ እዚያም ቢሆን ጥያቄዎቻችሁ ኢሜይል አድርጉልኝና መልስ እሰጣለሁ ብሎ እንደዘገየብንና እንዳልተሳካልን አካተን ዜናውን ሰርተነዋል ብሏል ጋዜጠኛው፡፡ በ15 ቀኑ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኩል ቅሬታ ሲደርሰን፤ ቅሬታ ካለው እናስተናግዳለን ብለን መልስ ሰጥተናል ያለው ጋዜጠኛ ጌታቸው፤ ሐሙስ እለት ወደ ማእከላዊ ምርመራ ተጠርቼ ቃሌን እንድሰጥ ከተደረግሁ በኋላ በዋስትና ተለቅቄያለሁ ብሏል፡፡ “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጠኞች በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክስ ቀርቦባቸው በቀጠሮ ቀን ለመከራከር በተጓዙበት አጋጣሚ በስራ ባልደረባቸው ላይ አደጋ እንደደረሰባቸው ይታወሳል፡፡ ለሁለት ቀናት በለገጣፎ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደነበረም አዘጋጁ ተናግሯል፡፡

Read 1184 times